ያልተከፈለ ውለታ…

የወታደሩ ልጅ …

የአዲስ አበባ ልጅ ነው ፡፡ ስድስት ኪሎ ‹‹ቸሬ›› ከተባለ ሰፈር ተወልዶ አድጓል ፡፡ ስለ ልጅነቱ ሲያስታውስ ፊቱ በደማቅ ፈገግታ ይበራል፡፡ ልጅነቱ ለእሱ መልካም የሚባል ነበር ፡፡ በዕድሜው እንደ እኩዮቹ ተጫውቶ ቦርቆ አሳልፏል ፡፡ ያን ጊዜ ሲያስታውስ በአእምሮው የማይጎረብጥ ትዝታ ውል እያለው ነው ፡፡

የወታደር ልጅ ነው ፡፡ ገና ከልጅነቱ ወታደር አባቱን በአትኩሮት ሲከታተል አድጓል፡፡ ወታደር ሀሞተ ኮስታራ ነው፡፡ ቆራጥና ሀገር ወዳድ፡፡ ወታደር ድንበር ጠባቂ ርቆ ተጓዥ ነው ፡፡ ከእኔ ይልቅ ለእኛ፣ ከቤተሰብ ይበልጥ ለሀገር ፣ ወገን ቅድሚያውን ይሰጣል ፡፡

ትንሹ ጥላሁን ይህ አይነቱ ሀቅ ለእሱ ብርቅ አይደለም፡፡ አባቱ ሁሌም ድንበር ሊያስከብሩ ከመላው ቤተሰብ ርቀው ይሄዳሉ፡፡ አለባበሳቸው ያምራል፣ አቋማቸው ይማርካል፡፡ በርካቶች ስለ እሳቸው የሚሰጡት ክብር ለየት ይላል፡፡ ይህ ሁሉ እውነት ለጥላሁን ትርጉሙ ብዙ ነው ፡፡ ሁሌም ወታደር አባቱ ከሌሎች እንደሚለዩ፣ ይሰማዋል፡፡ ክብራቸው፣ አቋምና ባህሪያቸው ይማርከዋል።

ጥላሁን ዕድሜው ከፍ ማለት ሲይዝ ውስጡ ብዙ አሰበ ፡፡ ለእሱ ከአባቱ ሙያ የበለጠ ሥራ የለም፡፡ ውትድርናን ከልብ ይወደዋል፡፡ ቆራጥነት ጀግንነት፣ ሀገር መውደድ ይሉትን ትርጉም ከወታደር አባቱ ተምሯል። ትምህርቱ እንደጓደኞቹ ነው ፡፡ ከእኩዮቹ ጋር ቀለም ቆጥሮ ይመለሳል፡፡ ልጅነትን ተሻግሮ ወጣትነቱ ሲጀምር ግን የውስጡ መሻት ከትምህርት ራቀ፡፡ ውትድርናን አጥብቆ ተመኘ ፡፡

የወታደር ልጅ ወታደር …

በዕድሜው ልጅ ቢሆንም ካሰበው እቅድ አልዘገየም። የዘመኑን ግዴታ አሟልቶ በክቡር ዘበኛ ክፍል የጦር አባል መሆን ቻለ ፡፡ ጥላሁን በሚወደው የአባቱ ሙያ ላይ መገኘቱ አስደሰተው። በሙሉ ልብ ለሀገሩ ድንበር ዘብ ሊቆም ቃል ገባ። ልክ እንደ አባቱ ቆፍጣና ወታደር ሊሆን ራሱን አዘጋጀ፡፡

ከማሰልጠኛ እንደወጣ የመጀመሪያ ምድቡ አዲስ አበባ ሆነ፡፡ ተወልዶ ባደገበት አካባቢ በወታደር ልብስ መታየት ለእሱ ክብር ነበር፡፡ አሁን ወዶና ፈቅዶ የገባበት ውትድርና ግርማ ሞገሱ ሆኗል፡፡

ጥቂት ጊዜያትን አዲስ አበባ የቆየው የክቡር ዘበኛው ወታደር ወደ አሰብ እንዲሄድ ግዳጅ ተሰጠው፡፡ አሰብ ከአዲስ አበባ በብዙ ይርቃል፡ የአየሩ ባህሪ ሞቃታማና ለእንግዳ የሚከብድ ነው፡ ግዳጅ ነውና ጥላሁን ስፍራው መሄድ አለበት፡ ለውትድርናው አዲስ የሆነው ወጣት አሰብ ደርሶ ስራውን ጀመረ፡፡

