ኢትዮጵያ የበርካታ ዓይነቶች ማዕድናት ባለጸጋ ናት፤ ከእነዚህም መካከል ኦፓል፣ ኤምራልድ፣ ሩቢ፣ ሳፋየር ፣አኳመሪን፣ ቶርመሪን፣ አማዞናይት፣ ኳርትስና ሌሎች የከበሩ ማዕድናት ይጠቀሳሉ። ማዕድናቱ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ። በቅርቡ የተካሄደው የማዕድን ኤክስፖም ይህንኑ አመላክቷል።
ስለከበሩ ማዕድናት ሲነሳ ከከበሩ ማዕድናት ስለሚሰሩ ጌጣጌጦች አለማንሳት አይቻልም። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከከበሩ ማዕድናት ጌጣጌጦች በስፋት እየተመረቱ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እየቀረቡ ናቸው። በአሁኑ ወቅት የማዕድን አቅራቢዎቹ በከበሩ ማዕድናት ላይ እሴት በመጨመር ጌጣጌጦችን በማምረት ወደ አሜሪካ፣ ህንድ፣ ቻይና እና ሌሎች ሀገራት እየላኩ ናቸው።
ከእነዚህ ማዕድን ላኪዎች መካከል የሶዞ ትሬዲንግ ፒኤልሲ አንዱ ነው። የድርጅቱ ባለቤት ወይዘሮ ባንቺዓለም ማሩ እንዳሉት፤ ድርጅቱ በከበሩ ማዕድናት ላይ እሴት በመጨመር እና ወደ ጌጣጌጥነት በመቀየር ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ያቀርባል። ድርጅቱ የከበሩ ማዕድናት ላይ እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ መላክ ከጀመረ 15 ዓመታት ያህል አስቆጥሯል። የከበሩ ማዕድናት ወደ ጌጣጌጥነት የመቀየር ሥራን ከጀመረ ግን ሦስት ዓመቱ ነው። እነዚህን እሴት የተጨመረባቸውን ማዕድናትና ጌጣጌጦችን ለአሜሪካ፣ ለቻይና፣ ለካናዳ፣ ለህንድ እና ለመሳሳሉት ሀገራት ገበያ ያቀርባል።
ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪም ሆነ የከበሩ ማዕድናት በብዛት እንደሚገኙባት ወይዘሮ ባንቺዓለም ጠቅሰው፤ እነዚህን ማዕድናት ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከሚገኙ አምራቾች ድርጅታቸው ተረክቦ እሴት በማከል ለተለያዩ አገልግሎት እንዲውሉ አድርጎ እንደሚሰራቸው ይገልጻሉ።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ከማዕድናቱ የሚሰሩት ጌጣጌጦች አንገት፣ ጆሮ እና እጅ ላይ የሚደረጉ ሲሆን፤ በተለየ መልኩ ደግሞ ድርጅቱ ለጋብቻ የሚሆን ቀለበት ሰርቶ ለገበያ ያቀርባል። ጌጣጌጦቹን ለመሥራት ኦፓል፣ ኤመራልድ፣ ሩቢ፣ ሳፋየር፣ አኳመሪን፣ ቶርመሪን፣ አማዞናይት፣ ኳርትስ፣ ስትሪን፣ ጋርኔት እና የመሳሳሉ በርካታ ማዕድናት ጥቅም ላይ ይውላሉ።
በዓለም ላይ አሉ ከሚባሉት ዘጠኝ በጣም ውድ የከበሩ ማዕድናት ሰባት ያህሉ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚገኙ የጠቆሙት ወይዘሮ ባንቺ ዓለም፤ ድርጅቱ ከወርቅ፣ ከብርና ከከበሩት ማዕድናት የተሰሩ የእጅ፣ የአንገት እና የጆሮ ጌጣጌጦች እንደሚያመርት ተናግረዋል። ሰው እንደፈለገውና እንደመረጠው ጌጣጌጦችን በትዕዛዝ እንደሚሰራ ይገልጻሉ።
ሶዞ ትሬዲንግ ፒኤልሲ ማዕድናቱን የሚያመርትባቸው ሁለት የማምረቻ ቦታዎች አሉት፤ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለ ሲሆን፣ አሁን ላይ 70 በቋሚነት እና በርከት ያሉ ጊዜያዊ ሠራተኞች አሉት።
