የከተሞች ፎረም- ለዘመናዊ የከተሞች ዕድገት

በከተሞች መካከል የሚደረጉ ውድደሮች እና የልምድ ልውውጦች ለከተሞች ፈጣን እድገት ጉልህ ፋይዳው እንዳለው ይታመናል። ባለፉት ዓመታት ከተሞች በጋራ ለመሥራት ያግዘናል ያሉትን የከተሞች ፎረም መስርተው ሲሠሩና የልምድ ልውውጥ ሲያደርጉ ከነበረበት ሁኔታም መረዳት የሚቻለው ይህንኑ ነው።

የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም በ2002 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ነበር የተጀመረው፡፡ ፎረሙ ለስምንት ጊዜ በተለያዩ ከተሞች ተካሂዷል። ይህ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ሲስተናገድ የነበረ መድረክ፣ ከተሞች የልምድ ለውውጥ እንዲያደርጉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉም ይታወቃል፡፡ ዘንድሮም መድረኩ በቅርቡ እንደሚካሄድ ተጠቁሟል፡፡

የዘንድሮው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም በአዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ሶዶ ከተማ ከየካቲት ዘጠኝ እስከ አስራ አምስት ቀን 2016 ዓ.ም ይካሄዳል፡፡ ይህ ለዘጠነኛ ጊዜ የሚካሄደው የከተሞች ፎረም “የዘመኑ ከተሞች ለኢትዮጵያ ብልፀግና” በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄድ ስለመሆኑ በቅርቡ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተጠቁሟል፡፡

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ ይህን ዘጠነኛውን የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ በፎረሙ ለማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ትርጉም ባላቸው መሠረተ ልማቶች ላይ ትኩረት ይደረጋል።

በከተሞች መካከል ጤናማ የውድድር መንፈስ እንዲኖር ይሠራል ያሉት ሚኒስትሯ፤ በዘጠነኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ላለፉት ዓመታት ለስምንት ጊዜ ከተካሄዱት ፎረሞች በተለየ መንገድ ብዙ እውቀት እና ልምድ የሚገኝበት እንደሆነም አመላክተዋል፡፡

ሚኒስትሯ እንዳሉት፤ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር በአዋጅ 1663/2014 መሠረት ከተሰጠው ኃላፊነት አኳያ በዋናነት በከተማው አመራር እና አስተዳደር ጉዳዮች ላይ በትኩረት ይሠራል። በከተሞች የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚችሉ የወል መሠረተ ልማቶች፣ የእግረኛ መንገዶች፣ የሳይክል መሄጃ መንገዶች የትኞቹ ከተሞች ቴክኖሎጂን አስቀድሞ በመጠቀም እና ችግሮችን ቀድሞ በማወቅ ወደ ተግባራዊ የግንባታ እንቅስቃሴ ስለመግባታቸውም በፎረሙ ላይ የሚፈተሽ ይሆናል፡፡

የከተማ ነዋሪዎች እና ተቋማትን በማቀናጀት በተለይ ከተማውን የሚመራው አካል ከተማውን ለመምራት የሚያስችል አቅም እና አውቀት ሊኖረው ይገባል። ከተሞች እየሰፉ እና እያደጉ እንደመሄዳቸው ሁሉ ፍላጎቶችም በዚያው ልክ እየሰፋ የሚሄድ በመሆኑም በተለመደው አሠራር መራመድ አይቻልም፡፡

ለእዚህም በከተሞች አመራር ላይ ትኩረት በማድረግ የአቅም ግንባታ ሥራዎች እየተሠራ ነው። ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆንም እያደገ የመጣውን የከተማ ልማት ፍላጎት መምራት የሚያስችሉ አቅሞች የማሳደግ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው።

በኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም የከተሞች ኤግዚቢሽን፣ ከተማን የማስተዋወቅ፣ ከተማን የማነቃቃት፣ የትኛው ከተማ ምን ላይ ነው ያለው ከተማውን የሚመራው አካል ምን ዓይነት ቁርጠኝነት አለው፤ ምን ግብ አለው፤ ምንስ ማሳካት ይፈልጋል፤ የሚለው ይታያል ያሉት ሚኒስትሯ፤ ይም ፎረሙ የከተማው ነዋሪ የልማቱ አካል እንዲሆንና የእኔነት ስሜት እንዲያዳብር በማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ በዚህም ተሞክሮ ያላቸው ከተሞችን የማወዳደርና የመሸለም ሥራዎች ተግባራዊ ይደረጋሉ ሲሉም አስታውቀዋል።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ በተመሳሳይ ደረጃ ያሉ ከተሞች ይወዳደራሉ፡፡ ለክልል ተጠሪ የሆኑ ከተሞችም እንዲሁ ክልሉ ባወጣው ስታንዳርድ መሠረት ያሸነፈውን ከተማ ከሌላው ክልል ጋር በማወዳደር የውድድር ስሜቱን ለማጠናከር ይሠራል። የአገልግሎት አሰጣጣቸውም እንዲሁ በነዋሪዎቻቸው እና በገለልተኛ ወገን ስለመሻሻሉ ይታያል። በዚህም ዜጎችን መሠረት ባደረገ መልኩ የዜጎች የእርካታ ደረጃ ይረጋገጣል፡፡ ይሄንን ሙሉ በሙሉ መተግበር ባይቻልም በርካታ ከተሞች አገልግሎታቸውን የማዘመን፣ በቴክኖሎጂ የማስደገፍ፣ ከሕዝብ ጋር በቅርበት የመሥራት ጥረቶች በመኖራቸው እውቅና የሚሰጥባቸው ይሆናል፡፡

የልማት አጋሮች እና ከተማን የሚረዱ፣ ከተማ ውስጥ ሆነው የሥራ እድል የሚፈጥሩ እንዲሁም በተለየ መንገድ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ በፎረሙ እውቅና እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል። ሴሚናሮች፣ የፓናል ውይይቶች እና የተለያዩ ሁነቶች እንደሚካሄዱም ጠቅሰው፤ የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች፣ ሃሳባቸውን የሚያንሸራሽሩበት፣ የከተማና መሠረተ ልማት አዲስ ፖሊሲ እያዘጋጀ የሚገኝ መሆኑንም አመልክተዋል፣ ለዚያ የሚሆኑ ግብዓቶች በፎረሙ የሚሰበሰብ እንደሆነም አስረድተዋል።

‹‹ከተሞች ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የራሳቸው ሚና አላቸው›› ያሉት ሚኒስትሯ፤ የዘመኑ ከተሞች ለኢትዮጵያ ብልፅግና በሚለው መሪ ቃል የተዘጋጀው ዘጠነኛው ፎረም ከተሞች መዘመን አለባቸው በሚለው ቁርጠኝት እንደሆነ ገልጸው፤ ከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ከደቡብ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጋር በጋራ በመሆን በወላይታ ሶዶ የሚዘጋጀው ፎረሙ የተቀናጀ የከተሞች ልማት ላይ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።

የልማት አንዱና ትልቁ አቅም መንግሥት መሆኑን ጠቅሰው፤ ልማትን ከግብ ለማድረስ መንግሥት፣ የልማት አጋሮችንና ነዋሪዎችን በማስተባበር እንደሚሠራም ገልጸዋል። የከተሞች ፎረም ዓላማም ለልማት ድርሻ ያላቸው አካላት፣ መንግሥት እና የልማት አጋሮች አንዲሁም የከተማ ነዋሪዎችን እውቀት፣ ሙያ እና ሀብት በማስተባበር የሚከናወን መሆኑን አስታውቀዋል።

