የኢትዮጵያ አይነ ስውራን ብሔራዊ ማህበር ከተመሰረተ 59 ዓመታትን ያስቆጠረ አንጋፋ ማህበር ነው። ማህበሩ የተቋቋመበትን ዓላማ መሰረት በማድረግ ዓይነ ስውራን ዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የተለያዩ ስራዎችን ሲሰራ የቆየና በዚህ ስራውም በርካታ ዓይነ ስውራንን በማስተማርና በማሰልጠን እራሳቸው ስለራሳቸው፤ እንዲሁም ማህበረሰቡ ስለ ስለእነርሱ ግንዛቤ እንዲኖረው ሲሰራ የቆየና አሁንም እየሰራ ያለ ማህበር ነው።
ማህበሩ ቀደም ሲል ያስተዳድራቸው የነበሩ ሁለት የዓይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤቶች የነበሩት ሲሆን፤ በነዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥም በርካታ ተማሪዎች ተምረው ለቁም ነገር ደርሰዋል። ይሁንና ማህበሩ በአሁን ወቅት እያስተዳደረ የሚገኘው ብቸኛውና አንድ ለእናቱ የሆነውን በደቡብ ክልል የሚገኘውን የወላይታ ሶዶ ኦቶና ዓይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ነው። ይህ ትምህርት ቤት በ1957 ዓ.ም የተቋቋመና አዲስ ሕይወት የተባለ የውጭ ድርጅትና መንግስትም ለአጭር ጊዜ ሲተዳድር መቆየቱን አቶ ወሰን ዓለሙ፤ የኢትዮጵያ ዓይነ ስውራን ብሔራዊ ማህበር ፕሬዚዳንት፤
የኢትዮጵያ ዓይነ ስውራን ብሔራዊ ማህበር የዓይነ ስውራንን ጉዳይ በሚገባ ሊያውቅና ሊረዳ የሚችል መሆኑን በማመን ከ1971 ዓ.ም ጀምሮ ማህበሩ ትምህርት ቤቱን ሙሉ በሙሉ ተረክቦ እንዲያስተዳድር መደረጉን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል። “አንድ ዓይን ያለው በአፈር አይጫወትምና” ማህበሩ ይህን ዕድሜ ጠገብና አንጋፋ የወላይታ ሶዶ ኦቶና ዓይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ከ1971 ዓ.ም ጀምሮ ከተለያዩ የውጭ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች፤ በተለይም ሲቢኤም ከተባለው የጀርመን ተራድኦ ድርጅት በሚያገኘው ገቢ ሲያስተዳድር ቆይቷል።
ትምህርት ቤቱ ለበርካታዎቹ እንደ እናትና አባት ሆኖ በመንከባከብ፤ ከቀለም ትምህርት በተጨማሪም የሕይወት ክህሎትን በማስተማር ለቁም ነገር ማድረስ የቻለ ባለውለታ ትምህርት ቤት መሆኑን ብዙዎች ይመሰክራሉ። በዚሁ ብቸኛ ትምህርት ቤት ተምረው ዛሬ በተለያዩ የስራ ዘርፎች ተሰማርተው ራሳቸውን በማስተዳደር ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ የቻሉና ትልቅ ደረጃ የደረሱ በርካታ ዓይነስውራን ዜጎችም አሉ። ከነዚህም መካከል ማየት የተሳነው መምህር በላይ ባሳ አንዱ ነው።
“በወላይታ ሶዶ ኦቶና ዓይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ከጀማሪ እስከ ስምንተኛ ክፍል በመማሬ ዕድለኛ ነኝ” የሚለው መምህር በላይ፤ ትምህርት ቤቱ በ1957 ዓ.ም ሲመሰረት 10 ተማሪዎችን ይዞ የጀመረና ከዓመት ዓመት የተማሪዎችን ቁጥር በመጨመር በርካታ ዜጎችን ለቁም ነገር ያበቃ ትምህርት ቤት መሆኑን ያስታውሳል። እርሱን ጨምሮ በርካታ ማየት የተሳናቸው ህፃናትን የትምህርት ወጪ ከመሸፈን በተጨማሪ የምግብ፣ የአልባሳት፣ የህክምናና አጠቃላይ የህይወት ክህሎትን በማስተማርና በማሰልጠን እንደ እናትና አባት ተንከባክቦ ያሳደገና ያስተማረ ትምህርት ቤት መሆኑን ይናገራል።
መምህር በላይ፤ እስከ ስምንተኛ ክፍል በዚሁ ትምህርት ቤት በመማሩ ብዙ ማትረፉንና አሁን ለሚገኝበት የኑሮ ደረጃ መሰረት የተጣለበት ስፍራ ነው። በሚለው የወላይታ ሶዶ ኦቶና አዳሪ ትምህርት ቤት በቆየባቸው ዓመታት ከቀለም ትምህርት በተጨማሪ ማህበራዊ ሕይወትን በመለማመድ ዓይነ ስውራን በቀላሉ ከማህበረሰቡ ጋር እንዴት መኖርና መግባባት እንደሚችሉ ያሰለጠናቸው መሆኑንም ይናገራል።
የዘጠነኛና የአስረኛ ክፍል ትምህርቱን በወላይታ ሶዶ ተከታትሎ አዲስ አበባ በዳግማዊ ምኒሊክና በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤትም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቅቋል። በመቀጠልም በዲላ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪውን በታሪክ ትምህርት የተከታተለ ሲሆን፤ ሁለተኛ ዲግሪውን ደግሞ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በገቨርናንስ ዴቭሎፕመንት ሰርቷል።
