የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ጥረት የሚያሻው የከተማ ግብርና

ለአንድ ሀገር የዜጎችን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ወሳኝና ቀዳሚ ሥራ ነው። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ኢኮኖሚያቸው በግብርና ላይ ተመስርቶ ለኖረ ሀገሮች የምግብ ዋስትና ዋነኛው ማረጋገጫ መንገድ ግብርና እንደመሆኑ ለእዚህ ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ወሳኙ ተግባር ይሆናል። የግብርና ምርቶች ፍላጎት እየጨመረ ላለበትና ዋጋቸውም እየናረ ለመጣበት ሀገር ደግሞ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የቅድሚያ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ነው፡፡

ከከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዞ በከፍተኛ መጠን እያደገ የመጣውን ህዝብ ለመመገብ በግብርና ውስጥ ያለውን እምቅ አቅም አሟጦ መጠቀም ይገባል። የከተማና ከተሜዎች መስፋፋት መሰረቱን ግብርና ላይ ባደረገበት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ከተማና ከተሜነት ሊያሳደር የሚችለውን አሉታዊ ተጽእኖ ለመቀነስ ግብርናው ላይ መስራትን የግድ ይላል። በተለይ በግብርና ምርቶች ላይ የሚታየውን የዋጋ ማሸቀብ ለመቆጣጠር አንዱ መፍትሄ ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ነው።

ይህንን ችግር ለመፍታት የኢትዮጵያ መንግሥት በገጠር የአርሶና አርብቶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ሰፋፊ የድጋፍ ፕሮጅክቶችን ነድፎ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል። ይህን ተከትሎም የግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት እያደገ ይገኛል።

ከዚሁ ጎን ለጎንም በከተሞችና በከተሞች ዙሪያ የከተማ ግብርና ስራዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ። በእዚህም የወተት፣ የዶሮና እንቁላል፣ የአትክልትና የመሳሰሉት ልማት ስራዎች በስፋት እየተሰሩ ናቸው። ይህም ስራ በተለይ በሌማት ቱሩፋት የበለጠ እንዲጠናከር እየተደረገ ነው።

የከተማ ግብርና ስራው በተቀናጀ መልኩ እንዲመራ ለማደረግም የተለያዩ መርሃ-ግብሮች እየተከናወኑ ይገኛሉ። ለዚህም ይረዳ ዘንድ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የከተማ ግብርና አሁናዊ ገፅታ ምን እንደሚመስል ፤ ያሉ ምቹ ሁኔታዎችንና ተግዳሮቶችን የሚዳስስ ጥናት አጥንቶ በቅርቡ ይፋ አድርጓል።

በጥናቱ በዋናነት ባለድርሻ አካላት በኩል ተቀናጅቶና ተናቦ ያለመስራት ችግር መስተዋሉ ተለይቷል። ይህ ችግር ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንዳታገኝ ያደረጋት መሆኑን ለማወቅ መቻሉን የኢንስቲዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ድሪባ ገለቴ ጠቁመዋል።

እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ ኢንስቲትዩቱ የሀገሪቱን የግብርና ዘርፍ ለማዘመንና የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት የሚጨምሩ ቴክኖሎጂዎችን ከማፍለቅና ከማላመድ ጎን ለጎን የከተማ ግብርና በሰፊው ይተገበር ዘንድ በርካታ ተግባሮችን አከናውኗል። በአሁኑ ወቅት የከተማ ግብርና እንደሀገር ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት ያለ ዘርፍ ሲሆን፣ ተቋሙም ይህን ዘርፍ በመደገፍ የበኩሉን ለመወጣት የከተማ ግብርና አቅም፣ አተገባበር ልምዶችና ተግዳሮቶች ላይ ምርምር ሲያደርግ ቆይቷል።

ዶክተር ድሪባ በጥናቱ በከተማና በከተማ ዙሪያ የሚካሄደው ግብርና ትልቅ የገቢ ምንጭ መሆኑን፤ የእንስሳት ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በስፋት እየተመረቱ መሆናቸውን ለማየት መቻሉን ይጠቅሳሉ። በተለይም ዶሮ እርባታ፤ እንስሳት ማደለብ እና የወተት ሃብት ልማት የከተማዋን ህዝብ ፍላጎት ለማሟላት ትልቅ አቅም እየሆነ መምጣቱን ለመዳሰስ መቻሉን ያመለክታሉ።

