ሥልጣኔ እና ሰብዓዊ መብት

 ሰሞኑን ከዜግነት ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ጋር በተያያዘ የሄድኩባቸው ተቋማት ነበሩ፡፡ ክፍያ የሚከፈልባቸው ቦታዎች ላይ ዘመኑ ያመጣቸው የቴክኖሎጂ አማራጮች አሉ፡፡ ከእነዚህ አንዱ ቴሌ ብር ነው፡፡ በቴሌ ብር ክፍያዬን ከፍየ ለፈጣን አገልግሎታቸው አመስግኜ ወጣሁ፡፡ እዚህ ቦታ ላይ በቴሌ ብር የሚከፈለው በፍላጎት ነው፤ በጥሬ ገንዘብ የመክፈል አማራጩም አለ ማለቴ ነው፡፡

ለሌላ ጉዳይ ሌላ ቦታ ስሄድ ደግሞ ክፍያው በሞባይል ባንኪንግ ወይም በቴሌ ብር መሆኑ አስገዳጅ ነው። ከወራት በፊትም እንዲህ አይነት አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም አጋጥሞኛል፤ ተቋሙ በብዙ ሺህ (በሚሊዮንም ሊሆን ይችላል) ሰዎች ስለሚያስተናግድ ለጥሬ ብር አከፋፈል አይመችም፡፡

በእነዚህ አሠራርን በሚያቀላጥፉ የቴክኖሎጂ አማራጮች እያመሰገንኩ ሳለሁ፤ እዚያው ቦታ ላይ ግን የሚያማርሩ ሰዎችን አየሁ፡፡ ለምን በጥሬ ብር አልሆነም ነው ወቀሳቸው፡፡ የሚገርመው የሚያማርሩትና የሚገላምጡት በብዛት የተማሩ ናቸው፤ የያዙት ስልክ የመስኮት በር የሚያክል ነው፡፡ በተደጋጋሚ የሚያነሱት ወቀሳ ግን ለምን በሞባይል ባንኪንግ ወይም በቴሌ ብር ሆነ የሚል ነው፡፡ በፈለጉት መንገድ መክፈል መብት መሆኑን ነው። በቴክኖሎጂ አማራጮች መደረጉ ጭቆና እንደሆነ አድርገው ነው፡፡

እነዚህ የቴክኖሎጂ አማራጮች ለጊዜው ሁሉም ሰው ሊጠቀማቸው አይችልም፤ መጠቀም የማይችሉ ሰዎች እንደሚኖሩም ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ አስገዳጅ መሆናቸው ለጊዜው ልክ ነው ልክ አይደለም የሚለው ማከራከሩ አይቀርምና ልክ ነው ልክ አይደለም የሚለውን እንለፈው። በዚህ አጋጣሚ ግን ሰብዓዊ መብት ከሥልጣኔ ጋር የሚሄድ መሆኑን ልብ እንበል፡፡

‹‹መብቴ ነው›› የሚባሉ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ መብት ግን ተግባራዊ የሚሆነው ነባራዊ ሁኔታዎችን መሠረት አድርጎ ነው፡፡ አንድ ሰው ከሺህ እና ከመቶ ዓመታት በፊት የነበሩ ነገሮችን ዛሬ ላይ መጠቀም መብቴ ነው ቢል ነባራዊ ሁኔታው አይፈቅድለትም፡፡ ለምሳሌ፤ ማመልከቻ የማስገባው በብራና ነው ብሎ ድርቅ ቢል አይሆንም፤ ምክንያቱም በዚህ ዘመን በብራና አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም የለም፡፡ አንድ ተቋም ማመልከቻ የምቀበለው በኢሜል ወይም በቴሌግራም ነው ብሎ ቢያሳውቅ፤ ‹‹አይ! እኔ በወረቀት ብቻ ነው ማስገባት የምፈልገው›› የሚል ሰው ቢኖር መብቱ አይሆንም ማለት ነው፡፡ መብቱ የሚሆነው በተፈቀዱ ነገሮች ላይ ነው፤ መብቱ የሚሆነው የዘመኑ እና የአካባቢው (የተቋሙ) ነባራዊ ሁኔታዎች በሚፈቅዱት ነው፡፡

