በሀገሪቱ የሕትመት ሚዲያ ታሪክ ግንባር ቀደም የሆነው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት መቋቋም መሠረት የሆነው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ሕትመት መጀመር ነው። ስሙም የተወሰደው ንጉሡ ከስደት መመለሳቸውን አስመልክቶ በሚያዚያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ባደረጉት ንግግር ነው። “ዛሬ በኢትዮጵያ አዲስ ዘመን ተጀመረ” ሲሉ ከተናገሩት አረፍተ ነገር ላይ መሆኑን የታሪክ መዛግብት ያትታሉ።
አዲስ ዘመን ሲጀመር አርበ ጠባብ ሆኖ ቁመቱ 42 ሴንቲ ሜትር ስፋቱ ደግሞ 31 ሴንቲ ሜትርም ነበር። ዓምዱም በሦስት የተከፈለ ሲሆን ይህን የብራና ጽሑፎች ተፅዕኖ ሊሆን እንደሚችል ታሪክ ሰናጆች ያብራራሉ። የጋዜጣው ስያሜ የግዕዝን የአፃፃፍ ሥርዓት በጠበቀ መልኩ በሥርዓተ ነጥብ ታጅቦ ይፃፍ ነበር። ድርብ ሰረዝ ለእርሱ መጠቀም የተጀመረው ቆይቶ ነበር። በጋዜጣው ላይም ርዕሰ አንቀፅና የዋና አዘጋጅ ስም ቆይቶ እንደመጣም የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ጋዜጣውን የሚመራው የጋዜጣና ማስታወቂያ ጽሕፈት ቤት እየተባለ የሚታወቀው ተቋም እንዳሁኑ መሐል አራት ኪሎ ላይ ሳይከትም በፊት ሰባራ ባቡር አካባቢ ነበር። ጋዜጣው ሲመሠረት እውነት፤ አገልግሎትና ረዳትነት የሚሉ ዓላማዎችን ይዞ መነሳቱን ያገኘነው የታሪክ ድርሳን ያትታል። በወቅቱ የነበረው የጋዜጣው መሸጫ ዋጋ ሦስት የጣሊያን ሊሬ ሲሆን አሁን የአንድ ጋዜጣ ዋጋ አስር ብር ላይ መድረሱ ይታወቃል።
በወቅቱ አብዛኛው የጋዜጣው የጽሑፍ ይዘት ስለ ንጉሠ ነገሥቱ ክብርና ስለሀገር ፍቅር የሚሰብክ ሲሆን ከጥቂት የኅትመት ቆይታዎች በኋላ የግሪክ ፈላስፋዎችን ሥራዎች በተከታታይ በማተም ሕዝቡ እንዲያውቅና እንዲመራመር ሰፊ ጥረት ሲያደርግ እንደቆየም ታሪክ ያወሳል። በወቅቱ በጋዜጣው ላይ የዜናም ሆነ የርዕሰ አንቀጽና የአስተያየት ገጽ ያልነበረ መሆኑንም ታሪክ ይናገራል።
ዘመን ዘመንን እየወለደ ሲሄድ በርካታ ዋና አዘጋጆችን ይዞ ያለፈ የታሪክ መዝገቡ አንጋፋው አዲስ ዘመን ጋዜጣ የመጀመሪያው ዋና አዘጋጅ የነበሩት ሰው ብላታ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ ነበሩ። እኚህ ሰው በወቅቱ የታወቁ የቤተ ክህነት ሊቅ ነበሩ። እኚህ ሰው ዋና አዘጋጅ ብቻ ሳይሆኑ ከ1933 እስከ 1953 ዓ.ም ለሃያ ዓመታት በዋና አዘጋጅነት ያገለገሉ ጠንካራ ሰው ነበሩ።