‹‹እነዚህ የከተማ ግብርና ሥራዎች የቤተሰብ የምግብ ዋስትናንም ከመደገፍ፤ ገቢ ከማስገኘት ፤ ለወጣቶችም ሆነ ለሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች የሥራ እድል ከመፍጠር አኳያ ትልቅ ሚና የሚጫወቱ መሆናቸውን አይተናል›› ይላሉ።

ይህ ዘርፍ የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ እንደመሆኑ እና በተለይ በሌማት ቱሩፉት ፕሮጀክት የሚደገፍ መሆኑንም ጠቅሰው፣ የከተማ አስተዳደሮች ይህንን ሥራ እንደ ዋና ስራቸው አድርገው በመንቀሳቀስ በኩል ክፍተት እንዳለባቸው በዚህ ጥናት መለየቱን ተናግረዋል። ‹‹በተለይ ይህንን ሥራ በቋሚነት ለመስራት የመዋቅር ችግር መኖሩን ለማወቅ ተችሏል። የግብዓት አቅርቦት ችግር ፣ የሰለጠነ እና በቂ ባለሙያ እጥረት መኖሩንም ባደረግነው ጥናት አውቀናል›› ሲሉ ያስረዳሉ።

እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ በኢትዮጵያ ብዙ ጊዜ ጥናትና ምርምር ቢካሄድም፣ ወደ ተግባር ማምጣቱና በተጨባጭ አርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ሰፊ ክፍተት ይታያል። ይህንን በሚመለከተም ኢንስቲትዩቱ በህግ ከተሰጠው ምርምር የማድረግ፤ ቴክኖሎጂ የማመንጨት፤ የማማከር፤ የቴክኒክ ደጋፍ ማድረግና መነሻ ቴክኖሎጂዎችን ከማባዛት ባለፈ ሰፋ ያለ የማባዛትና ቴክኖሎጂዎችን የማከፋፋል ሥራ አይሰራም። ተቋሙ ያወጣውን ቴክኖሎጂ መረጃ ካስተዋወቀ በኋላ ወደ አርሶ አደሩ ይዞ መሄድ የሚገባው የኤክስቴሽን ስርዓቱ ነው።

ኢንስቲትዩቱ ለከተማ ግብርና ምርትና ምርታማነት ማደግ በሚገባ ሚናውን ስለመወጣቱ ተጠይቀውም ‹‹እኛ በህግ የተሰጠነን ሃላፊነት ብንወጣም ምርታማትን ለማሳደግ በአጠቃላይ በእሴት ሰንሰለቱ ያሉ አካላት ካልደገፉ የምርምር ተቋሙ ብቻውን ለውጥ ሊያመጣ አይችልም፡›› ሲሉ መልሰዋል። አያይዘውም ‹‹እኛ በዋናነት ተግባራዊ ምርምር ላይ አተኩረን በተግባር ውጤት ሊያመጣ የሚችል ሥራ ብንሰራም፣ በሀገሪቱ በአጠቃላይ በእሴት ሰንሰለቱ ላይ ያለነው አካላት ተሳስረን ባለመስራታችን የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አልተቻለም›› ሲሉ አመልክተዋል።

በተለይም በከተማና በከተማ ዙሪያ ለሚከናወን የግብርና ሥራ ቴክኖሎጂውን ተደራሽ ማድረግ የሚችል አካል መፈጠሩ አጠያያቂ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ቴክኖሎጂ ከማመንጨት ጀምሮ አርሶ እና አርብቶ አደሩ ዘንድ እስከሚደርስ ድረስ ያሉት አካላት ተሳስረው ለውጤታማነት መስራት ላይ ሰፊ ክፈተት መኖሩን ይጠቅሳሉ። ምርምሩ የሚያከናውናቸው ተግባራዊ የምርምር ውጤቶች በቀጥታ አርሶ አደሩ ጋ ሄደው ውጤት የሚያመጡ መሆናቸውን አመልክተዋል። ለአመታት የዘለቀው ተቀናጅቶ አለመሰራት የኢንስቲትዩትን ልፋት አመድ አፋሽ እንዳደረገው ያስረዳሉ።

