በውስን ወቅቶች ተገድቦ የሚገኘውን የቱሪስቶች ፍሰት ለመለወጥ ምን ይደረግ?

የገና በዓልን በላልይበላ፣የጥምቀት በዓልን ደግሞ በጎንደር፣ በዓላቱና አካባቢዎቹ ተነጣጥለው የማይታዩ ናቸው። በእነዚህ የበዓላት ወቅት አስጎብኝ ድርጅቶች፣ሆቴልቤቶች፣መዝናኛዎች፣ ባህላዊ አልበሳትና ጌጣጌጥ መሸጫዎች፣ ሌሎችም ተያያዥ ሥራዎችን የሚሰሩ ሁሉ በዚህ ወቅት በስፋት ስለሚንቀሳቀሱ ቱሪዝሙ ይነቃቃል።

እንደ ሀገር በምጣኔ ሀብት እድገት ላይ ከፍ ያለ ሚና ይኖራቸዋል ተብለው ከተመረጡ አምስት የእድገት ምንጮች አንዱ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ነው። ቀደም ብለው የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከዘርፉ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለመሆን፤እንደሀገር ሰባት ነጥብ አራት ሚሊዮን ቱሪስቶችን ለመሳብ ታቅዶ ሲሰራ ቆይቷል። የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ሰላምና መረጋጋትን ይፈልጋል።

ኢትዮጵያ ከዘርፉ የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን እየተንቀሳቀሰች ባለችበት ወቅት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ተካሂዶ በነበረው ጦርነት፣ በሌሎችም አካባቢዎች ሰላምና መረጋጋት ባለመኖሩ ይህን ተከትሎም የተለያዩ ድጋፎች እንዳታገኝ በውጭ በተፈጠረባት ተጽእኖ፣ በዓለም ተከስቶ በነበረው ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያቶች እና ይህንኑ ተከትሎ የዓለም ሀገራት ለዜጎቻቸው የጉዞ ክልከላ ማድረጋቸው የቱሪስት ፍሰቱን በእጅጉ ቀንሶታል።

ኢትዮጵያ በዚህ ተግዳሮት ውስጥ ሆና ዘርፉን ለማንቀሳቀስ ጥረቶች ስታደርግ የቆየች ቢሆንም አሁንም ብዙ ሥራ ይጠበቃል። በተለይም ሰላም ማስፋትና ለቱሪዝሙ አቅም የሚሆኑ የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን እና መስህቦችን ማስተዋወቅ ይገባል።

ገናና የጥምቀት በዓላት ለዘርፉ መነቃቃት መልካም አጋጣሚዎች ናቸው። በዚህ ጊዜ በሀገር ውስጥም በውጭም ቱሪስቶችን በመሳብ ተጠቃሚ ለመሆን የተከናወኑ ስላሉ ተግባራት እንዲሁም ኢንዱስትሪው ከወቅታዊ እንቅስቃሴ ወጥቶ ዘላቂ እንዲሆን ምን መደረግ አለበት? ስንል የዘርፉን ባለሙያዎች አነጋግረናል።

የኢትዮጵያ ቱር ኦፕሬተርስ አሶሴሽን ፕሬዚዳንት አቶ ፍጹም ገዛኸኝ እንደገለጹት፤ኢትዮጵያ በውስጥ የገጠማትን የሰላም እጦት ተከትሎ ኤምባሲዎች የሚያሰራጯቸው እንዲሁም ሀገራት ለዜጎቻቸው የሚያስተላልፉት ማስጠንቀቂያዎችና የጉዞ ክልከላዎች የቱሪስቱን ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ሁኔታ ገድቦታል። በዚህ ምክንያት የጉዞ ጥቅሎችን ለጎብኚዎች ለማቅረብ እና ቱሪስቶችን ለመሳብ ፈተና ሆኗል።

