የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ጉዞ ከድሮ እስ ከ ዘንድሮ

ዲፕሎማሲ በሀገራትና መንግሥታት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ተቋማት መካከል የሚካሄድ ዘርፈ ብዙ የውጭ ግንኙነቶች የሚከወኑበት ሁነኛ ጥበብ ነው። የዲፕሎማሲ ዋና ተግባር በአገራት መካከል ዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን ማስተዳደር እና ሰላማዊ ግንኙነትን ማረጋገጥ ፤ የንግድ ስምምነት ድርድሮችን፣ በጋራ ችግሮች ዙሪያ ውይይትን፣ አዳዲስ ፖሊሲዎች መተግበርን እና አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታትን ያካትታል፡፡

ዲፕሎማሲ ወይንም የኹለትዮሽ ግንኙነት ማለት ሀገራት በሰላማዊ መንገድ እርስ በእርሳቸው አገራዊ ጉዳዮቻቸውን የሚፈጽሙበት እና ሰጥተው በመቀበል መርህ የየአገራቸውን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብሩበት መንገድ ነው። ኢትዮጵያም ጥንታዊ የዲፕሎማሲ ታሪክ ካላቸው ሀገራት አንዷ ነች፡፡

ሀገሪቱ ከጥንት ጀምሮ በሃይማኖት በባህልና በንግድ እንቅስቃሴ ከበርካታ ሀገራት ጋር የጠነከረ ግንኙነት መሰረት የጣለችና በዲፕሎማሲው መስክም ተጠቃሽ ተሞክሮ ማዳበር የቻለች ሀገር ነች፡፡ ከዋሻ ዲፕሎማሲ ዛሬ እስከ ደረስንበት እስከ ዘመነኛው የዲጂታል ዲፕሎማሲ ድረስ ዕምቅ ታሪክና ተሞክሮ ያላት ነች፡፡

በእነዚህ የዲፕሎማሲ ሂደቶች ኢትዮጵያ በውጭው ዓለም ገናና ሆና እንድትታይና ሉላዊነቷና አንድነቷ ተጠብቆ እንዲቆይ ያስቻሉ ስራዎች ተከናውነዋል። በየዘመናቱ የነበሩ የኢትዮጵያ መሪዎችም ሀገሪቱን ከውጭውም አለም ጋር የሰመረ ግንኙነት እንዲኖራትና አልፎ ተርፎም ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገር እንድትሆን ዘርፈ ብዙ ግንኙነቶችን ሲመሰርቱ ቆይተዋል፡፡

በዘመነ አክሱም የዲፕሎማሲ ዘመን የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ መሰረቶች ተጥለዋል።ከእነዚህ መካከል በንጉስ ኢዛና ዘመን ንግድና ኃይማኖትን መሰረት ያደረጉ ግንኙነቶች ተፈጥረዋል፡፡ ወደ መካከለኛው ዘመን ስንመጣ የዲፕሎማሲው ዋነኛ አቅጣጫ የሀገርን ሉአላዊነትና አንድነትን ማጽናት ነበር፡፡

ኢትዮጵያ ከውስጥም ከውጭም የሚመጡባትን የሉአላዊነት አደጋዎች በመጋፈጥና አንድነቷን አስጠብቆ መሄድ የዲፕሎ ማሲው ቁልፍ አቅጣጫ ነበር፡፡በተለይም በኃይማኖትና በባህል ታጥሮ የቆው የዲፕሎማሲ ግንኙነት ወደ ንግድና ወታደራዊ ግንኙነት ያደ ገበት ጊዜ ነበር፡፡

19ኛው ክፍለ ዘመን የአውሮፓና የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያንሰራራበት ፤ አውሮፓውያን የአፍሪካ አህጉርን በተጠናከረ ሁኔታ ማሰስ የጀመሩበት ጊዜ ነበር፡፡ አውሮፓውያን በሳይንስ ምርምር እና በሚሽነሪዎች አማካኝነት የክርስትና ሃይማኖትን ለማስፋፋት ከፍተኛ ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡ በተጨማሪም ንግድን ማስፋፋት ሌላው ዓለማቸው ነበር፡፡