ወልደ ጊዮርጊስ በጋዜጣው ላይ ከአራሚ ጀምሮ፤ በወቅቱ አጠራር የዜና ሠራተኛ፤ አዘጋጅ፤ ዋና አዘጋጅ በመሆን ለዓመታት አገልግለዋል። ከ1936 ዓ.ም ጀምሮ ለኅትመት የበቃው የዘኢትዮጵያን ሄራልድም አማርኛ ለማይችሉ ለውጭ ሀገር ዜጎች እንዲያነቡት የተዘጋጀ ነበር። ጋዜጣው የሀገሪቱን ማኅበራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ለውጭ ማኅበረሰብ በማስተዋወቅ ረገድ የላቀ አስተዋፅዖ እንደ ነበረው መረጃው ያመለክታል።
በርካታ ጋዜጦችና መጽሔቶች በተለያዩ ጊዜያቶች ቢታተሙም ከአዲስ ዘመንና ከኢትዮጵያን ሄራልድ በስተቀር ሌሎቹ በመንግሥት ለውጦችና ከእነሱ ጋር ተከትሎ የመጣው የርዕዮተ ዓለም ፍልስፍና ምክንያት ብዙም ሳይቀጥሉ ቀርተዋል። አዲስ ዘመን መታተም ከጀመረ ከአስራ ስምንት ዓመታት በኋላ እለታዊ የሆነ ሲሆን ሰኞ ሳይታመም በሳምንት ስድስት ቀን ብቻ እየታተመ ለረዥም ዓመታት ቆይቷል። አዲስ ዘመን ጋዜጣ ሰኞንም ጨምሮ በሳምንት ለሰባት ቀናት መታተም የጀመረው በ1993ዓ.ም ጀምሮ ነበር። የአፍሪካ ኢኮኖሚክስ ኮሚሽን አዲስ አበባ ውስጥ መቋቋሙን ተከትሎ ዘኢትዮጵያን ሄራልድም ከ1951 ዓ.ም ጀምሮ እለታዊ ሆኗል።
ከኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማኅበር በተገኘው ማስረጃ መሠረት ድርጅቱ የሚያሳትማቸው ጋዜጦች በ1997 ዓ.ም የነበራቸው ስርጭት፤ ዘኢትዮጵያ ሄራልድ 6500 ቅጂ፤ አል-ዓለም ጋዜጣ በየሳምንቱ 2500 ቅጂ፤ በሪሳ ጋዜጣ በየሳምንቱ 2000 ቅጂ ነበረው።
ይህ ተቋም ጋዜጦችንና መጽሔቶችን ከማሳተም ባለፈ በሀገሪቱ አንቱ የተባሉ ስመጥር ደራሲያንን በማፍራት አቻ ያልተገኘለት እንደ ነበር የታሪክ መዛግብት ያብራራሉ። በወቅቱ ጉምቱ ጸሐፍት መካከል አቤ ጉበኛ፤ ብርሃኑ ዘርሁን፤ በዓሉ ግርማ፤ ጳውሎስ ኞኞ፤ ከበደ ሚካኤል፤ ብላታ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ፤ ነጋሽ ገብረ ማሪያም፤ የሺጥላ ኮከብ ፤ ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር፤ ደምሴ ፅጌ፤ ታደለ ገድሌ፤ አበረ አዳሙ እና ሌሎችም በርካታ ደራሲያን የፈሩበት በቀጣይም የሚፈሩበት ታላቅ ተቋም ነው።
በዚህ ታላቅ ተቋም ውስጥ ከጋዜጠኛችም በላይ እነዚህን ታዋቂ የሕትመት ወጤቶች አንባቢያን ዘንድ ማልደው በትኩሱ መረጃን ለማድረስ የሚታትሩ ጋዜጣ አከፋፋዮች ይገኙበታል። ከእነዚህ ጋዜጣ አዳይ ሰዎች መካከልም የእድሜያቸውን አጋማሽ በተቋሙ ያገለገሉ እና የሀገር ባለውለታ የሆኑ አንድ ሰውን ለዛሬ የሕይወት እንዲህ ናት ዓምድ ይዘንላችሁ ቀርበናል መልካም ቆይታ።
ገና በልጅነት እድሜያቸው ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ውስጥ ሲሠሩ የነበሩ ዘመዳቸው ተከትለው ወደ ተቋሙ ብቅ ያሉት እኝህ ሰው “ይችን ጋዜጣ እዛ አድርሰህ ና፤” እየተባሉ ሲላኩ አደጉ። ጉልበታቸው ሲጠና ጠንካራ ጎረምሳ ሲሆኑ ደግሞ ጋዜጣውን በሳይክል ይዘው በመዞር በከተማዋ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የሚደርስባቸው ቦታዎች በሙሉ ያደርሱ ነበር።
