ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ መተግበር ከተጀመረ አጭር ጊዜ ቢሆንም፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተደራሽነትን በማስፋፋት ረገድ ብዙ ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው፤ ይህን ተከትሎም ለውጦች መመዝገብ ጀምረዋል። የዲጂታል ፋይናንስን በማሳደግ ረገድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትና እየተገኘ ያለው አበረታች ውጤቶች ለእዚህ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
በሀገሪቱ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ገና በጅማሮ ላይ ያለ እንደመሆኑ ተግዳሮቶች ያሉበት ቢሆንም፣ ዲጂታል ሥርዓትን በማስፋት የኤሌክትሮኒክስ ግብይትና የክፍያ ሥርዓት ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ለውጦች እንዲመጡ እያስቻለ ይገኛል። ይህንንም የዘርፉ ባለሙያዎችም ይመሰክራሉ። ይህም ጤናማ የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓትን በማስፈን ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እውን መሆን መሠረት ለመጣል ያስችላል ተብሎ ታምኗል።
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኤሌክትሮኒክስ መንግሥት ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አብዮት ሲናሞ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የገንዘብ ዝውውርን በማሳለጥ ከባንክ ወጪ የሆንን የገንዘብ እንቅስቃሴ ወደ ባንክ ሥርዓት በማምጣት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ይናገራሉ።
የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓት ከተጀመረ አምስት ዓመታትን አስቆጥሯል የሚሉት ኢንጂነር አብዮት፤ በተለይ በሞባይል ባንኪንግ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እየተዘዋወረ መሆኑን ይጠቅሳሉ። በቅርቡ እንኳ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ በኤሌክትሮኒክ የገንዘብ ዝውውር ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ሊዘዋወር ችሏል።
አሁን የኢንተርኔት ባንኪንግ፣ ዋሌቶች፣ የመንግሥት አገልግሎቶች ጭምር በተለይም የነዳጅ ክፍያዎች በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ሥርዓት እንዲሆኑ መደረጉ የዲጂታል ገንዘብ ዝውውር መጠኑን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ ማስቻሉን ነው የተናገሩት።
የገንዘብ ዝውውር በተለያዩ የክፍያ አማራጮች እንዲከናወን እየተደረገ መምጣቱ የገንዘብ መጠኑ እያደገና እየተስፋፋ ለመምጣቱ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነም ያመለክታሉ። ይህም የገንዘብ ዝውውሩ በትክክል በቁጥጥር ውስጥ መሆኑን እንደሚያሳይ ጠቅሰው፤ መንግሥትም ሊቆጣጠረውና ጥቅም ሊገኝበት የሚችል የፋይናንስና የገንዘብ ዝውውር ሥርዓት እንዲኖር እንደሚያደርግ ይገልጻሉ። ‹‹ይህን ማዕቀፍ ስንመለከት የገንዘብ ዝውውሩ በዲጅታል ሥርዓት እንዲከናወን መደረጉ ትልቅ ጠቀሜታ አለው፤ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ግለሰብ በብዙ መልኩ ተጠቃሚነት የሚፈጥር ነው›› ሲሉ አስረድተዋል።