በወቅቱ የነበሩት የኢትዮጵያ መሪ አጼ ቴዎድሮስ ሀገራችውን ከዘመነ መሣፍንት ትርምስ በመታደግ አንድነቷን ለማረጋገጥና ለማዘመን ራዕይ ሰንቀው መታገል ቢጀምሩም በአገር ውስጥ የተጠናከረ አመጽ ስለተነሳባቸው ይህንኑ ለማስታገስ ላይ ታች የሚሉበት ጊዜ ነበር፡፡ በተጨማሪም ከአውሮፓ የመጡ የሃይማኖት ሰባኪዎች ጋር ግብግብ በመግጠም ለአገራቸው የሚያስፈልጋት የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎችን ማስፋፋት እንጂ የሃይማኖት ትምህርትማ እዚህ ያሉት የኔ ሰዎች ምን ይሰራሉ በማለት ይሞግቱ ነበር፡፡

የአጼ ቴዎድሮስ አገራዊ የተማከለ አስተዳደር የመፍጠርና የማፅናት ትግል ጠንካራ በሆነ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ታጅቦ እ.ኤ.አ በ1861 ዓ.ም ተጀመረ። በዚህም በ1862 ዓ.ም ለታላቋ ብሪታኒያ ንግስት ቪክቶሪያ በወቅቱ ለኢትዮጵያ ሉዐላዊነትና የግዛት አንድነት ስጋት ነው ባሉት ጉዳይ ላይ ካሜሩን በተባለ የእንግሊዝ ቆንሲል አማካይነት የትብብር ጥያቄና መልዕክት ፣መላካቸውን የታሪክ መዛግብ ያትታሉ ፡፡

የብሪታኒያ መንግሥት ይህን የትብብር ጥያቄ ሳይቀበለው በመቅረቱና መልስ በማጣታቸው ንጉሱ ተቆጥተው የብሪታኒያ መልክተኞችን እና ሌሎች አውሮፓዊያንን አማሰራቸው፤ይህ ርምጃቸው በሁለቱ መንግሥታት መካከል ዲፕሎማሲያዊ መቃቃር በመፍጠሩ ብሪታኒያ ጦር ወደማዝመት አድርሷታል።

በ1868 ዓ.ም በታላቋ ብሪታንያ ወራሪ ኃይልና በአፄ ቴዎድሮስ መካከል በመቅደላ ጦርነት ተካሄዷል ፤በወቅቱ አጼ ቴዎድሮ ስ የውስጥ ድጋፍ በማጣታቸውም በመቅደላ ለመሸነፍ የተገደዱበት እውነታ ተፈ ጥሯል ፡፡

በተመሳሳይም ከአጼ ሚኒሊክ አሁን እስከ ያሉ መሪዎች በሙሉ በየዘመናቸው የውጭ ወራሪዎችን በመመከትና የኢትዮጵያን አንድነትና ሉአላዊነት በማስከበር ረገድ የበኩላቸውን ተጋድሎ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ በተለይም አጼ ሚኒሊክም እና አጼ ኃይለ ስላለሴ ጣሊያንን የሚረቱበትን ዲፕሎማሲ ሲያማትሩና በተቻላቸው አቅም ሁሉ መሲዮኖቻቸውን በማሰማራት የሀገር ሉላዊነትና አንድነትን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተው ተንቀሳቅሰዋል ፡፡

በተለይ ኢትዮጵያ ከአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት (ከ1950ቹ) ጀምሮ የአፍሪካ አንድነት አስጠባቂ መሠረት፣ የፓን አፍሪካኒዝም መከታ ሆኖ ዘልቃለች፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ በየዘመናቱ የሚያጋጥማትን የሉአላዊነት ፈተናዎች በማለፍ ከራሷ አልፋ ሌሎች ጥቁር ህዝቦች መከታ በመሆን ዛሬ ላይ ደርሳለች፡፡የአፍሪካ አንድነትን በመመስረትና ለአፍሪካ ህብረት መመስረት ጉልህ አስተዋጽኦ በማበርከት የአፍሪካ ዲፕሎማሲ አንድርምጃ እንዲጓዝ የበኩሏን ድርሻ ተወጥታለች።፡

እንደሀገር ለዲፕሎማሲና ለውጭ ግንኙነት ትኩረት ከተሰጠ 116 ዓመታት የተቆጠሩ ሲሆን በእነዚህ አመታት በርካታ ፈተናዎችንና ስኬቶችን በማስመዝገብ ኢትዮጵያን ከነሙሉ ክብሯ ለዛሬው ትውልድ ለማስረከብ ተችሏል፡፡ 116 አመታትን ያስቆጠርው የኢትዮጵያ ዘመናዊ ዲፕሎማሲ በተለይ ባለፉት አምስት አመታት አዳዲስ ገጽታዎችን በመላበስ አድማሱን አስፍቶ ቀጥሏል፡፡