አሰብና ጥላሁን ዓመታትን በአብሮነት ዘለቁ፡፡ ሙቀት፣ ግለቱ የወታደር ሌላው ግዳጅ ነበር፡፡ በዚህ ስፍራ ችግርን ተቋቁሞ በአሸናፊነት መውጣት ግድ ይላል፡፡ ጥላሁን የሙያውንና የተፈጥሮን ፈተናዎች በጥንካሬው አሸንፎ ጊዜያትን ቆጠረ፡፡

ወታደር ማረፊያው ከአንድ አይደለም፡፡ ‹‹ተነስ›› ባሉት ጊዜ ጓዙን ሸክፎ ሊሮጥ ይፈጥናል፡፡ ወታደር ቋሚ ቤት የለውም፡፡ በየደረሰበት እግሩን ይተክላል። ጥላሁን ወታደር ሆኗልና በዚህ ግዳጅ ውስጥ አለፈ። አሰብን በለቀቀ ጊዜ ማረፊያው ከአንድ አልሆነም ፡፡ በየሀገሩ በየስፍራው ተጓዘ ፡፡

ከውጊያ አውድማው፣ ከጦርነቱ እሳት ተገኘ። ወታደሩ ጥላሁን መገኛው የኤርትራ ተራሮች ሆኑ፡፡ ጀበርናውን ይዞ፣ ቆቡን ደፍቶ፣ መሳሪያውን አንግቶ ከቀበሮ ጉድጓድ መሸገ፡፡ የከረን ምድር እጁን ዘርግቶ ተቀበለው፡፡

ኤርትራ በቆየ ጊዜ ከአስር ቦታዎች በላይ ተዘዋውሯል። የሄደበት ግዳጅ ከጦርነት ስጋት አልራቀም፡፡ በየቀኑ የጥይት ድምጽ በጆሮው ያፏጫል፡፡ ታንክና ፣መድፉ ፣ በላዩ ያጓራል፡፡ ጥላሁን ይህ እውነት የማንነቱ መለያ ነው፡፡ የአባቱ ሙያ፣ የልጅነቱ ምኞት ነውና ችግር መከራውን አምኖ ተቀብሏል፡፡

ቁስለኛው ወታደር…

ጦርነት ክፉ ነው፡፡ ህይወት ያጠፋል፣ አካል ያጎድላል። በጦርነት የትግል ጓድን ከቅርብ ማጣት ብርቅ አይደለም። ጥላሁን ግዳጅ ላይ በቆየባቸው ዓመታት እነዚህን እውነታዎች በግንባር ተጋፍጧል፡ በጦር ሜዳ ውሎ ወድቆ መነሳት፣ ገድሎ መሞት፣ ያለ ነው፡፡

ጥላሁን በጦር ሜዳ ውጊያ አካሉን በፈንጂ ተመቷል፡፡ ከዚህ ቁስሉ ሲያገግም ግን ‹‹በቃኝ›› ብሎ ቤቱ አልቀረም፡፡ በተለየ ሞራልና ስሜት ዳግም ከግዳጅ ዋለ፡፡ እንዲያም ሆኖ ችግር አላጣውም። በሌላ አውደ ውጊያ በጥይት ተመቶ ቁስለኛ ሆነ ፡፡

ህይወት በዓመታት የውትድርና ጉዞ ቀጠለ። ጥላሁን ከጦርሜዳ ውሎ ግዳጁን መወጣቱን አላቆመም፡፡ የኤርትራ በረሀ፣ የከረን ምድር ከዕድሜው ቀንሰው ዋጋ አስከፈሉት። የወታደር ልጅ ነውና በሆነው ሁሉ አልተማረረም፡፡ ግዴታውን በብቃት እየተወጣ ለሌላው አዲስ ግዳጅ ራሱን አዘጋጀ ፡፡

ውሎ አድሮ ግን በሀገሪቱ አዲስ ነገር ተከሰተ ፡ ፡ ኢህአዴግ መላው ሀገሪቱን ሲቆጣጠር የደርግ ሥርዓት ወደቀ፡፡ ይህ አጋጣሚ በውትድርና ዓመታትን ለዘለቁ የሠራዊቱ አባላት የበዛ ፈተናን አቀበለ፡፡ በድንገት ነገሮች ተለዋወጡ፣ የነበረው እንዳልነበረ ተቀይሮ በአዲስ ታሪክ ተተካ፡፡