በየዓመቱ በገና እና የጥምቀት በዓላት ላይ ለመታደም አስቀድመው ምዝገባ ያካሄዱ ቱሪስቶች ጉዞአቸውን በመሰረዝ ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣው የቱሪስት ቁጥር እየቀነሰ ነው። ጥቂቶቹም ቢሆኑ የሚመጡት ቱር ኦፕሬተሮች ኃላፊነት እንደሚወስዱ በሚሰሩት ከፍተኛ የማሳመን ሥራ ነው። እየተደረጉ ያሉት ዝግጅቶችም ይመጣሉ ተብሎ በሚጠበቁ የእንግዶች ልክ ነው።

እንደ አቶ ፍጹም ገለጻ፤ ቱሪስቶችን ከተለያዩ ዓለማት ለመሳብ የአስጎብኝ ድርጅቶች(ቱር ኦፕሬተሮች) ድርሻ ከፍተኛ ነው። ቱሪስቱ በሚመቸው ጊዜ እንዲመጣ፣በመጓጓዣ፣በሆቴል፣በመዝናኛ አገልግሎቶች፣ ለሚያገኘው አገልግሎት ስለሚከፍለው ዋጋ፣ የሚጎበኛቸውን አካባቢዎች ጨምሮ የጉዞ ጥቅሎችን በማዘጋጀት አስቀድሞ በማሳወቅ ቱሪስቱን ለመሳብ ጥረት ያደርጋሉ።

ባለው ተሞክሮ ቱሪስቶች ለመጎብኘት የሚዘጋጁት ከሁለትና ከሶስት ዓመት በፊት ነው። ከያዙት ፕሮግራም ውጪ የሚንቀሳቀሱ ባለመሆናቸው ዛሬ ነገሮች ቢስተካከሉ በአንድ ጊዜ ተነስተው የሚመጡ አይደሉም። አሁን ባለው ሁኔታም ጉዞ የሚሰርዙ እንጂ ለመምጣት የሚዘጋጁ አይደሉም።

ጎብኚዎች ያለኢንሹራንስ ስለማይንቀሳቀሱ ከሀገራቸው ከመነሳታቸው በፊት የጉዞ ኢንሹራንስ ይገዛሉ። በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከሀገራቸው ኢንሹራንስ ማግኘት ስለማይችሉም ጭምር ነው የማይመጡት። ኢንሹራንሳቸው ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሸፈንላቸው ለማድረግ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የጉዞ ኢንሹራንስ እንዲሸጡ የሚያስችል ህግ የለም። ይህ ሁሉ ነው ለዘርፉ ተግዳሮት የሆነው።

አቶ ፍጹም እንደሚሉት አሁን አማራጩ ክፍተቱን ለመሙላት የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን በማበረታት መጠቀም ነው። አንዳንድ አስጎብኚ ድርጅቶች ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ጎብኚዎችን በማነቃቃት ወደ ላልይበላ፣ጎንደርና ወደ ሌሎችም የቱሪዝም መዳረሻዎች በመውሰድ እና በመንቀሳቀስ ሁኔታዎችን ለመቀየር ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ፤ ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ክትባትን ጨምሮ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በመሥራት ሁኔታዎች ከተስተካከሉና የፀጥታውም ሥጋት መጠነኛ ለውጦችን ካሳየ ወዲህ እንደሀገር የቱሪዝም እንቅስቃሴው መሻሻል እያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።

በጦርነቱ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ተጎድቶ የነበረው በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል መሆኑንና ሰላም ባለባቸው የሀገሪቱ ክፍሎች በደቡብ ኢትዮጵያ፣በአዲስ አበባ ከተማም የኮንፈረንስ ቱሪዝም ጋር በተያያዘ በርካታ እንቅስቃሴዎች መደረጋቸውን አስረድተዋል። በሀገር ውስጥ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ብቻ ሳይሆን፤ ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑ በውጭ ከሚገኙ አስጎብኚ ድርጅቶች ጋር በመሥራት ቱሪስቶችን እንዲልኩ ጥረት መደረጉን አቶ ስለሺ ጠቁመዋል።

