ኢትዮጵያ የኤችአይቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ሥራዎችን በማጠናከር፣ ቅንጅታዊ አሠራርን በማጎልበት፣ መንግሥታዊ እና ዓለም አቀፍ ተቋማትን፣ አጋር ድርጅቶችን፣ ሲቪክ ማኅበራትን እና የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ወረርሽኙ በማኅበረሰቡ ጤናና በሰብዓዊ ደህንነት ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቧ በሚመለከታቸው ሁሉ የተመሰከረለት አፈፃፀም ነው።
ለአብነትም የኤችአይቪ ስርጭት ምጣኔን እ.ኤ.አ በ2010 ከነበረበት 1 ነጥብ 26 ከመቶ፣ እ.ኤ.አ በ2022 ወደ 0 ነጥብ 91 ዝቅ ማድረግ ተችሏል። ኤችአይቪ በደማቸው ይገኛል ተብለው ከሚገመቱ ወገኖች መካከል 84 ከመቶ የሚሆኑት ተመርምረው ራሳቸውን እንዲያውቁ፣ ከእነዚህ ውስጥ 98 በመቶ ያህሉ ደግሞ የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት እንዲጠቀሙና መድኃኒት ከሚወስዱት ውስጥ 96 ነጥብ 3 በመቶ ያህሉ የቫይረስ ልኬት መጠን በሚፈለገው ልክ እንዲወርድ ተደርጓል።
በሌላ በኩል በዓመት ውስጥ የሚኖረውን በኤድስ ምክንያት የሚከሰትን የሞት መጠን እ.ኤ.አ ከ100ሺህ 125 ሰው፣ እ.ኤ.አ በ2022 ከ100ሺህ ሰው ወደ 11 በማውረድ ከ52 ከመቶ በላይ እንዲቀንስ ማድረግ ተችሏል። በተመሳሳይ ቫይረሱ በደማቸው ከሚገኝ እናቶች የሚወለዱ ሕፃናት የምርመራና ሕክምና አገልግሎት በወቅቱ እንዲያገኙ ለማድረግ የማፋጠኛ እቅድ በማዘጋጀት በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል።
ኤችአይቪ/ኤድስን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ እነዚህ ሥራዎች ተሠርተው ውጤት የመጣ ቢሆንም፤ አሁንም ተጨማሪ የቤት ሥራዎች እንዳሉና በተለይ የቫይረሱ የስርጭት ምጣኔ ከክልል ክልልና ከከተማ ከተማ የሚለያይ እንደመሆኑ በዋናነት በከተሞች አካባቢ ጠንከር ያለ ሥራ መሥራት እንደሚጠይቅ መረጃዎች ያመላክታሉ። ለምሳሌ በከተማ የቫይረሱ ስርጭት መጠን ከፍተኛው ጋምቤላ በ3 ነጥብ 69 በመቶ፣ አዲስ አበባ 3 ነጥብ 47 በመቶ፣ ሐረሪ 2 ነጥብ 97 በመቶ፣ ድሬዳዋ 2 ነጥብ 9 በመቶ እና ዝቅተኛው ሶማሌ 0 ነጥብ 18 በመቶ መሆኑን ከተለያዩ መረጃዎች ለመመልከት ተችሏል። የኤችአይቪ ስርጭት ጥቅል ምጣኔ በከተማ 2 ነጥብ 9 በመቶ፤ እንዲሁም በገጠር 0 ነጥብ 4 በመቶ እንደሆነም እነዚሁ መረጃዎች ያሳያሉ።
ኤችአይቪን በመከላከል ረገድ የማኅበረሰቡን ሚና ለማጉላትና አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎችም ከተሞች እየጨመረ የመጣውን የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የዓለም ኤድስ ቀን ‹‹የማኅበረሰብ መሪነት ለላቀ ኤችአይቪ መከላከል›› በሚል መሪ ቃል በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ35ኛ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ36ኛ ጊዜ በቅርቡ መከበሩ ይታወሳል። ከዚሁ ጎን ለጎን የቫይረሱ ስርጭት በአዲስ አበባ ከተማ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በርብርብ መሥራት እንደሚጠበቅ ተነግሯል።
የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ እንደሚናገሩት ኤችአይቪ/ኤድስ ዓለም አቀፍ ችግር መሆኑ ከተረጋገጠበት ጊዜ ጀምሮ ዓለም አቀፍ ምላሽ ለመስጠት የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል። በተወሰዱትም የተቀናጁ ምላሾች ለውጥ ማምጣት ተችሏል። የዓለም አቀፉ ዘርፈ ብዙ የተቀናጀ ምላሽ አሰጣጥና ስልትን ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ማኅበረሰብ አቀፍ የኤችአይቪ/ኤድስ ስርጭትና በአዲስ የመያዝ ምጣኔ እንዲሁም በኤድስ ምክንያት ከሚከሰት ሞትና ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅኅኖ አንፃር ትርጉም ያለው ውጤት ማስመዝገብ ስለመቻሉ የተለያዩ ጥናቶችና ሪፖርቶች ያሳያሉ።
