ተመልካች የተራቡ የቲያትር ደጃፎች

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ቲያትር ታሪክ ከሀገር ፍቅር ማህበር ምስረታ ይጀምራል፡፡ የሀገር ፍቅር ማህበር የተመሠረተው በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን በ1927 ዓ.ም በወቅቱ የሀገሪቱ የንግድና መገናኛ ዳይሬክተር በነበሩት በአቶ መኮንን ሀብተወልድ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ማህበሩ በዛን ጊዜ ሲቋቋም የፋሽስት ጣልያን ጦር ኢትዮጵያን ለመውረር ሽርጉዱን በማጠናቀቅ ላይ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል፡፡

ማህበሩ የተቋቋመበት ዋነኛ ዓላማ የሕዝቡን ሞራልና ወኔ በተለያዩ ስሜት ቀስቃሽ በሆኑ ጽሑፎችና ንግግሮች ለማይቀረው ጦርነት ማነሳሳትና ማነቃቃት ነበር፡፡ በዚህ ረገድ የነ ብላቴን ጌታ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሐንስና ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሴ ሥራዎች በግምባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እሑድ እሑድ በአደባባይ የሚደረጉ ንግግሮችና ለጦርነቱ የርዳታ ማሰባሰብ ዘመቻዎች ነበሩ፡፡

ይሁንና ፋሽስት ጣልያን አዲስ አበባን ሲቆጣጠር የማህበሩ ህልውና አደጋ ላይ በመውደቁ ዋነኞቹ የማህበሩ መስራቾች ሀገር ጥለው ቢሰደዱም ጥቂቶቹ ግን በውስጥ አርበኝነት ትግሉን ቀጠሉ፡፡ ከድል በኋላ የሀገር ፍቅር ማህበር እንደገና ወደቀደመ ተግባሩ ሲመለስ በወረራው ዘመን የጣልያን መኮንኖች ክበብ ወደነበረው የአሁኑ የሀገር ፍቅር ቲያትር ሕንፃ ገባ፡፡ በዚህ ወቅትም ማህበሩ ለሕዝቡ አነቃቂ በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያውያን በንግድና ኢንቨስትመንት በመሳተፍ ሀገራቸውን ማሳደግና አንድነቷንም ማስጠበቅ እንዳለባቸው የሚያሳስቡ ንግግሮችን ያስተጋባ ነበር፡፡

ከአነቃቂ ንግግሮቹ በተጨማሪ ሕዝቡን እያዝናኑ የሚያስተምሩ ጥበባዊና ኪናዊ እንቅስቃሴዎች መካተት እንዳለባቸው ስለታመነበት ባህላዊ የሙዚቃ ባንድ ተቋቁሞ ሙዚቃዊ ትእይንቶች ለሕዝቡ መታየት ጀምረዋል። ይህንኑ እንቅስቃሴ በመምራት ረገድ ደግሞ አቶ በሻህ ተክለማሪያምና እዩኤል ዮሐንስ ተጠቃሽ ነበሩ፡፡ በተለይ አቶ እዩኤል ዮሐንስ ከሙዚቀኝነታቸው በተጨማሪ የሀገር ፍቅር ማህበር ዳይሬክተር ሆነው እስከ 1967 ዓ.ም ድረስ መርተዋል፡፡

ለውጡን ከአርበኝነት እንቅስቃሴ ወደ ኪነጥበብ እንቅስቃሴ እያሳደገ የመጣው የሀገር ፍቅር ማህበር ስሙንም እንደተግባሩ በ1950 ዓ.ም ወደ ሀገር ፍቅር ቲያትር ቀይሯል፡፡ ከቀደምቶቹ እነ ንጋቷ ከልካይ፣ ጥላሁን ገሠሠና ፍሬው ኃይሉን የመሳሰሉ ድምፃውያን በዚህ ቲያትር ቤት ድምፃቸውን አሟሽተዋል፡፡ የቀለጠው መንደርን መሰሉና ሌሎችም አይረሴ ቲያትሮችም በሀገር ፍቅር ቀርበው ተመልካችን አዝናንተዋል፡፡

