ዘመናትን ያስቆጠረው የበጎነት ምግባር- ተቋማዊ አደረጃጀቱ ሲፈተሽ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከአንድ ቢሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች በበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ በመሳተፍ አንድነታችንና ሰብዓዊነታቸውን እንደሚገልጹ መረጃዎች ያመለክታሉ። ዓለምአቀፍ በጎ ፍቃደኞች በተለያዩ ሀገራት በመዘዋወር በህክምና ፣ በትምህርት ፣ የአየር ንብረትና አካባቢን በመጠበቅና በመሳሰሉት እውቀታቸውን፣ ልምዳቸውን ያካፍላሉ። በዚህ ውስጥም የሀገራትን የርስበርስ ግንኙነት ያጠናክራሉ፤ የእውቀት እና የባህል ሽግግርም በሀገራቱ መካከል እንዲኖር በማድረግ እንደሚታወቁ እነዚሁ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በሀገራችንም ‹‹ድር ቢያብር አንበሳ ያስር ›› በሚለው ብሂል መሠረት ኢትዮጵያውያን በዙሪያቸው ላሉ ሰዎች በጎደላቸው ጊዜ በመሙላት ፣ በደስታም ሆነ በኀዘን ጊዜ አብረው በመሆን ያላቸውን ሳይሰስቱ በመስጠት ይታወቃሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ይህ የኢትዮጵያውያን የመረዳዳትና የመተሳሰብ እሴት የበጎ አድራጎት ተግባር በሚያከናውኑ ተቋማትና በክረምት የበጎ ፈቃድ ፈቃድ አገልግሎት በኩል ጎልቶ እየወጣ ይገኛል።

በሀገሪቱ የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን በማሳደግ በኩል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራበት የሚገኝ ስለመሆኑ በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት እየተከናወኑ ካሉ ተግባሮች መረዳት ይቻላል። ይህ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መምጣቱንም መረጃዎች ያመለክታሉ።

በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ብሄራዊና የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብይ ሀይለመለኮት በቅርቡ ዓለም አቀፍ የበጎ ፈቃድ ቀን አካባበር ላይ እንደተናገሩት ፤ በ2015 ዓ.ም ክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ 21 ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ወጣቶች በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ አሳልፈዋል። ወጣቶቹ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሰጡ ሲሆን፣ 53 ሚሊዮን የሚጠጋ የማህበረሰብ ክፍልን ማገልገላቸው ይገመታል። ይህ በገንዘብ ሲሰላ 17 ቢሊዮን ብር ይደርሳል። በዚህም ወጣቶቹ አገልግሎትን ለወጡበት ማህበረሰብ በመስጠት የማህበረሰቡን ችግርም ፈትተዋል፤ ከፍተኛ ሀብትም አድነዋል።

በጎ ፍቃደኞቹ በማህበራዊ ጤና አገልግሎት ፣ በደም ልገሳ ፣ በሆስፒታል ውስጥ ፣ በትምህርትም እንዲሁ የክረምት የትምህርት ማጠናከሪያዎችን፣ የትራፊክ አገልግሎትን በማሳለጥ ፣ በችግኝ ተከላ ፕሮግራምና በአፈር ውሃና አካባቢ ጥበቃ ተሳትፈዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንዳሉት፤ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት በነበረው ስጋት ምክንያት የዓለም አቀፍ የበጎ ፍቃደኞች እንቅስቃሴ ተቀዛቅዞ የነበረ ቢሆንም፣ በሀገር ውስጥ የነበረው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ግን ጎልቶ ታይቷል። በሁሉም የህብረተሰብ አካላት ላይ ስጋት እና ውጥረት በተፈጠረበት በዚያ ወቅት በጎ ፈቃደኞች ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ያላቸውን ትብበርና አብሮነት አሳይተዋል።