በህዳር ወር በእንግሊዝ ሀገር በተካሄደው ዓለም አቀፍ የቱሪዝም የጉዞና የንግድ ጉባኤ ላይ ሚኒስቴሩ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር መሳተፉንና በዚህም ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ፣የገበያ ዕድል በመፍጠር፣በዓለም መገናኛ ብዙኃንም መረጃዎችን በማድረስ ቱሪስቶችን ለመሳብ አጋጣሚውን መጠቀም መቻሉን አስረድተዋል።

በሀገር ውስጥም ቱሪስቶችን ተቀብለው የሚያስተናግዱ የተለያዩ አገልግሎት ሰጪዎች እንዲነቃቁ ስልጠና መሰጠቱን፣ ቱሪስቶች ከመጡ በኋላ የመረጃ መዛባት እንዳይፈጠር በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ የቱሪስት መረጃ ማዕከል መቋቋሙን ገልጸዋል።

አቶ ስለሺ እንዳሉት፤ በዚህ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ቱሪስቶች ገናን በላልይበላ፣ጥምቀትን ደግሞ በጎንደር ለማክበር ስለሚመጡ የአየር መጓጓዣ ችግር እንዳይገጥማቸው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ቀድሞ በጋራ ምክክር አድርጓል። አየር መንገዱ አውሮፕላኖችን መድቦ 24 ሰአት ለመሥራት ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጧል።

ከመስከረም እስከ ጥር ባሉት ወቅቶች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ቱሪስት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣበት ወቅት መሆኑንና በተለይም ገና እና ጥምቀት በዓላት በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ቱሪስቶች የሚታደሙበት፣ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውም ከመቼውም ጊዜ በላይ የሚነቃቃበትና ዘርፉ ለኢኮኖሚው የሚያበረክተው ድርሻም ከፍ የሚልበት እንደሆነ ያለፉ ጥናቶችና መረጃዎች ዋቢ አድርገው ገልጸዋል። ከአውሮጳ፣ከአሜሪካን እና ከሌሎችም አካባቢዎች ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ኢትጵያውያን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ቱሪስት ይጠበቃል ብለዋል።

እንደ አቶ ስለሺ ማብራሪያ ቱሪስቶች በነዚህ ወቅት የሚሳቡት፤ በሌሎች የዓለም ክፍሎች የማያገኙት በዓል መሆኑ አንዱ ሲሆን ሌላው ገፊ ምክንያት የውጪዎቹ የራሳቸውን የገና በዓል እና አዲስ ዓመት ካከበሩ በኋላ የእረፍት ጊዜ ስለሚኖራቸው ለጉብኝትና ለመዝናናት ያውሉታል። ኢትዮጵያ ሳቢ የሆነ የቱሪስት መዳረሻ ስላላትም ቀዳሚ ምርጫቸው አድርገው ይመጣሉ። በገናና በጥምቀት በዓላትም በብዙ ሺ የሚቆጠር ቱሪስት እንደሚመጣ ተስፋ ተደርጓል።

በዘላቂነት ግን ሥራዎችን መሥራት እንደሚያስፈልግ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። በዚህ በላይ አቶ ፍጹም እንዳስረዱት፤ቱሪስቶች በተደጋጋሚ ጉዞ ሲሰርዙ ኢትዮጵያ የቱሪዝም መዳረሻ መሆኗን ከሚያመልክት ማፕ ላይ የምትሰረዝበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል። ይሄ ሁኔታ ከተፈጠረ ዘርፉን ወደነበረበት ለመመለስ ወይንም ቱሪስት ለመሳብ ረጅም ጊዜ ሊወስድና ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል።