ድርጅቱ የማዕድንና የጌጣጌጥ ምርቶቹን በሀገር ውስጥ የተለያዩ ቦታዎችም ለገበያ ያቀርባል የሚሉት ወይዘሮ ባንቺዓለም፤ የሀገር ውስጥ ገበያ በየጊዜው መሻሻሎችን እያሳየ እንደሆነም ገልጸዋል። ‹‹የጌጣጌጥ ማዕድናት ለማንኛውም ጊዜ የሚደረጉ ከመሆናቸውም በላይ ለምንወዳቸው ሰዎች ደስታችንን፣ አክብሮታቸውንና ፍቅራቸውን የምንገልጽባቸው ውድ ስጦታዎች ሊሆኑ ይችላሉ።›› ሲሉ ጠቅሰው፣ የማዕድናት ጌጣጌጦች ከሀገር ልብሶችም ሆነ ከየትኛዎቹም አልባሳት ጋር የሚሄዱ ውበና ማራኪ መዋቢያዎች መሆናቸውን አስታውቀዋል። የከበሩት ማዕድናት በውጭ ዓለም ከልጅ ልጅ የሚተላለፉ በአክብሮት የሚያዙ የተከበሩ ውድ ስጦታዎች መሆናቸውንም ተናግረዋል።
የማዕድን ዘርፉ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እምብዛም ትኩረት አልተሰጠውም ነበር የሚሉት ወይዘሮ ባንቺዓለም፤ «ይህ ዘርፍ እስከ 20 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን መመገብ ይችላል ብዬ አምናለሁ፤ ይህ ደግሞ ዝም ብሎ በምኞት የሚሆን ሳይሆን በጥናት የተረጋገጠ እውነታ ነው። ዘርፉ ከቁፋሮ ጀምሮ ምርቱን እስከ ማውጣት፣ ማስዋብ፣ መቅረጽ እና አደራጅቶ ለገበያ እስከ ማቅረብ ድረስ ባሉት ሰንሰለቶች ብዙ የሰው ኃይል ማቀፍ የሚችል ነው።›› ሲሉም አብራርተዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ የከበሩ ማዕድናት የጌጣጌጥ ምርት በዓለም ከዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ይዘዋወርበታል። ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ድርሻ ምን ያህል ይሁን የሚለው የሚወሰነው በዘርፉ ብዙ ባለሀብት ሲገባ ነው፤ ወጣቶች እውቀቱና ልምዱ እንዲኖራቸው ሲደረግ ነው።
የጌጣጌጥ ማዕድናት ከዋጋ አንጻር ተመጣጣኝና የኅብረተሰቡን ኪስ የማይጎዱ መሆናቸውን የሚገልጹት ወይዘሮ ባንቺዓለም፤ የጌጣጌጦቹ ዋጋ ከ500 ብር ጀምሮ እንደየዓይነታቸው የተተመነ እንደሆነ ይናገራሉ። አሁን ግን በተለየ መልኩ ለሕፃናት የሚሆኑ ጌጣጌጦችን ከዚህ ባነሰ ዋጋ ለማዘጋጀትና ለማቅረብ እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል። የማዕድናቱ ዋጋ ከፍ እንዲል የሚያደርገው ጌጣጌጦችን ለመሥራት የሚያገለግሉት ግብዓቶች ከውጭ ሀገር በውድ ዋጋ ስለሚገዙ መሆኑን ነው ወይዘሮ ባንቺዓለም የገለጹት።
በሀገራችን አርቴፊሻል ጌጣጌጦችን ገዝቶ መጠቀም እየተለመደ መምጣቱን ጠቅሰው፤ እነዚህን ጌጣጌጦች በየጊዜው እየገዙ ከመጠቀም ይልቅ የተፈጥሮ ስጦታ የሆኑ የከበሩ ማዕድናት ጌጣጌጦችን መጠቀም እንደሚገባ ይጠቁማሉ። ይህን ማድረግ የሀገራችንን ማዕድናት በማስተዋወቅ ጠቃሚ መሆን እንደሚያስችልም ይናገራሉ።
እሳቸው እንደሚሉት፤ እነዚህን የማዕድን ምርቶች ለማስተዋወቅ በተለያዩ ኤግዚቢሽንና ሌሎች ቦታዎች ላይ ይሳተፋሉ። ቀደም ሲል የከበሩ ማዕድናት የሚገዙት የውጭ ሀገር ዜጎች ነበሩ፣ ኢትዮጵያዊያን እምብዛም አልነበሩም። አሁን ኢትዮጵያውያን እነዚህን ምርቶች ለመግዛት ሆነ ስለማዕድናቱ ለማወቅ ፍላጎት እያሳዩ ናቸው።
