የቱሪዝም ዘርፉ ስኬቶች

ኢትዮጵያ በቱሪዝም ሀብታቸው ከሚታወቁት የዓለም ሀገሮች አንዷ ናት። ሁሉም ዓይነት የቱሪዝም ሀብቶች ያሉባት በመባልም ትታወቃለች። በአያሌ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መስህቦቿ፣ ብሔራዊ ፓርኮቿ፣ ደማቅ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ሥርዓቶቿ፣ የአያሌ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እናት መሆኗ በፈጠረላት ቱባ ባህል፣ በአየር ንብረቷ ምቹነት ትታወቃለች።

የሰው ዘር መገኛ ናት፣ ለእዚህ በምስክርነት የሚጠቀሱት የታችኛው የአዋሽ ሸለቆና የታችኛው የኦሞ ሸለቆ፣ በሰው ዘር አመጣጥ ላይ ምርምር የሚያደርጉ የውጭ ሀገርና የሀገር ውስጥ ዜጎች ይመላለሱባቸዋል።

ብርቅዬ አእዋፋትና አራዊቶችን በማቀፍ በዓለም ደረጃ በከፍታቸውና በቀዝቃዛ ስፍራነታቸው የሚታወቁ እንደ ራስ ዳሸን ያሉ ተራሮች፣ በዓለም ዝቅተኛው ስፍራ በመባል የሚታወቀው የዳንክል ሞቃታማ ስፍራ እንዲሁም የቡና መገኛ መሆኗ፣ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙት እነ ቀይ ቀበሮና ዋሊያን የመሳሰሉት የዱር አንስሳት ሌሎች በቱሪስት መዳረሻነታቸው በእጅጉ የሚታወቁ ስፍራዎች ናቸው።

የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የጎንደር አብያተመንግሥት፣ የአክሱም ሀውልት፣ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ የጥያ ትክል ድንጋይ፣ የጀጎል ግንብ፣ የመስቀል ደመራ እንዲሁም የጥምቀት በዓላት፣ የገዳ ሥርዓት፣ ፍቼ ጨምባላላ፤ የኮንሶ ላንድ ስኬፕ፣ የታችኛው አዋሽ ሸለቆና የታችኛው የኦሞ ሸለቆ ዓለምም ጭምር በሚገባ የመዘገባቸው የሀገሪቱ ውድና ብርቅ የቱሪስት መዳረሻዎች ናቸው። እነዚህ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ በሚል በሁለት ተከፍለው በዩኔስኮ የተመዘገቡት ቅርሶች የዓለምም ቅርስ በመሆን ሀገሪቱን የቅርሶች ባለጸጋ በማድረግ ዓለም እንዲመሰክር አድርገውታል።

ሀገሪቱ በዓለም ቅርስነት ባይመዘገቡም ለመመዝገብ ተራ የሚጠብቁና ሌሎችም በዓለም ታዋቂ ቅርሶች ሞልተዋታል። በዓለም በርዝመቱ ትልቁ በመባል የሚታወቀው የዓባይ ወንዝ /ናይል/ መነሻዋ ኢትዮጵያ፣ የበርካታ ሐይቆች፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች መገኛም ናት፤ በዚህም የውሃ ማማ በመባል ትታወቃለች።

ሐይቆቿንና ወንዞቿን እንዲሁም የደን ሀብቶቿንና የአየር ንብረቷን ተገን ያደረጉ አእዋፋትና የዱር አራዊት በብዛት ይገኙባታል። የዓባይ ወንዝ ቱሩፋት የሆነው የጢስ ዓባይ ፏፏቴ፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያዎቹ ጥብቅ የደን ሀብቶች፣ የድሬ ሼህ ሁሴን የሃይማኖት ስፍራ፣ የአልነጃሺ መስጊድ፣ ሶፍኡመር ዋሻ፣ የእሬቻ በዓል፣ ሌሎች የኢትዮጵያ የቱሪስት ሀብቶች ናቸው።