‹‹በመሰረቱ ጠንካራም ባይሆን ከተወሰኑ አካላት ጋር ተቀናጅተን የምንሰራበት አግባብ አለ። ቅንጅቱም ሆነ ትስስሩ ቀጣይነት ያለው ያለመሆኑ የሚፈለገው ውጤት እንዳይመጣ አድርጎታል›› ይላሉ። የግንኙነት መስመሩ እስከ ወረዳ ድረስ መዝለቅ እንዳለበት ተናግረው ፣ ለዚህም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተናበውና ተቀናጅተው አብረው የመስራት ባህላቸውን ሊፈትሹ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት። ሁሉም በጓዳው የራሱን ስራ ብቻ ቢሰራ ውጤት አያመጣም፣ ይልቁንም በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ያለውን ግንኙነት መሬት ላይ በማውረድ ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት መሰራት ይኖርበታል ሲሉም አስገንዝበዋል።

‹‹ይህንን ማድረግ ሰንችል ነው የአርሶ አደሩንም ሆነ የሌላውን ማህበረሰብ ህይወት ማሻሻል እና እንደ ሃገር ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆን የምንችለው›› የሚሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ለዚህ ደግሞ ምቹ የሆነ ፖሊሲ መኖሩንም አመልክተዋል። በፖሊሲው ማዕቀፍ ውስጥ እያንዳንዱ የዘርፉ ተዋናይ በቅንጅት በመስራት ሃላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቀዋል።

በግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የግብርና ኢኮኖሚክስ ምርምር አስተባባሪ ዶክተር እንሻው ሃብቴ በበኩላቸው፤ የከተማ ግብርና በመንግስት ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው መስኮች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከፖሊሲ ጀምሮ በምርምር ሆነ በልማት መደገፍ እንደሚገባ ታምኖበት እየተሰራ መሆኑንም ያመለክታሉ። ይህንን ታሳቢ በማድረግም በዘርፍ ያሉ የመረጃ ክፍቶችንን ለመለየት ታሳቢ ተደርጎ ጥናት መካሄዱን ያነሳሉ። ኢንስቲዩቱ በአዲስ አበባ ደረጃ ያካሄደው መነሻ ጥናት የባለድርሻዎች ሃሳብ ታክሎበት፤ ዳብሮ ለፖሊሲ ፣ ለምርምርና ለልማት ግብዓት በሚሆን ደረጃ የሚቀመር መሆኑን ነው የሚጠቁሙት።

የከተማ ግብርናን ማጠናከሩ ፋይዳው ብዙ እንደሆነ የሚናገሩት አስተባባሪው፤ በተለይም የከተማውን ህዝብ የገበያ ፍላጎት ሙሉ ለሙሉ ለመመለስ እንኳን ባይቻል የአቅርቦት ችግሩን ለማቃለል ወሳኝ ሚና እንዳለው ይገልጻሉ። አቅርቦቱ በተሻሻለ ቁጥር በከተማ ውስጥ የሚታየውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት የላቀ አስተዋፅኦ ማድረግ እንደሚችልም ይናገራሉ፡፡

በሌላ በኩል ከከተማ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ፈታኝ እየሆነ የመጣውን ሥራ አጥነት ለመቀነስ ሌላ አማራጭ እንደሚሆን ይጠቁማሉ። ‹‹ግብርና በባህሪው ሰፊ የሰው ሃይል ይፈልጋል፤ የከተማ ግብርና በተስፋፋ ቁጥር የስራ እድል የሚያገኙ በርካታ ወጣቶች ይፈጠራሉ፤ ከአምራቹ በተጨማሪ በገበያ ትስስር ውስጥ የስራ እድል የሚፈጠርለት ይኖራል›› ይላሉ። በተጨማሪም እያንዳንዱ ቤተሰብ በማምረቱ ምክንያት ሊያወጣ የሚችለውን ወጪ ለማስቀረትና የገቢ ምንጩንም ለማሳደግ እንደሚያስችል አስታውቀዋል።