ሚኒስትሯ እንዳሉት፤ ጤናማ የውድድር መንፈስ በከተሞች መካከል እንዲፈጠር ከማድረግ አንፃር የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም የጎላ ሚና አለው። ከተማን ከከተማ የማወዳደሩ ጉዳይ ባደጉት ሀገራት ጭምር በከፍተኛ ደረጃ ከተሞቻቸውን እያሳደገ ነው። የልምድ ለውውጥ የማስፋት አቅሙ ከፍተኛ በመሆኑ ጤናማ የውድድር መንፈስ በከተሞቻችን መካከል እንዲደረግ በትኩረት ይሠራል።

የሀገሪቱ ከተሞች ከተለያዩ ካምፓች ተነስተው የተጀመሩና እየሰፉ የመጡ ናቸው፡፡ አሁን ግን የትኛው አካባቢ ለየትኛው መሠረተ ልማት ይዋል የሚለው በትኩረት የሚሠራበት ይሆናል። ዘጠነኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም በከተሞች መካከል ጤናማ የእርስ በእርስ ውድድር እንዲኖር የሚያግዝ በመሆኑ የምርጥ ከተሞች ውድድርና ሽልማት ይኖራል።

ፎረሙ የከተማ ከንቲባዎች እና አመራሮች የነዋሪዎቻቸውን ችግሮች ለመፍታት በጋራ እንዲመክሩ እድል ይፈጥራል፤ ከንቲባዎች በሚመሯቸው ከተሞች በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በመኖሪያ ቤት ግንባታ እና በመሠረተ ልማት አቅርቦት ባለሀብቱን እና ኅብረተሰቡን በማሳተፍ እንዲሁም ባለቤት በማድረግ ከተሞች ላይ ውጤት ማምጣትን መሠረት ያደረገ ነው፡፡

ከተሞችን ውብ፣ ጽዱ እና አረንጓዴ በማድረግ ለነዋሪዎች ምቹ ሁኔታን በመፍጠር፣ ድህነት ቅነሳ እና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ በትኩረት ይሠራል። ከዚህም ባለፈ ፎረሙ በከንቲባዎች መካከል የእርስ በእርስ ትብብር እና የተሞክሮ ልውውጥ እንዲኖር ያስችላል ሲሉም ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ አብራርተዋል፡፡

በከተሞች ለሚታዩ ችግሮች መፍትሄ ለማኖር የተናጠል ሳይሆን የጋራ መፍትሔ ለማምጣትና የልምድ ልውውጦችን ለማድረግ እንደሚያስችል ገልጸዋል። ፎረሙ የከተማ ከንቲባዎች ተገናኝተው በወቅታዊ የከተሞች የትኩረት አጀንዳ ላይ ጽሁፍ ቀርቦ የሚወያዩበት፣ የተሻለ አሠራር ካላቸው ከንቲባዎች ልምድ የሚለዋወጡበት፣ ያጋጠማቸው ፈተና ካለም መፍትሔ በጋራ የሚያፈላልጉበት እና የተሻለ አፈጻጸም ላከናወኑ ከንቲባዎች ዕውቅና የሚሰጥበት እንደሆነም ተናግረዋል።

የድቡብ ኢትዮጵያ ክልል የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ በበኩላቸው እንዳሉት፤ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አዲስ የተደራጀ ክልል እንደመሆኑ፣ የፎረሙ በክልሉ መካሄድ መልካም አጋጣሚዎችን ይፈጥራል። በክልሉ ያሉ ከተሞች እንዲነቃቁና የመሠረተ ልማት ግንባታ ተሞክሮ እንዲያገኙ ያስችላል።

ክልሉ በአዲስ መልኩ ከተደራጀ በኋላ በተለይ ከተሜነት ላይ ልዩ ትኩረት አድርጎ እየሠራ እንደሚገኝ የቢሮ ሃላፊው አስታውቀዋል። በተለይም በክልሉ በጥሩ እድገት ላይ ከሚገኙት ከተሞች አንዷ የሆነችው የወላይታ ሶዶ ከተማ ዘጠነኛውን የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ማዘጋጀቷ በክልሉ ለሚገኙ ሌሎች ከተሞች ተስፋ የሚሰጥ መሆኑን አስታውቀዋል። ከ30 በላይ የሚሆኑ የክልሉ ከተሞች በፎረሙ ላይ ተሳታፊ እንደሚሆኑ ጠቅሰው፣ ይህም ብቃት ያለው ተሳትፎ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል።

ደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን ተወዘዋውሮ ለመጎበኘት ሰላማዊ ሁኔታ እንዳለ ጠቅሰው፣ የዚህ መሰል ሀገራዊ እና ብዙ ከተሞች የሚሳተፉበት፣ ብዙ ልምድ ልውውጥ የሚደረግበት ምናልባትም በአቅራቢያው ያሉ ከተሞችን ተዘዋውረው የሚጎበኙበት አጋጣሚ የሚፈጠርበት መሆኑን አስታውቀዋል።

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ይህ ሀገራዊ ሁነት ፍጹም ሰላማዊ እንዲሆን በቂ ዝግጅት እየተደረገ ነው፤ ከቦታ ልየታ ጀምሮ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመሆን ከቀደሙት የከተማ ፎረሞች ምን መልካም ልምዶች አሉ? ምን ዓይነት ዝግጅቶች መጨመር አለባቸው? የሚለውም ተለይቶ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በመሆን ዝርዝር እቅድ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ ይደረጋል።

መድረኩ ከሌሎች ከተሞች ጋርም በጥምረት መሥራት እድል የሚሰጥ ነው ያሉት አቶ ብርሃኑ፤ ለፎረሙ ስኬታማነት ሁሉም የደቡብ ኢትዮጵያ ከተሞች ከወላይታ ሶዶ ከተማ ጋር በትብብር እየሠሩ መሆናቸውን አመላክተዋል።

የወላይታ ሶዶ ከተማ ከንቲባ አቶ ጀግና አይዛ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ የወላይታ ሶዶ ከተማ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ካሉ ከተሞች ዘጠነኛውን የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ለማከበር ከተመረጠች ጊዜ አንስቶ ከክልሉ ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ እና ከወላይታ ዞን አስተዳደር ጋር በመሆን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናወን ጀምረዋል፡፡

በከተማው እምብርት ላይ ለፎረሙ የሚሆን 25 ነጥብ 33 ሄክታር ቦታ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል፡፡ ለዚህም አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን በማሟላት የቦታ ማጽዳት ሥራዎች ከወዲሁ መሠራታቸውን ጠቁመዋል። የአካል ጉዳተኞችንና ፆታን ታሳቢ ያደረገ የመጸዳጃ ቤት ዝግጅቶች፣ መንገድና ፓርኪንግ እየተዘጋጁ ናቸው ያሉት ከንቲባው፣ የፎረሙ ተሳታፊ ከተሞች ራሳቸውን የሚወክሉ ሥራዎችን የሚያሳዩባቸው ቦታዎችን የሚያሳይ የውሃ፣ የመብራት መስመር፣ የሚዘረጉበት ቦታ የሚያሳይ፣ በዲዛይን ደረጃ መሠራት እንዳለባቸውና እየተዘጋጁ እንደሆነም አመላክተዋል።

ሰባት መግቢያ በሮች ያሏት የወላይታ ሶዶ ከተማ ዘጠነኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም በደማቁ እንዲከናወን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠራ ሲሆን፤ ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆንም “የወላይታ ሶዶ ከተማ ከየት ወደየት” የሚል ጥናታዊ ፅሁፍ የሚቀርብ እንደሆነ ተጠቁሟል።

የከተማውን ጽዳትና ውበት የመጠበቅ፣ ሰላምና ጸጥታን የማስጠበቅ በተለይ የሕዝብ ውይይት ሥራ የማከናወን፣ የእንግዳዎች አቀባበልና ማረፊያ ቦታዎችን የማመቻቸት ሥራዎችን ለመከናወን ከዚህ ቀደም ፎረሙ የተካሄደባቸውን ከተሞች ተሞክሮ የመቅሰም ሥራ ቀደም ብሎ መሠራቱን ተገልጿል፡፡

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You