በተለይም ለቀጠናዊ ግንኙነት የመጀመሪያውን ትኩረት በመስጠት ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የጠበቀ ዲፕሎማሲያ ግንኙነት እንዲኖራት ተደርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ልማት በአስተማማኝ መሠረት የሚቆመው የኢትዮጵያ የውስጥ ሰላምና መረጋጋት ሲረጋገጥ እንደሆነ እና ይኸው ሰላምና መረጋጋት የሚጸናው ደግሞ ከጎረቤት አገራት ጋር ሰላማዊ ግንኙነትን በማዳበርና የአገራቱ ሰላምና መረጋጋት ሲረጋገጥ ነው ።

ለዚህም ከጎረቤት አገራት ጋር በወዳጅነት፣ በትብብርና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን በሚያመጣ መልኩ የተቃኘ ዲፕሎማሲ በመስራት መሆኑን ያስቀምጣል። ይህንኑ መሰረት በማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ(ዶክተር) ወደ ስልጣን በመጡ በጥቂት ቀናት ውስጥ የመጀመሪያ የውጭ ጉዟቸውን ያደረጉት ወደ ጎረቤት ሀገር ጂቡቲ ነው፡ ፡

ጂቡቲ ለኢትዮጵያ 95 በመቶ የወደብ አገልግሎት የምትሰጥ በመሆና እና ሁለቱ ሀገራት በኢኮኖሚው መስክ ከፍተኛ ትስስር ያላቸው ከመሆናቸው አንጻር ከጎረቤት ሀገራት ጂቡቲን ማስቀደማቸው ተገቢ ነበር ማለት ይቻላል፡ ፡ ከዚያም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀኑት ወደ ሱዳን ሲሆን በቀውስ ውስጥ የነበረችውን ሀገር ወደ ተሻለ መረጋጋት የሚወስድ የአስታራቂነት ሚና ተጫውታለች፡፡

በመቀጠልም ለ20 ዓመታት ያህል በጦርነት ስጋት ውስጥ የቆዩትን ኢትዮጵያንና ኤርትራን በማስታረቅና ግንነታቸውንም ወደ ተሻለ ደረጃ በማድረስ ቀጠናዊ ዲፕሎማሲው ወደ ከፍታ እንዲሸጋገር ኢትዮጵያ የመሪነቱን ሚና ተወጥታለች ፡፡ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ብሎም በአፍሪካ ደረጃ ሰላም አስጠባቂ ኃይል ሆና መውጣት ችላለች።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የጎረቤት አገራትን ሰላምና መረጋጋት የራስ ሰላምና መረጋጋትን ማስጠበቂያ መንገድ ነው ብሎ ስለሚነሳ፣ ኢትዮጵያ በተመድ እና በአፍሪካ ሕብረት ማዕቀፍ በአፍሪካ ቀንድ ብሎም በመላ አፍሪካ በሚከሰቱ ግጭቶች በወታደራዊ መስክ ሰላም አስከባሪ፣ በፖለቲካ መስክም የሰላም ሂደቶች (peacemaking) ዋና ተዋናይ በመሆን በአለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ በጎ ገጽታ መገንባት እና በቀጠናውም ዋና የሰላም አስጠባቂ ኃይል ሆና እንድትወጣ ያስቻለ ዲፕሎማሲ ተሰርቷል።

ሌላው ባለፉት አምስት ዓመታት በዲፕሎማሲው መስክል ላይ የታየው እምርታ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ መከተሏ ነው፡፡አዲስ በሆነው በዚህ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የበሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው በክብር ለመመለስ ችለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶክተር) በሱዳን በነበሩበት ወቅት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በእስር ቤት ይኖሩ የነበሩትን በማስፈታት በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ለመጀመሪያ ጊዜ ራሳቸው በተሳፈሩበት አውሮፕላን ከልዑካቸው ጋር ወደ ሀገር ቤት እንዲጓዙ ማድረጋቸው መንግሥታቸው ለዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳ የ ነበር፡፡