ነገሩን ሰፋ አድርገን ካየነው ሰብዓዊ መብት የሚባለው ራሱ ከሥልጣኔ ጋር የሚሄድ ነው፡፡ ከአንድ ሺህ ዓመት በፊት የነበረው የሰው ልጅ ሁኔታ እና ዛሬ ላይ ያለው የሰው ልጅ ሁኔታ ልዩነቱ ሰፊ ነው፤ ሌላ ፍጥረት እና ሌላ ፍጥረት እንደማለት ነው፡፡ የሰው ልጅ በዋሻ ውስጥ ይኖር የነበረበት ዘመን እና ዛሬ ጨረቃ ላይ የሚኖርበት ዘመን ልዩነቱ የሌላ ፍጥረት እና የሌላ ፍጥረት ያህል ነው፡፡ ስለዚህ ሰብዓዊ መብት ከዘመን ዘመን እየሰፋ እና እየተለወጠ ነው የሚሄደው። ከዘመን ዘመን ብቻ ሳይሆን ከሀገር ሀገር ይለያያል፤ የሠለጠነ ሀገር ሰብዓዊ መብት እና ያልሠለጠነ ሀገር ሰብዓዊ መብት በእጅጉ ይለያያል፡፡

ለምሳሌ፤ በሠለጠነው ዓለም በባዶ እግር መሄድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው፡፡ የቆሸሸ ልብስ መልበስ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው፡፡ ጥራቱን ያልጠበቀ ምግብ መመገብ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው፡፡ በድሃ እና በኋላቀር ሀገራት ግን የወዳደቀ ምግብ ማግኘት ራሱ ቅንጦት ሊሆን ይችላል፡፡ የቆሸሸ ልብስ ማግኘት በራሱ ምናልባትም እንደ ዕድለኛነት ሊታይ ይችላል። በሠለጠነው ዓለም የጉልበት ብዝበዛ የሚባለው ነገር በድሃ እና ኋላቀር በሆኑ ሀገራት ደግሞ ‹‹ምነው ሰውነቴ እስከሚቆስል በሠራሁና በበላሁ›› የሚባልበት ሊሆን ይችላል፡፡

ለዚህም ነው በአውሮፓ ሀገራት እና በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ እጅግ የተለያየ የሆነው፡፡ ዓለም አቀፍ ተቋማት በየጊዜው በአፍሪካ ሀገራት መንግሥታት ላይ የሚያወጧቸው ሪፖርቶች በአፍሪካ የሰብዓዊ መብት እንደማይከበር የሚገልጽ ነው፡፡ እነዚህ ዓለም አቀፍ ተቋማት የመለኪያ መስፈርቶቻቸው የሠለጠኑት ሀገራት ናቸው። የአንዲት ልጃገረድ ኩበት መልቀም ለእነርሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው፤ በድሃ አገር ውስጥ ግን የዕለት እንጀራዋ ነው፡፡ ያንን ሥራ ለመተው የሚያስችላት ምቹ ሁኔታ የለም፡፡

ድሃ እና ኋላቀር መሆን በራሱ የዘመኑን ሰብዓዊ መብት የጣሰ ነው፡፡ መንግሥት ወይም ሌላ አካል ባያፍን እንኳን ሁኔታው በራሱ ሰብዓዊ መብትን የጣሰ ነው፡፡ እንደ ሰው መኖር ያለበትን ነገር መኖር አይችልም፣ እንደ ሰው ማግኘት ያለበትን ነገር አያገኝም፡፡ ሌላው ይቅርና በጤና የመኖር መብታችንን እንነፍጋለን፡፡ ያለመረበሽ መብታችንን እንነፍጋለን። በመጥፎ ሽታ ለመታመም ሁኔታዎች አስገዳጅ ናቸው፣ በኃይለኛ ጩኸትና ጫጫታ ለመረበሽ የነገሮች አለመሠልጠን ያስገድዳል፡፡