እንደ እሳቸው ገለፃ፤ የዲጂታል ሥርዓቱ በርካታ ፋይዳዎች አሉት። አንደኛው ፋይዳው የግለሰቦችን ጊዜ፣ ጉልበትና አላስፈላጊ ወጪን መቆጠብ ነው። ሁለተኛው የዲጂታል ፋይናንስ ተደራሽነት ማሳደግ ሲሆን በተለይ በገንዘብ ዝውውሩ ባንክ ወይም መንግሥት ሊቆጣጠር የሚችለው የገንዘብ መጠን ለመቆጣጠር ስለሚያስችል አጠቃላይ የገንዘብ ዝውውሩ እንዲታወቅ ይረዳል። በተጨማሪም ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውሮችን ሁሉ ለመቆጣጠር ያግዛል። አጠቃላይ ለኢኮኖሚ እድገትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።
በዲጂታል ሥርዓቱ የገንዘብ ዝውውርን የተሳለጠና ውጤታማ ለማድረግ የሕግ ማዕቀፎች እንደሚያስፈልጉ የሚጠቅሱት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤ ለዚህም በብሔራዊ ባንክ የተዘጋጀ የዲጂታል ፋይናንስ አዋጅ እንዲሁም በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በኩል የተዘጋጀው ‹‹የኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽን›› አዋጅ በአስቻይነት የሚጠቀሱ እንደሆነ ይናገራሉ። አዋጆቹ በዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓቱ ለሚደረገው እንቅስቃሴ መሠረታዊ ጉዳይና መዳላደሎችን እንደሚፈጥሩ ጠቅሰው፣ በዲጂታል ፋይናንስ ዝውውር ውስጥ ደግሞ ለተጠቃሚው ከለላ የሚሰጥ አዋጅ መኖር እንዳለበት ያመለክታሉ።
‹‹ተጠቃሚው ለሚፈጽመው ክፍያ የሚገባውን አገልግሎት ማግኘት ስላለበት ከለላ የሚሰጠው ሕግ መኖር አለበት›› ያሉት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤ ይህንንም በሕግ መደገፍ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ። ይህም በትራንዛክሽን አዋጁ በኢ-ኮሜርስ ውስጥ እንዳለ ይጠቅሳሉ። ኢ-ኮሜርስ በዋናነት የሚያተኩረው ለተጠቃሚው ከላለ በሚሰጡ ጉዳዮች እንደሆነም ያስረዳሉ። ከዚህ አንጻር የሕግ- ማዕቀፎቹ ተግባራዊ እየተደረጉ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት።
እሳቸው እንዳሉት፤ የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓቱ የማስፈጸሚያ ፕላትፎርሞች አሉት። በባንኮች እና በተለያዩ ተቋማት እየተሰጡ ያሉ አገልግሎቶች በተለያዩ ፕላትፎርሞች በመጠቀም ይሰጣሉ። እነዚህ ፕላትፎርሞችም ሌሎች ማስቻያ መንገዶች ናቸው። ሌሎቹ በየተቋማቱ የሚሰጡ አገልግሎቶች ሲሆኑ ከእነዚህ ውስጥም ክፍያ የሚፈጸምባቸው አገልግሎቶች አሉ። በእነዚህም ሰዎች ባሉበት ቦታ ሆነው እንዲገለገሉ በማድረግ የአገልግሎት አሰጣጡና የክፍያ ሥርዓቱን በአንድ ላይ በማቀናጀት ክፍያ እንዲፈጸሙ ይችላሉ።
አሁን ባለው አሰራር ግን አብዛኛዎቹ አገልግሎት የሚፈልጉ ሰዎች አገልግሎቱን በኤሌክትሮኒክ ሥርዓቱ ካገኙ በኋላ የመጨረሻውን አገልግሎት ለማግኘት በአካል ወደ ተቋሙ እንዲሄዱ እንደሚጠይቅ ጠቅሰው፤ እንደዚህ ዓይነቱ አሠራር ማስቀረት የሚቻለው የክፍያ ሥርዓቱንም አብሮ በማቀናጀት ማስኬድ ሲቻል መሆኑን ይገልጻሉ። አሁን እየተከናወኑ ያሉ ተግባሮች አቀናጅቶ ማስኬድ የሚያስችሉ መሆናቸውን መሪ ሥራ አስፈጻሚው ያስገነዝባሉ።
ኢንጂነር አብዮት እንደሚሉት፤ የዲጅታል አገልግሎቱ ለፋይናንስ ዘርፉ የሚኖረው አስተዋጽኦ ለማሳደግ በመሠረተ ልማት ደረጃም ሰፊ ሥራዎች መሥራት አለባቸው። ለዚህም መንግሥት ሀገራዊ ግብረ-ኃይል አቋቁሞ በተቀናጀ አግባብ ሥራዎች እንዲሰሩ እያደረገ ይገኛል። በቅንጅት በሚሰራው ሥራ መናበብ እንዲኖር የሚያደርግ ነው። ዲጂታል ትራንስፎርሜሽኑ ለፋይናንስ ዘርፉ የበለጠ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ መሟላት ያለባቸው መሠረተ ልማቶችን በማሟላት ረገድ ሰፊ ሥራዎች እየሰሩ ነው።