የኤችአይቪ ስርጭትን የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራው በተጠናከረ ሁኔታ ቀጣይነት እንዲኖረውና በጤናው ዘርፍ የተቀመጡትን ግቦች ለማሳካት ያስችል ዘንድ ማኅበረሰቡን በግምባር ቀደምትነትና በባለቤትንት የሚመሩ የኤችአይቪ/ ኤድስ የንቅናቄ መድረኮችን እያዘጋጁ ሚናቸውን እንዲወጡ ማስቻል ይጠበቃል።
በአውሮፓውያኑ የጊዜ ቀመር መሠረት በየዓመቱ ታኅሣሥ 1 የዓለም የኤችአይቪ/ኤድስ ቀን ሆኖ እንዲከበር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከወሰነበት ግዜ ጀምሮ እለቱ በልዩ ልዩ መሪ ቃሎችና ዝግጅቶች በየዓመቱ እየተከበረ ይገኛል። ከበዓሉ አከባበር ጋር በተያያዘም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኤችአይቪ/ ኤድስ የጋራ ፕሮግራም በየዓመቱ ትኩረት ሊሰጥባቸው የሚገቡ መሪ ሃሳቦችና አጀንዳዎችን እየቀረፀ በመላው ዓለም በይበልጥ ትከረት ተደርጎ እንዲሠራባቸው ሲያደርግ ቆይቷል። በዚህም ዓመት ‹‹የማኅበረሰብ መሪነት ለላቀ የኤችአይቪ መከላከል›› በሚል መሪ ቃል የሃሳብ ንቅናቄ በመፍጠር የአገልግሎቱን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ሰፊ የማኅበረሰብ ተሳትፎ ያደርጋል።
እንደ ኃላፊው ገለፃ ኤችአይቪ/ኤድስ የማኅበረሰብ ጤና ችግር ከመሆን አልፎ ኢኮኖሚያዊ፣ ሥነ-ልቦናዊና የሥነ ሕዝብ ችግር ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል። ችግሮቹም ውስብስብና ዘርፈ ብዙ በመሆናቸው ስትራቴጂ ተነድፎ ዘርፈ ብዙ ምላሽ ሲሰጥ በመቆየቱ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ቢቻልም አሁንም ኤችአይቪ/ኤድስ የከተማዋ (አዲስ አበባ) የጤና፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስጋት ስለሆነ በቀጣይ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታትና ተፅዕኖዎቹንም ለመቆጣጠር የሚደረገውን ማኅበረሰብ መር ተሳትፎ አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮም የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት በኅብረተሰቡ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ የመከላከልና የመቆጣጠር ተግባሩን ከሕክምና አገልግሎቱ ጋር በቅንጅት እየመራና ኅብረተሰቡን ማዕከል ያደረገ የመከላከልና የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነት በዘላቂነት መሠረት ለመጣል ከባለድርሻ አካላት ጋር ሆኖ እየሠራ ይገኛል።
በዓለም አቀፍና በሀገር አቀፍ ደረጃ እ.ኤ.አ በ2030 ኤድስን ለመግታት የተያዘውን ግብ ለማሳካት በየምዕራፉ የሚከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማጠናከር የተቀመጡትን ሦስት ግቦችን ለኤችአይቪ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን 95 ከመቶ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ያለውን ደረጃ እንዲያውቁ የማድረግ፣ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ እንዳለ ካወቁት ደግሞ 95 ከመቶዎቹ መድኃኒት እንዲጀምሩ የማድረግ፤ እንዲሁም መድኃኒት የጀመሩትና ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ 95 ከመቶ የኅብረተሰብ ክፍሎች በደማቸው ውስጥ ያለው ቫይረስ መጠን እንዲቀንስ የማድረግን ግብ ለማሳካት ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ።
ግቡን ለማሳካት በስትራቴጂ እቅዱ በተለይ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ ማድረግ የሚያስችሉ ስልቶችና ፕሮግራሞች ተቀርፀው ተግባራዊ እየተደረጉ ይገኛሉ። በመሆኑም የሀገሪቱ የኤችአይቪ/ ኤድስ ስርጭት ከአጠቃላይ ማኅበረሰብ አንፃር ሲታይ 0 ነጥብ 91 በመቶ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ከተማ ደግሞ የስርጭት ምጣኔው 3 ነጥብ 47 ሆኗል። የኢትዮጵያ የኤችአይቪ/ኤድስ ስርጭት ከአጠቃላይ ተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎች አኳያ ሲታይ 23 በመቶ ነው።