በእጅ ጋዜጣ እየተሰጣቸው እዚህና እዛ ሲላኩ የነበሩት ሰው በሳይክል ጋዜጣ አድርሱ ሲባሉ በፍጥነት ለየተቋማቱ በማድረሳቸው የበላይ ኃላፊዎችን ይሁንታን አግኝተው ገና በአስራ አምስት ዓመታቸው ጋዜጣን ማከፋፈል ሥራቸው ሆኖ ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን ተቀላቀሉ። እኚህ ሰው በጡረታ እስከተገለሉባት ቀን ድረስ በድርጅቱ ለአራት አስርተ ዓመታት ያለማቋረጥ አገልግለዋል።
አቶ ዕቁባይ ዮሴፍ ወልደ ኪዳን ይባላሉ። በ1940 ዓ.ም በትግራይ ዓድዋ ከተማ ነበር የተወለዱት። ከአባታቸው ከአቶ ዮሴፍ ወልደኪዳንና ከእናታቸው ዘውዴ ውነህ የተወለዱት እኚህ ሰው እንደማንኛውም የትግራይ አካባቢ ሕፃን በቤተክህነት ደጅ ነበር ከፊደል ጋር የተዋወቁት።
በቄስ ትምህርት ተምረው ፊደል የለዩ ቢሆነም ገና በአፍላ እድሜያቸው ከተወለዱባት ከዓድዋ አንድ የቅርብ ዘመዳቸውን ተከትለው ወደ አዲስ አበባ መጡ። ከትውልድ ቀያቸው ከወጡ በኋላ ያመጧቸውን ሰው እግር እግር እየተከተሉ የሚሠሩትን ማየት፤ ያዩትን ለመሞከር መታተር ጀመሩ። በዚህም የሞከሩት ቶሎ የሚገባቸው ንቁ አዕምሮ ያላቸው ኣፍላ ወጣት ሆኑ።
በመላላክ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን የተዋወቁት እኚህ ሰው በ1955 ዓ.ም ብስክሌት በመንዳት ጋዜጣ የማዞር ሥራ ላይ በመሰማራት የመጀመሪያ የቅጥር ፊርማቸውን አስቀምጡ። ወጣቱ ዕቁባይ በወቅቱ የአስራ አምስት ዓመት አፍላ ወጣት ሆነው ነበር ድርጅቱን የተዋወቁት።
በመቀጠል ሞተር ሳይክል የመንዳት የሚያስችል ሥልጠና ወስደው በሞተር መጀመሪያ ሲሠሩት የነበረውን የጋዜጣ ስርጭት በበለጠ ቅልጥፍና ያካሂዱት ጀመር። ከሞተር ብስክሌት ቀጥሎ ሾፌር በመሆን በመሥሪያ ቤቱ አስፈላጊ የሆኑ ሥራዎችን በሙሉ ሲሠሩ ቆይተዋል። በተቋሙ የተመለከትነው የቅጥር ማኅደር እንደሚያመለክተው እስከ 1977 ዓ.ም ድረስ በሹፍርና ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
ከጥቅምት 16 ቀን 1977 ዓ.ም እስከ መጋቢት 16 ቀን 1978 ዓ.ም ድረስ በተጠባበቂ የሰርቪስ ተቆጣጣሪነት አገልግለዋል። ሙሉ የሥራ ሕይወታቸውን በድርጅቱ ያደረጉት እኝህ ሰው ከመጋቢት 16 ቀን 1978 ዓ.ም እስከ ሚያዚያ 18 ቀን 1978 ዓ.ም ድረስ በንብረት ከፍል ሠራተኝነት አገልግለዋል። ከሚያዚያ 19 ቀን 1978 ዓ.ም እስከ ሰኔ 30 ቀን 1986 ዓ.ም ዳግም በሾፌርነት በከፍተኛ ትጋት ሲያገለገሉ ቆይተዋል።