ያልተከፈለ ዋጋ…

ጥላሁን በቆየባቸው የውትድርና ዓመታት ከንጹህ ደመወዙ ያለፈ ሀብት ንብረት አላፈራም፡፡ እስከዛሬ ከሚከፈለው ጥቂት የወታደር ገቢው ለእናቱ እየሰጠ ሲጦራቸው ቆይቷል፡፡ ድንገቴው አጋጣሚ ለእሱና መሰሎቹ ያልተጠበቀ ነበር። ብዙዎቹ ከነበሩበት ተፈናቀሉ፡፡ በርካቶች ያለአንዳች ጥቅም ከጎዳና ወደቁ። ለሀገር ውለታ የከፈሉ አንጋፋዎች ዋጋቸው ተረስቶ እንደዋዛ ተቃለሉ ፡፡

ለጥላሁን ድንገቴው የመንግሥት ለውጥ ያደረሰበት ጅራፍ ቀላል አልነበረም፡፡ ዓመታትን ያለፈበት የውትድርና ህይወት እንደ ልፋቱ አልከፈለውም፡፡ እሱም እንደ ትግል አጋሮቹ በፈተና መንገዶች ተመላለሰ፡፡ ከቀናት በአንዱ ግን ለጆሮው መልካም ነገር ደረሰ፡፡ የእሱን ልምድ በሚመጥን ደረጃ ከአንድ ታዋቂ ድርጅት በጥበቃ ሥራ ተቀጠረ። ይህ ሥራ ዓመታትን በውትድርና ላሳለፈው ጥላሁን አልከበደውም፡፡ የተሰጠውን ኃላፊነት በብቃት እየተወጣ ዓመታትን ዘለቀ፡፡

አምስት ዓመታትን በጥበቃ ሙያ የገፋው የቀድሞ ወታደር ህይወትን ሊያሸንፍ ቀን ተሌት ታተረ፡፡ ከውትድርናው ያተረፈው የሀገር ፍቅርና የሙያን ክብር ብቻ ነው፡፡ ስለደማ ፣ ስለቆሰለበት ታሪክ የተቀበለው የጀግንነት ሜዳይ አልነበረም ፡፡

ጥላሁን በምስጋና ተቀብሎ በይሁንታ የሚኖርበት የጥበቃ ሥራ እንደነበረው አልቀጠለም፡፡ ከቀናት በአንዱ አምስት ዓመታት ካገለገለበት ኩባንያ መቀነሱ ተነገረው፡፡ ይህኔ የቀድሞው ቁስለኛ ወታደር ይይዘው፣ ይጨብጠው አጣ፡፡ ባሰለፋቸው የውትድርና ዓመታት አቅሙን በሚደግፍ ዕውቀትና ትምህርት አልታገዘም፡፡ ሙሉ ህይወቱን የሰጠው ለዋለበት ግዳጅና ለተሰጠው ኃላፊነት ብቻ ነው፡፡

አሁን በድንገት የሆነበት ሥራ ማጣት ለማንነቱ ፈተና ሊሆን ግድ ብሏል፡፡ ጥላሁን ምርጫ አልነበረውም። ከሥራ ሊሰናበት ራሱን አዘጋጀ፡፡ ሥራ መልቀቁን ተከትሎ ግን ሰላም አላገኘም፡፡ ጤናው ተቃወሰ፡፡ እንደ ቀድሞው የህክምና ምርመራን መቀጠል አልቻለም፡፡ ድርጅቱን ሲለቅ ይህ ዕድል አብሮት ተቋረጠ፡፡ ዕለት በዕለት ህመሙ ተደራርቦ በሽታውን አባሰው፡፡

ትዳርና ህይወት…

ጥላሁን ከውትድርና መልስ ትዳር ይዞ ፣ ጎጆ ለማቅናት ሞክሯል፡፡ ከባለቤቱ ጋር የነበረው አብሮነት ግን በሰላም አልዘለቀም፡፡ ፍቅር የጠፋበት ጥምረት ኑሯቸውን አቀዝቅዞ ህይወታቸውን ረበሸው። ትዳሩ መልካም ሳይሆን ቢቀር ውሎ አድሮ በፍቺ ተቋጨ፡፡

