በእድሜ ትንሿ ኢትዮጵያዊት ሞዴል

የሞዴሊንግ ሙያ የእድሜ ገደብ ያልተቀመጠለት የሙያ ነው። ለሙያ ፍቅር ያለው ማንኛውም ሰው አስፈላጊ የሆኑ መስፈርቶችን አሟልቶና ተምሮ የሙያው ባለቤት መሆን ይችላል። ይሁን እንጂ እስካሁን ድረስ በሀገራችን የተለመደውና ወደ ሙያውን ሲገቡ የምናያቸው አብዛኛዎቹ በወጣትነት እድሜ ክልል ናቸው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ባልተለመደ መልኩ በእድሜያቸው በጣም ትንሽ የሆኑ ታዳጊዎች ሙያውን ሲቀላቀሉ ይስተዋላል።

ከሰሞኑ የአስራ አንድ ዓመት እድሜ ያላት ታዳጊ ‹‹በእድሜ ትንሿ ኢትዮጵያዊት ሞዴል›› በሚል በአፍሪካ ድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ ስሟ መስፈሩ ይታወሳል። የሚገርመው ግን በአፍሪካ ድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ የሚሰፍረው የኢትዮጵያውያኑ ስም በዚች ታዳጊ ብቻ የሚያቆም አለመሆኑ ነው። ኢትዮጵያውያኑ የራሳቸውን ሪከርድ በራሳቸው ለመስበር ቆርጠው የተነሱ እስኪመስል ድረስ አንዱን አድንቅን ሳንጨርስ ሌላው አስደናቂ ክስተት ሆኖ ብቅ ይላል። እናም አሁን ላይ ከአስራ አንድ ዓመቷ ታዳጊ በእድሜ በጣም የምታንስ ኢትዮጵያዊት ሞዴል ብቅ ብላለች።

ሞዴል ፍቅር አሸናፊ ትባላለች። ተወልዳ ያደገችው በአዲስ አበባ ነው። እድሜዋ ስድስት ዓመት ሲሆን የአንደኛ ክፍል ተማሪ ናት። ሞዴል ፍቅር ገና በለጋ እድሜዋ የሞዴሊንግ ፍቅሩ በውስጧ አድሮባታል። ቤት ውስጥ የምታከናወናቸው እያንዳንዳቸው ተግባራት የአለባበስ ምርጫዋ እና አረማመዷ ጭምር ሙያው በውስጧ ነፍስ መዝራቱን በደንብ እንደሚጠቁም ወላጆቿ ይመሰክራሉ።

በተለይ በቴሌቪዥን የምታያቸውን ትርዒቶች ወደ ተግባር በመቀየር ለእናቷ የምታሳይበት መንገድ ሙያው ውስጧ እንደሆነ ከሚያሳዩ ድርጊቶች መካከል አንዱ ነው። ዝንባሌዋን በውል የተገነዘቡት የፍቅር ወላጆች ወደ ሞዴሊንግ ሙያ እንድትገባ የሚያስችላትን መንገድ ጠርገውላታል። በመሆኑም የሞዴሊንግ ትምህርት ቤት እንድትገባ ትምህርቱን እንድትከታተል አደረጉ።

ሞዴል ፍቅር አፍሮ ፊንገርስና ኒው ሀብ የተሰኙ የሞዴሊንግና ፋሽን ትምህርት ቤቶች እንድትገባና ትምህርቷን እንድትከታተል አደረጉ፤ ትምህርቱን ለስድስት ወራት ተከታትላም ተመረቀች። በቆይታዋ ያገኘችው ብቃት ተረጋግጦ ዓለም አቀፍ ሞዴል መሆኗን የሚያረጋግጥ ሰርተፊኬት አግኝታለች።

የኒው ሀብ የሞዴሊንግ ትምህርቷን ደግሞ በቅርብ የምታጠናቅቅ ሲሆን፤ ይህ ትምህርትም ለሞዴሊንግ ሙያ ብቁ የሚያደርጋት እውቀት ለማግኘት ያስችላታል። ይህ ጥረቷ ደግሞ ወደፊት ለመሆን ለምትፈልገው ዓለም አቀፍ ሞዴልነት የሚያበቃትን መደላድል የሚፈጥርላት ነው።

ሞዴል ፍቅር በመደበኛ ትምህርቷም ቢሆን በጣም ጎበዝ እና ታታሪ እንደሆነች ወላጆቿ ይናገራሉ። በትምህርቷም ይሁን በሞዴሊንግ ሙያዋ የሚገርም የራስ መተማመን እንዳላትም ይገልፃሉ። ሞዴል ፍቅር፤ በትምህርት ሰዓት ትምህርቷን ትከታተላለች፣ የሚያስፈልጋት ድጋፎች ሁሉ በወላጆቿ ይደረግላታል። ከትምህርት ውጭ ባሉ የእረፍት ጊዜዎቿ ደግሞ የሞዴሊንግ ሥራዎችን በመሥራት ጊዜዋን በአግባብ እንድትጠቀም ለማድረግ ጥረት እንደሚያደርጉም ወላጆቿ ይገልጻሉ።