በ2001 ዓ.ም በጡረታ እስከተገለሉበት ጊዜ ድረስ በሰርቪስ ክፍል ተቆጣጣሪነት፤ የትራንስፖርት ክፍል ኃላፊና ሌሎች ትራንስፖርት ነክ በሆኑ ኃላፊነቶች ላይ ሲያገለገሉ መኖራቸውን የግል ማኅደራቸው ያስረዳል። በዚህ ሁሉ የአገልግሎት ዘመናቸው ጋዜጣውን ከማሰራጨትም በላይ ጋዜጠኞችን ለዘገባ ይዞ መውጣት ተቀዳሚ ሥራቸው እንደነበር አብረዋቸው የሠሩ አንጋፋ ጋዜጠኞች ይመሰክራሉ።
አቶ እቁባይ በሥራ ባልደረቦቻቸው አንደበት
አቶ ተሾመ ቀዲዳ የበሪሳ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ባልደረባ
” ለረዥም ዓመታት በበሪሳ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ውስጥ አገልግያለሁ። ለሠላሳ ዓመታት የዘለቀ ትውውቅ ያለን ሲሆን አቶ ዕቁባይ ከሾፌርነት እስከ የተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ሲያገለግሉ አውቃለሁ። በሥራ ላይ በነበሩበት ወቅት አቶ ዕቁባይ ከሁሉም ሰው ጋር ጤናማ ግንኙነት የነበረው አይነት ሰው ነበር።
አቶ ዕቁባይ እንዳጫወተኝ ከሹፍርና በፊት ለዓመታት በብስክሌት በየቋማቱ ጋዜጣ ያድል እንደ ነበረ ነው። አብረን በሠራንባቸው ዓመታት በጣም መልካም ሰው ነበር። የጋዜጠኝነት የሥራ ባሕሪን በመረዳት በአግባቡ ሲያገለግል የኖረ ሰው ነው። እኔ ስፖርት ጋዜጠኛ ስለሆነኩኝ እስታድየም በማመሽበት ወቅት ያለ ምንም ቅሬታ ሰብሰቦን በየቤታችን በየምሽቱ ካደረሰን በኋላ ነበር እሱ የሚያርፈው።
ለአቶ ዕቁባይ አለቃም ሆነ የበታች ሠራተኛ እኩል ቦታ ነበረው። ቀድሞ አገልግሎቱን የጠየቀው የበታች ሠራተኛ ከሆነና አንድ መኪና ብቻ ካለ ቅድሚያ የሚያገኘው ቀድሞ የሚመጣው መሆኑ ልዩ ያደርጋቸዋል። አቶ ዕቁባይ መልካምነቱ ማሳያ የሚሆነው ጡረታ በወጣበት ወቅት ሙሉ የመሥሪያ ቤቱ ሰው ነበር ታላቅ ፕሮግራም አዘጋጅቶ የሸኘው።
ከዕቁባይ ከሥራ ባልደረባነት አልፎ ማኅበራዊ ትሰስራችን የጠበቀ ነበር። ያ ማለት ለበዓላት መጠራራትን፤ ለችግር መደራረስን፤ አብሮ ማምሸትንና ቤተሰብ እስከ ቤተሰብ መተሳሰር ድረስ መልካም ግንኙነትን መፍጠር የሚያውቅበት ታላቅ ሰው ነበር። ̋ ሲል አቶ ተሾመ ቀዲዳ ትውስታውን አካፍሎናል፡፡
ሰለሞን ጥዑመ ልሳን የቀድሞ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ባልደረባ
̋ከአቶ ዕቁባይ ጋር የተዋወቅነው እኔ የጋዜጠኝነት ሥራን ስቀላቀል ጀምሮ ነው። ሹፌርም ሆኖም ሆነ የሥራ ክፍሉ ኃላፊ በነበረበት ጊዜዎች ጥሩ ግንኙነት ነበረን። በአዲስ አበባ ከተማና በመስክ ሥራዎች ጋር አብረን ተንቀሳቅሰናል፤ አቶ ዕቁባይ ሥራዎችን በሠላማዊ መልኩ መሥራት የሚወድ ለእያንዳንዱ ሥራ ኃላፊነትን የሚወስድ ሰው ነበር። የጋዜጠኝነትን ሥራ በአግባቡ ተረድቶ የሚሠራ ሁሉንም እንደ አመሉ ተቀብሎ ባለው ውስን አቅም ለሁሉም የሚያደስ ሰው ነበር።