አሁን ላይ ቱሪስት ባይመጣ፤ለሚቀጥለው ይመጣል ብሎ ቀለል አድርጎ መውሰድ አይገባም። አስጎብኚ ድርጅቶች ላይም ሆነ በሀገር ደረጃ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ በማሳጣት ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል ብለዋል።

ወቅትን ተከትሎ ቱሪስትን ለመሳብ ከሚደረግ እንቅስቃሴ ለመውጣት ሀገራዊ የንቅናቄ ሥራ ይጠይቃል። በዚህ ረገድም የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ በአየርና በየብስ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ላይ የተሰማሩ፣ አስጎብኚ ድርጅቶች፣ሆቴልና መዝናኛዎች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በአጠቃላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚሰሩ ባለድርሻ አካላት በአንድነት መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው እንደሚሉት፤ በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ላይ የሚሰሩ ሌሎችም ሀገሮች ወቅታዊነትን ቀይረው ያልተቋረጠ የቱሪስት ፍሰት እንዲኖራቸው ማድረግ የቻሉት የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በጋራ ንቅናቄ በመፍጠር ነው።

‹‹እንደ አንድ አስጎብኚ ድርጅት ወቅትን የተከተለ ሳይሆን ዓመቱን ሙሉ ቱሪስቶች ወደ ሀገራችን እንዲመጡ ነው የምንፈልገው። ዘርፉን ወቅታዊ ያደረገው አንዱና የመጀመሪያው የአየር ንብረት ሁኔታ ነው። የክረምት ወቅት ቱሪስት ለመሳብ ምቹ አይደለም። ቀድሞም ቢሆን የነበረው የመሠረተ ልማት አለመሟላት በክረምት ወቅት ለጉዞ የበለጠ አስቸጋሪ ነው። ስለዚህም ከመስከረም እስከ ጥር ያለው ወር ለቱሪስቶች ተመራጭ ነው።

ሌላው ዘርፉ ወቅታዊ እንዲሆን ያደረገው የገበያ ሁኔታ ነው። ገበያው ትኩረት ያደረገው በምዕራብ አውሮፓና ሰሜን አሜሪካን ባሉ ሀገሮች ላይ ስለነበር ነው። ከእነዚህ ሀገራት የሚመጡ ቱሪስቶችን መሳብ የሚቻለው ከመስከረም እስከ መጋቢት ባሉት ጊዜያቶች ነው። ከዚህ ውጪ ከነዚህ ሀገራት ገበያ ማግኘት አይቻልም። ›› ብለዋል።

አቶ ስለሺ እንደሚሉት በውስን ወቅቶች ተገድቦ የሚገኘውን የቱሪስቶች ፍሰት ለመለወጥ እና የገበያ እድል ለማስፋት በቱር ኦፕሬተሮች በኩል ከቱሪዝም ሚኒስቴር እና ኬሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የበኩላቸውን ሚና ሲወጡ ቆይተዋል።

በኢትዮጵያ የቱሪስት መሳቢያ ወቅቶች አይደሉም በሚባሉ ጊዜያቶች ቱሪስቶችን ሊያመነጩ ይችላሉ ተብለው በሚታሰቡ ደቡባዊ አውሮፓ ሀገሮች ጭምር በመሄድ እንዲሁም ክረምቱ ጠንካራ ባልሆነባቸውና የቱሪዝም መዳረሻ በሆኑ የኢትዮጵያ ክፍሎችን በመለየት፣ የቱሪስቱን አቅም ያገናዘበ የጉዞ ጥቅሎችን በማዘጋጀት ጭምር ቱሪስቱን ሊስቡ የሚችሉ የተለያዩ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ቱሪስቶችን ለመሳብ የተደረጉ ጥረቶች ይጠቀሳሉ።

