ለመከላከያ ሠራዊት ክብር እንስጥ!

 የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ዕድሜ ያለው የሀገርና ሕዝብ አለኝታ የሆነ ተቋም ነው። በረጅም ዘመን ታሪኩ ሀገርን እና ሕዝብን ከቅኝ ገዥዎች ከመታደግ ጀምሮ፤ ከውስጥ እና ከውጭ ከሚቃጡ የትኛውም አይነት ጥቃቶች በመከላከል ሉዓላዊነቷ እና ነፃነቷ የተጠበቀች ሀገር ከትውልድ ትውልድ በማስተላለፍ ተጠቃሽ ነው።

ከፍ ባለ የሀገር ፍቅር እና የነፃነት መሻት የተመሠረተው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፤ በየዘመኑ በዚሁ የሀገር ፍቅር እና ከፍ ባለ የሕዝባችን የነፃነት መሻት እየተመራ፤ በብዙ የጀብዱና የተጋድሎ ትርክቶች ታጅቦ ዛሬ ላይ ደርሷል። በየዘመኑም በተሰለፈባቸው የግዳጅ ተልዕኮዎች አንቱታን ያተረፉ ብሔራዊ ጀግኖችን በመፍጠር በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ሆኗል።

ሠራዊቱ ከሀገር ውስጥ የግዳጅ ተልዕኮም ባለፈ በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች በመሳተፍ ሀገርና ሕዝብን ያስጠሩ ገድሎችን በመፈጸም፤ የኢትዮጵያውያንን ጀግንነት በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ የማይተካ አስተዋፅዖ ያበረከተና እያበረከተ ያለ ተቋም ነው። ከ1950 ዓ.ም አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር ሰላም በማስከበር ተልዕኮ ግንባር ቀደም ነው፡፡

ተቋሙ እንደ አንድ በለውጥ ውስጥ ያለች ሀገር ተቋም፤ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በተለያዩ የሪፎርም ሥርዓት ውስጥ በማለፍ ላይ ይገኛል። ይህንንም ተከትሎ እያስመዘገበ ያለው ስኬት፤ ለሀገርና ለሕዝብ የበለጠ ኩራት የሚሆንበትን ዕድል እየፈጠረለት ነው፤ ግዳጅ የማስፈጸም አቅሙንም ከፍ ባለ ደረጃ እያሳደገለት ይገኛል ።

ለዚህም መከላከያ ሠራዊቱ ላለፉት ሦስት ዓመታት ሀገሪቱ በየአቅጣጫው ያጋጠማትን የሕልውና አደጋ ከፍ ባለ የተጋድሎ መስዋዕትነት ፊት ለፊት በመጋፈጥ ሀገር እንደ ሀገር ጸንታ መቆም እንድትችል አድርጓል። ብዙ የጥፋት ትርክቶችን በመቀልበስ ሀገር ከሕልውና አደጋ ስጋት ነፃ የሆነችበትን ተጨባጭ ሁኔታ ፈጥሯል።

በጦርነት ውስጥ ራሱን እያበቃ፤ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ጸንቶ እየተራመደ፤ ሀገርና ሕዝብ የሰጡትን ተልዕኮ በብዙ መስዋዕትነት በመወጣት ላይ ያለው የመከላከያ ሠራዊታችን፤ ሠላማችን እና ልማታችን የሚያስጨንቃቸው ታሪካዊ ጠላቶቻችንና የእነርሱ ቅጥረኛ የሆኑ ባንዳዎች በተለይም ባለፉት ሦስት ዓመታት በብዙ ተስፋ የተንቀሳቀሱባቸውን የጥፋት ተልዕኮዎች በማምከን በታሪክ መዝገብ አዲስ ታሪክ መጻፍ የቻለ ነው።

ከጀርባው ሳይቀር እየተመታ፤ ከፍ ባለ ሕዝባዊነት፤ በብዙ ትዕግስትና ሆደ ሰፊነት የተሰጠውን ሕገ-መንግሥታዊ ኃላፊነት በመወጣት አሁን ላይ እንደ ሀገር፤ ጠላቶቻችን አስበው እና በብዙ መክረው የተረባረቡባቸው የጥፋት ተልዕኮዎች እንዲከስሙ አድርጓል። በዚህም ጠላቶቻችን ስለ ሠራዊቱ ደግመው፤ ደጋግመው እንዲያስቡ አስገድዷቸዋል ።

በግንባር በባንዳዎቻችው በኩል ገጥመው ያጡትን ድል፤ የሠራዊቱን ስም በማጥፋት በእጃቸው ለማስገባት የሞከሩትም ጥረት ቢሆን፤ ሠራዊቱ ከሕዝቡ ውስጥ የወጣ፤ የሕዝብ ልጅ ከመሆኑ ባለፈ፤ በተላበሰው ከፍተኛ ወታደራዊ ዲሲፕሊን ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ይህም ለሠራዊቱ የተጨማሪ ኩራትና ሞገስ ምንጭ ሆኖለታል ።

መከላከያ ሠራዊቱ ትናንት ሆነ ዛሬ የተሰጠውን የሀገርና የሕዝብ ኃላፊነት በብቃት ስለመወጣቱም ሆነ አሁንም እየተወጣ ስለመሆኑ፤ ሀገር እንደ ሀገር ከነበረችበት የሕልውና ስጋት ወጥታ አሁን ላይ ያለችበት ቁመና ተጨባጭ ማሳያ ነው ። ከትናንት ዛሬ ላይ ሆነን የምንተነፍሰው የሰላም አየርም በራሱ ተናጋሪ ነው።

ይህንን እውነታ መካድ የሚቻል አይደለም ፤ይህንን የመከላከያን አዲስ ሀገርን የመታደግ በብዙ ገድል የተሞላ ትርክት ላለመስማት መሞከር አይቻልም። ሠራዊቱ ዘመኑን በሚዋጅ መንገድ በሁለንተናዊ መንገድ ራሱን እያበቃ የሚሄድበት አሁነኛ የለውጥ ጉዞም፤ የጀመርነውን ልማት በማስቀጠል ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ለጀመርነው አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ዋነኛ ስትራቴጂክ አቅም ነው!

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You