የሀገር ፍቅር ቲያትር በኢትዮጵያ የዘመናዊ ቲያትር ተቀዳሚ ቢሆንም በኋላ ላይ ለመጡት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የአሁኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲያትር፣ ራስ ቲያትርና የአዲስ አበባ ባህልና ቲያትር ቤት መመስረት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል። እነዚህ ቲያትር ቤቶች ሥራ በጀመሩባቸው ዘመናት ልዩ ልዩ ዘመኑን የዋጁ ቲያትሮችን ከሙዚቃ ጋር አጣምረው በማቅረብ በጊዜው የነበረውን የጥበብ አፍቃሪ አስደስተዋል፡፡

እዚህ ጋር የቲያትር ቤቶቹን አመሰራረት እንደመንደርደሪያ አነሳን እንጂ የዚህ ጽሑፍ ዋነኛ ማጠንጠኛ በኢትዮጵያ ቲያትር እንዴት በጊዜ ሂደት እየተቀዛቀዘ እንደመጣ ለማሳየት ነው። ርግጥ ነው እነዚህ ቲያትር ቤቶች ከተመሰረቱበት ጊዜ አንስቶ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የቲያትር ጥበብ አፍቃሪው ከነዚህ ቲያትር ቤቶች ደጃፍ አይጠፋም ነበር። ‹‹የጥበብ ሥራ ቁንጮ ቲያትር ብቻ ነው›› እስኪባል ድረስ ታዳሚው ሳይታክት ቲያትሮችን ይመለከት ነበር ።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የቲያትር ጥበብ አፍቃሪው ከቲያትር ደጃፎች እየቀረ መጥቷል። ለምን? ለዚህ ከቲያትር ጥበበኞችና ባለሙያዎች በኩል በርካታ ምክንያቶች ይቀርባሉ። ለቲያትር ሥራ ከመንግሥት የሚጠየቀው ታክስ /ግብር/ ከፍተኛ መሆን፣ ተመልካቹ ከቲያትር ሥራ ይልቅ ወደ ሲኒማ ሥራዎች ማድላት፣ ሳቢና ምቹ ቲያትር ቤቶች አለመኖር፣ የቲያትር ሥራዎች በአብዛኛው በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ መወሰን፣ ነባር ቲያትሮች በአዲስ መልክ ለተመልካች አለመቅረብ፣ ሌሎች አዳዲስና ወቅታዊ የሆኑ ቲያትሮች አለመሠራትና ሌሎችም ለቲያትር ኢንዱስትሪው መቀዛቀዝ በምክንያትነት ከሚጠቀሱት ውስጥ ይገኙበታል።

ይህ ብቻ ሳይሆን የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ከቲያትር ይልቅ በአብዛኛው ወደ ፊልም ሥራ ፊታቸውን ማዞር፤ ይህንኑ ተከትሎ የጥበብ አፍቃሪያንም ከቲያትር ይበልጥ የፊልም ሥራዎችን የመመልከት ፍላጎት ማሳደር የቲያትር ሥራዎች እንዲቀዘቅዙና ከተመልካች ዓይን እንዲርቁ የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል።

በሌላ በኩል የዘመኑ ቴክኖሎጂ በተለይም ኢንተርኔት የፈጠራቸው እንደ ፌስቡክ ፣ዩቲዩብ አሁን ደግሞ ቲክቶክ በተለያየ ይዘትና አቀራረብ በገፍ የመዝናኛ አማራጮችን ለታዳሚው መፍጠራቸውና ታዳሚውም በቀላሉ እጁ ላይ በያዘው ስልክ የመጠቀም እድል ስለተፈጠረለት ለቲያትር ያለው ፍላጎት በእጅጉ እንዲቀንስ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ቲያትር ከተጀመረ መቶ ዓመትን ተሻግሯል፡፡ በዚህ የረጅም ዓመት ጉዞው በበርካታ ውጣውረዶች ውስጥ አልፏል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ዘመናዊ ቲያትር የተጀመረበት 100ኛ ዓመት ‹‹ስለቲያትር›› በሚል መሪ ቃል ሲከበር የተቀዛቀዘው የኢትዮጵያ ቲያትር እንዲያንሰራራ በአንጋፋና ወጣት ቲያትረኞች ሰፊ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡

ከነዚህ እንቅስቃሴዎች ውስጥ አንዱ ወጣትና ነባር ተዋንያን የቲያትሩ ስብራት የት ጋር እንደሆነ መመርመርና ማጥናት ነው። ይህንንም እያደረጉ ነው። ከዚህ በመነሳት ከያኒያኑ አንድ ውጤት ላይ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከዚሁ ጎን ለጎን የቲያትር ተመልካቹን ወደቲያትር ቤቶች ለመመለስ ምን መደረግ እንዳለበት ከያንያኑ የመፍትሔ ሃሳብ እንደሚጠቁሙ ይገመታል።