ባልና ሚስቱ በመሀላቸው የተፈጠረው አለመግባባት ለብዙ እንዳደረሳቸው ዛሬም ድረስ ያስታውሳል። ግጭታቸው በከፋ ጊዜ የእሱ ውሳኔ ከፍች በላይ ነበር። በሰላም ተለያዩ እንጂ አብሮነታቸው ቢቀጥል ኖሮ ውጤቱ መልካም እንደማይሆን ያውቃል፡፡ ከተስማሙበት ፍቺ በኋላ አባወራው በብቸኝነት ሊኖር ግድ አለው፡፡

ጥላሁን የጤናውን ጉዳይ በቀላሉ መቆጣጠር አልቻለም፡፡ እንደዋዛ አልጋ ያስያዘው ህመም ደም ብዛት ስኳርና ኮሌስትሮን አስከትሎ ሰላም ነሳው፡፡ ከበሽታ የሚታገለው ህመምተኛ አሁን ከጎኑ ማንም የለም፡፡ ከህመሙ እኩል ችግር አብዝቶ እየፈተነው ነው፡፡

የሚኖርበት ቤት የቀበሌ ቢሆንም ለዓመታት ሳይከፍለው የቆየ የኪራይ ውዝፍ አለበት፡፡ ይህን ቢያውቅም ለመፍትሄው ፈጥኖ አልሮጠም። ባልተመቸ ህይወት ዕዳውን እያሰበ መኖሩን ቀጠለ። ትንሽ ሻል እንዳለው ራሱን አበርትቶ መቆሙ አልቀረም፡፡ ዳግም የዘበኝነት ሥራ ጀምሮ ለህይወቱ መታገል ያዘ፡፡

የፈረሰው ጎጆ …

አንድ ቀን ጥላሁን ሥራ አድሮ ወደቤቱ ጉዞ ጀመረ። ውስጡ ድካምና እንቅልፍ እየተሰማው ነው፡፡ ሰፈሩ አካባቢ ሲደርስ ግን ዓይኖቹን ማመን ተሳነው፡፡ ደሳሳዋ የድሀ ጎጆው በባለ ብርቱዎቹ ክንድ ተሰብራለች። አፉ እንደደረቀ ጠጋ ብሎ ሊጠይቅ ሞከረ፡፡ ምላሽ ከማግኘቱ በፊት የቤት ዕቃውና ጥቂት ልብሶቹ ከደጅ ተዝረክርከው ተመለከተ፡፡ የቀበሌ ቤቱን በውዝፍ ዕዳው ሰበብ እንዲለቅ ሲባል የተደረገ ውሳኔ ነበር ፡፡

በወር ሰባት ብር ብቻ ይከፍልበት የነበረው ቤት ከእይታ ለመግባት ቀላል ነበር ፡፡ ዙሪያውን ያለው ሰፊ ቦታ ተጨማሪ ቤት ለመስራት አመቺ ነው። ውዝፉን አሰበው ለሌላ ሰው ለመስጠት ያሰቡት የቀበሌው ኃላፊዎች እሱን መንቅረው ለማስወጣት ፈጽሞ አላዘኑም፡፡

ከዚህ በኋላ ጥላሁን በኪራይ ቤት ኑሮ መንከራተት ያዘ፡፡ ጤና ማጣቱ ከእጅ መንጣቱ ተዳምሮ በእጅጉ ተፈተነ ፡፡ ብቸኝነት የዞረበት ማንነቱ ባይተዋርነትን አክሎ በብዙ አንገላታው፡፡ ውሎ አድሮ አቅሙ ተዳከመ። ብስጭትና ጤና ማጣት ተጋግዘው አቅሉን አሳጡት፡፡ ጥላሁን ተስፋ ቆረጠ፡፡ ‹‹አለንህ›› የሚል ወዳጅ ዘመድ ነጠፈበት፡፡

ጥላሁን ጤናውን አጥቶ በደከመበት ጊዜ ውትድርናውን አስቦ ስለ ሀገር ዕድሜውን የገበረበትን አስታውሶ የጦር ኃይሎች ሆስፒታልን ደጅ ጠንቷል። በወቅቱ ግን ስለእሱ ውለታ ማንም ግድ ያለው አልነበረም፡፡ እሱን ጨምሮ ሌሎች አጋሮቹ የዕድሉ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ከበር ተመልሰዋል፡፡

