እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት እንዲሁም እንደ ሀገር በምግብ ራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት መንግሥት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ሰፋፊ ተግባራት እየተከናወኑ ሲሆን፣ በእነዚህም ምርትና ምርታማነት በየዓመቱ እየጨመረ ይገኛል። በተለይ በመስኖ እየለማ ያለው ስንዴ ምርት እየጨመረ ያለበት ሁኔታም ይህንን ያመለክታል፡፡
ምርትና ምርታማነት የማሳደጉ ሥራ በገጠር ብቻ የተወሰነ አይደለም፤ በከተማ ግብርናም እየተሰራበት ነው፡፡ በተለይ በሌማት ትሩፋት ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተሰሩ ሲሆን፣ ይህን ተከትሎም አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል፡፡ መንግሥት በከተሞች መስፋፋት ምክንያት በከተማ ዳርቻ የሚገኙ አርሶ አደሮችን መልሶ በማቋቋም የግብርና ሥራቸውን መቀጠል እንዲችሉ በማድረግ እና ለገበያ ማረጋጋቱ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ትርጉም ያለው ሥራ እየሠራ ነው፡፡
ለዚህም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ሥር የተቋቋመው የእንስሳት ልማትና ልህቀት ማዕከል እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባራት ማሳያዎች ናቸው፡፡
ከማዕከሉ የተገኘው መረጃ እንዳመለከተው፤ ማዕከሉ በአዲስ አበባ ከተማ ኮዬ ፈጬ አካባቢ የሚገኝ ሲሆን፤ በልማት ምክንያት የተፈናቀሉ አርሶ አደሮችን ያቀፈ ነው፡፡ አርሶ አደሮቹን መልሶ ለማቋቋም የተገነባው ይህ ማዕከል ሁለት ዋና ዋና ዓላማዎችን አንግቦ ይሠራል፡፡ አንደኛው ዓላማ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን መልሶ ማቋቋምና ማሻገር ነው፡፡ በመሆኑም መንግሥት ለአርሶ አደሩ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ተከታትሎ ወደ መካከለኛ ኢንቨስትመንት እንዲሸጋገር ያደርጋል፡፡
ሁለተኛው ዓላማ ገበያን ማረጋጋት ነው፡፡ በዚህም የማዕከሉን ምርቶች ለሸማቹ ማኅበረሰብ በማቅረብ ገበያውን የማረጋጋት ሥራ ይሠራል፡፡ በዚህም አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል፡፡ ወደ ሥራ ከገባ ስምንት ወራትን ያስቆጠረው ይህ የእንስሳት ልማትና የልህቀት ማዕከል በአሁኑ ወቅት በአምስት የሥራ ዘርፎች ማለትም በወተት ልማት፣ በከብቶች ማደለብ፣ በእንቁላል ጣይ ዶሮ እርባታ፣ በእንስሳት መኖ ማቀነባባሪያ ዘርፎች አርሶ አደሮቹ እንዲሰሩ እየተደረገ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በልማት ምክንያት የተነሱ አርሶ አደር ቤተሰቦች ተደራጅተው በግቢ ውስጥ በተገነቡ የመሸጫ ሱቆች በሽያጭ ሥራ የተሰማሩበት ሁኔታም የልማቱ ዘርፍ ነው፡፡
በማዕከሉ ተደራጅተው ወደ ሥራ የገቡት አርሶ አደሮች 550 የሚደርሱ ናቸው:: እነሱም 150 አባላት በወተት ከብቶች እርባታ፣ 100 በማደለብ፣ 110 በዶሮ እርባታ፣ 30 በመኖ ማቀናበር እና 160 አባላት ከአምራቾቹ ምርቶቹን ተቀብለው በማዕከሉ መግቢያ በር በተዘጋጁ ሱቆች በመሸጥ ሥራ ላይ የተሰማሩ የአርሶ አደር ቤተሰቦች ይገኙበታል። እነዚህ የአርሶ አደር ቤተሰቦች በማዕከሉ የሚመረተውን እንቁላልና ወተት ተረክበው በአካባቢው ለሚገኙ ነዋሪዎች፣ ለኅብረት ሥራ ማህበራትና ለመንግሥት ሠራተኞች በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡
የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን መልሶ ከማቋቋም ባለፈ ገበያን በማረጋጋት ጉልህ አበርክቶ ያለው የእንስሳት ልማትና የልህቀት ማዕከሉ የእንቁላል እና የወተት ምርትን በተለይም እንቁላልን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ በማቅረብ ገበያውን እያረጋጋ ይገኛል። የዝግጅት ክፍላችንም ወደ ማዕከሉ ባቀናበት ወቅት ከሸማቾችና ከአምራቾቹ መረዳት የቻለው ይህንኑ ነው።
በማዕከሉ መግቢያ ግራና ቀኝ ላይ ከተደረደሩት የወተትና የእንቁላል መሸጫ ሱቆች መካከል እንቁላል መሸጫ በሆነው አንደኛው ሱቅ እንቁላል እየገዛች ያገኘናት ወይዘሪት ሜላት ዓለሙ፣ በማዕከሉ አቅራቢያ ከሚገኘው የኮዬ ፈጬ የጋራ መኖሪያ መንደር ነዋሪ ናት፡፡
ሜላት በተደጋጋሚ ወደ ማዕከሉ በመምጣት እንቁላል ትገዛለች፡፡ በአካባቢው ከዚህ ቀደም አንድ እንቁላል ከ12 እስከ 16 ብር ድረስ ሲሸጥ እንደነበረ አስታውሳ፣ ማዕከሉ ተገንብቶ ሥራ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ ግን አንድ እንቁላል በስምንት ብር እየገዛች መሆኑን ገልጻለች፤ እንዲህ ዓይነት ማዕከላት በከተማዋ ያለውን የኑሮ ውድነት በማቃለል ገበያን ማረጋጋት እንደሚችሉ አስረድታለች፡፡
ሜላት እንዳለችው፤ እንዲህ ዓይነት ማዕከላት በየአካባቢው ቢኖሩ አሁን ላይ ያለውን የኑሮ ውድነት ማረጋጋት ይቻላል፡፡ መንግሥት በዚህ ዙሪያ በተለይም በከተማ ግብርና እየሠራ ያለው ሥራ የሚበረታታ ነው፡፡ በተለይም በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ እንዲህ ዓይነት ለሕፃናት ጠቃሚና ገንቢ የሆኑ የእንቁላልና የወተት ምርቶች ነጋዴው እጅ ሳይገቡ በቀጥታ ከአምራቹ ማግኘት መቻሉ በራሱ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ ለመጪዎቹ በዓላትም ምርቱ በተለያዩ አካባቢዎች ተደራሽ ቢሆን መልካም መሆኑን ጠቁማለች፡፡
ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ ብሩህ ፋና ዩኒየን የመጣችው ወይዘሮ ሐረግ መኮንን በበኩሏ በክፍለ ከተማው ሥር ለሚገኙ ዩኒየኖች የእንቁላል ምርት ለመግዛት እንደመጣች አጫውታናለች፡፡ እሷ እንደምትለው፤ ዩኒየኑ በኅብረት ሥራ ኤጀንሲ በኩል ከማዕከሉ 25 ሺ እንቁላል በየሳምንቱ መውሰድ ይችላል፡፡ በክፍለ ከተማው 11 ወረዳዎች እንዳሉ ጠቅሳ፣ ይህን አቅርቦት ለሁሉም በአንድ ጊዜ ማዳረስ አይቻልም፡፡ ስለዚህ ዩኒየኑ በየሳምንቱ በመመላለስ በተራ ያዳርሳል ብላለች፡፡
የሸማች ኅብረት ሥራ ማህበራት በተለያየ ስፍራ የሚገኙ ናቸው፤ ሱቅ ያላቸው፣ መዝናኛ ክበብ ያላቸውና በእሑድ ገበያ የሚያቀርቡ በመሆናቸው ዩኒየኑ በቅድሚያ ፍላጎት ሰብስቦ በቀን ለአምስት ወረዳዎች ከአራት ሺ እስከ አምስት ሺ እንቁላሎችን ያቀርባል፡፡
የሸማች ኅብረት ሥራ ማህበራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የገለጸችው ወይዘሮ ሐረግ፤ በተለይም በአሁኑ ወቅት ያለውን የኑሮ ውድነት ከማረጋጋት አንጻር ከማዕከሉ በተጨማሪ ዩኒየኖች አበረታች ሥራ እየሠሩ ነው ብላለች፡፡ ማህበራቱ በተለይም እንቁላልን ጨምሮ ጤፍ፣ ዱቄትና የጽዳት ዕቃዎችን ጭምር በተመጣጣኝ ዋጋ ለማኅበረሰቡ በማቅረብ ገበያን የማረጋጋት ሥራ እየሠራ መሆኑን ገልጻለች፡፡
