የብረትናብረትነክማዕድናትልማትንእውንየማድረግጅማሮዎች

በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ሰፊ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች መካከል አንዱ የማዕድን ዘርፍ ነው። ይህ ሁኔታ ሀገሪቱ በዘርፉ ያላትን እምቅ የማእድን ሀብት በማልማት የሀገር ውስጥ የማእድን ፍላጎትን በመሸፈንና ከውጭ የሚመጡትን የማእድን ምርቶች በሀገር ውስጥ በመተካት ሥራ ላይ ትኩረት ሰጥታ እንድትሰራ እያደረጋትም ይገኛል።

በድንጋይ ከሰል ማእድን ልማት በኩል እየተከናወነ ያለው ተግባር ለእዚህ በአብነት ይጠቀሳል። በኢትዮጵያ ለትላልቅ ፋብሪካዎች የኃይል ምንጭ የሆነው በሲሚንቶ፣ በሴራሚክና በጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች በስፋት ጥቅም ላይ የሚውለውን ይህን የድንጋይ ከሰል ከውጭ የማስመጣቱ ሥራ ሀገሪቱን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ሲያስወጣ ኖሯል። ለማእድን ዘርፉ የተሰጠው ትኩረት በሀገሪቱ ያለውን ከፍተኛ መጠን ያለው የድንጋይ ከሰል ክምችት ወደ ልማቱ እንዲገባ እያስቻለ ነው። የድንጋይ ከሰል የማምረቱ ሥራ ለከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች የሚያስፈልገውን የድንጋይ ከሰል ምርት በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ያስቻለበት ሁኔታም ተፈጥሯል።

ሀገሪቱ ለግንባታው ዘርፍ የሚያስፈልጋትን ብረትም ከውጭ እንደምታስመጣ ይታወቃል። መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፤ በዓለም ላይ በየዓመቱ በአማካይ አንድ ቢሊዮን ቶን ብረት ይመረታል፤ በዓለም በከፍተኛ ደረጃ ብረት በማምረት በግንባር ቀደምነት ከሚታወቁት ሀገራት መካከል አውስትራሊያና ብራዚል ይጠቀሳሉ። በተመሳሳይ በአፍሪካ ደቡብ አፍሪካ እና ናይጄሪያ ብረትን በስፋት ያመርታሉ።

የማእድን ሚኒስቴር መረጃ እንደሚጠቁመው፤ ኢትዮጵያ ከአንድ ቢሊዮን ቶን በላይ የሚገመት የብረትና ብረት ነክ የማዕድናት ክምችት አላት። ይሁን እንጂ ሀገሪቱ በየዓመቱ አምስት መቶ ሺ ቶን ብረትና ብረት ነክ ማዕድናት ከዩክሬን፣ ከሩሲያ፣ ከቱርክና ከሌሎች ሀገሮች ታስገባለች። ይህም አገሪቱ ብረትና ብረት ነክ ማዕድናት ከውጭ ለማስገባት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪን እንድታወጣ አድርጓታል።

የብረት ፍላጎቱ ከግንባታው ዘርፍ መስፋፋት ጋር ተያያዞ እየጨመረ በመጣበት ሁኔታ በዚህ አይነት ሁኔታ መቀጠል እንደማይቻል ታምኖበት ወደ ብረት ልማት ስራም ተገብቷል። ከውጪ የሚመጡ የማዕድን ምርቶችን በአገር ውስጥ የመተካቱ ሥራ በግንባታው ዘርፍ በእጅጉ ተፈላጊ የሆነውንና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪን ሲጠይቅ የኖረውን ይህን ብረት በሀገር ውስጥ ለማምረት ሥራ ለማዋልም ጥረት እየተደረገ ይገኛል።

ለዚህም በሀገር ውስጥ ያለውን የብረት ማዕድን ክምችት ለመለየት እና ብረት ለማምረት ለሚፈልጉ ኩባንያዎች ፈቃድ የመስጠት ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ከማእድን ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል። ይህ ሲሆን ብረት ከውጭ ለማስገባት የሚወጣውን ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ ማስቀረት ይቻላል።

ሀገሪቱ ካላት የብረት ማእድን ክምችት ውስጥ ከ72 ሚሊዮን ቶን በላይ የሚሆነው የብረት ክምችት ባለባቸው አካባቢዎች ላይ የብረት ፍለጋ ለማካሄድና ለማምረት የሚያስችል ፈቃድ ለጠየቁ ኩባንያዎች የምርት ፈቃድ ተሰጥቷል። በተቀረው የብረት ሀብት ክምችት ላይ ደግሞ የጥራትና የመጠን ተጨማሪ ጥናት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ታምኖበት እየተሰራ ነው።

ማእድኑ በአብዛኛው በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል የሚገኝ ሲሆን፤ የብረት ማእድኑ ያለበትን አካባቢና የክምችት መጠኑን የሚያመለክት ሥራ እየተሰራም ይገኛል። ኩባንያዎች በአማራ፣በትግራይና በኦሮሚያ ክልል የብረት ማእድን የፍለጋና የምርት ፈቃድ ወስደው በሥራ ላይ እንደሚገኙ መረጃው ያመላክተ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥም ሰቆጣ ማይኒንግ፣ኤም ኤስ ፒ ስቲልና ኮዬጻ ማይኒን ሼር ኩባንያ (Koyetsa Mining share company) እንደሚጠቀሱ መረጃቸው አመልክቷል።