እንዳለ መታደል ሆኖ የሚዲያ ተቋማት የሚዋከቡት በትራንስፖርት ክፍል ኃላፊዎች ነበር። እንደ እቃ ቀላል አድርጎ ሰውን የመመልከት ሁኔታ ይታያል። ዕቁባይ ጋር ግን ያ የለም። ሥራ የሚያግዝ በፈገግታ የተሞላ የሥራ ቀናትን በደስታ ለማሳለፍ የሚያስችል ስሜት የሚፈጥር አይነት ጥሩ ሰው ነበር።
ሰው ቢታመም ጠያቂ፤ ለቅሶ ቢኖር ቀድሞ ደራሽ፤ የእሱን እርዳታ ለፈለጉ ሁሉ እጁ የማይታጠፍ፤ ሰጥቶ የማይጠግብ፤ አብልቶ ሰው የጠገበ የማይመስለው ሰው ነው፤ በኃዘን ሁሉንምን ሠራተኛ በየተራ እየወሰደ የማኅበራዊ ትሰስሩ ተቋም ውስጥ እንዲጠብቅ የሚያደርግ ሰው ነበር።
በመስክ ሥራ ላይ በአግባቡ ሥራው እንዲሸፈን የሚያደርግ፤ መስክ ሥራ ላይ የተለያዩ ቦታዎች ጋዜጠኞችን በአግባቡ በማድረስ ሥራው እንዲሳለጥ በማደረግ፤ ሥራ አልቆ እረፍት የሚሆንበት ጊዜ ላይ በጣም ደስ የሚል ግንኙነት ያለው፤ መደሰት መሳቅ የሚወድ፤ የሚጫን ነገር ካለ ጭኖ ተባብሮ መምጣት የሚወድ ሰው ነው።
ዕቁባይ ከልብ የማይጠፋ አይነት ሰው ነወ። እቁባይ ግልጽ ሰው ነው። ፊለፊት የሚናገር፤ የመሰለውን ከማድረግ ያለፈ ክፋት የሌለው የብዙኃኑ በወቅቱ የነበሩ ጋዜጠኞች የሕይወት ቅመም እንደሆነ መናገር ይቻላል። የፕሬስ ማከፋፈያ መምሪያ በሚባል ጊዜ ጀምሮ ሰለቸኝ ደከመኝ ሳይል ሥራውን በአግባቡ የሚሠራ ጠንካራ ሰው የነበረ ሕይወቱን በሙሉ በተቋሙ ያገለገለ ሰው ነው” ሲል አቶ ሰለሞን ሃሳቡን አካፍሎናል፡፡
አቶ ዳኜ አበራ የፎቶግራፍ ባለሙያ
“ከአቶ ዕቁባይ ጋር የተዋወቅነው በ1987 ዓ.ም ነው። እኔ ወደ ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ስቀላቀል እሱ ሾፌር ነበር። ከዛ የስምሪት ኃላፊ ሆኖም ረዥም ጊዜ ሠርቷል። በጦር ሜዳ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት አብረን የመዝመት እድልም ገጥሞን ነበር። ከጦርነቱም በተጨማሪ በርካታ የሀገራችንን ክልሎች አብረን ለመርገጥ ችለን ነበር።
ከዕቁባይ ጋር በጣም የተግባባነው በጦርነቱ ጊዜ ነበር። ወደ ዘመቻው ስንሄድ በሁለት ቡድን ተከፍለን ነበር፤ አንደኛው እሱ የያዘው ቡድንና ሌላው ደግሞ ሰይፉ የሚባል የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሹፌር የያዘው ቡድን ነበር። እኔም ከኢቲቪዎች ጋር ነበርኩኝ፤ ግንባሩ አንድ ነው። የመጨረሻው ውጊያ ሲካሄድ በጣም የተፋፋመ ነበር፤ ብዙዎቹ ሲፈሩ እሱ የያዘው ቡድን ግን ወደኋላ ቀርቶ ሲዘግብ በከባድ መሣሪያ ተመተው ከአፈር ውስጥ ነበር ተጎትተው የወጡት።
በወቅቱ ሁለት ከቴሌቪዥን ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ደግሞ አንድ ፎቶግራፈር ሲሞቱ ብዙዎቹ ሲቆሰሉ ከዛ አደጋ የተረፈ ሰው ነው። በተፈለገው ሰዓት የተፈለገው ቦታ ያለምንም ቅሬታ የሚደርስ የሀገር ባለውለታ ነው። ሥራውን ወዶና ፈቅዶ የሚያገለግል አይነት ሰው ነው። ቁጡ ተናዳጅ የፎቶ ግራፍ ባለሙያው አቶ ዳኜ አበራ ትውስታውን አካፍሎናል፡፡