በሀገሪቱ ኤችአይቪ በደማቸው ያለባቸው ሰዎች 610ሺህ 350 ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል 61 ከመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው። እ.ኤ.አ በ2022 ብቻ 8ሺህ 257 ሰዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ አዲስ ኤችአይቪ ተይዘዋል። በአዲስ አበባ ከተማ ደግሞ 489 ሰዎች አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ናቸው። በአዲስ አበባ ከተማ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝባቸው ወገኖች 112ሺህ 185 ሲሆኑ፣ ከዚህ ውስጥ 3ሺህ 206ዎቹ ህፃናት ናቸው። ይህም ምጣኔው 2 ነጥብ 8 ከመቶ መሆኑን ያሳያል። 68ሺህ 240፤ ወይም 61 ከመቶ ያህሉ ኤችአይቪ/ ኤድስ በደማቸው አለባቸው።
ኃላፊው እንደሚያብራሩት ኤችአይቪ/ኤድስን የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ ከሌላው የሕክምና አገልግሎት ጋር ተቀናጅቶ በመሠራቱ የኤችአይቪ/ ኤድስ ስርጭት ምጣኔን እ.ኤ.አ በ2010 ከነበረበት 1 ነጥብ 26 ከመቶ፤ እ.ኤ.አ በ2022 ወደ 0 ነጥብ 91 መቀነስ ተችሏል። በዚሁ መሠረት በኤችአይቪ/ ኤድስ ምክንያት የሚከሰት ሞት ምጣኔ 125 ከ100ሺህ፣ ወደ 11 ከ100ሺህ ማውረድ ተችሏል። ከእናት ወደ ልጅ የሚተላለፈውን ኤችአይቪ ቫይረስ በተሠራ ጠንካራ ሥራ ከ46 በመቶ ወደ 12 በመቶ መቀነስ ተችሏል።
በ2020 ዓ.ም ከኤችአይቪ ነፃ የሆነ ትውልድ ለመፍጠር የተያዘውን ራዕይ እውን ለማድረግ አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ የሚገኙ ቢሆንም ራዕዩን እውን ለማድረግ ሰፊ ሥራ መሥራት ይጠበቃል። በተለይ የዘንድሮው የዓለም ኤችአይቪ/ኤድስ ቀን ‹‹የማኅበረሰብ መሪነት ለላቀ የኤችአይቪ/ኤድስ መከላከል›› በሚል መሪ ቃል የተከበረ እንደመሆኑ እለቱ ሲታሰብ ኤችአይቪ/ ኤድስ በደማቸው ውስጥ ለሚገኝ ወገኖች አጋርነትን ማሳየት ያስፈልጋል። ቫይረሱ በሰው ልጅ ጤናና በማኅበረሰቡ ላይ የሚያስከትለውን ዘርፈ ብዙ ችግር በዘላቂነት ለማስወገድ እ.ኤ.አ በ2030 ኤችአይቪ/ኤድስን ለመግታት የተያዘውን ግብ ለማሳካት ሁሉም ቃል መግባትና ቃሉን መፈፀም ይጠበቅበታል።
በቀጣይም የማኅበረሰቡን የመሪነት ሚና ለማጉላት የጤና ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ የተቀናጀ የኤችአይቪ/ ኤድስ ስርጭትን ለመከላከልና ለሕክምና ሥራ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ባለድርሻ አካላት እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ተባብረው ሊሠሩ ይገባል።
ኢትዮጵያ በ1980ዎቹ መጨረሻና በ1990ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የኤችአይቪ/ኤድስ ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሮ ከታየባቸው ሀገሮች መካከል አንዷ ነበረች። ሆኖም በግዜው በኤችአይቪ መከላከልና መቆጣጠር ላይ ከታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል አንስቶ እስከ ላይኛው የመንግሥት መዋቅር ድረስ በተሠራ ከፍተኛ የንቅናቄና የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ የቫይረሱን ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ተችሏል።
ሆኖም ቀደም ሲል በተሠሩ ሥራዎች መርካትና ይህንኑ ተከትሎ በመንግሥትም ሆነ በሕዝቡ በኩል መዘናጋት በመፈጠሩ ኢትዮጵያ የኤችአይቪ/ኤድስ ስርጭት አደጋ እንዳለባት በርካታ ጠቋሚ ምልክቶች አሳይተዋል። ከዚህ በመነሳት እንደ ሀገርም ሆነ እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኤችአይቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ሥራ ላይ የማኅበረሰቡ የመሪነት ሚና ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ ከወዲሁ ብዙ ሥራ እንደሚሠራ ይጠበቃል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 27 ቀን 2016 ዓ.ም