‹‹በአሁኑ ወቅት ግን በመንግስትም ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ በመሆኑ በከተማ ደረጃ ዘርፉን የሚያስተባብሩ ፅህፈት ቤቶች ተከፍተዋል›› ያሉት አስተባባሪው፤ ይህም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፤ የገበያ ፍላጎቱን ለማርካት ከማገዙም በተጨማሪ ራሱን ችሎ የስራ እድል ለመፍጠር ያስችላል የሚል እምነት አላቸው።

በከተማ ደረጃ የሚከናወን የግብርና ስራ የከተማውን የምግብ ፍላጎት ማሟላት ያስችላል ተብሎ እንደማይታመን ጠቅሰው፣ ‹‹ያም ቢሆን ግን ከከተማ ግብርና የሚገኘው ምርት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ችግሩን ለማቃለል ያግዛል፤ አቅርቦቱም እንዲሻሻል ያደርጋል›› ብለዋል።

ከዚህ ባሻገር ግን የከተማ ግብርና በራሱ ብዙ ተግዳሮቶች እንዳሉበትም ነው ዶክተር እንደሻው ያስታወቁት፤ ‹‹ የከተማ ግብርና በባህሪው በጣም በዙ ውስብስብ ችግሮች አሉበት ፤ ግብርና መሬት ፤ ካፒታል፤ የሰው ሃይልና ግብዓቶች ይፈልጋል፤ እነዚህን በበቂ ሁኔታ አሟልቶ ምርታማነትን ማስቀጠል ፈታኝ ነው›› ይላሉ።

በተለይ ከተሞች እያደጉና እየሰፉ በመጡ ቁጥር የግብርና ሥፍራዎች እየቀነሱ መምጣታቸው ትልቅ ስጋት መሆኑንም አስታውቀዋል። ከመሰረተ ልማት ዝርጋታ ጎን ለጎን የእርሻ ቦታዎችን ከመለየትና ማዘጋጀት፤ በዘርፉ ለተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለየ መንገድ ድጋፍ ከማድረግ አኳያ የሚሰጠው ትኩረት እምብዛም እንዳልሆም ጠቁመዋል።

እንደ አስተባባሪው ማብራሪያ፤ በከተሞች ግብርና መስፋፋት አለበት ተብሎ መሬት በተለየ መልኩ ማዘጋጀት ከባድ መሆኑ ሥራው እንደታሰበው ውጤታማ እንዳይሆን ያደርገዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ህዝብ ተጨናንቆ በሚኖርበት ከተማ ውስጥ ከብት ማርባት አልያም ንብ ማነብ ሊያስከትሉ የሚችሉት አሉታዊ ተጽእኖ እንዳለም ጠቁመዋል።

የከተማ ግብርና ጥቅም ጥያቄ ውስጥ እንደማይገባም ጠቅሰው፣ ተናቦ መስራት ካልተቻለ የጎንዮሽ ጉዳት እንዳለው ሊሰመርበት የሚገባ መሆኑ ላይ እሳቸውም እምነቱ እንዳላቸው ተናግረዋል። ‹‹በተለይ ከመሬት አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ግልፅ የሆነ የመሬት አጠቃቀም መሪ እቅድ ሊኖር ይገባል። በተጨማሪም የከተማ ግብርና የሚካሄድባቸው የተከለሉ ቦታዎች ቢዘጋጁ የበለጠ ጠቃሚ ነው›› በማለትም አስገንዝበዋል።

ዶክተር እንደሻው እንዳሉት፤ ከግብርና ስራው የሚወጡ ተረፈ ምርቶች ለሌላ ጥቅም የሚውሉበትንም አማራጭ ማሰብ ያስፈልጋል። ባለሙያው፤ የከተማ አስተዳደሩና አማራቹ ተናበው የሚሰሩበት የግንኙት መስመር ሊኖር ይገባል። ይህ ሲሆን ነው ማህበረሰቡም ሆነ መንግስት ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉት።