በዚሁ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ቱር ኦፕሬተርስ አሶሴሽን ፕሬዚዳንት አቶ ፍጹም ገዛኸኝ እንደገለጹት፤ ዓመቱን ሙሉ የቱሪስት ፍሰት እንዲኖርና የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ዘላቂነት ለማረጋገጥ የተጀመሩት ሥራዎች ተጠናክረው እንዳይቀጥሉ ሀገሪቱን የገጠማት የውስጥ አለመረጋጋትና ከዚህ ጋር ተያይዞም የተፈጠረው ጫና እና ተያያዥ ጉዳዮች ተጽእኖ አሳድረዋል።

ችግሮች ቢኖሩም ጥረቶች መቀጠል እንዳለባቸው የሚገልጹት አቶ ፍጹም፤ ‹‹ኢትዮጵያ እምቅ የቱሪዝም ሀብት ባለቤት ናት ማለት ብቻውን በቂ አይደለም ወደ ገንዘብ መለወጥ ያስፈልጋል። የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ሲኖራቸውና ማህበረሰቡም የጥቅሙ ተካፋይ ሲሆን ነው ትርፍ አግኝተንበታል ማለት የምንችለው ››ሲሉ አስረድተዋል።

እንደ አቶ ፍጹም ማብራሪያ፤ በዘርፉ ላይ የሚንቀሳቀሰው ሁሉ እያንዳንዱ ኃላፊነቱን ሲወጣና በቅንጅትም ሲንቀሳቀስ ነው ውጤት ማስመዝገብ የሚቻለው። አስጎብኚ ድርጅቶችም ያሉትን ቅርሶች በደንብ አውቀውና መዝግበው በዘርፉ ላይ በቂ እውቀት ኖሮአቸው የጉዞ ጥቅሎችን አዘጋጅተው ለገበያ ማቅረብ ሲችሉ ነው ቱሪስቶችን መሳብ የሚቻለው ብለዋል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ስለሺ እንደሚያብራሩት ሰሜን አሜሪካና አውሮፓ ላይ ተንጠልጥሎ የቆየው ቱሪዝም ገበያ ወደ አፍሪካም ፊቱን እንዲያዞር የማድረግ ሥራ እየተሰራ ነው። አፍሪካ ውስጥ ትልቅ የቱሪዝም ገበያ እንዳለ ከኬንያ ተሞክሮ መውሰድ ይቻላል። ኬንያ ሁለት ሚሊዮን ቱሪስት ስትቀበል አንድ ሚሊዮን ቱሪስት የምትቀበለው ከአፍሪካ ሀገራት ነው። ኢትዮጵያ ግን እንዲህ ያለው ተሞክሮ አልነበራትም።

‹‹አፍሪካውያን የጋራ ታሪክ አለን፣ አፍሪካውያን አፍሪካውያንን ያፈቅራሉ የሚል እሳቤ ይዘን የአፍሪካ ገበያ ላይ እየሰራን ነው። በቅርቡ በሚካሄደው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ የአፍሪካ መሪዎች ሲመጡ በጥሩ መስተንግዶ ለመቀበል ለአፍሪካ መሪዎች የሚሆኑ የተለያዩ የቱሪዝም ፓኬጆች ቀርጸናል። በአዲስ አበባና በዙሪያው እንዲጎበኙ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እንሰራለን››ሲሉ አስረድተዋል።

የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባም ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ትልቅ እድል ይፈጥራል ያሉት አቶ ስለሺ፤ ኢትዮጵያ የጥቁር ህዝቦችን ነፃነት ከማረጋገጥ፣የአፍሪካ ኅብረትም እንዲመሰረት አስተዋጽኦ ከማበርከት አንጻር ትልቅ ታሪክ እንዳላት ገልጸዋል።

በተለያየ ምክንያቶች የተጎዳውን የቱሪዘም ኢንዱስትሪ ለማነቃቃት ሁሉም ባለድርሻ አካላት እንዲረባረቡ የዘርፉ ባለሙያዎች ጥሪ አቅርበዋል።

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን ታህሳስ 30/2016

Recommended For You