ሀገሪቱ ቅርሶችን በዓለም ቅርስነት በማስመዝገብ በኩል በቅርቡም ሌሎች ሶስት ስኬቶችን ጨብጣለች። ባለፈው መስከረም ወር የጌዲኦ መልከዓ ምድርና የባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ፣ ሰሞኑን ደግሞ የሀረሪ ብሔረሰቡ የሸዋሊድ በዓል በዩኔስኮ ተመዝግበዋል። የእነዚህ ቅርሶች በዩኒስኮ መመዝገብ በዩኔስኮ የተመዘገቡ የሀገሪቱን ቅርሶች ቁጥር ከ13 ወደ 16 አሳድጎታል። ሶስቱ ቅርሶች የተመዘገቡት ካለፈው መስከረም ወዲህ ሲሆን፣ የእነዚህ ቅርሶች በዩኒስኮ መመዝገብ እንዲሁም የዓለም ቅርስ መሆን የቱሪዝም ዘርፉ ስኬት ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስና ባህል ድርጅት/ ዩኔስኮ/ ባለፈው መስከረም ወር በሳኡዲ አረቢያ ሪያድ ባደረገው ስብሰባ በዓለም ቅርስነት የመዘገበው የጌዲኦ ጥብቅ ደንና መልከዓ ምድር የጌዲኦ ብሔረሰብ ዘመናትን በተሻገረው የሚተዳደርበት ባህላዊ ሥርዓት ጠብቆ ያቆየውን ደንም ያካተተ ነው።

ዩኔስኮ በዚያው በሪያዱ ስብሰባው ነው የባሌ ተራራች ብሔራዊ ፓርክን በዓለም ቅርስነት የመዘገበው። የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የተመሰረተው እአአ በ1962 ሲሆን፣ የበርካታ ሐይቆች፣ ረግረግ ሥፍራዎች፣ የእሳተ ገሞራ ቅሬቶች መገኛ ነው። ይህ ሁሉና ውብ አቀማመጥ ያለው ለቱሪስት መዳረሻነት የሚመች እንዳደረገው ከቱሪዝም ሚኒስቴር የተገኙ መረጃዎችን ዋቢ ያደረጉ ዘገባዎች ይጠቁማሉ። በርካታ የእጽዋት ዝርያዎች፣ እጥቢ እንስሳት፣ የአእዋፋት ዝርያዎች መኖሪያም ሲሆን፣ አብዛኞቹም በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ናቸው።

የሸዋሊድ በዓል በሀረሪ ብሔረሰብ ዘንድ በተለያዩ መስጊዶች በልዩ ልዩ ሥነ ሥርዓት የሚከበር ዓመታዊ በዓል ነው። የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሪት ሌንሳ መኮንን ለቀጣዩ ትውልድ በረከት የሚሰጥበት መሆኑንም ጠቅሰው፣ ወጣቶች ባህላዊ እሴቶችንና ወጎችን እንዲማሩ እንደሚያስችልም ተናግረዋል። የቅርሱ በዩኔስኮ መመዝገብ የቱሪስት ፍሰት እንዲጨምር የሀገር መልካም ገጽታ እንዲገነባ እንደሚያደርግ፣ የክልሉን የቱሪስት ማዕከልነት እንደሚያጠናክር ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል።

ሀገሪቱ ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ መሆኗን የሚያመላክቱ የተለያዩ መረጃዎች በታዋቂ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችና ተቋማት በየጊዜው እየወጡ ያለበት ሁኔታም ሌላው የቱሪስት መዳረሻዎችን፣ በዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ ተግባሮችን ለማስተዋወቅ፣ አንዳንድ የቱሪስት መደረሻዎች ለመጎብኘት ያላቸውን ምቹ ሁኔታ ጭምር ማመላከታቸው ለዘርፉ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው።

የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት የጮቄ ተራሮች ኤኮ መንደርን የ2022 ምርጥ የቱሪዝም መንደር ብሎ መሰየሙ፣ በተመሳሳይም ድርጅቱ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን የሚገኘውን ሌጲስ ኢኮ የቱሪዝም መንደርን በፈረንጆቹ 2023 የዓለም ምርጡ የቱሪዝም መንደር ማለቱን በአብነት መጥቀስ ይቻላል።

ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ጥር ወር ናሽናል ጂኦግራፊ ዩኬ በጥር ወር ጉዞ ሊደረግባቸው ከሚገቡ አምስት ሀገሮች መካከል ኢትዮጵያን አካቷት እንደነበርም ይታወሳል። ድርጅቱ ሀገሪቱን በእዚህ ዝርዝር ውስጥ ያካተታት በተጠቀሰው ወር በላሊበላና ጎንደር የጋናና ጥምቀት በዓላት በድምቀት የሚከበሩ መሆናቸው ተጠቁሟል።