የማዕድን ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አወቀ ተስፋው ብረትና ብረት ነክ ማዕድናት በኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች እንደሚገኙ ይናገራሉ። ከእነዚህ ማዕድናት መካከል ብረት፣ ታንታለም፣ መዳብ፣ ሊቲየም፣ ክሮማይት፣ኒኬል፣ ማንጋነስ ፣ ዚንክን ለአብነት ጠቅሰዋል።

እሳቸው እንደሚሉት፤ ብረት ለመሰረተ ልማት በጣም ወሳኝ ከሆኑ የማዕድን አይነቶች አንዱ ነው። ያለብረት መሰረተ ልማትን ማሰብ አይቻልም። ኢንዱስትሪና ትልልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶችም የሚሰሩት በብረት ነው። ለሁሉም መሰረተ ልማት ግንባታዎች ብረት ያስፈልጋል። ሰፊ የልማት እቅድ ያላት ኢትዮጵያ ደግሞ ከእድገቷና ከፍላጎቷ ጋር የሚጣጣም የብረት ማዕድን አቅርቦት ያስፈልጋታል።

ኢትዮጵያ ብረትና የብረት ውጤቶችን ከውጭ እንደምታስገባ የጠቆሙት አቶ አወቀ፤ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ብረትና ብረት ነክ ማዕድናት ለማምረት ከፍተኛ ፋይናንስና ቴክኖሎጂ የሚፈልግ መሆኑ እንደሆነ ያመላክታሉ። የአገር ውስጥ ባለሃብቶች አቅማቸውን አሰባስበው ብረት ማምረት ላይ ትኩረት አድርገው መስራት እንዳለባቸው ጠቁመው፤ የውጭ ኩባንያዎችም በዘርፉ ላይ እንዲሰማሩ መንግሥት ልዩ ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።

‹‹ለብረት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረት በአገር ውስጥ የሚያስፈልገውን ፍጆታ መሸፈን የሚያስችል ከፍተኛ መጠን ያለው የብረት ክምችት በሀገሪቱ ይገኛል›› የሚሉት አቶ አወቀ፤ ከአንድ ቢሊዮን ቶን በላይ የብረት ማዕድን ክምችት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እንደሚገኝ ጥናቶችን ዋቢ አርገው ጠቁመዋል።

አቶ አወቀ አገሪቱ ያላትን የብረት ማዕድን አውጥታ እንድትጠቀም ለማድረግ ትኩረት የሚሰጠው ቀዳሚ ጉዳይ እንደሆነም ያነሳሉ። የሌሎች አገራት ተሞክሮን ስንመለከት ለብረት ማዕድን ትኩረት ሰጥተው መስራታቸው ውጤታማ አድርጓቸዋል ይላሉ ።

አቶ አወቀ የቀድሞዋ ሶቬት ህብረት /የአሁኗ ሩሲያ/ መሪ የነበሩት ጆሴፍ ስታሊን ሀገሪቱን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር በተከናወነው ተግባር በብረት ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱን በአብነት ጠቅሰዋል። ይህም ሀገሪቱ ሁሉንም አቅሟን ብረት ላይ በማድረግ ከፍተኛ ለውጥ በማምጣት ተጠቃሚ እንድትሆን እንዳደረጋት ነው ያመለከቱት።

እንደዚህች ያሉ አገራት በተከተሉት ጠንካራ ፖሊሲ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም መትረፍ መቻላቸውንም ጠቅሰው፤ ብረትን ማውጣት መቻል ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ይገልጻሉ። ‹‹አገራችን ለልማቷና ለዕድገቷ ሊያግዛት የሚችል የብረት ሃብት ባለቤት ነች። ስለዚህ ብረትና ብረት ነክ ማዕድናት ማልማት ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው›› ሲሉም አስታውቀዋል።

አሁን በኢትዮጵያ በብረት እና ብረት ነክ ማዕድናት ፍለጋና ማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩ 18 ኩባንያዎች እንዳሉ አቶ አወቀ ይገልጻሉ። ከእነዚህ ውስጥም 13 ኩባንያዎች በብረት እና ብረት ነክ ማዕድናት ፍለጋ ላይ የተሰማሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ አምስቱ ደግሞ ብረት የማምረት ፈቃድ ወስደው እየሰሩ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

የማዕድን ክፍለ ኢኮኖሚ የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ትኩረት ከሰጣቸው ክፍለ ኢኮኖሚዎች አንዱ ነው ያሉት አቶ አወቀ፤ የማዕድን ዘርፍ በዋነኝነት በውጭ ምንዛሪ ግኝት አስተዋጽኦ እንዲኖረው በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገቡ የማዕድናት ውጤቶችን እና የማዕድን ኢንዱስትሪ ግብአቶችን በአገር ውስጥ መተካት፤ በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ለዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር ለኢትዮጵያ የመጪዎቹ ዓመታት የብልፅግና ጉዞ የጎላ አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ተልዕኮ ተይዞ እየተሰራ እንደሆነ ይገልጻሉ።

