በሀገሪቱ በርካታ አውደ ርዕይና ባዛሮች //የንግድ ትርኢቶች/ እየተካሄዱ ይገኛሉ፡፡ በተለያዩ የግልና የመንግሥት ተቋማት አዘጋጅነት የሚሰናዱ መርሀ ግብሮች የንግዱን ማህበረሰብንና አርሶ አደሮችን ከሸማቹ ጋር በቀጥታ በማገናኘት ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚኖራቸው ይታመንባቸዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲዘጋጁ ደግሞ የሀገሪቱ ኩባንያዎች፣ አቅራቢዎች እና ላኪዎችን ከዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር ትስስር እንዲፈጥሩ በር ከፋች ይሆናሉ። የንግድ ትርኢቶች በዋናነት የገበያ ትስስርን በመፍጠር፣ የልምድ ልውውጥ በማድረግና በሀገር ውስጥ ያለውን የቴክኖሎጂና የምርት አቅም ለመረዳት የሚያግዙ ናቸው።
በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶችን ማካሄድ ጉልህ አበርክቶ እንዳለው ይታሰባል፡፡ ምክንያቱም ኢንዱስትሪዎች ምርቶቻቸውን ከማስተዋወቅና የገበያ ትስስር ከመፍጠር ባለፈ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የልምድ ልውውጥ ማድረግ የሚችሉበትን ሰፊ ዕድል መፍጠር ስለሚያስችል ነው። በተለያየ ጊዜ የተካሄዱ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን እንዳስገኙላቸው ተሳታፊዎች ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
ከሰሞኑም በአምራች ኢንዱስትሪዎችና በንግዱ ማህበረሰብ መካከል ትስስር ይፈጥራል፤ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ያመላክታል የተባለለት 14ኛው ዓለም አቀፍ የእርሻ እና የምግብ ንግድ ትርዒት ከሰሞኑ ተካሂዷል፡፡ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቱ በአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አዘጋጅነት ለሦስት ተከታታይ ቀናት የተካሄደ ሲሆን፤ የተለያዩ አምራቾች እና ኢንዱስትሪዎች ተሳታፊ ሆነውበታል፡፡
አምራቹን ከሸማቹ እንዲሁም ግብዓት አቅራቢውን ከኢንዱስትሪዎች ጋር የሚያገናኘው ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶች የገበያ ትስስር በመፍጠር፣ የቴክኖሎጂና የልምድ ልውውጥን ለማቀላጠፍ የጎላ አበርክቶ እንዳላቸው በዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቱ የተሳተፉ አምራቾች፣ የግብርና ግብዓት አቅራቢዎችና ኢንዱስትሪዎች ይናገራሉ፡፡
በንግድ ትርዒቱ ከተሳተፉት አምራቾች መካከል የማሸጊያ ምርቶችን ይዞ የቀረበው ክላሲክ ፓኬጂንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት አንዱ ነው፡፡ የዝግጅት ክፍላችን ያነጋገራት የድርጅቱ የገበያ ልማት ባለሙያ ወይዘሪት ፋንቱ ደገፉ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቱ የገበያ ትስስር ለመፍጠርና እርስ በእርስ ለመተዋወቅና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ ገልጻለች። በዚህ ረገድ ውጤታማ ተሞክሮ ማግኘታቸውንም ትገልፃለች።
እሷ እንዳለችው፤ ክላሲክ ፓኬጂንግ ለተለያዩ አገልግሎት የሚውሉ ማሸጊያዎችን ያመርታል፡፡ ለአብነትም ለምግብ፣ ለጨርቃ ጨርቅ፣ ለኮንስትራክሽን፣ ለወተትና ለሌሎችም አገልግሎት የሚውሉ ማሸጊያ ምርቶችን ያመርታል፡፡ መድረኩም እነዚህን ምርቶች ከሚፈልጉ አምራቾች ጋር በመተዋወቅ የገበያ ትስስር መፍጠር ያስችላል፡፡ ከዚህ ባለፈም ግብዓት አቅራቢ ከሆኑ ድርጅቶች ጋርም እንዲሁ የመተዋወቅ ዕድል በመፍጠር ለማሸጊያ ምርቶቹ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን የማግኘት ዕድል ፈጥሯል፡፡
የማሸጊያ ምርቶቹ ለምግብና ምግብ ነክ ላልሆኑ ምርቶች አገልግሎት የሚውሉ በመሆናቸው ድርጅቱ ማሸጊያዎቹን በሀገር ውስጥ ለሚገኙ የተለያዩ አምራች ድርጅቶች ያቀርባል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙ አምራች ድርጅቶች በተጨማሪ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ጭምር ምርቶቹን ተደራሽ ያደርጋል፡፡
በዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቱም ድርጅቱን ማስተዋወቅ መቻሉን የጠቀሰችው ወይዘሪት ፋንቱ፤ ደንበኞችን ማግኘትና ፕላስቲክ ማሸጊያዎቹን ከሚፈልጉ አምራች ድርጅቶች ጋር የገበያ ትስስር መፍጠር መቻሉንም ነው ያስረዳችው፡፡ ከግብዓት አቅራቢዎች ጋርም እንዲሁ የመተዋወቅ ዕድል መፍጠሩን በመጥቀስ የንግድ ትርዒቱን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አመልክታለች፡፡
በዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቱ ተሳታፊ በመሆን የተለያዩ ጠቀሜታዎችን አግኝቻለሁ የሚለው ሌላኛው ተሳታፊ ያሳርት ኢንጅነሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ ላለፉት 18 ዓመታት በኤሌክትሮ ሜካኒካል ቢዝነስ ውስጥ የቆየና በዘርፉ በጎ ተጽዕኖ እየፈጠረ ስለመሆኑ የድርጅቱ የጨረታና ማርኬቲንግ ባለሙያ ወጣት ናዝራዊት አርዓያ ትናገራለች፡፡
ወጣት ናዝራዊት እንዳለችው፤ ድርጅቱ በንግድ ትርኢቱ የተለያዩ ምርቶችን ይዞ ቀርቧል፤ በተለይም በግብርና ግብዓቶች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራቱና ከአርሶ አደሩ ጋር ቅርበት ያለው ድርጅት በመሆኑ በተለይም የግብርና ሥራዎችን ቀልጣፋና ምቹ ሊያደርጉ የሚችሉ ግብዓቶችን ያስመጣል፡፡ ለአብነትም የጠብታ መስኖ፣ የቡና መፈልፈያና መገልፈፊያ እንዲሁም ማቀነባበሪያ ማሽኖችን ለአርሶ አደሩ እያቀረበ ይገኛል፡፡
ድርጅቱ አርሶ አደሩን ለማገዝና የግብርና ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩትና ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በመሆን ይሠራል፡፡ በእስካሁኑ የሥራ እንቅስቃሴውም ኢትዮጵያ ውስጥ 160 በሚደርሱ አካባቢዎች የግብርና ግብዓቶችን በማቅረብ ተደራሽ ማድረግ ችሏል፡፡
ከሚያቀርባቸው ቴክኖሎጂዎች መካከልም በሶላር የሚሰሩ ፓምፖች ይገኙበታል፤ ፓምፓቹ ገጠራማ በሆኑ አካባቢዎች ሥራ ላይ ቢውሉ አርሶ አደሩ ከወንዝና ከተለያዩ የውሃ አካላት ውሃ እየጠለፈ በመስኖ እንዲያለማ ማድረግ የሚያስችሉ ናቸው፡፡ ድርጅቱ የግብርና መሣሪያዎችንና ማሽነሪዎችን በሀገር ውስጥ ገጣጥሞ የሚያቀርብ ሲሆን፣ ለዚህም ዋና ዋና የተባሉ ግብዓቶችን ከውጭ በማስገባት እንደሚሠራ ነው ወጣት ናዝራዊት የገለጸችው፡፡
እሷ እንዳለችው፤ ከውጭ ዋና ዋና ግብዓቶችን በማስመጣት በሀገር ውስጥ የሚገጣጠሙ የተለያዩ የእርሻ መሣሪያዎች አሉ፡፡ እነዚህን የእርሻ መሣሪያዎች በማምረት በአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫዎች ምርቶቹን ተደራሽ እያደረገ ይገኛል፡፡ በተለይም ለአርሶ አደሩ የቡና ማሽን፣ የወተት እንዲሁም የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያና ሌሎችንም በማቅረብ ምርትና ምርታማነታቸው እንዲጨምር የማድረግ ሥራን በስፋት ይሠራል፡፡
እንዲህ ያሉ መድረኮች ድርጅቱን በማስተዋወቅና የገበያ ትስስር በመፍጠር ረገድ ትልቅ አቅም መፍጠር እንደሚያስችሉ የጠቀሰችው ወጣት ናዝራዊት፤ በተለይም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እየተመሩ የሚመጡ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮችን የመተዋወቅ ዕድል ሰፊ እንደሆነ ጠቅሳለች፡፡ ይህም ሰፊ የሆነ የገበያ ትስስር እንደሚፈጥርና ከተለያዩ ድርጅቶች ጋርም እንዲሁ ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠር እንደሚያስተሳስር አስረድታለች፡፡
ዋና ዓላማውን በገበያ ማረጋጋት ላይ አድርጎ የሚሠራው የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቱ ከተሳተፉ ድርጅቶች መካከል ነው፡፡ ወይዘሮ ስንታየሁ እንዳለ የኮርፖሬሽኑ የምርት ጥራት ባለሙያ ናት፡፡ እሷ እንደተናገረችው፤ የምርት ጥራት ባለሙያዋ ኮርፖሬሽኑ አራት ዘርፎችን አዋቅሮ የያዘ ሲሆን፣ እነሱም አለ በጅምላ፣ ኢትፍሩት፣ እህልና ቡና እንዲሁም ግዢ ማማከር ናቸው፡፡ ኮርፖሬሽኑ ገበያ የማረጋጋት ሥራ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ይገኛል። በዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቱም የተለያዩ ምርቶችን ይዞ ቀርቧል፡፡
ኮርፖሬሽኑ የምግብ ሸቀጦችን ለሸማቹ የሚያቀርበው በተመጣጣኝ ዋጋ ነው፡፡ በተለይም ስኳር፣ ዘይት፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ጤፍን ጨምሮ በተመጣጣኝ ዋጋ ያቀርባል፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጤፍ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ የጨመረበት ሁኔታ መፈጠሩን ወይዘሮ ስንታየሁ በመጥቀስ፤ ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት ኮርፖሬሽኑ ከህብረት ሥራ ማህበራት ጋር በቅንጅት በመሥራት ምርቶቹን በቀጥታ በመግዛት ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ሲያቀርብ ቆይቷል፤ አሁንም እያቀረበ ይገኛል ብላለች፡፡ በዚህም ገበያውን ማረጋጋት መቻሉን ጠቅሳ፣ ለአብነትም ጤፍ ለተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በማቅረብ ለሠራተኛው መፍትሔ መሆን ችሏል ብላለች፡፡