እሷ እንዳለችው፤ በተለይም ማዕከሉ ከተከፈተ ጊዜ ጀምሮ አንድ እንቁላል በስምንት ብር በመግዛት ማህበራቱም የትራንስፖርት ወጪያቸውን በሳንቲም ቤት ጨምረው ለማኅበረሰቡ እያቀረቡ ይገኛሉ። ከተማ ውስጥ 16 ብር ደርሶ የነበረው የእንቁላል ዋጋም በአሁኑ ወቅት እየወረደ እንደሚገኝና በመደበኛው ገበያ እስከ 12 ብር እየተሸጠ መሆኑን አመላክታለች፡፡
በማዕከሉ ከሚገኙ እያንዳንዳቸው አምስት አምስት አባላት ካላቸው 11 የዶሮ እርባታ ሼዶች በአንዱ አቶ ጌትነት ፍቃዱ ይሰራሉ፡፡ አቶ ጌትነት፤ የልማት ተነሺ የአርሶ አደር ቤተሰብ ሲሆኑ፣ የመጡትም ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ነው፡፡ ቄብ ዶሮዎችን ይዘው ወደ ማዕከሉ በመምጣት ለሁለት ወራት ቀልበዋቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ዶሮዎቹ እንቁላል መስጠት ጀም ረዋል፡፡
እሳቸው ያሉበት ማህበር 3ሺ200 ዶሮዎች እንዳሉት የጠቀሱት አቶ ጌትነት፤ በቀን እስከ 2ሺ100 እንቁላል እያገኙ ናቸው፡፡ በሳምንት ሶስት ቀናትም እንቁላሉን በማዕከሉ ለሚገኙ የሽያጭ ሠራተኞች ያቀርባሉ፡፡ እንቁላሉን የሚያስረክቡት በማዕከሉ ግቢ ውስጥ ለተደራጁ ማህበራት ሲሆን፣ አንድ እንቁላል በሰባት ብር ያስረክባሉ፡ ፡ ማህበራቱም በሰባት ብር የተረከቡትን እንቁላል በስምንት ብር ለሸማቹ ያቀርባሉ፡፡ ይህም አሁን ያለውን የኑሮ ውድነት በማረጋጋት ረገድ ትልቅ አበርክቶ እንዳለውና ገበያውን ማረጋጋት ችሏል ብለው እንደሚያምኑም ገልጸዋል፡፡
ማህበሩ በቀጣይ እንቁላል ከማምረት በተጨማሪ ወደ ዶሮ ሥጋ የመሸጋገር እቅድ እንዳለው የጠቀሱት አቶ ጌትነት፤ በዶሮ እንቁላል ልማቱ ላይ በሚገባ ልምድ አዳብረዋል፡፡ ሌሎችን ማስተማርና ማሰልጠን እንደሚችልም ተናግረዋል። ማዕከሉ የልማት ተነሺ ለሆኑ አርሶ አደሮች የሥራ ዕድል በመፍጠሩ መደሰታቸውን ገልጸው፣ ማኅበረሰቡም በተለይም የእንቁላልና የወተት ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእንስሳት ልማትና የልህቀት ማዕከል ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ ተስፋዬ እንዳሉት፤ ማዕከሉ የከተማ ግብርና በማስፋት ሰፊ ሥራ እየሠራ ይገኛል። በ11ዱም ክፍለ ከተሞች የሚገኙ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን መልሶ የማቋቋም ሥራ እየተሰራ ነው። አርሶ አደሮችን መልሶ ከማቋቋም ባለፈ ገበያ በማረጋጋትም እንዲሁ ትርጉም ያለው ሥራ እየሠራ ይገኛል፡፡
በአሁኑ ወቅትም ማዕከሉ በስድስት ክፍለ ከተሞች ሥራውን ተግባራዊ ማድረግ ችሏል፡፡ እነሱም የካ፣ ቦሌ፣ ለሚ ኩራ፣ አቃቂ ቃሊቲ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶና ኮልፌ ቀራኒዮ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን መልሶ ማቋቋም ተችሏል፡፡
በአሁኑ ወቅትም እንቁላል፣ ወተትና የደለቡ በሬዎች በማዕከሉ የሚገኙ ስለመሆናቸው ያነሱት አቶ ታደሰ፤ በተለይም እንቁላል በስፋት እያመረተ ለገበያ በማቅረብ ከተማ ውስጥ ያለውን የእንቁላል ዋጋ ማረጋጋት ችሏል ነው ያሉት፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ አንድ እንቁላል በስምንት ብር ሲሸጥ ንጹህ የላም አንድ ሊትር ወተት በ70 ብር ይሸጣል። አንድ ሰው በቀን እስከ 20 እንቁላል መግዛት ይችላል፡፡ ምርቶቹን ለነጋዴዎች አይሸጥም፤ በተለይም በበዓላት ወቅት እንቁላል ተፈላጊ በመሆኑ ለመጪዎቹ የገና እና የጥምቀት በዓላት በበቂ ሁኔታ ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