የትናንትናው ክንደ ብርቱ ጥላሁን አሁን በባዶ ቤት በር ተዘግቶበት ‹‹የሰው ያለህ›› ማለት ይዟል፡፡ ያለፈበት የህይወት ውጣውረድ ፈተና ሆኖ ቢጥለውም ለሀገር የከፈለው ታላቅ ዋጋ አልተመዘገበለትም። ጥላሁን ይህን ሲያስብ ውስጡ ያዝናል፣ ዓይኖቹ በዕንባ ይሞላሉ፡፡ ጠዋት ማታ በንዴት ሲበግን ቆሽቱ እያረረ መሆኑ ይሰማዋል፡፡ የዚህ ውጤት ለስኳር ህመሙ መባባስ ምክንያት ሆኗል፡፡ አንዳንዴ ሁሉን በትዕግስት ማለፍ ቢችል ህመም እንደማይበረታበት ያስባል፡፡

በዚህ ስሜቱ ለመዝለቅ ግን ሁኔታዎች ቀላል አይደሉም፡፡ አንዱ ሲሞላ ሌላው እየጎደለ ብሶቱን ያንረዋል፡፡ ከቀናት በአንዱ ግን ይህን ታሪክ ከሚቀይር አጋጣሚ ድንገት ተገናኘ፡፡ ችግሩን በውል የሚያውቅ አንድ ወንድሙ ‹‹የወደቁትን አንሱ ››ከተባለ ግብረሰናይ ድርጅት ማረፊያ እንደተገኘለት ነገረው፡፡

ህይወትን በእፎይታ …

ይህ ዜና ብዙ ላየው ጥላሁን ታላቅ የምስራች ነበር። ዓመታትን ለሀገር ዋጋ ለከፈለው፣ በችግር ለተፈተነው፣ በህመም ለተሰቃየው ሰው እፎይታ ሆኖታል፡፡ ከወደቀበት ደሳሳ የኪራይ ቤት በአምቡላንስ በተወሰደ ጊዜ ውስጡ ያደረውን ስሜት ዛሬ በተለየ ትውስታ ያወጋዋል፡፡

ጥላሁን የዛኔ አሁን ላለበት ህይወት ላበቃው ወንድሙ የተለየ ክብር ይሰጣል፡፡ ዛሬም ቢሆን ከነባለቤቱ እየመጣ ዓይኑን የሚያየው እሱ ብቻ ነው። ሌሎች በቅርብ የሚያውቁት ግን ከነመፈጠሩም አስበውት አያውቁም። ትናንት ከእሱ እጅ የበሉ፣ አብረውት ክፉ ደግ ያሳለፉ ዛሬ ጎኑ ያለመኖራቸው ሀዘን ከቁጭት ያሳድርበታል፡፡

በውትድርና ዓለም ሳለ ሁለት ልጆችን ወልዷል። አንዱ አሰብ እያለ ተለይቶታል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ኑሮው በሀገረ አሜሪካ ስለመሆኑ ሰምቷል፡፡ ይህ ሁሉ ግን ለዛሬ ማንነቱ ያኖረለት አሻራ የለም፡፡ ሁኔታዎች ተለውጠው ታሪኩን ቀይረውታል ፡፡

አሁን ላይ ጥላሁን እግሮቹ ፈጽሞ አይታዘዙትም። እንደ ልቡ መቆም ያለመቻሉም የዊልቸር ተጠቃሚ አድርጎታል፡፡ ለችግሩ መፍትሄ እንዲሆን ግን ህክምናውን በወጉ ቀጥሏል፡፡ ያለፈበትን ውጣውረድ ሲያስበው ሀዘን የሚመላለስበት ይህ ሰው ዛሬ ላይ ስላቆመው ፈጣሪ ምስጋናውን ያቀርባል፡፡

ጥላሁን ‹‹የወደቁትን አንሱ›› የተባለው ድርጅት ከወደቀበት አንስቶ ታሪኩን ቀይሮለታል፡፡ ዛሬ ትናንት ያለፈበት የብቸኝነት ፣የችግርና መከራ ህይወት ከእሱ የለም፡፡ ቢታመም ይታከማል፣ ቢራብ ጠግቦ ያድራል። ለሀገሩ በከፈለው ዋጋ ልክ ውለታው ባይመለስም። ህይወት በፈቀደችለት ዕድል ዛሬን እንዲህ እየኖረ ስለነገው ህይወት በተስፋ ይሻገራል፡፡ ጥላሁን ኩማ መንፈሰ ጠንካራው የቀድሞ ጀግና፡፡

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You