መምህር በላይ፤ በአሁኑ ወቅት በወላይታ ሶዶ ሁለተኛ ደረጃ መሰናዶ ትምህርት ቤት የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት እያስተማረ ይገኛል። በዚሁ ትምህርት ቤት ማስተማር ከጀመረ ከአስር ዓመት በላይ ያስቆጠረው መምህር በላይ፤ ትዳር ይዞ አራት ልጆች አፍርቷል። የመጀመሪያ ልጁ የኮሌጅ ተማሪ፤ ሁለተኛ ልጁ ማትሪክ ተፈታኝ፤ ሶስተኛዋ ልጁ ደግሞ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን የመጨረሻ ወንድ ልጁ የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ነው።
የአራት ልጆች አባት የሆነው መምህር በላይ ቤተሰቡን በጥሩ ሁኔታ የሚመራና በአካባቢውም ተቀባይነት ያለው ሰው መሆኑን ይናገራል። ከዚህ በተጨማሪም በኢትዮጵያ አይነ ስውራን ብሔራዊ ማህበር የቦርድ አባል እንዲሁም በወላይታ ሶዶ ኦቶና ዓይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ደግሞ ሰብሳቢ በመሆን በሁለቱም አካላት የተሰጠውን ድርብ ኃላፊነት ባለው አቅም እየተወጣ ይገኛል። ይሁን እንጂ፤ በአሁን ወቅት በወላይታ ሶዶ ኦቶና ዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት ላይ የተጋረጠው አደጋ እያሰጋው መሆኑን ይናገራል።
ይህ ብቸኛውና አንድ ለእናቱ የሆነው የወላይታ ሶዶ የኦቶና ዓይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ማየት ለተሳናቸው ህፃናት እየሰጠ ያለው ጠቀሜታ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። የሚለው መምህር በላይ፤ ከዕለት ዕለት የተማሪዎቹ ቁጥር እያሽቆለቆለና የትምህርት ጥራቱም እየቀነሰ የመጣ መሆኑን ሲናገር በቁጭት ነው። ለዚህም ምክንያቱ ቀደም ሲል ያግዘው የነበረው የጀርመን እርዳታ ሰጪ ድርጅት እርዳታውን በማቆሙና የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ዓይነ ስውራን ብሔራዊ ማህበር ደግሞ የበጀት አቅም የሌለው በመሆኑ ነው።
ታዲያ “አንድ ዓይን ያለው በአፈር አይጫወትም” እንዲሉ አበው በበጀት እጥረት ምክንያት ለበርካታ ህፃናት የነገ ተስፋ የሆነውን የወላይታ ሶዶ ኦቶና አዳሪ የዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት ከተጋረጠበት አደጋ የማዳንና ህፃናቱን መርዳት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት ቢሆን መልካም ነው የሚለው መምህር በላይ፤ ማየት የተሳናቸው ህፃናት ከአንድ እስከ ስምንተኛ ክፍል በአዳሪ ትምህር ቤት ቢቆዩና ዘጠነኛ ክፍል ላይ ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ቢቀላቀሉ ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ያምናል። በቀጣይም፤ ከታች ያሉትን ማየት የተሳናቸው ህፃናት ባላቸው አቅም ለመርዳትና እሱ ያገኘውን ዕድል አግኘተው እንዲማሩ ፅኑ ምኞቱ እንደሆነ ይናገራል።
ትምህርት ቤቱ በአሁን ወቅት እስከ አራተኛ ክፍል ያሉ ከ43 የማይበልጡ ተማሪዎችን ይዞ እየተንገዳገደ ይገኛል። ማህበሩ በዓመት ከመቶ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎችን ለማስተማርና ለማሰልጠን ዕቅድ የነበረው መሆኑን የሚናገረው መምህር በላይ፤ ማህበሩ የገጠመውን የበጀት እጥረት ለመቅረፍ የክልሉን ትምህርት ቢሮ፣ የተለያዩ የመንግስት አካላትንና አጋዥ ድርጅቶችንም ጭምር የጠየቀ ቢሆንም እስካሁን ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጣ የሚያስችል ምላሽ አልተገኘም። በመሆኑም ትምህርት ቤቱ ለ2012 የትምህርት ዘመን ቀጣይነቱ ያጠራጥረኛል በማለት ሀሳቡን ይቋጫል።