በተመሳሳይም የማኅበረሰብ ንቃተ ህሊና ደረጃ ማሳደግ የሚችሉ ሰፊ ሥራዎች መሥራት ያስፈልጋል ያሉት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤ ዲጂታል ክፍያዎች እንዴት መፈጸም ይቻላል?፤ የፋይናንስ ኢኮ ሲስተሙ ላይ ምን ዓይነት አስተዋጽኦ ማበርከት ይቻላል? በሚሉት እና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ። አሁን ላይ በእነዚህ ሥራዎች በስፋት የሚሰራባቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም ውጤቱ እየታየ ለውጦች እየተመዘገቡ መሆናቸውን ያመለክታሉ።
ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽኑ አስቻይ ተብለው የቀረቡት ነገሮች በሚፈለገው ልክ ሳይሆኑ ሲቀሩ እንደ ተግዳሮት እንደሚወሰዱ የሚገልጹት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤ ለአብነት መሠረተ ልማትንና የኢንተርኔትን ተደራሽነት በሀገሪቱ ሁሉም ቦታዎችና አካባቢዎች ላይ ሁሉም ማኅበረሰብ ያለበት ቦታ ተደራሽ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ። እነዚህን ተግዳሮቶች ለመፍታት የዩኒቨርሳል አክስስ ፈንድ እና መንግሥት የኔትወርክ ማስፋፊያ ሥራዎች መሥራት እንዳለባቸው የሚያሳይ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት።
የሲስተም ልማት ችግር ሌላው ተግዳሮት መሆኑን የጠቆሙት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤ አሁን ላይ የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎቶች ውስን እንደሆነ ይገልጻሉ። እነዚህ የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎቶችን በማስፋፋት በሀገር ደረጃ ማምጣት እንደሚያስፈልግ ያመለክታሉ።
መሪ ሥራ አስፈጻሚው የፋይናንሻል ተደራሽነትንና አካታችነትም ችግር መኖሩን ያነሳሉ። ‹‹በዚህ ረገድ ሰፊ ሥራዎች መሥራት አለባቸው፤ አሁን ላይ እየወጡ ያሉ ስትራቴጂዎችና ፖሊሲዎችም ይህን የሚደግፉና አበረታች ስለሆኑ እነዚህ አስፋፍቶና በደንብ አጠናክሮ መሥራት ይጠይቃል›› ይላሉ።
ሌላኛው ተግዳሮት የማኅበረሰብ ንቃተ-ህሊና እንደሆነ የገለጹት ኢንጅነር አብዮት፤ እንደ ሀገር ያለው መሠረታዊ የንቃተ-ህሊና ደረጃ በራሱ ዝቅተኛ መሆኑን ነው ያስታወቁት፤ ‹‹ወደ ዲጂታል ሲመጣ ደግሞ ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም›› ሲሉ ገልጸዋል። መሠረታዊ የንቃተ-ህሊና ደረጃ ዝቅተኛ ከሆነ የዲጂታል ኢኮሲስተሙ /ምህዳሩ/ ከዚህ ቀጥሎ የሚመጣ ከመሆኑ አንጻር በዲጂታል ዘርፉ በጣም ከፍተኛ የንቃተ-ህሊና ደረጃ ያስፈልጋል ይላሉ።
‹‹በዲጂታል ዘርፍ የሚፈልገው ከፍተኛ የንቃተ-ህሊና ደረጃ ለማምጣት ሰፊ ሥራዎች መሥራትን የሚጠይቅ ነው›› ያሉት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤ ይህ ደግሞ ትኩረት ተሰጥቶት በዲጂታል ያለውን ግንዛቤና ክህሎት ለማስፋት ሊሰራበት የሚገባ ያመለክታሉ። በኢኮሲስተሙ ላይ ባሉት ተግዳሮቶች ላይ መንግሥትም በስፋት ለመሥራት በዲጂታል 2025 ስትራቴጂ ላይ በእነዚህ ተግዳሮቶች ላይ እየሰራባቸው እንደሆነም ነው ያመለከቱት።
«አጠቃላይ የዲጂታል ፋይናንስ እናስፋፋለን፤ ተደራሽነት እናደርጋለን›› ስንል ተግዳሮት ተብለው የተለዩት ነገሮች መፈታት አለባቸው የሚሉት ኢንጂር አብዮት፤ በገጠር ላለው ማኅበረሰብ ከመሠረተ ልማት ጋር በተያያዘ ሊፈቱ በሚገባ ችግሮች ላይ ሰፊ ሥራ መሥራት እንዳለበትም ያመለክታሉ።
አሁን የታዩ ለውጦችና የመጡ ውጤቶች አበረታች መሆናቸው ጠቅሰው፣ ሁሉንም አካባቢ ተደራሽ ለማድረግ የኔትወርክና መሠረት ልማት ዝርጋታ ማስፋፋት ትልቁ ተግዳሮት እንደሆነ ይናገራሉ። እነዚህ ተግዳሮቶች ተፈቱ ማለት ተደራሽነት እና የአካታችነት ጉዳዮች ይፈታሉ ማለት ነው ሲሉ ያስረዳሉ።