‹‹ጥናቱ ከሁለት ዓመት በፊት በእኛ እንዲከናወን የከተማ ግብርና ፅህፈት ቤት ነው ጠይቆን ነው ወደ ስራው የገባነው›› ሲሉ በኢንስቲትዩቱ የግብርና ኢኮኖሚክስ ተመራማሪው ዶክተር ቶለሳ አለሙ ይናገራሉ። በተለያዩ ምክንያቶች ሥራው ወደኋላ መጓተቱን አስታውሰው፤ ከመስከረም ወር ወዲህ ግን በኢንስቲትዩቱ ቡድኖች ተዋቅረው በአዲስ አበባ ከተማ የግብርና ሥራዎች ምን እንደሆኑ፤ ምንስ ነው የሚፈልጉት? ፤ ያሉት ችግሮችና ችግሮቹን ከመፍታት አንፃር ከባለድርሻ አካላት ምን ይጠበቃል? የሚሉትን ጉዳዮች ለመለየት መቻሉን ይጠቅሳሉ፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን የገበያውን ፍላጎትና ከአቅርቦቱ ጋር ተያይዞ ያለውን እንቅስቃሴ ለመዳሰስ መሞከሩን ጠቅሰው፤ በዚህም በዘርፉ ትልቅ አቅም መኖሩን ለማወቅ መቻሉን ተናግረዋል። በተለይም በዶሮ እርባታ፣ በወተት ሀብት ልማት፣ በእንስሳት ማድለብ፤ በማር ልማት ረገድ እየተሰሩ ያሉት ሥራዎች በቀላሉ የሚታዩ አለመሆናቸውን በጥናቱ ማረጋገጥ እንደተቻለ አመልክተዋል። ‹‹እነዚህ ሥራዎች ምርትና ምርታመነታቸው እንዲጨምር ፤ የምግብ ዋስትናውን ከማረጋገጥ ፤ የስራ እድል ከመፍጠር አንፃር የገቢ ምንጭም እንዲሆኑ ከተፈለገ ሥራውን በጥናት አስደግፎ መደገፍና በዕቅድ መምራት ያስፈልጋል›› ይላሉ።

ለዚህም ይረዳ ዘንድ እያንዳንዱ አምራች ምን ችግር አለበት? ፤ ምንአይነት ቴክኖሎጂ ይፈልጋል?፤ የሚለውን ለመለየት ተሞክራል ሲሉ ገልጸው፣ በዚህም የተጀመሩት ሥራዎች አበረታች መናቸውንና በቴክኖሎጂ ከመደገፍ፤ ከዘር አቅርቦት ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ችግር እንዳለ መታወቁን ጠቅሰዋል። የእውቀትም የስልጠናም ከፍተት መኖሩ መለየቱንም አስታውቀዋል።

የምርምር ተቋሙም ሆነ በከተማ አስተዳደሩ ሥር ያሉ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ዶክተር ቶለሳ ያስገነዝባሉ። ‹‹ይህንን ማድረግ ስንችልነው የምግብ ዋስትናችንን ማረጋገጥም ሆነ ገበያ ማረጋጋት እንዲሁም ተጠቃሚውም ደግሞ ምርቱ ሲኖር በተሻለና በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት የሚችለው›› በማለት አፅዕኖት ሰጥተው አስታውቀዋል።

እንደ ተመራማሪው ገለፃ፤ በዘርፉ ያለው ችግር አንድ ተቋም ብቻውን የሚፈታው አይደለም፤ ይልቁንም የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ይሻል። በተለይ ከግብርናው ዘርፍ ውጪ ያሉ የመሰረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት ብርቱ እገዛ ሲታከልበት ነው ስኬታማ መሆን የሚቻለው። በተጨማሪም ትልቁ እና ሊሰመርበት የሚገባው ነገር የተሻሻሉ ዝርያዎችንና ቴክኖሎጂዎችን እንዲያገኙ የማገዙ ሥራ ተቀናጅቶ መስራትን የሚጠይቅ መሆኑ ላይ ነው። በከብድር አቅርቦት ጋር ተያይዞም ተከተታይነት ያለው ስራ ሊሰራ ይገባል፡፡

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 29 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You