የሠላምን ጥሪ መቀበል ሀገርንና ሕዝብን የመውደድ ምልክት ነው!

 መልማት የዛሬ ሳይሆን የመላው ሕዝባችን የዘመናት መሻት ነው። ይህንንም እውን ለማድረግ በየዘመኑ የነበሩ ትውልዶች በብዙ መነቃቃት ተነሳስተው ረጅም ርቀት ለመጓዝ ሞክረዋል። ሙከራቸው ግን ሀገሪቱን እስካሁን አልጠፋ ካለው የግጭት አዙሪት ምክንያት ውጤታማ ሳይሆን ቀርቷል ።

ሀገሪቱ እንደ ሀገር በብዙ የተፈጥሮ ሀብቶች የታደለች፤ ይህን ሀብት ማልማት የሚያስችል ሰፊ የሰው ኃይል ባለቤት እና ሀብቱን ማልማት የሚያስችል ከፍ ያለ መሻት ባለቤት መሆኗ፤ ሀገራዊ ልማቱን እውን በማድረግ የዜጎችን ሕይወት መቀየር ከባድ እንደማይሆን ብዙዎች ይስማማሉ ።

በተለይም በአለንበት ዘመን፤ ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት ለሀገር ዕድገት ትልቅ አቅም እየሆነ ባለበት ሁኔታ፤ ያሉንን የማደግ ዕድሎች ተጠቅመን፤ የትውልዶች የዘመናት መሻት የሆነውን ሀገራዊ ልማት ተጨባጭ ማድረግ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ለኛ የቀረበ ስለመሆኑ አጠያያቂ አይደለም።

ችግሩ ግን ዛሬም ቢሆን የፖለቲካ ልዩነቶቻችንን፣ ልማትን በማፋጠን ሕዝባችንን ተጠቃሚ በሚያደርግ መንገድ፣ በውይይት በሠላማዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ፤ ይዋጣልን ከሚለው፣ በየዘመኑ ብዙ ዋጋ ካስከፈለን የኪሳራ መንገድ መመለስ አለመቻላችን ነው።

ይህ የይዋጣልን የኃይል አምላኪነት የፖለቲካ መንገድ የሕዝባችን የመልማት መሻት ትልቁ ተግዳሮት በመሆን፤ እንደ ሀገር ትናንት ለነበርንበት ሆነ አሁን ለምንገኝበት ድህነትና ኋላቀርነት ዋነኛ ምክንያት ሆኗል። ችግሩ ብሔራዊ ክብራችንን ሳይቀር በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሳነሰና አንገታችንን ያስደፋ ነው።

ከዚህም ባለፈ ለታሪካዊ ጠላቶቻችን የጥፋት ተልዕኮ ስኬት ጉልበት በመሆን፤ ሀገራችን እንደ ሀገር እየተፈታተነ ይገኛል። ዛሬ ለምንገኝበት ሀገራዊ ትርምስምስ/ዝብርቅርቅ ዋንኛ ምክንያት ከመሆን ባለፈ የሀገርን ሕልውና ስጋት ላይ ጥሎ እንደነበርም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው ።

ይህን ችግር ለዘለቄታው መፍታት የሕዝባችንን የመልማት ጥያቄ ከመመለስ ባለፈ፤ የሀገርን ሕልውና አስጠብቆ ለመጪው ትውልድ ከማስረከብ አንጻር የሚታይ ትልቅ ወቅታዊ ሀገራዊ አጀንዳ ነው። እያንዳንዱ ዜጋም ጉዳዩ ይመለከተኛል/ያገባኛል በሚል መንፈስ ሊንቀሳቀስበት የሚገባ ነው።

በተለይም በተለያዩ ወቅቶች በመንግሥት በኩል ለሚቀርቡ የሰላም ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ፤ በማወቅም ባለማወቅም ልዩነቶችን በኃይል/በአሸናፊ ተሸናፊ ትርክት/ለመፍታት የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች፤ ለዚህ ዘመን ተሻጋሪ ሀገራዊ ችግር ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው ሊንቀሳቀሱ ይገባል።

እያንዳንዱ ዘመን ችግሮቹን የሚፈታበት የራሱ የአስተሳሰብ መሠረት/አዕምሮ ውቅር አለው፤ ይህን ተከትሎ መሄድ በተለይም፣ ለሕዝብ ፍላጎት ተገዥ ነኝ ለሚል ቡድን የሕዝባዊነቱ ትልቁ መገለጫ ነው። እወክለዋለሁ ወይም እቆረቆርለታለሁ የሚለውን ሕዝብ ችግር በተጨባጭ መዋጀት የሚችለውም ይህንን መንገድ ተከትሎ ሲንቀሳቀስ ብቻ ነው ።

ለዚህ ደግሞ እንደ ሀገር የመጣንበትን መንገድ መመልከቱ ተገቢ ነው። የሕዝባችን የዘመናት የመልማት መሻት ስለ ምን ስኬታማ መሆን ሳይችል ቀረ? ለዚህ በዋነኛነት ተጠያቂው ማነው? ለሚሉት እና ተያያዥ ጥያቄዎች በተረጋጋ አዕምሮ፤ በሰከነ መንፈስ፤ ኃላፊነት በሚሰማው መልኩ ምላሽ መስጠት አስፈላጊ ነው ።

አሁን ላይ እንደ ሀገር ከገባንባቸው ፈተናዎች በመውጣት፤ የጀመርነውን ልማት በተሻለ መልኩ አስቀጥለን፤ የሕዝባችንን የዘመናት የመልማት መሻት እውን ለማድረግ፤ ወደ ቀልባችን ልንመለስ ይገባል፤ ከኃይል ይልቅ ድርድርንና ውይይት ማስቀደም፤ ይህንንም የፖለቲካ ባሕል አድርገን ማስቀጠል ይጠበቅብናል።

ከዚህ አንጻር በአማራ ክልል ያለውን ወቅታዊ ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከክልሉ መንግሥት የቀረበውን የሰላም ጥሪ የሚመለከታቸው አካላት፤ የክልሉ ሕዝብ ካለበት አሁናዊ ፈተና አንጻር በአዎንታዊነት ተቀብለው ተገቢውን ምላሽ ሊሰጡት ይገባል ።

በተለይም የክልሉን ችግሮች ምንነትና ምንጫቸውን፤ ከዚያም ባለፈ ዘላቂ መፍትሔያቸውን በአግባቡ ሳይረዱ በተዛቡ ትርክቶች፤ በሐሰተኛ መረጃዎችና በጥላቻ ነጋዴዎች ተሳስተው ብረት ለማንሳት የተገደዱ አካላት የክልሉን መንግሥት የሰላም ጥሪ እንደ መልካም አጋጣሚ ሊወስዱት ይገባል።

የአማራ ሕዝብ ፍላጎት እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በልማት ድህነትን አሸንፎ የተሻለ ሕይወት መምራት ነው፤ ለዚህ ደግሞ ከሁሉም በላይ የሚስፈልገው ሰላም ነው። ያለ ሰላም ድህነትን እንጂ የሕዝቡን የመልማት ፍላጎቱን እውን ማድረግ አይቻልም። ከዚህ አንጻር የአማራ ሕዝብ ከሁሉም በላይ ለሰላም ከሚሰጠው ትልቅ ቦታና ክብር አንጻር የሚመለከታቸው ሁሉ ለሰላሙ ቅድሚያ ሊሰጡ ይገባል።

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You