ይህን ዘገባ ይዞ የወጣው ታዋቂው የጉዞና አድቬንቸር ሚዲያ በሀገሪቱ በጥር ወር ያለው የአየር ሁኔታ ሙቀት የሚቀንስበት እንዲሁም መንገዶች ለተጓዦች ምቹ የሚሆኑበት መሆኑን በመጥቀስ ሁኔታው በአፋር ክልል የሚገኘውን ሞቃታማ ስፍራ እንዲሁም የኦሞ ሸለቆን ለመጎበኙ ምቹ መሆኑንም አያይዞ ጠቁሟል። እነዚህ የተቋማቱ መረጃዎች ቱሪስቶችን ለመሳብ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው።

እንደሚታወቀው ሀገሪቱ ፊትም በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ሀብቶቿ በእጅጉ ትጠቀሳለች፤ ከእነዚህ ሀብቶቿ መካከል 16ቱ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት መዝገብ ሰፍረዋል፤ ሌሎች በርካታ የቱሪስት መስህብ መሆን የሚችሉ ያለሙ መዳረሻዎች ያሉባት ናት፤ ከእነዚህ መስህቦች ማግኘት የሚገባትን ያህል ጥቅም እያገኘች እንዳልሆነች ሁሌም ይገለጻል። በርግጥም ተጠቃሚ አይደለችም።

የቱሪዝም ዘርፉ ይህ ሁሉ እምቅ አቅም እንዳለው የተገነዘበው በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የአስር ዓመቱ መሪ እቅድ ዘርፉን የምጣኔ ሀብቱ ምሰሶ ካላቸው አምስት ዘርፎች አንዱ አድርጎት እየሰራ ይገኛል። ለእዚህም ዘርፉ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ደረጃ ራሱን ችሎ እንዲቋቋም አድርጓል።

የግሉ ዘርፍ በዘርፉ እያከናወነ ያለው ተግባር እንዳለ ሆኖ መንግሥት የዘርፉን መስህቦች ለማስተዋወቅ፣ ለማልማትና ለመሸጥ በሰፊው እየሰራ ይገኛል። በተለይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ለቱሪስት መዳረሻ ሊሆኑ የሚችሉ የተለያዩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተገንብተው ወደ ሥራ ገብተዋል፤ እነዚህ በገበታ ለሸገር ፕሮጀክት በአዲስ አበባ ከተማ የተገነቡት የአንድነት፣ የወዳጅነትና የእንጦጦ ፓርኮች የከተማዋና የሀገሪቱ የቱሪስት መስህብ መሆን ችለዋል። ፓርኮቹ በከተማዋ የቱሪስት እንቅስቃሴ ላይ አዎንታዊ ለውጦች እያመጡ መሆናቸውም እየተጠቆመ ነው።

ይህ በገበታ ለሸገር የተጀመረው የቱሪስት መዳረሻ ልማት ወደ ገበታ ለሀገር ተሸጋግሮ በወንጪ፣ በጎርጎራ፣ በኮይሻ ልማቱ እየተካሄደ ይገኛል። የኮይሻ አካል የሆነው የሀላላ ኬላ ሪዞርት ግንባታ ተጠናቅቆ አገልግሎት ወደ መስጠት ተሸጋግሯል። ሀላላ ኬላ ሪዞርት የዳውሮ ንጉስ ያስጀመረውና ለ300 ዓመታት የዳውሮ ነገሥታት እየተቀባበሉ እንደገነቡት የሚነገርለት ብዙ ኪሎ ሜትሮችን የሚረዝመው ግንብ፣ የጊቤ ሶስት ግድብ በሚገኙበት እንዲሁም ውብ የተፈጥሮ ሀብት ባለበት አካባቢ የተገነባ ነው።

የጎርጎራና የወንጪ ፕሮጀክቶችም እንዲሁ በፍጻሜ ምእራፍ ላይ እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት ደግሞ ወደ ስምንት በሚደርሱ አካባቢዎች ላይ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ግንባታዎች ይካሄዳሉ። የአንዳንዶቹም ሥራ ተጀምሯል።

ጎርጎራ ውብ ስፋራ ሲሆን፣ በተፈጥሮ የታደለ፣ ምቹ አየር ያለው ነው። የውሃና የመንገድ ትራንስፖርት መጠቀም በሚያስችል ስፍራ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ እነዚህ ምቹ ሁኔታዎቹ ምርጥ ከሚባሉት የሀገሪቱ የቱሪስት መዳረሻዎች አንዱ እንዲሆን እንደሚያደርጉት እየተገለጸ ይገኛል። በተመሳሳይም ኮይሻና ወንጪም በተፈጥሮ ጸጋዎች የተዋቡ ናቸው፤ እነዚህ የቱሪስት መዳረሻዎች ወደ ሥራ ሲገቡ የቱሪዝም ዘርፉን በእጅጉ ሊያነቃቁት ለበርካታ ዜጎችም የሥራ እድል ሊፈጥሩ እንደሚችሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

