በኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪን ለማስፋፋት ሲሰራ ቆይቷል፤ በእዚህም በተለይ የውጭ ምንዛሬ ሊያስገኙ ለሚችሉ የጨርቃ ጨርቃ ኢንዱስትሪዎች ትኩረት መሰጠቱ ይታወቃል። ዓለም አቀፍ ብራንድ ያላቸው የውጭ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው አልባሳትን በማምረት ለውጭ ገበያ እያቀረቡም ይገኛሉ፡፡
ከዚህ በተጓዳኝ በተለይ በባህል አልባሳት ማምረት በኩልም እየተሰራ ነው፡፡ ይህን ተከትሎም በባህል አልባሳት ማምረት ሥራና አልባሳቱን ሸምቶ በመጠቀም በኩል ለውጦች እየመጡ ስለመሆናቸው በዘርፉ የተሰማሩ ዲዛይነሮች፣ አምራቾችና ነጋዴዎች ሲገልጹም ይደመጣል።
በአንጻሩ ከውጭ ሀገሮች የሚመጡ ልባሽ ጨርቆች በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በግልጽ ሳይቀር እየተቸበቸቡ ይገኛሉ፡፡ የቦንዳ ቤቶች መስፋፋትም ልባሽ ጨርቆቹ በስፋት ገበያ ላይ እየዋሉ መሆናቸውን ይጠቁማል፡፡
እነዚህ በምእራባውያን ሀገራት ጥቅም ላይ ውለው በበርካታ የአፍሪካ ሀገሮች ገበያዎች የሚሰራጩ ልባሾች (በተለምዶ ሰልባጅ እየተባሉ የሚጠሩት) በኢትዮጵያም በስፋት መሰራጨታቸው ለሀገር ውስጥ የአልባሳት ምርት ገበያ ስጋት ሊሆኑ እንደሚችሉ እየተጠቆመ ይገኛል፡፡
የእነዚህ በተለያዩ መንገዶች ወደ ሀገሪቱ የሚገቡ አልባሳት ግብይት እንደ አዋጭ የሥራና የገበያ አማራጭ እየታየ መጥቷል፡፡ ይህ ሁኔታ ለሀገር ውስጥ አልባሳት አምራቾችንና በጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎችን እንቅስቃሴ ፈታኝ ሊያደርግ እንደሚችል እየተጠቆመ ነው፡፡
በእነዚህ ልባሽ ጨርቆች ጉዳይ ላይ ያነጋገርናቸው የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይል እና ፋሽን ኢንስቲትዩት መምህር እስጢፋኖስ ምንቸግሮት፤ የልባሽ ጨርቆች ጉዳይ ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት አጀንዳ ሆኖ በስፋት እየተዘዋወረ እንደሚገኝ ያስረዳሉ፡፡ የጉዳዩን ተጽዕኖ በሁለት መልኩ ማየት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡
በአንዳንድ ሀገሮች የልባሽ ጨርቆችን መጠቀም የዘመናዊነት መገለጫ ተደርጎ እንደሚወሰድ ጥናቶች እንደሚያመላክቱ መምህሩ ጠቅሰው፣ ለዚህ እንደ ምክንያትነት የሚጠቀሰውም ‹‹አልባሳቱ አዲስ ልብስ ተመርቶ ለገበያ እስኪቀርብ ድረስ ጥቅም ላይ የሚውሉ ግብዓቶች ያስቀራል›› የሚለው መሆኑን ይገልጻሉ፤ በድጋሚ ጥቅም ላይ ሲውሉ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ይቀንሳሉ የሚል እሳቤ እንዳለም ይናገራሉ።
በሌላ በኩል የልባሽ ጨርቆች ገበያው ለበርካታ ሰዎች የሥራ እድል መፍጠር ችሏል ቢባልም፣ ከጉዳቱ ጥቅሙ ያመዝናል በሚል የሚሞግቱ እንዳሉም ይናገራሉ። እነዚህ የልባሽ ጨርቆች ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ተደራሽ የማያደርጉና፣ የሚፈጥሩትም የሥራ እድል በዘርፉ የተሰማሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከሚፈጥሩት የሥራ እድል ጋር የሚነጻጸር አይደለም የሚል ሀሳብ በማቅረብ የሚከራከሩም እንዳሉም ይገልጻሉ።
የልባሽ ጨርቆች ተጠቃሚነት በአፍሪካ እጅግ በጣም የበዛ መሆኑንም ጠቅሰው፣ አህጉሩ የምዕራባውያን የማይፈለጉ ምርቶች ማስወገጃ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ከጊዜ ወደጊዜ ቁጥሩ ሲጨምር ከኢኮኖሚያዊ ጫናው በዘለለ ማህበራዊ ጫናው እንደሚበልጥም ነው ያስገነዘቡት፡፡