ለበርካታ ሀገራት በምሳሌነት የሚጠቀስና የዘመናዊ ዲፕሎማሲ አዲስ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ አንዱ ክስተት ኢትዮጵያ የተከተለችው አረንጓዴ ዲፕሎማሲ ነው፡፡ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት አመታት ከ32ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል አለም አስደንቃለች።በእነዚሁ አመታት አረንጓዴ አሻራ የአካባው መድህን መሆኑን በመረዳት ከራሷ አልፎ የጎረቤት ሀገራትም ተጠቃሚ እንዲሆኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች ወደ ጎረቤት ሀገራት በመላክና አብሮ በመትከልም የጋራ አካባቢን በጋራ የመጠበቅ መርህ እውን እንዲሆን መሰረት ጥላለች፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎንም የጎረቤት ሀገራት በኃይል አቅርቦት እንዲተሳሰሩ ኢትዮጵያ እያከናወነችው ያለችውም ተግባር አንዱ የኃይል አቅርቦት ዲፕሎማሲ ነው፡፡ኢትዮጵያ ከአባይ ግድብ እና ከግልገል ግቤ ሶስት የኃይል ማመንጫዎች የምታገኘውን ኃይል ከራሷ አልፋ የጎረቤት ሀገራትን ልማት እንዲያቀላጥፍ ለኬንያ፤ለጅቡቲ፤ለሱዳን፤ለደቡን ሱዳን ኃይል በማቅረብ ላይ ትገኛለች፡፡

ዘመናትን የዋጀው የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ጉዞ ሀገርን አጽንቶ ህዝብን ማዕከል አድርጎ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ዛሬም ግስጋሴውን ቀጥሎ ከሀገር አፍሎ ቀጠናዊ ትስስርን ማዕከል አደርጎ ዕይታውን አስፍቷል።ከመንግሥት ለመንግሥት ግንኙነት አልፎ ወደ ኢኮኖሚያዊና ቀጠናዊ ትስስር የሰፋው ዲፕሎማሲዊ ግንኙኘትም አዲስ ገጽታ የተላበሰ ከመሆኑም ባሻገር ኢትዮጵያን በዲፕሎማሲው መስክ ያላትን ተጽዕኖ ፈ ጣሪነት የሚያጎላ ነው፡፡

ከጥንት እስከ ዛሬ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ አንዱ መለያ ስደተኞችን የመቀበል ዲፕሎማሲ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በቀደመ ታሪኳ የፍልሰት መነሻ ሳትሆን መዳረሻ ነበረች። ከተለያዩ ሀገሮችም ፈልሰው የመጡ የሌላ ሀገር ዜጎችን ማለትም አይሁዶንች፣ አርመኖችን፣ ዓረቦችን፣ ግሪኮችን፣ ቱርኮችንና ሌሎችን ተቀብላ በማስተናገድ ትታወቃለች፡፡የነብዩ ሞሃመድ ተከታዮችን ከተቀበለችበት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ የበርካታ ሀገራትን ስደተኞች በመቀበል ስሟ በታሪክ ድርሳናት ጭምር የሚወሳ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ስደተኞችን የመቀበልና የማስጠለል የረዥም ጊዜ ታሪክ አላት፡፡ አሁንም የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን በመሸሽ ሀገራቸውን ጥለው የሚሰደዱ የጎረቤት ሀገር ዜጎችን አስጠልላለች። በዚህም ወደ አንድ ሚሊዮን ለሚጠጉ ስደተኞች ኢትዮጵያ ቤታቸው ሆናለች፡፡ ይሄም ሰብዓዊነት ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ግዴታዋን ለመወጣት ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል።

የቡና ዲፕሎማሲ ሌላኛው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ መገላጫ ነው፡፡ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ሀገር እንደመሆኗ መጠን ቡናን በማስቀደም በየትኛውም ሀገር በሚዘጋጁ ባዛሮችና ኤግዚቢሽኖች ላይ በመሳተፍ ዲፕሎማሲያዋን በማጠናከር ላይ ትገኛለች፡፡ኢትዮጵያን የሚጎበኙ የሀገር መሪዎችም የኢትዮጵያን ጥዑም ቡና እንዲቀምሱ በማድረግ አይረሴ ጊዜ እንዲያሳልፉና ኢትዮጵያን ከልባቸው እንዲያኖሩ የማድረግ ስራ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ 44ኛው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የዚሁ ዕድል ተቋዳሽ ነበሩ፡፡

ዓለም በፈጣን የቴክኖሎጂ ለውጥ ውስጥ ትገኛለች፡፡ ዲፕሎማሲውም እንደጥንቱ በሰው አቅም ብቻ ሳሆን በቴክኖሎጂ የሚታገዝበት ደረጃ ላይም ደርሷል፡፡ ይህን መነሻ በማድረግም ዲጂታል ዲፕሎማሲን ሁነኛ የዲፕሎማሲ ማሳለጫ መንገድ ማድረግ ጀምራለች፡፡ የዲጂታል ዲፕሎማሲ አውዶችን የንግድና ኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስተዋወቅ፣ የኢኮኖሚ አቅሟን ለማሳየት እንዲሁም የውጭ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ትገኛለ ች፡፡

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን  ጥር 2 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You