በርካታ ባለሀብቶች በዘርፉ መሰማራት ይኖርባቸዋል የሚሉት ወይዘሮ ባንቺዓለም፤ የእነሱ ኢንቪስት ማድረግ ዘርፉ እንዲጠናከር እድል ይፈጥራል ብለዋል። አሁን በዘርፉ ከላይ ያሉት ጥቂቶች መሆናቸውም ጠቅሰዋል። ዘርፉ ለብዙ ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር እንደሚችል አመልክተው፣ በተለይ ኅብረተሰቡ ለትውልድ ተሻጋሪ ሀብቶች ለሆኑት የከበሩ ማዕድናት ትልቅ ዋጋ መስጠት እንዳለበት አስገንዝበዋል። ‹‹በራሳችን ሀብት እኛው አጌጠንና ደምቀን ሀብታችንን ለሌላው ዓለም ማስተዋወቅ አለብን›› ብለዋል።
ሌላኛው የከበሩ ማዕድናት ላኪ ‹‹ሰበሀን ጀም ስቶን ኢምፓየር ፒኤልሲ›› የተሰኘው ድርጅት ነው። ድርጅቱ ለረጅም ዓመታት በጌጣጌጥ ሥራ ላይ የቆየ ሲሆን፤ በከበሩ ማዕድናት ማስዋብና ማስጌጥ ሥራ ላይ አራት ዓመት ያህል አስቆጥራል።
የድርጅቱ ባለቤት ወይዘሮ ሐና ዮሐንስ ድርጅቱ የከበሩ ማዕድናትና ጌጣጌጦችን በማምረት ለሀገር ውስጥ ገበያና ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርብ ይናገራሉ። ቀደም ሲል ከሚሰሩት የጌጣጌጥ ሥራዎች አንጻር ሲታይ የከበሩ ማዕድናትን ጌጥ አድርጎ መሥራቱ ምንም ዓይነት ልዩነት እንደሌለው ይገልጻሉ። የከበሩ ማዕድናትን ወደ ጌጥነት መቀየር የመቅረጽ፣ የመቁረጥና የማስዋብ እና መሰል የተለየ እውቀትና ትምህርትን ይጠይቅ እንደነበርም ነው ወይዘሮ ሀና የገለጹት።
እሳቸው እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ከ300 በላይ የሚሆኑ ለጌጣጌጥ መሥሪያ የሚውሉ ማዕድናት አሉ። እንደ ኦፓል፣ ኤምራልድ፣ ሳፋየር፣ ሩቢ፣ ፔሪዶት እና የመሳሰሉት ሁሉም ዓይነት የከበሩ ማዕድናት የወርቅ፣ ብር እና መሰል አክሰሰሪዎችን በመጠቀም የተለያዩ ጌጣጌጦች ሊሰሩባቸው እንደሚችሉ ይገልጻሉ። እንደየሰው ፍላጎት በቅርጽም ሆነ በዓይነት የተለያዩ ጌጦጌጦችን ማምረት ይቻላል።
እነዚህን ማዕድናት በክልል ከሚገኙ በማህበር ተደራጀተው ከሚሰሩ ቆፋሪዎች ድርጅታቸው ተረክቦ በማሽን በመጠቀም አስውቦና አሳምሮ /እሴቶች ጨምሮ/ ጌጣጌጦችን እንደሚያመርት የሚገልጹት ወይዘሮ ሀና፤ ለአንገት፣ ለጆሮ፣ የእጅ እና ለጣት ቀለበትና ለመሳሰሉት የሚውሉ ጌጣጌጦችን እንደሚያመርት ጠቁመዋል። ምርቶቹን ለሴቶችም ለወንዶችም እንዲሆኖ አድርጎ እንደሚያምርትም ነው ያስታወቁት። የሰዎችን ፍላጎት መሠረት በማድረግ የሚሰሩ ጌጣጌጦች እንዳሉም አመላክተዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ድርጅቱ በሀገር ውስጥ ምርቶቹን የሚያስተዋወቅባቸውና የሚሸጥባቸው መደብሮች አሉት፤ በአውሮፓ እና ሌሎችም ሀገራት ምርቶቹን ለገበያ ያቀርባል። ከማዕድናት የሚሰሩት ጌጣጌጦች ጥራታቸውን ጠብቀው የሚሰሩ በመሆናቸው በዓለም ገበያ ይፈለጋሉ። ምርቶቹ በዋጋም ቢሆን በጣም ውድ የሚባሉ፣ መካከለኛ እና ዝቅተኛ የዋጋ ደረጃ ያላቸው ናቸው። ዝቅተኛ ዋጋ ያላቸው፣ ማንኛውም ሰው ገዝቶ ሊጠቀምባቸው የሚችሉ ዓይነቶችም አሉ። እነዚህ ዋጋቸው በጣም ባልተወደደ ማዕድናት የሚሰሩ ምርቶች ናቸው። ማኅበረሰቡ በራሱ የማዕድን ሀብት እንዲያጌጥ ታሰቦ የተሰሩ በመሆናቸው ግንዛቤን ለመፍጠር ያስችላሉ።