አቶ ሰለሞን በቀለ ሾፌር
” ከአቶ ዕቁባይ ጋር ሥራ ከተቀጠርኩበት ጊዜ አንስቶ እንተዋወቃለን። ከሌላው ሠራተኛ ጋር የመኪናው ተገልጋይና ሠራተኞች አይነት ግንኙነት በዛው የተመሠረተ ወዳጅነት ቢኖርም፤ በሰርቪስ ክፍል ውስጥ በመተጋገዝና በመደጋገፍ መሥራቱ፤ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል የብዙዎችን ቦታ ሸፍኖ መሥራቱ፤ ድካምን ኃዘንን ችግርን በሙሉ በመተጋገዝ ማለፉ የበለጠ ይታይ ነበር።
አቶ ዕቁባይም ለችግር ደራሽ ደከመኝ ሰለቸኝ የማያውቅ ሌሎች ያዘኑበት ነገርን በፈገግታ እንዲረሱት የሚያደርግ ጥርስ አያስከድንም የሚባል አይነት ሰው ነበር። ከሁሉ በላይ ከልጅነት እስከ እውቀት የሠራበት ቤት ሥራ እንዳይበደል የነበረው የማስተባበር ችሎታ ከፍ ያለ ነበር።
ለሰው ደራሽ፤ ለጋስ እጅግ በጣም ጠንካራ ሠራተኛ ነገሮችን ደባብቆ ማለፍ የማይችል ነገር ግን ተናግሮ ወዲያው የሚረሳ አይነት ሰው ነበር። የያዘውን ነገር ዳር ሳያደርስ የማያቆም የጥንካሬ ተምሳሌትም ነበር፤ በተለይ ሥራ ላይ አይሆንም የሚባል ነገር አያውቅም፤ ሁልጊዜ እችላለሁ፤ አደርገዋለሁ በሚል መንፈስ የሚተጋ በአመራርነት ጊዜውም ሆነ በሾፌርነት ዘመኑ አንድም ቀን ሳያርፍ ለድርጅቱ የለፋ ሰው ነው።
በሁሉም ሠራተኞች ዘንድ የነበረው ተቀባይነት የላቀ እንደነበረ የሚታየው በጡረታ ተገልሎ ከመሥሪያ ቤቱ ሲሸኝ በታላቅ ክብር ነበር። ሠራተኛው በስጦታ አንበሽብሾት በፍቅር እንባ ነበር የሸኘው። በአጠቃላይ ዕቁባይ መገለጫው መልካምነት ደግነት ተታሪነት እንደነበር አስታውሳለሁ”
ከባለቤታቸው አንደበት
“ከአቶ ዕቁባይ ጋር የተዋወቅንው ያደኩበት ሰፈር ሾላ አካባቢ ስለነበረ ከቤት ተልኬ ወደ ሱቅ በወጣሁበት አጋጣሚ ነበር። ያኔ በእድሜ በጣም አፍላ ወጣት የምባል አይነት ልጅ ነበርኩ። በአጋጣሚ የተጀመረው ትውውቅ አድጎ ለትዳር እንበቃለን የሚል ሀሳብ ግን አልነበረኝም።
ዕቁባይ በልጅነቴ ያወኩት እንደ አባት አስተምሮ አሳድጎኝ የኖረ አባቴም ባሌም ነበር። በትዳር አሥራ ስድስት ዓመታትን አብረን አሳልፈን ሁለት ልጆች አፍርተናል። ቤቱን አክባሪ ፤ጎዶሎ የማይወድ በፈገግታ የተሞላ ሰው ነበር። ለልጆቹ የሚሳሳ ድንቅ አባት ነበር።
ከሦስት አስርታት በላይ የእድሜ ልዩነት መኖሩ እንደ ባልና ሚስት ሳይሆን አንደ አባትና ልጅ ተከባብረን እንድንኖር አድርጎን ነበር። በወቅቱ አስቸጋሪ የነበሩ ነገሮች ቢኖሩም ትዳሩን አክባሪ ቤቱን ወዳድ ሳቅ ጫወታን የሚወድ አይነት ሰው እንደነበረ መናገር እችላለሁ። ለልጆቹ የሚሳሳ ልጆቹን ከማየት ከእነሱ ጋር ከመጫወት በላይ ደስታ የሚሰጠው ነገር እንዳልነበር አስታውሳለሁ”ስትል ወደኋላ የኋሊት ተሻግራ የነበረውን የፍቅርና የትዳር ሕይወት አጫውታናለች፡፡