ቲያትር ሰፊ ፅንሰ ሃሳብ የያዘ የጥበብ ሥራ ነው። ከሰው ልጅ የእለት ተእለት ክዋኔ ጋር የተቆራኘ የጥበብ ውጤት ነው፡፡ በመሠረታዊ መልኩ ሲታይ ቲያትር ለሰው ልጅ ትርጉም ያለው ጣዕም ከሚሰጡ ክህሎቶች ውስጥ መሠረታዊውና አንደኛው መሆኑ ይነገራል፡፡ ቲያትር ሰውን ከሰው የሚያገናኝ መድረክ ነው፡፡ በቲያትር ሰዎች ይገናኛሉ፡፡ በቲያትር ውስጥ የድርጊት ከዋኝ ሰዎች ይገናኛሉ፡፡ ከዚህ ባለፈም በቲያትር ተዋንያንና በተመልካች በኩል ግንኙነት አለ፡፡ ቲያትር የማያነሳውና የማይዳስሰው ጥግ የለም፡፡

ከዚህ ቀደም በሁሉም ቲያትር ቤቶች ሲቀርቡ የነበሩ ቲያትሮች የታዳሚያንን ቀልብ ስበዋል፡፡ የጥበብ አፍቃሪያንን ልብ በሀሴት ሞልተዋል፡፡ በሀገር ፍቅር ቲያትር፣ በብሔራዊ ቲያትር፣ በራስ ቲያትርና በአዲስ አበባ ቲያትርና ባህል አዳራሽ በርካታ ቲያትሮች ቀርበው ታዳሚያንን ዘና ፈታ አድርገዋል፡፡ እነ ሀ ሁ በስድስት ወር፣ እናት ዓለም ጠኑ፣ ኦቴሎ፣ የባላገር ፍቅር፣ የቀለጠው መንደር፣ ባለካባና ባለዳባ፣ የቴዎድሮስ ራዕይ፣ ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት፣ የአዛውንቶች ክበብ፣ ህንደኬ፣ ለዕረፍት የመጣ ፍቅር፣ ፍቅር የተራበ፣ አምታታው በከተማውና ሌሎች በቁጥር የበዙ ቲያትሮች በጊዜው በበርካታ ሰልፎች ታጅበው እንደጉድ ታይተዋል፡፡

ምንም እንኳን ቲያትር ቤት በተመልካች ድርቅ የተመታ ቢሆንም አሁንም ድረስ እየታዩ ያሉት እነ ባቢሎን በሳሎን፣ እነ ኮከቡ ሰው፣ የእኛ ሰፈር፣ ጣይቱ፣ ባሎችና ሚስቶች፣ የጉድ ቀን እና ሌሎችም አሁንም ደረስ የቲያትር ጥበብ ነግሳ እንዳለች የሚያሳዩ ናቸው፡፡ እነዚህ ጥበብ አፍቃሪው ወደ ቲያትር ደጃፎች እንዲቀርብ እየታገሉ ያሉ ትያትሮች ናቸው፡፡ አሁን ደግሞ በሀገር ፍቅር ቲያትር እየታዩ የሚገኙት የሌሊት ሙሽራና በዓሉ ግርማ ቤርሙዳ የተሰኙት ቲያትሮች ቲያትር አፍቃሪው ዳግም ወደ ቲያትር ሥራ ፊቱን እንዲያዞር ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ እነዚህን የመሰሉና በኢትዮጵያ የቲያትር ባለሙያዎች ተከሽነው ለመድረክ እየቀርቡ ያሉ ቲያትሮች በሚገባቸው ልክ ተመልካች እያገኙ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ የተመልካች ያለህ እያሉ ነው፡፡

ቲያትር ማህበረሰቡን በሁለንተናዊ መልኩ የሚቀይር ትልቅ የጥበብ መሳሪያ ነው፡፡ በቲያትር ከመዝናናት በዘለለ ቁም ነገር መጨበጥ ይቻላል፡፡ በቲያትር ካለፈው ስህተት መማር ይቻላል፡፡ በቲያትር የዛሬውን ጥፋት ማረም ይቻላል፡፡ ቲያትር ከዛሬ ስህተት መማርና ነገን በተሻለ መንገድ ለመሥራት ያስችላል፡፡