ወደ ማዕከሉ መጥተው መግዛት ለማይችሉ የማኅበረሰብ አካላትም እንዲሁ የገበያ አማራጭ ያላቸው ሲሆን፤ በዩኒየኖች አማካኝነት በየክፍለ ከተማው ለማኅበረሰቡ እንዲቀርብ እየተደረገ ነው:: ወደ ሌሎች የማኅበረሰቡ አካላት ለመድረስ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከመሥሪያ ቤታቸው የሠራተኞቻቸውን ዝርዝር አቅርበው እንቁላል በስምንት ብር ማግኘት ይችላሉ፡፡ እያንዳንዱ ሠራተኛም አንድ ትሪ እንቁላል መውሰድ ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በእሑድ ገበያና በበዓላት ወቅት በባዛርና ኤግዚቢሽኖች ላይ ምርቶቹን ያቀርባል፡፡
የማዕከሉ ግንባታ አንደኛውና ሁለተኛው ተጠናቅቆ ወደ ሥራ የገባ ቢሆንም፣ ሶስተኛው ምዕራፍ አሁን ያለውን ያህል ግንባታ እንደሚጠይቅ ጠቅሰዋል። ማዕከሉ ወደፊት በቀን መቶ ሺ እንቁላል የማምረት ዕቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት በማዕከሉ የሚገኙ 36 ሺ ዶሮዎች በቀን እስከ 28 ሺ እንቁላል እየጣሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በመልሶ ማቋቋም የተደራጁ አርሶ አደሮች በመንግሥት ድጋፍ የሚደረግላቸው መሆኑን ያነሱት አቶ ታደሰ፤ በቅድሚያ ለግብርና ሥራቸው መነሻ ገንዘብ 50 በመቶ በቀጥታ ይሰጣቸዋል። 50 በመቶውን ደግሞ ከወለድ ነጻ በሆነ መንገድ ብድር ያመቻችላቸዋል፡፡ ይህንን ድጋፍ ያገኙ አርሶ አደሮችም በተሰማሩበት የግብርና ዘርፍ እየሠሩ ውጤት ማስመዝገብ የቻሉ ሲሆን፤ በየዕለቱ ለገበያ ከሚያቀርቡት እንቁላልና የወተት ምርቶች የሚያገኙትን ገቢ ቆጥበው የሚከፍሉ ይሆናል፡፡
ከእንቁላልና ወተት በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት በርካታ ቁጥር ያላቸው የደለቡ በሬዎች ለመጪዎቹ ሁለት በዓላት የተዘጋጁ መሆናቸውን እና በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ እንደሚቀርቡ የጠቆሙት አቶ ታደሰ፤ የደለቡ ከብቶች በዓመት ውስጥ እስከ ሶስት ጊዜ እንደሚያቀርብ አስታውቀዋል። ወተትም እንዲሁ በቀን ሁለት ጊዜ ጠዋትና ማታ ለአካባቢው ማኅበረሰብ በሊትር 70 ብር ሂሳብ እየቀረበ መሆኑን ጠቁመዋል፤ ማኅበረሰቡ ወደ ማዕከሉ በመምጣት የእንቁላል፣ የወተትና የደለቡ ከብቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲገዛም ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ሥር የተቋቋመው የእንስሳት ልማትና የልዕቀት ማዕከል በ140 ሺ ካሬ ሜትር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፤ ግንባታው በሶስት መርሃ ግብር ተከፋፍሎ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት አንደኛውና ሁለተኛው የግንባታ መርሃ ግብር ተጠናቅቆ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ በቀጣይም ሶስተኛው የግንባታ መርሃ ግብር ሲጠናቀቅ ማዕከሉ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ማስፋትና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 24 ቀን 2016 ዓ.ም