‹‹የገንዘብ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው አካላት በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ የሚገኙ በጎ አድራጊዎች ገንዘብ አሰባስበዋል›› ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ በተጨማሪ ከሥራቸው የተገለሉ እና በኢኮኖሚ ውጥረት ላይ የሚገኙ ዜጎችን በመጎብኘት፣ ወረርሽኙ የሚጠይቃቸውን የጥንቃቄ መርሆች ለመከተል የሚያስችሉ የጤና አጠባበቅ መስመሮችን በመዘርጋት፣ በየአካባቢያቸው በህብረት የእጅ መታጠቢያ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሁኔታዎችን በመፍጠር፣ በለይቶ ማቆያ ማዕከላት የሚገኙ ታካሚዎችን በመንከባከብ ኢትዮጵያውያን በችግር ጊዜ ያላቸውን የእርስ በርስ አጋርነት በእጅጉ ማስመስከራቸውን ገልፀዋል።

የአዲስ አበባ የህብረተሰበ በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሸነር አቶ አብርሃም ታደሰ በበኩላቸው፤ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች በከተማዋ ሲጀመር በርካታ ተቋማት አቅም ቢኖራቸውም የቱ ጋር ምን መሥራት እንደሚገባቸው ብዙም ግልጽ አልነበረም። የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተቋም ደረጃ በከተማዋ 21 ዓመት ሞልቶታል። ክረምትን ጠብቀው የሚደረጉ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ውስን የነበሩ ሲሆን ፣ በ2011 ዓ.ም ተቋሙ በአዲስ አበባ ደረጃ የበጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮው ሲመሰረት ፕሮግራሞቹም እየበዙ መምጣታቸውን አስታውሰዋል።

አቶ አብርሃም አንዳሉት፤ ማስተባበሪያው በተለይ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮም በአዲስ አበባ በሚያከናውነው የበጎ ፈቃድ ማስተባበር ሥራው የ10 ዓመት ፍኖተ-ካርታ ተዘጋጅቶ በጎ ፈቃደኝነት ባህል እንዲሆን በየተቋማቱ እየሠራ ይገኛል። በአሁኑ ሰዓትም በትምህርት ሥርዓት ውስጥ ተካቶ ሲቲዝንሽፕ የሚል የትምህርት አይነት ውስጥ የበጎፍቃድ አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል። ተቋማዊ አሠራር በመፈጠሩም በየዓመቱ ያለው የበጎ ፈቃድ ተሳትፎ እያደገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በ2015 በጀት ዓመት በነበረው አጠቃላይ የበጎ ፈቃድ ተግባራት ወደ ሰባት ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ብር የሚገመት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በ 14 ፕሮግራሞች እና በ 18 መርሀግብሮች ሲከናወኑ ቆይተዋል። በዚህም መሠረት ወደ ስድስት ሺህ 415 የሚጠጉ ቤቶች ታድሰው ለችግረኞች ተላልፈዋል። ከ860 ሺህ በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች መአድ የተጋሩበት፤ እንዲሁም ሌሎች የደም ልገሳ፣ የፅዳት፣ የውበት፣ እንዲሁም የአካባቢ ሰላም የማስጠበቅ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው በዚህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ያነጋገርናቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሺዮሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር እና ተመራማሪ ዶክተር ኢዛና አምደወርቅ እንደሚሉት፤ በጎፍቃድ አገልግሎት ምንም አይነት ቀጥታ የገንዘብም ሆነ መሰል ክፍያዎችን ሳይጠብቁ ሰዎች በራሳቸው ተነሳሽነት ጊዜያቸውን ፣ ገንዘባቸውን ፣ እውቀታቸውን ወይንም ንብረታቸውን ለግለሰብ ፣ ለሌሎች ሰዎች ፣ ለማህበረሰብ ወይንም ከአካባቢያቸው ወጣ ብለው ለሀገር ብሎም በዓለምአቀፍ ደረጃ የሚያርጉት ድጋፍ ነው ።

የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በብዙ መንገድ እንደሚገለጽ የገለጹት ዶክተር ኢዛና፤ ሰዎች በራሳቸው ፍቃድ የሚያደርጉት ማንኛውም ድጋፍ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ውስጥ ይካተታል ይላሉ። አገልግሎቱ ያደጉ በምንላቸው ሀገራት ተቋማዊ በሆነ መልኩ የራሱ አሠራርና ሥርዓት ተፈጥሮለት መደበኛ ሆኖ የተማሪዎች፣ የሠራተኞች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተብሎ እንደሚከፈልም ይናገራሉ። ለዚህም እድሜ ጠገብ የሆኑት የወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማህበር (ወወክማ) ፣ የቀይ መስቀልና የቀይ ጨረቃ ማህበራትን በአብነት ጠቅሰዋል። ተቋማትም የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን በእቅዳቸው ውስጥ በማስገባት ለማህበረሰባቸው የራሳቸውን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ይላሉ።

ባደጉት ሀገራት የበጎፍቃድ አገልግሎት በዚህ መልኩ ይነሳ እንጂ በሌሎች ሀገራት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የለም ማለት እንዳልሆነም ዶክተር ኢዛና ያመለክታሉ። ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የመረዳዳት ባህል የተለመደ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሰዎች የተለያዩ ተፈጥሯዊ አደጋዎች ሲከሰቱ በአካባቢያቸው ፣ በሃይማኖት ተቋማት እና ባሏቸው ነባር ሥርዓቶች እስርበርስ ሲደጋገፉ እንደኖሩና እንደሚኖሩ ይናገራሉ።

‹‹የበጎ ፍቃድ ገልግሎት አይነቱና የሚሰጥበት መልኩ ይለያይ እንጂ በዓለም ላይ ያለ የተለመደ ተግባር ነው›› ሲሉ ጠቅሰው፣ በአሜሪካ አንድ በጎፍ ቃደኛ በማንኛውም አገልግሎት ተግባር ላይ የሚያሳልፈው አንድ ሰዓት የሚሰጠው ጉልበት እና ክህሎት ተደምሮ 22 የአሜሪካ ዶላር እንደሚያወጣ በተለያዩ ጥናቶች መቀመጡን ይገልጻሉ። ይህ ባለው የበጎ ፍቃደኞች ብዛትና የሚያገለግሉበት ሰዓት ቢሰላ ምን ያህል ዋጋ እንዳለው እንደሚያሳይ ያመለክታሉ።

የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በሀገራችን ያለው እንቅስቃሴ እየተለመደ መጥቷል የሚለው ሃሳብ መስተካከል የሚገባው እንደሆነ ዶክተሩ ጠቅሰው፣ ‹‹አሁን ላይ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተቋማዊ የሆነ አሠራር ተፈጥሮለት፣ ፕሮግራም ተቀርጾለት ትኩረት ተሰጠው እንጂ በጎፍቃድ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለና የነበረ ነው ›› ሲሉ ይገልጻሉ።

ለአብነትም በገጠሪቱ የሀገራችን ክፍል ወላጆች ጉልበታቸው ሲደክም ልጆቻቸውን በሞት ቢያጡ አልያም በቅርባቸው ባይኖሩ በአካባቢው ያሉ ወጣቶች መሬታቸውንበማረስ ፤ እህል በመሰብሰብ ፣ ቤታቸውን በመስራትና በመጠገን እና ሌሎች ተግባራትን በማከናወን ድጋፋቸውን የሚያሳዩበትን ሁኔታ ጠቅሰዋል። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ተቋማዊ የሆነ የበጎፍቃድ አሠራር እየተስተዋለ መምጣቱን ገልጸዋል። በሌላው ጊዜ በተበታተነ መልኩ ይታገዙ የነበሩ አረጋውያንና አቅመ ደካሞች በአንድ ጥላ ስር ተከልለው በጎፍቃደኞችም በተለያየ መልኩ ወደቦታው በመሄድ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ መቄዶኒያ የአረጋውያን መርጃ ማእከል በማሳያነት በመጥቀስ አብራርተዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህም መንግሥት እንደ አንድ የማህበረሰብ እድገት መንገድ በመያዝ በክረምትና በበጋ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ፣ የማዕድ ማጋራት ፣ የቤቶች እድሳት፣ የተማሪዎች የትራፊክ አገልግሎት ፣ እንዲሁም የኮቪድ ወረርሽኝ በሀገራችን በተከሰበት ወቅት የነበረውን ትብብር ዶክተር ኢዛና ጠቅሰው፣ በጎፍቃደኞችን በማስተባበር በርካታ ተግባራት ተቋማዊ በሆነ መልኩ እየተገበሩ መሆናቸውና ጉዳዩ ትኩረት አግኝቷል ማለት እንደሚቻል አስታውቀዋል። ይህ ሁኔታም ተቋማት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሲያከናውኑ በዙሪያቸው ካለው ማህበረሰብ ጋር የተጣጣመ ግንኙነት እንዲኖራቸው ያስችላል ብለዋል።