‹‹የዲጂታል ፋይናንስ ጉዳይ እንደማኅበረሰብ የሚታይ ነው›› ያሉት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤ ተግዳሮቶቹ ሲፈቱ ተደራሽነት በማስፋት ጭምር ስለሆነ በዚህ ረገድ የሚሰሩ ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆን መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሆነ ያመለክታሉ።
የቴክኖሎጂ አማካሪ አቶ ሰለሞን ሙሉጌታ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዓለም የደረሰበት ደረጃ ታይቶ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ተቃኝቶ ሊጎዱ የሚችሉትን በማስወገድ፤ መልካሞቹን በመውሰድ የሚሰራ ከሆነ ለሀገር ያለው ጠቀሜታ ብዙ ነው። በዚህ ረገድ ብዙ ሥራዎች መሥራት ያስፈልጋል።
ኢትዮጵያ ብዙ ወጣቶች ያሉባት ሀገር ናት። ቴክኒክ ላይ የወጣቶች መነቃቃት አለ፤ ሶፍትዌር ኢንጂነሮች እና በቴክኖሎጂ ላይ ተሰማርተው የሚሰሩ ባለሙያዎች አሉ። ለእነርሱ የሚሆን የተመቻቸ የሥራ አካባቢ ግን የለም።
ይህ የሆነበትን ምክንያት ‹‹ገና ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስላልተስፋፋና መክፈልም ስለማንችል ነው›› በማለት ያስረዳሉ። በሀገር ውስጥ ያለው የመክፈል አቅም ውስን መሆኑን ይናገራሉ። ለዚህም ሀገር ውስጥም ያሉት ሶፍት ዌር ባለሙያዎች እዚሁ ሆነው ለውጭ ሀገራት የሚሰሩበት ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰው፤ ይህ ጥሩ ሆኖ ሳለ በሌላ መልኩ ደግሞ ሀገር ውስጥ ያለው አሰራር እንደሚጎዳ ያብራራሉ።
‹‹እንደ ሀገር ለባለሙያው የመክፍል አቅም ዝቅተኛ ስለሆነ ባለሙያው ውጭ ሀገራት ላይ መሥራት ይመርጣል፤ ይህንን አቅም በሀገር ደረጃ ለመጠቀም ደግሞ ሀገር ውስጥ ያሉ የመንግሥት፣ የግል ተቋማት እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ለሶፍትዌር ኢንጂነሮችና ለቴክኖሎጂ ባለሙያዎች የሚቻለው ያህል መክፈል እስካልተቻለ ሀገር ውስጥ ያለው አሠራር ይጎዳል›› ይላሉ።
በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዘርፍ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉ ጠቅሰው፤ ‹‹የቴክኖሎጂ ባለሙያ፤ በዚህ ውስጥ ወጣቶች ይጠቀማሉ፤ የውጭ ኢንቨስትመንት መሳብ ይቻላል። እንዲሁም በብዙ ሁኔታዎች ተጠቃሚነት ማስፋት ይቻላል›› በማለት አብራርተዋል። በመሆኑም ይህንን ለማመጣጠን የሚያስችል ሥራ መሥራት የግድ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት።
እንደ እሳቸው ገለፃ፤ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ውስጥ የሚነሱ ጉዳዮች ብዙ ናቸው። ከእነዚህ መካከል የመሠረተ ልማት፣ የኢንተርኔት፣ የዲጂታል ሊትረሲ፣ የኤሌክትሮኒክስ የመገልገያ ቁሳቁስ ተደራሽነት ይጠቀሳሉ። ለአብነት ዘመናዊ የስልክ ቀፎ በኢትዮጵያ እንደ ቅንጦት እቃ እንደሚታይ ጠቁመው፤ በሌሎች ሀገሮች ደግሞ ታክስ የማይከፈልበት እንደ መሠረታዊ ነገር ልክ እንደ ምግብ የሚታይ ነው ብለዋል። ይህም በኢትዮጵያ በፖሊሲ ደረጃ ታይቶ የሚስተካከለው፤ ተስተካክሎ ሁሉም ሰው የሚጠቀምባቸው የኤሌክትሮኒክስ የመገልገያ ቁሳቁስ ከሌሉ ሲስተም ሆነ የኢንተርኔት ተደራሽነት ቢሰፋም ጥቅም አይኖረውም። እነዚህን ችግሮች መፍታት ከተቻለ የሚፈለገው ለውጥ ማምጣት ይቻላል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 23 ቀን 2016 ዓ.ም