‹‹በሀገራችን የልባሽ ጨርቆች መበራከት በአልባሳት ኢንዱስትሪው ዘርፍ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ እንደዚሁ በቀላሉ የሚተው አይደለም›› የሚሉት መምህሩ፤ ተቀባይነቱ በጨመረ ቁጥር በሀገራችን ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ እየተሰራበት ያለውን እንቅስቃሴ እንደሚያቀጭጭ ይናገራሉ። በሥራ ላይ ያሉ ፋብሪካዎችንም ጭምር ሙሉ ለሙሉ ከገበያው ሊያስወጣ እንደሚችልም ያስረዳሉ፡፡
ሰዎች ልባሽ ጨርቆችን ሲያስቡ ለየት ያሉ ልብሶች መሆናቸውን ፣ በጣም በቅናሽ ዋጋ መቅረባቸውን ሊያስቡ ይችላሉ፤ ጥራታቸውን የጠበቁ የሚሉ ጉዳዮች ቀድሞ ወደአዕምሯቸው ሊመጣ ይችላል የሚሉት መምህር እስጢፋኖስ፣ ይህ አዕምሮን የተቆጣጠረ ነገር በሀገር ውስጥ ለሚመረቱ ልብሶች ያለውን አመለካከት ይቀይረዋል ይላሉ፡፡ የሀገር ውስጥ ምርቶች ጥራት የወረደ ነው የሚል እሳቤን እንደሚፈጥርም ጠቅሰው፣ ይህ እሳቤ እየተቆጣጠረን ሲሄድ ፍጹም ጥገኛ የሆነ አመለካከት ያለው ማህበረሰብ እንዲፈጠር ያደርጋል ሲሉም ያስገነዝባሉ፡፡
የአልባሳት ኢንዱስትሪው ልብስ በማምረት ሂደት ውስጥ ከሚፈጠረው የሥራ እድል ባሻገር ለማምረት የሚረዱ ግብዓት አቅራቢዎችንም ጨምሮ ረጅም የገበያ ሰንሰለት እንዳለው የሚገልፁት መምህሩ፤ የዘርፉ ማደግ የሀገር ውስጥ አምራቾችን ከማበረታታት ባሻገር ዜጎች ባህላቸውን ጠብቀው እንዲቆዩ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ይናገራሉ፡፡
እንደ መምህሩ ማብራሪያ፤ የልባሽ ጨርቆች ገበያው ውስጥ መበራከት የሀገር ውስጥ አልባሳት አምራቾች በኢንዱስትሪው ውስጥ ጸንተው እንዳይቆዩ በገበያው ላይ ተቀባይነት አግኝተው ደንበኞችን እንዳያፈሩ ያደርጋል፤ በልባሹና በሀገር ውስጥ በሚመረቱት አልባሳት መካከል ያለው የዋጋ ልዩነት የሀገር ውስጥ ምርቶችን ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ያደርጋል፡፡ በተለይ በማምረት ሂደትም የሚያወጡት ወጪ ከፍተኛ በመሆኑ አምራቾች ዘንድ ተጨማሪ ፈተና ነው ፡፡
በተጠቃሚዎች ዘንድ የቦንዳ ልብሶች ጥራት አላቸው የሚል እሳቤ እንዳለም ጠቅሰው፣ የሀገር ውስጥ ባለሙያዎች በጥራት የተሻሉ ልብሶች የማምረት ደረጃ ላይ ሊደርሱ እንደሚችሉ መታወቅ እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ አንዳንድ አምራቾችም የሚያመርቷቸውን ጥራት ያላቸው ልብሶች ለውጭ ገበያ ብቻ የሚያቀርቡ መሆናቸውም የኢንዱስትሪው ክፍተት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
የልባሽ ጨርቅን ታንዛኒያ፣ ሩዋንዳ ፣ ዚምቡዋቤ እና ኡጋንዳ ወደ ሀገራቸው እንዳይገባ በተለያየ ጊዜ አግደዋል ያሉት መምህር እስጢፋኖስ፤ ሀገራቱ ይህንን ሕግ በማውጣታቸውም የተለያዩ ጫናዎች እንደደረሰባቸውም ጠቁመዋል፡፡ ለእዚህም ምክንያቱም በዚህ ገበያ ቀላል የማይባል ገንዘብ ይዘዋወራል፡፡
በኢትዮጵያም የልባሽ ጨርቅን ሙሉ ለሙሉ ማስቆም ባይቻልም መንግሥት ትልቁን ድርሻ መውሰድ እንደሚገባው መምህር እስጢፋኖስ አመልክተዋል፡፡ ሕጎችን በማውጣት ፖሊሲዎችን በማውጣት ጫናውን መቀነስ እንደሚቻልም ነው ያስገነዘቡት፡፡
የሀገር ውስጥ አምራቾች የሚበረታቱበት ሁኔታ መፈጠሩ ብቻውን ውጤታማ እንደማያደርገው ጠቅሰው፤ የልባሽ ጨርቆች ንግድ ገደብ ካልተበጀለት ውጤታማ መሆን እንደማይቻል አስታውቀዋል፡፡
‹‹የሀገር ውስጥ አምራቾች ተወዳዳሪ ሆነው መዝለቅ እንዲችሉ የታክስ እፎይታ መስጠት ይገባዋል›› የሚሉት መምህር እስጢፋኖስ፤ መንግሥት በብዛት ለማምረት ችግር በሚፈጥሩ አሰራሮች ላይ ከባለሙያዎች ጋር ተቀራርቦ በመስራት ችግሩን ማቃለል እንደሚጠበቅበትም ይገልፃሉ፡፡ የዘርፉ አሰራር በየጊዜው እንደሚቀያየር ጠቅሰው፤ አምራቾችም ተወዳዳሪ ሆነው ለመቆየት ራሳቸውን የማብቃት ሀላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 22 ቀን 2016 ዓ.ም