ዶክተር ኢዛና እንዳብራሩት፤ የበጎፍቃድ አገልግሎት መስጠት በመጀመሪያ ደረጃ መንፈሳዊ የውስጥ እርካታን ይፈጥራል፣ ሰዎች የሚያከናውኑት ተግባር የሚያመጣውን ለውጥ በሚያዩበት ጊዜ ለራሳቸው ያላቸው ዋጋ ከፍ እንዲል ያደርጋል። ወጣቶች በዚህ ተግባር ቢሰማሩ ከሌሎች ሰዎች ጋር የመግባባትና ራሳቸውን የመግለጽ ክህሎታቸውን ያዳብራሉ፤ የሥራ ባህላቸውን ያሳድጋሉ፤ ተባብሮ የመሥራት ባህልን ያጎለብታሉ። የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ማንኛውም ሰው በየእለት ተዕለት ተግባሩ ላይ ሊያደርገው የሚችለው ነው።

ዶክተር ኢዛና ያለበጎ ፍቃድ አገልግሎት የማይከናወኑ ተግባራት የመኖራቸውን ያህል በጎ ፍቃደኞች ሁሉንም ዘርፍ ሊሸፍኑ እንደማይችሉ መረሳት የለበትም ሲሉም ያስገነዝባሉ። እንደ ደም ልገሳ ፣ የዓይን ብሌን ልገሳ ያሉ ተግባራት በገንዘብ የማይገኙ ሙሉ ለሙሉ በሰዎች በጎ ተነሳሽነት ወይንም የአንድ ግለሰብ በጎ ተነሳሽነት ካልታከለባቸው የማይከናወኑ ተግባራት መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በአንጻሩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ የማይተካቸው ተግባራት እንዳሉም አመልክተዋል።

‹‹የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የመንግሥት ሃላፊነትን አይተካም›› የሚሉት ዶክተር ኢዛና፣ በተለያዩ ጊዜያት ሰዎች በህብረት የአካባቢያቸውን ደህንነት ለመጠበቅ ይተባበራሉ። ነገር ግን በዚህ የጸጥታና የደህንነት ሥራ ላይ የተሰማሩ አካላትን የሚተኩ አይደሉም። በከተማችን አዲስ አበባ በየእለት ዕለት የእቅስቃሴ ተግባር ላይ የትራፊክ ፍሰቱን ሰላማዊ በማድረግ ረገድ የተማሪዎች ትራፊክ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው ቢሆንም፣ በዘርፉ የተሰማሩትን ሕግ የሚያስከብሩ ባለሙያዎችና አካላትን የሚያግዙ እንጂ የሚተኩ አይደሉም ሲሉ ያብራራሉ። የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ጎን ለጎን የሚሄዱ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በሀገራችን ያለው የበጎፍቃድ አገልግሎት እንቅስቃሴ አሁን ካለበት በበለጠ እንዲያድግ ማድረግ እውቅና ከመስጠት እንደሚጀምር ዶክተር ኢዛና አስገንዝበዋል። በቀጥታም ባይሆን የተለያዩ የእውቅና ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት ሰርተፍኬቶችን በመስጠት በጎፍቃደኞችን በማበረታታት ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ ይቻላል ሲሉም ይመክራሉ።

