ከኃይማኖት ተቋማት የሚለቀቁ ከደረጃ በላይ የሆኑ ድምጾችን በጋራ መከላከል ይገባል

አዲስ አበባ፡- ከኃይማኖት ተቋማትና በኃይማኖት ተቋማት ስም የጎዳና ላይ ስብከትና ልመና የሚውል ከደረጃ በላይ የሆኑ የድምጾችን ከኃይማኖት ተቋማት ጋር በጋራ መከላከል እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ከአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጋር በመተባበር ከደረጃ በላይ የሆኑ የድምፅ ብክለት ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ የውይይት መድረክ ሰሞኑን ተካሂዷል።

የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዲዳ ድሪባ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ በከተማው ከእምነት ተቋማት ውስጥ የሚወጡ ድምጾች ከደረጃ በላይ ናቸው። እነዚህን ድምጾች ጉዳት እንደሚያደርሱ በመረዳት ለመፍትሄው ከኃይማኖት ተቋማት ጋር በጋራ መሥራት አስፈላጊ ሆኗል።

የድምጽ ብክለት ምንጮች በዋነኝነት የትራንስፖርት፣ ግንባታና ማምረቻ ኢንዱስትሪዎች፣ ከንግድ እና ከመኖሪያ ቤት የሚወጡ ድምጾች እንዲሁም ከኃይማኖታዊ ተቋማት የሚወጡ ከልክ በላይ ድምጾች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በተለይ ከኃይማኖት ተቋማት በሚለቀቁ እና በኃይማኖት ተቋማት ስም በየመንገዱ የሚሰሙ ድምጾችን ከወዲሁ በጋራ ለመከላከል በውይይት መፍታት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በኃይማኖት ተቋማት የሚከሰቱትን የድምፅ ብክለት ለመቀነስ የሚያስችል ቴክኖሎጂ በመጠቀም አማራጭ መኖሩም አመልክተዋል።

አቶ ዲዳ ከተማዋ የአፍሪካ መዲና ከመሆና በተጨማሪ ከ150 በላይ ኤምባሲዎች፣ 600 በላይ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም 67 ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚገኙባት ከተማ እንደመሆኗ ለነዋሪዎቿ ንጹህ እና ጤናማ አካባቢን መፍጠር እንደሚገባ ተናግረዋል።

ባለሥልጣኑም በዚህ መነሻ መሠረት በከተማው የድምጽ ብክለት የሚያደርሱ ተቋማት ላይ የተለያዩ የክትትል እና ርምጃዎችን ይወስዳል ብለዋል።

በዘንድሮው በበጀት ዓመት ስድስት ወራት ውስጥ በተሠራ የአካባቢ ብክለት በሚያደርሱ ክትትል ከተደረገባቸው ተቋማት ውስጥ በአንድ ሺህ 221 ተቋማት ላይ ርምጃ እንደተወሰደ አቶ ዲዳ አስታውቀዋል።

ብስጭት፣ እንቅልፍ ማጣጥ፣ ራስ ምታት፣ ጭንቀትና አለመረጋጋት በከተማዋ የድምጽ ብክለት ጋር በተያያዘ በዋነኝነት የሚስተዋሉ አሉታዊ የጤና ችግሮች መሆናቸውን ጠቁመው፤ የድምጽ በክለት የሥነልቦና እና የአእምሮ ችግሮችን መከሰት ወይም ማባበስ እና ጆሮን የመስማት ሁኔታ በጊዜያዊነት ወይም በቋሚነት ሊያናጋ ይችላል ብለዋል።

ችግሩንም ለመቀነስ በጉዳዩ ላይ በቀጣይነት ችግር ፈቺ ጥናት የማካሄድ፣ማህበረሰቡን ማስተማር፣ የወጡ ሕጎች መተግበር እና ከፍተኛ የድምጽ ብክለት ምንጮችን በመደበኛነት መከታተልና መቆጣጠር ሥራን ከባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚሠራ አስታውቀዋል።

በመድረኩ ላይ የአዲስ አበባ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ዋና ጸሐፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ እንደገለጹት፤ አብሮነትና ወንድማችነትን ሊሸረሽሩ የሚችሉ ችግሮችን ከኃይማኖት አባቶች ጋር በውይይት መፍታት ተገቢ ነው።

በመሆኑም በኃይማኖት ተቋማት እና በኃይማኖት ተቋማት ስም የሚፈጠሩ የድምጽ ብክለቶችን በጥናት በመለየት ችግሮቹን በጋራ መፍታት ተገቢ ነው። ለማህበረሰቡም በቂ ግንዛቤ በመፍጠር በጋራ ችግሩን መፍታትና መከላከል ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

ማህሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You