በሞዴሊንግ ትምህርት ቤቶች በሚዘጋጁ ትርዒቶች ላይ ሥራዎቿን ማቅረቧን የምትናገረው ሞዴል ፍቅር፤ ብዙዎች የሰጧት አድናቆትና ማበረታታት ሙያውን ከአሁኑ አጥብቃ ይዛ ወደፊት ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሳ ሀገሯን ለማስጠራት እንድትችል የሚያደርጋት እንደሆነ ትናገራለች።

ሥራዎቿን አፍሮ ፊንገርስ ትምህርት ቤት ባዘጋጀው የፋሽን ሳምንት ላይ በመገኘት አቅርባለች። ከዚህ በተጨማሪም የተለያዩ የመጽሐፍት ምረቃ በሚካሄዱባቸው ቦታዎች፣ በቲክቶክ የፈጠራ ሥራ የሽልማት ሥርዓት እና ሌሎችም ዝግጅቶችና ሁነቶች ላይ ተጋባዥ በምትሆንበት ጊዜ ሥራዎቹን ማቅረቧን አጫውታናለች።

ከዚህ በተጨማሪ በትምህርት ቤት በተከበሩ የአሸንዳና የኢሬቻ በዓላት ላይ የሀገሯን ባሕል የሚያስተዋወቁ አልባሳት በመልበስ የማስተዋወቅ ሥራ መሥራቷን ትናገራለች። በአሁኑ ወቅት ደግሞ በቲክቶክ እና ኢንስታግራም (ሶሻል ሚዲያ ፕላትፎርም) ገጾች ላይ የምትሠራቸውን የሞዴሊንግ ሥራዎችና ፎቶዎችን በመልቀቅ የሀገሯን ባሕል ለማስተዋወቅ ጥረት እያደረገች ትገኛለች።

የሞዴሊንግ ሥራዎቿን የትምህርት ጊዜዋን በማይሻማ መልኩ እንደምትሠራ ወላጆቿም ይገልጻሉ። ለዚህም ወላጆቿ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ከጎኗ ሆነው እያገዟት እንደሆኑ ይናገራሉ።

የፍቅር ወላጆች የሞዴሊንግ እና የማስተዋወቂያ ሥራዎችን የሚያሠሩ ብዙ ኤጀንቶች ሥራዎችን ለማሠራት እንዳነጋገሯቸው ይናገራሉ። ሆኖም ግን እነዚህ ሥራዎች ከትምህርቷ ጋር እንዳይጋጩ በመፍራት ፍቃደኛ አልሆኑም። እነርሱ እንደሚሉት፤ በመደበኛ ትምህርቷ መታነጽ ስለሚኖርባት ትኩረቷ በዚያ ላይ መሆን አለበት። ራሷን ስትችል ግን በራሷ ተንቀሳቅሳ ዓለም አቀፍ ሞዴል የመሆን ሕልሟን እውን ለማድረግ ትችላለች ብለዋል ።

ሞዴል ፍቅር ሀገሯን የምትወድ ልጅ መሆኗን በሥራዎቿ እያሳየች ነው የሚሉት ወላጅ አባቷ አቶ አሸናፊ ተስፋዬ፤ ይቺ ትልቅ ራዕይ ያላት ታዳጊ የምታሰበው እንዲሳካላትና ዓለም አቀፍ ሞዴል ሆና ሀገሯን እንድታስጠራ ማገዝ እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ።

በራስ መተማመን እንዲኖራት እና የምትፈልገውን መሆን እንድትችል የሚያበረታቷት ወላጆቿ እንደሆኑ የምትናገረው ሞዴል ፍቅር፤ ‹‹ በትምህርቴ በጣም ጎበዝ ተማሪ ነኝ። መደበኛውን ትምህርቴንና የሞዴሊንግ ሙያን ጎን ለጎን እያስኬድኩት እገኛለሁ። ለወደፊት ዓለም አቀፍ ታዋቂ ሞዴል ሆኜ ሀገሬን ለማስተዋወቅ እፈልጋለሁ›› ብላለች። ልጆች በራስ መተማመን እንዲኖራቸው፣ ዝንባሌያቸውን አውቀው እና ስንፍናን አስወግደው ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ለማካሄድ ጥረት ማድረግ አለባቸው ስትል ትመክራለች።

ሞደል ፍቅር ‹‹በእድሜ ትንሿ ኢትዮጵያዊት ሞዴል›› የሚለውን ስያሜ ለማግኘት የሚያስችላት አስፈላጊዎቹን መስፈርቶች አሟልታ ሂደቶቹን በሙሉ ያለፈች ሲሆን፣ በቅርቡ የአፍሪካ ድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ ስሟ መስፈሩን የሚገልጽ ሰርተፊኬት እንደምታገኝ ወላጆቿ አስታውቀዋል።

ወርቅነሽ ደምሰው

 አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You