በተለምዶ ጌጣጌጦች ከሚሸጡበት ዋጋ በታች የሚሸጡ የከበሩ ማዕድናት ጌጦጌጦች እንዳሉም ጠቁመዋል። ጌጣጌጦቹ ከከበሩ ማዕድናት የተሰሩ ናቸው ሲባሉ ጥርጣሬ የሚያድርባቸው እንዳሉም ጠቅሰው፣ ቀረብ ብለው ሲያዩና ሲጠይቁ በመገረም ለስጦታና ለተለያየ ጉዳይ እየገዙ የሚጠቀሙ እንዳሉም ወይዘሮ ሀና ይጠቁማሉ። አሁን ላይ ያለው የሰው አመለካከትም ሆነ የመግዛት ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸው፣ በርካታ ሰዎች ለስጦታና ለተለያዩ ዝግጅቶች ጌጣጌጦቹን ለመጠቀም እንደሚገዙ አስታወቀዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ድርጅቱ ለሦስት ሰዎች ቋሚ፣ ለበርካታ ሰዎች ደግሞ ጊዜያዊ የሥራ እድል መፍጠር ችሏል። እነዚህን ምርቶቹን በተለያዩ ኤግዚቢሽኖችና በማህበራዊ ሚዲያዎች አማራጮች እያስተዋወቀ ይገኛል።
የከበሩ ማዕድናትን እሴት ጨምሮ በማስዋብ ጌጣጌጥ አድርጎ ለመሥራት በሀገሪቱ በቂ የከበሩ ማዕድናት ሀብት እንዳለ የጠቀሱት ወይዘሮ ሀና፣ ማዕድናቱን በሚፈለገው ልክ ከተለያዩ አካባቢዎች ማግኘት እንደሚቻል አስታውቀዋል። ጌጣጌጦቹን ለመሥራት የሚውሉ ግብዓቶች /አክሰሰሪዎች/ ችግር መኖሩን ጠቁመው፣ አብዛኛዎቹ ግብዓቶች ሀገር ውስጥ የማይገኙና ለማግኘትም አስቸጋሪ መሆናቸውን ወይዘሮ ሀና አስታውቀዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ አሁን ላይ እንደ ኦፓል፣ ኤምራልድ፣ ሳፋየር፣ ያሉት በዋጋ ውድ የሆኑትን ሳይጨምር የጌጣጌጦቹ ዋጋ ከሁለት ሺ እስከ 25 ሺ ብር ድረስ ይገመታል። አነስ ያለ ዋጋ ያላቸውን በሀገር ውስጥ ከከበሩ ማዕድናት በእጅ የተሰሩ ጌጣጌጦችን መግዛት እንደሚያኮራ አውቀው፣ ኅብረተሰቡ ጌጣጌጦቹን እንዲገዛም ጠይቀዋል። ‹‹የእኛን ምርቶች እኛው ገዝተንና ተጠቅመን ለዓለም ማስተዋወቅ አለብን፤ ይህ ሲሆን ዘርፉ ትኩረት እያገኘና እያደገ ይመጣል። እኛም የተሻለ መሥራት እንችላለን›› ሲሉ አስገንዝበዋል።
የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ በኅዳር ወር ከማዕድን ላኪዎች፣ ከከበሩ ማዕድናት እና ጌጣጌጥ አቅራቢዎች፣ ከአምራቾችና ላኪዎች ማህበር ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የከበሩ ድንጋዮችን እና ጌጣጌጥ ማዕድናትን ለውጭ ገበያ በብዛት የምታቀርብ ቢሆንም፣ ከዘርፉ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ከሌሎች ሀገሮች ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ነው።
ለዚህ በምክንያትነት ከሚጠቀሱት አንዱ በከበሩ ማዕድናት ላይ እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ ማቅረብ አለመቻል መሆኑን ጠቅሰው፣ ሁሉም ላኪዎች እሴት በመጨመር ላይ ትኩረት አድርገው ሊሰሩ እንደሚገባም አመላክተዋል።
በማዕድን ላኪዎች በኩል የሚነሱ ችግሮች እንዳሉም ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል። ችግሮቹ ለሥራቸው መሳለጥ እንቅፋት መሆናቸውን ተናግረው፣ በዘርፉ የሚስተዋሉት የሰለጠነ የሰው ኃይልና የማሽን እጥረት እና መሰል ችግሮች ቢቀረፉ የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻልም አመልክተዋል። በቀጣይ በምርቶች ላይ እሴት ለመጨመር የሚያስፈልጉ ማሽኖችን ለማስገባት በፋይናንስ፣ በክህሎት እንዲሁም የገበያ ትስስር መፍጠር ላይ መንግሥት በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 12 ቀን 2016 ዓ.ም