ከልጆቹ መካከል መና ዕቁባይ ስለ አባቷ
“አባቴ ከልጅነቴ ጀምሮ በፍቅር እያሳደገኝ ትምህርት ቤት እያመላለሰ ያስተማረኝ አባቴ ነው። እስካለሁበት ጊዜ ድረስ ለእኔ ያለው ፍቅር መግለፅ ስለሚያቅተው በስሜ እራሱ አይጠራኝም ‹‹እናቴ›› ብሎ ነው የሚጠራኝ፤ እንደዛ ብሎ ሲጠራኝ በጣም ደስ ይለኛል። ለእኔ ብሎ ሕይወቱን ለሠጠኝ አባት ምንም ሳላደርግለት እኔን የሚፈልግበት ደረጃ ደርሼ ሳያይ ተለየኝ። አባቴን በምንም በማንም የማልተካው የማልቀይረው የማለውጠው ብቸኛው ሰው አባቴ ነው።
አባቴ ለእኔ በጣም ጥሩ እና መልካም አሳቢ ሰው ነው:: ስለእሱ ሳወራ ቃል ያጥረኛል ምን ብዬ እንደምገልፀው ቃላቶች አይገልፁልኝም “
የዋህ ልበቀና እንደሆኑ የተነገረላቸው የእድሜያቸውን እኩሌታ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ብቻ ያገለገሉት አባት ኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል። አቶ ዕቁባይ ዮሴፍ ለሁሉም የሰው ልጆች የተቀመጠውን የሞት ፅዋ መጎንጨት ግዴታቸው ሆኗል።
ለሁሉ ደራሽ፤ አልባሽ አጉራሽ የሆኑት ሰው የሥራ ዓለም ታሪካቸው ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ብቻ የነበረ እራሳቸውን በተለያዩ ሥልጠናዎች እያሳደጉ ከብስክሌት አሽከርካሪነት እስከ ታዋቂ ሹፌርነት፤ ከጋዜጣ አዳይነት እስከ የተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች አገልግለው 2001 ዓ.ም በጡረታ በክብር ተገልለዋል።
ጡረታ ከመውጣታቸው በፊት ከጋዜጠኞች ጋር በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች የተዘዋወሩ ሲሆን በደርግ ዘመነ መንግሥት በወታደራዊ መንግሥቱና በወያኔ መካከል የነበረውን ጦርነት ለመዘገብ የወጡ ጋዜጠኞችን ይዘው በጦር ሜዳ ውለዋል። ዳግም በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት ጋዜጠኞችን ይዘው በተጓዙበት ወቅት በከባድ መሣሪያ በመመታታቸው የተነሳ መኪናው ውስጥ የነበሩት አብዛኞቹ ሲቆሰሉና ሲሞቱ እሳቸው ግን እግራቸው ላይ በፍንጥርጣሪ ከመጎዳት ያለፈ ምንም ችግር ያልገጠማቸው መሆኑን ወዳጆቻቸው በትዝታ ይናገራሉ።
ሆኖም ስራ ሁልጊዜ ከመቃብር በላይ ነውና ከብስክሌት በመዞር አንጋፋውን አዲስ ዘመን ጋዜጣ በማደል መረጃዎችን በጧት ሲያደርሱ የነበሩት እኒህ የሀገር ባለውለታ ለዘላለም ሥራቸው ሕያው ሆኖ ይኖራል፡፡ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ በታወሰ ቁጥርም የአቶ ዕቁባይ የስራ ትጋትና ውለታም አብሮ ይወሳል።
አስመረት ብሥራት
አዲስ ዘመን ጥር 5 ቀን 2016 ዓ.ም