በዚህም በ2016 በጀት ዓመት ከውጭ የሚመጣውን የድንጋይ ከሰል ፍላጎት ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ የድንጋይ ከሰል ምርት ለመተካት የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን ጠቅሰው፤ ከመካከለኛና ከረዥም ጊዜ አኳያ የብረት ልማትን እውን ለማድረግ የሚያስችሉ የዝግጅት ስራዎችም በተያዘው በጀት ዓመት እንደሚከናወኑ አመላክተዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ በ2015 በጀት ዓመት የማዕድን ሚኒስቴር የተሰጡትን ተልዕኮዎች ለማሳካት በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ነው። በአንጸሩ ልማቱን በማካሄድ ሂደት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳረፉ ተግዳሮቶችም አጋጥመዋል።

ከተግዳሮቶቹ መካከልም የማዕድን ኢንዱስትሪዎች ለጥሬ ዕቃ፣ ለመለዋወጫ መግዣ እያጋጠማቸው ያለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ ህገ ወጥ የማዕድናት ግብይትና የኮንትሮባንድ ንግድ፣ በማዕድን አምራችና ኩባንያዎች አካባቢ የተስተዋለው የፀጥታ ችግር ይገኙበታል። ችግሮቹ በተቋማዊ አፈፃፀሙ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅእኖ አሳድረዋል።

እነዚህን ተፅእኖዎች ሊቀርፉ የሚችሉ ሥራዎችን ከሚመለከታቸው ወሳኝ ባለድርሻ አካላትና የፀጥታ ተቋማት ጋር በቅንጅት በመስራት ህገወጦችን የመቆጣጠርና ሕጋዊ እርምጃዎች ተወስደዋል ያሉት አቶ አወቀ፣ ይህ ሥራ በ2016 በጀት ዓመትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በሀገሪቱ በብረትና ብረት ነክ ማዕድናት ፍለጋና ልማት ላይ ለመስማራት የሚፈልጉ አካላት የሚያተርፉባቸው በርካታ መልካም እድሎች እንዳሉም አቶ አወቀ ጠቁመዋል። እሳቸው እንዳብራሩት፤ ከእነዚህም መካከል መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ልዩ ትኩረት በዘርፉ ለመስማራት ለሚፈልጉ አካላት መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ እምቅ የማዕድን ሀብት ያላት ሀገር መሆኗ እና አቅምና ልምድ ያላቸው ኩባንያዎች በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎት እያሳዩ መምጣታቸው ሌላኛው መልካም አጋጣሚን የሚፈጥር ነው። ለማዕድን ዘርፋ የተሰጠው ትኩረትም በዘርፉ የትኛውንም የማዕድን አይነት ለማልማት ለሚሰማሩ ባለሀብቶች አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል።

እንደ አቶ አወቀ ማብራሪያ፤ አሁን ላይ ብረትና ብረት ነክ ማዕድናትን ለማምረት እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ። በዘርፉ ለተሰማሩ ኩባንያዎች ድጋፍና ክትትል በማድረግ ወደ ማምረቱ ስራ እንዲገቡና የውል ግዴታቸውን እንዲወጡ የማድረግ ሥራዎችም ይሰራሉ። ከዚህ በተጨማሪም በማዕድን ልማት አካባቢና በማህበረሰቡ ላይ ሊደርሱ የሚችሉ አሉታዊ ተፅዕኖዎች እንዲቀንሱ የሚያደርጉ ተግባሮችም ይከናወናሉ።

በማዕድኑ ልማት አካባቢ የሚኖሩ ማህበረሰቦች ከልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑና ልማቱን ከአካባቢ ጥበቃና የማህበረሰብ ፍላጎት ጋር የተጣጣመና ዘላቂ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ማዕድናት ምርት በመጠንና በጥራት በማሳደግ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘትና ከውጪ የሚገቡ ማዕድናትን በአገር ውስጥ ምርት የመተካቱ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ይገልጻሉ።

በቀጣይም ሀገሪቷ ለብረት ማዕድን የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ በማዳን ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በማሰብ መታቀዱን የጠቆሙት አቶ አወቀ፤ በዚህ ዙሪያ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል።

መንግሥት ለማዕድን ዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ ከውጭ የሚገቡ የማዕድን ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች የመተካት ጅማሮ ኢኮኖሚያዊ አንድምታው ከፍ ያለ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። አሁን ላይ ሀገሪቷ ያላትን የማዕድን ሀብት ክምችት በመለየት ትኩረት ተሰጥቶቸው እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች አበረታች እንደሆኑም ይናገራሉ። በተለይ የድንጋይ ከሰል ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየተሰራ ያለው ሥራና ብረትንም እንደዚሁ በሀገር ውስጥ ለመተካት እየተደረጉ ያሉት ጥረቶች አበረታች ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ መሆናቸውን ያመላክታሉ።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ጥር 3/2016

Recommended For You