በእነዚህ ሁኔታዎች ሰብዓዊ መብት የሚባለው የዚያ ዘመን ሰው የሚኖርበት መብት ማለት ነው፡፡ የዚያ ሀገር ሰው የሚኖርበት ሁኔታ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አንድን ነገር በግድ መጫንም ሰብዓዊ መብት ጥሰት ሊሆን ይችላል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ አንዲት ከገጠር አካባቢ የመጡና ስለቴክኖሎጂ ምንም የማያውቁ እናት በቴሌ ብር ካልሆነ የፈለጉትን አገልግሎት ማግኘት አይችሉም ብሎ መከልከል የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ የማያገናዝብ ነው ማለት ነው። ምክንያቱም በሀገሪቱ ውስጥ ብዙ መጻፍና ማንበብ የማይችል ማኅበረሰብ አለ፡፡ ስለዚህ ሰዋዊ መብት ሲባል የዚያች ሀገር ሰዎች መብት ማለት ነው፤ የግድ ከአውሮፓ ሀገራት ሰዎች ጋር ሊመዘኑ አይገባም፡፡

ሰብዓዊ መብቶቻችን ይከበሩልን ዘንድ ሥልጣኔን እንለማመድ፡፡ ሥልጣኔ ማለት የ100 ሺህ ብር ስልክ መያዝ አይደለም፡፡ ሥልጣኔ ማለት የዘመኑ ሰዎች የደረሱበት የአስተሳሰብና የዕውቀት ደረጃ ላይ መድረስ ነው፡፡ ይህ እንደ መንግሥትም እንደ ግለሰብም ልናደርገው የሚገባ ነው፡፡ መንግሥት አስገዳጅ ደንቦች ማውጣት ብቻ ሳይሆን ‹‹ምን አይነት ዜጋ ነው ያለኝ? የት ድረስ አስተምሬያለሁ? ምን ያህል ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሬያለሁ?›› ብሎ ማሰብ አለበት፡፡

እንደ ግለሰብ ደግሞ ዘመኑ የሚጠይቃቸውን ነገሮች መላመድ አለብን፡፡ ከዘመኑ ጋር ካልሄድን አሠራሮችና ሕጎች ዘመንን ተከትለው ይቀየራሉ፡፡ ለምሳሌ፤ ከዓመታት በፊት አድራሻ የሚነገረው ‹‹ይህን ያህል ሜትር ገባ ብሎ፣ ከምንድንትስ ፊት ለፊት…›› እየተባለ ነበር፡፡ አሁን ግን ድረ ገጽ ብቻ ሊነገር ይችላል። ብዙ ተቋማት የምዝገባ ማስታወቂያ ሲያወጡ በድረ ገጽ ብቻ መሆኑን ያሳውቃሉ፡፡ ስለዚህ አሠራሮች ተቀየሩ ማለት ነው፡፡ አንድ ኢንተርኔት መጠቀም የማይችል (የማይወድ) ሰው ቢኖር አገልግሎቱን ማግኘት አልቻለም ማለት ነው፡፡ ለእሱ ተብሎ የተለየ የአሠራር ሕግ አይወጣም፡፡ የማይሆንን ነገር መብቴ ነው ማለት አያስኬድም፤ መብት በአስገዳጅ ሁኔታዎች ይገደባል፤ የአንድ ሰው መብት በሌላ ሰው መብት ይገደባል፡፡

በአጠቃላይ፤ ዘመናዊውን ሰዋዊ መብት ለመጠቀም ዘመናዊ እንሁን፤ መንግሥትና ተቋማትም የምትመሩትን ሀገርና ሕዝብ ነባራዊ ሁኔታ አገናዝቡ!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You