ዶክተር ኢዛና በበጎ ፈቃድ ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታዩ ያሉ ጅምሮች እንዲበራከቱ ለማድረግ በበጎነት የሚከናወኑ ተግባራት ተቋማዊ ቅርጽ እንዲይዙ ማድረግ የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው ይገልጻሉ። በሌሎች ሀገራት በበጎፍቃድ አግልግሎት ላይ የተሰማሩ ተማሪዎች ወደ ትልልቅ ኮሌጆች በሚገቡበት ወቅት የሰጧቸው አገልግሎቶች ከግምት ውስጥ እንደሚገቡ ጠቁመው፣ ከግለሰብ ጀምሮ ተቋማት ድረስ በሠሯቸው የበጎፍቃድ ተግባራት ያበረከቱት ሰዓት፣ ጉልበትና እውቀት ተሰልቶ በዓመቱ መጨረሻ ከሚከፍሉት ግብር ላይ ታሳቢ ተደርጎ ተቀናሽ የሚደረግበት አሠራር እንዳለም ጠቁመዋል።

ይህም መንግሥት ለዘርፉ የሰውን ትኩረትና ተቋማትንም ሆነ ግለሰቦችን ለማበረታታት የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚያሳይ ገልጸዋል። የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በምንኖርበት አካባቢ ብቻ የተገደበ ተግባር አይደለም ያሉት ዶክተር ኢዛና፣ በጎ ፍቃደኞች ከአካባቢያቸው ባሻገር ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው የመሥራት ልምዳቸው እንዲዳብር ፀጥታና ደህነነት መጠበቅ እንዳለበትም አስታውቀዋል፤ ይህም ማህበራዊ መቀራረብን ይበልጥ እንደሚያጠናክርም ነው ዶክተር ኢዛና ያስገነዘቡት።

ዶክተር ኢዛና እንዳብራሩት፤ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለሚሰጠውም ሰው ሆነ አገልግሎቱን ለሚያገኘው ሰው ጥቅሙ ላቅ ያለ በመሆኑ ቀጣይነቱ ላይ መሥራት ይገባል፤ መበረታታት ያለበት መሆኑም ጥርጥር የለውም ። በመሆኑም ይህ የበጎፍቃድ አገልግሎት እንዲበራከት በዚህ ተግባር የሚሰማሩ ግለሰቦች በእርግጥም የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መርህ የሆነው በጎ ተነሳሽነት በውስጣቸው ሊፈጠር ይገባል። ይህ መሆኑ የሚሰማሩበትን ተግባር በርግጥም አምነውበት የሚያደርጉት እንጂ በሌላ አካል ተገደው የሚያደርጉት እንዳይሆን ማድረግ ያስችላል።

ሰዎች ሳይፈልጉና ሳያምኑበት ቢሳተፉም ሥራውም ለይስሙላ ፣ ውጤቱም አመርቂ አይሆንም ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት ዶክተር ኢዛና፣ በጎ ፍቃደኞች ጉልበታቸውን፣ ገንዘባቸውንም ሆነ ጊዜያቸውን አገልግሎቱን ማግኘት ለሚገባቸው ትክክለኛ ሰዎች እየሰጡ መሆኑን ያመኑበት መሆኑ አገልግሎቱ ግቡን እንዲመታ እና ውጤታማ እንዲሆን ያግዛል ሲሉ አስገንዘበዋል።

ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት በቀጣይነት በበጎፍቃድ አገልግሎት ላይ እንዲሰማሩ ከዚህ ቀደም የሠሩት የበጎፍቃድ ሥራ በሌላ አካል እንዳይፈርስ ወይም እንዳይባክን በተቋማት መካከል የእርስ በርስ መናበብ ሊኖር ይገባል ሲሉ ጠቅሰው፤ የበጎፍቃድ አገልግሎት መስጠት ለሚፈልጉ ሰዎች ክፍት የሆኑ አሠራሮችን በተቋማት ውስጥ መገንባት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You