እንደ መምህር በላይ ሁሉ፤ ቀደም ሲል የነበሩ በርካታ ማየት የተሳናቸው ተማሪዎች ከዚሁ ትምህርት ቤት ተምረውና ሰልጥነው በመውጣታቸው ዛሬ ህይወት ቀላል እንደሆነላቸው ብዙዎች ይናገራሉ። ይሁን እንጂ፤ ትምህርት ቤቱ አሁን በተጋረጠበት አደጋ ምክንያት መንግስት ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጠው ጥረት እየተደረገ ቢሆንም፤ ትምህርት ቤቱ ከማህበሩ ስር ወጥቶ በክልሉ ትምህርት ቢሮ እንደማንኛውም ትምህርት ቤት በአካቶ ትምህርት እንዲተዳደር የመንግስትም ሆነ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ፍላጎት መሆኑን የማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ወሰን ዓለሙ እና የማህበሩ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሱልጣን ኢስሙ ተናግረዋል።
አቶ ወሰን ዓለሙ፤ የኢትዮጵያ ዓይነ ስውራን ብሔራዊ ማህበር ፕሬዚዳንት፤ አካል ጉዳተኝነት ለድህነት የቀረበ በመሆኑ ድህነትና አካል ጉዳት እርስ በእርስ የተቆራኙ ናቸው በማለት ሀሳባቸውን ሲገልፁ፤ አካል ጉዳት በራሱ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ነው። ምክንያቱም እያንዳንዱ እንቅስቃሴ የሌሎችን እርዳታ ይጠይቃል፤ አጭር መንገድ በረጅም ለመሄድ ያስገድዳል፤ ለምሳሌ፤ ማየት የተሳናቸው ተማሪዎች በትንሹ ከሌሎቹ በተለየ መልኩ የመማሪያ ብሬል ያስፈልጋቸዋል። ከዚህም በላይ ተጨማሪ እንክብካቤና እገዛንም ያሻቸዋል።
የኢትዮጵያ ዓይነ ስውራን ብሔራዊ ማህበር፤ በወላይታ ሶዶ ኦቶና የዓይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ላይ ብዙ ራዕይ የነበረውና ሞዴል ትምህርት ቤት በማድረግ ኢትዮጵያ ውስጥ የሌሉ የሒሳብና የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶችን ማየት ለተሳናቸው ህፃናት በቀላሉ ለማድረስ ያለመ ነበር። ይህን ደግሞ መቀየር የሚቻለው እንደዚህ ዓይነት ብቸኛ የሆኑ ትምህርት ቤቶችን በማዋቀርና ሞዴል በማድረግ እንጂ አንድ ያለውን በማጥፋት አይደለም በማለት ማህበሩ ባጋጠመው የበጀት እጥረት የዓይነ ስውራን አለኝታ የነበረውና ብቸኛው የወላይታ ሶዶ ኦቶና ዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት በመዘጋት አፋፍ ላይ ነው ይላሉ።
አቶ ሱልጣን ኢስሙ የኢትዮጵያ ዓይነስውራን ብሔራዊ ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ በበኩላቸው፤ ማህበሩ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ የበጀት እጥረት ያጋጠመው በመሆኑ በርካታ ዓይነ ስውራንን በማስተማርና በማሰልጠን የሚታወቀው ብቸኛው የወላይታ ሶዶ ኦቶና ዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት ከዓመት ዓመት የተማሪ ቁጥርና ለህፃናቱ የሚሰጠው የአገልግሎት ጥራትም እየቀነሰ የመጣና በአሁን ወቅት ደግሞ ቀጣይነቱ ጥያቄ ውስጥ እንደወደቀ ይናገራሉ።
ማህበሩ ለችግሩ መፍትሔ ያለውን ከፌዴራልና ከክልል የመንግስት አካላት ጋር በመነጋገር የፋይናንስ እገዛ እንዲደረግለት የጠየቀ ቢሆንም እገዛውን ማግኘት አለመቻሉን ስራ አስኪያጁ ይናገራሉ። ከዚህም ባሻገር የተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመሔድ ሙከራ ቢያደርጉም ሊሳካ እንዳልቻለና የትምህርት ቤቱ ቀጣይ ዕጣ መዘጋት እንደሆነ ያስረዳሉ።
ለበርካታ ማየት የተሳናቸው ህፃናት የነገ ተስፋ በመሆን ለ59 ዓመታት ሲያስተምርና ሲያሰለጥን የቆየው ብቸኛው የወላይታ ሶዶ ኦቶና ዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት ዛሬ የመዘጋት አደጋ ተጋርጦበታል። ታዲያ “አንድ ዓይን ያለው በአፈር አይጫወትምና” አንድ ያለውን የዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት ለማዳን ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን ቢያደርግ፤ በተለይም የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በሙሉ የጉዳዩን አንገብጋቢነት በመረዳት ተገቢውን መፍትሔ ቢሰጡ መልካም ነው፤ እያልን ትኩረት ለዓይነ ስውራንና ለወላይታ ሶዶ ኦቶና ዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት በማለት አበቃን!
አዲስ ዘመን ግንቦት 21/2011
ፍሬህይወት አወቀ