ወይዘሮ ስንታየሁ ዓለም አቀፍ የእርሻ እና የምግብ ንግድ ትርዒቱ ፈላጊና ተፈላጊን በማገናኘት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጻለች፡፡ ኮርፖሬሽኑ ሸማቹን የሚያገኝበት ምንም አይነት መድረክ ባለመኖሩ አብዛኛው ሸማች ኮርፖሬሽኑ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች አያውቅም፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ መድረኮች ሸማቹን ከአምራቹና ከአቅራቢዎች ጋር በማገናኘት እንዲሁም ግብዓት አቅራቢዎችን ከኢንዱስትረዎች ጋር በማስተሳሰር ጉልህ አበርክቶ እንዳላቸው ገልጻለች፡፡
በንግድ ትርዒቱ ዓለም አቀፍ አምራች ኩባንያዎች መሳተፋቸው ሌላው ዓለም በቴክኖሎጂና በእውቀት የደረሰበትን ደረጃ ለማወቅ ዕድል የፈጠረ እንደሆነና የሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎችና አርሶ አደሮች ምርቶቻቸውን በላቀ ደረጃ ማምረት የሚችሉበትን የልምድ ልውውጥ ማግኘት የቻሉበት መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
የንግድ ትርኢቱ በተለይም በሀገር አቀፍ ደረጃ ለተጀመሩ የሌማት ትሩፋት ፕሮጀክቶች ውጤታማነትም የላቀ አበርክቶ እንዳለው የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የንግድና ግብይት ዘርፍ ምክትል የቢሮ ኃላፊ አቶ መስፍን አሰፋ ተናግረዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ የከተማ ግብርናን ለማስፋፋት በከተማ አስተዳደሩ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን ይበልጥ በማጠናከር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተደረገ ላለው ጥረት ስኬትም በጎ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መሰንበት ሸንቁጤ በበኩላቸው ስለ ንግድ ትርኢቱ ሲናገሩ እንደሚገልፁት፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ግብርና ላይ የተመረኮዘ እንደመሆኑ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቱ በተለይም በግብርናው መስክ የተሠማራውን የግሉን ዘርፍ ለማጠናከር ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎች ግብርናውን በማዘመንና የግብርና ውጤቶችን ምርታማነት በመጨመር ሀገሪቱ በዘርፉ ያላትን አቅም ማሳደግና ከዘርፉም መጠቀም እንድትችል ሰፊ ሥራ መሥራት ይገባል።
የኢንዱስትሪው ዘርፍ በኢኮኖሚው መስክ ያለውን አነስተኛ ሚና መጨመርና ግብርናውን በኢንዱስትሪ ማላቅ እንደሚገባ ያመለከቱት ፕሬዚዳንቷ፤ የተቀመጠውን ግብ ለመምታት እዚህም መሰል ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢቶች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እዳላቸው አመላክተዋል። በተለይም በአምራቾች፣ በኢንዱስትሪዎችና በንግዱ ማኅበረሰብ መካከል ትስስር ለመፍጠርና ለዓለም አቀፍ አምራቾች የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማመላከት ረገድ የሚኖረው አስተዋጽኦ ሰፊ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በ14ኛው ዓለም አቀፍ የእርሻ እና የምግብ ንግድ ትርዒት ከኬንያ፣ ሞሮኮ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች፣ ቱርክ፣ ኮሶቮ፣ ሞሪሺየስ እና ሕንድ የመጡ ኩባንያዎችን ጨምሮ በርካታ የሀገር ውስጥ አርሶ አደሮችና አምራች ኢንዱስትሪዎች ተሳትፈውበታል። የከተማ አስተዳደሩ ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ የግብርና ፕሮጀክቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልጿል። መሰል ዝግጅቶች በሀገር ውስጥና በውጭ ኩባንያዎች መካከል የንግድ ትስስር ለመፍጠርና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳደግ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን አዘጋጆቹና ተሳታፊዎቹ ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 3 ቀን 2016 ዓ.ም