የቲያትር ጥበብ ያለፈውን ታሪክ ከዛሬው ጋር አገናኝቶ አዲስ ነገር ለመፍጠር ይሞክራል፡፡ በዚህም በርካታ ነገሮች ይገኛሉ፡፡ የሰው ልጅ ሁል ጊዜ ለሕይወቱ ትርጉም ይፈልጋል፡፡ ይህም ገና ከፍጥረቱ ጊዜ ጀምሮ የነበረ ፍላጎቱ ነው፡፡ ሰዎች አዲስ ባህሪ እንዲያገኙና እንዲኖራቸው ወይም ደግሞ አዲስ ዓለም እንዲፈልጉ ያበረታታል፡፡

የቲያትር ጥበብ ሌላኛው ጉልበት ዘመን መሻገር ነው። ወቅትን ተከትሎ በጊዜው የነበረውን ሁኔታ የሚያሳይ ነው። ይህ ታዲያ ጥሩም መጥፎም ሊሆን ይችላል። ዋናው ጉዳይ ግን የተፈፀመው መጥፎም ይሁን ጥሩ ድርጊት ታሪክ ሆኖ ይመዘገባል፡፡ በትውልዶች መካከል ያለውን ግጭትና ክፈተት ፍንትው አድርጎ በማሳየት ረገድም ቲያትር ወደር አልተገኘለትም፡፡

ቲያትር የተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮችን እንደማሳየቱ ህብረተሰቡ ስለሕይወቱ ጥሩ ግንዛቤ እንዲኖረው ያደርጋል፡፡ በሕይወት ኡደት የሚያጋጥሙ አሳዛኝና አስደሳች ሁኔታዎችን ያስቃኛል፡፡ ግጭቶች ሲፈጠሩ ቆም ብሎ በማሰብ መፍትሔ ለማሻት አጋጣሚ ይፈጥራል፡፡

ከዚህ ባለፈ ቲያትር ትልቁና ዋነኛው ተግባሩ የሰውን ልጅ ስብእና መገንባት ነው፡፡ አዲስና የተሻለ ሰው መፍጠር ነው፡፡ በቲያትር ብዙ ጥያቄዎች ሊመለሱ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በጦርነት በተጠቁ አካባቢዎች ሥነ-ልቦናቸው የተጎዱ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ይህን ሥነ-ልቦናዊ ሕመም በማከም ረገድ ቲያትር ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፤ አስፈላጊም ነው፡፡ ውጤታማ እንደሆነም ተመስክሮለታል፡፡

ከዚህ አልፎ ቲያትር ማህበረሰቡ ከወሊድ ጋር፣ ከሕዝብ ቁጥር መቀነስ፣ ከልማት ጋር ተያይዞ የሚፈልጋቸውን መፍትሔዎች በመጠቆም በኩል ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡ ቲያትር እንደ ሕክምናውና እንደሌሎችም የትምህርት መስክ አስፈላጊ ነው ተብሎ ሁለንተናዊ ጥቅም ለማህበረሰቡ ይሰጣል፡፡ ለዛም ነው ቲያትር ‹‹የጥበባት ጉባኤ›› ነው የሚባለው፡፡ ለአምስቱም የስሜት ህዋሳት በእጅጉ የቀረበ እንደሆነም ይነገራል፡፡

እናም እነዚህን ሁሉ በረከቶች አቅፎ የያዘው የቲያትር ጥበብ ዛሬ ተዳክሟልና እንዲበረታ የሁሉም ሰው ድጋፍና ትብብር ያስፈልገዋል፡፡ ቲያትርን ወደቀደመ ክብሩ የመመለስ ሥራ ታዲያ የቲያትር ጠበብት ሥራ ብቻ ባለመሆኑ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ በዚህ ላይ ተሳትፈው የራሳቸውን መፍትሔ እንደሚያመጡም ብዙዎች ይጠብቃሉ፡፡ ቲያትሩን ለመጠገን በሚመለከታቸው አካላት ሁሉ የመፍትሔ ሃሳብ ከመጣ ተመልካቹም ቢሆን ፊቱን ወደቲያትር ጥበብ ሥራዎች ማዞሩ አይቀሬ ነው። ያኔ ‹‹ቲያትር ወደ ሙሉ ክብሯና ሞገሷ ተመለሰች›› ተብሎ ይወራል።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You