እነዚህ ፕሮጀክቶች የሀገሪቱን የቱሪስት መዳረሻዎች አውጥቶ በማሳየት፣ የቱሪስት ፍሰትንና ቆይታን በመጨመር አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ተደርገው ነው የተገነቡት፤ እየተገነቡም የሚገኙት።

ሀገሪቱ የተፈጥሮና የሰው ሰራሽ ቅርሶቿን መጠቀስ ብቻውን ለውጥ እንደማያመጣ በመገንዘብ የቱሪስት መስህቦቹን ለሚያስተዋውቁ ለሚያለሙ እንዲሁም ለሚሸጡ አካላት መድረኮችን ታዘጋጃለች፤ የዓለም የቱሪዝም ቀን ሲከበር ከቀን በዘለለ በቀናትና ሳምንታት ቀኑ የሚከበርባት ሀገር ናት።

ዘንድሮ ደግሞ ለአንድ ወር የዘለቀና ስኬታማ ሆኖ የተጠናቀቀ የቱሪዝም ኢግዚቢሽንና ሆስፒታለቲ አውደ ርዕይም ባለፈው ጥቅምት ወር አካሂዳለች። ይህ አውደ ርዕይ ክልሎች የቱሪስት መስህቦቻቸውን ያስተዋወቁበት፣ የሸጡበት፣ እርስ በርስ ልምድ የተለዋወጡበት መሆኑ ተነግሮለታል። የዘርፉ ተዋንያን በአንድ አዳራሽ ለአንድ ወር የቆዩ ሲሆን፣ በዚህም በቱሪዝም ሀብቱ እና ልማቱ እንዲሁም ተግዳሮቶቹና መፍትሔዎች ላይ ምክክር አድርገውበታል።

አውደ ርዕዩ ከ160 ሺ በላይ ሰዎች በአካል ተገኝተው እንደጎበኙት፣ ከዘጠኝ ሚሊየን በላይ በሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በተለያዩ የዲጂታል አማራጮችና በመገናኛ ብዙሃን ስለመጎብኘቱም የቱሪዝም ሚኒስቴርን ዋቢ ካደረጉ መገናኛ ብዙሃን የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ስለሺ ግርማ አውደ ርዕዩ በተጠናቀቀበት ወቅት “የዘርፉን ተዋንያን ለአንድ ወር በአንድ ስፍራ በማገናኘት የተካሄደው አውደ ርዕዩ እንደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የምንፈልገውን ዓላማ ያሳካ ነበር” ሲሉ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር (ዶ/ር) ዐቢይ አሕመድ አውደ ርዕዩን በከፈቱበት ወቅት፤ ኢትዮጵያ ብዙ ታሪክ፣ ቅርስ ፣ባህል፣ የተፈጥሮ ስጦታዎች፣ አዕዋፍ፣ የዱር አራዊት እና ሊጎበኙ የሚችሉ ድንቅ ሁነቶች እንዳላት ግምት ውስጥ በማስገባት ከኢኮኖሚው ዘርፍ ዋና ምሰሶዎች አንዱ የቱሪዝም ሴክተሩ እንዲሆን መደረጉን ገልጸዋል።

አውደ ርዕዩ ጎብኚዎች ኢትዮጵያን ምቹ መዳረሻ የሚያደርጋትን ሀብት በናሙና እንዲያዩ እድል የሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፣ የኢትዮጵያን ድንቅ የቱሪዝም አቅሞች ከማልማት ባሻገር ማስተዋወቅ ላይ በትብብር መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል። መዳረሻዎችን ከማልማት ባሻገር በይፋ ማስተዋወቅ እንደሚያስፈልግም ነው ያስታወቁት።

ኢትዮጵያ ከዘርፉ ያላትን ተጠቃሚነት በማሻሻል ረገድ አሁንም በርካታ ሥራዎች እንደሚያስፈልጉ ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መንግሥት ለቱሪዝም ልማት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። በቀጣይ ያሉንን ድንቅ የቱሪዝም አቅሞች ከማልማት ባሻገር ማስተዋወቅ ላይ በትብብር መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት የወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ቱሪዝም በየዓመቱ በአራት በመቶ እያደገ ይገኛል። በዓለም ከሚፈጠሩ አስር የሥራ እድሎች አንዱ በቱሪዝም ዘርፍ የሚፈጠር ነው፤ ዘርፉ ለዓለም አጠቃላይ እድገትም 10 በመቶ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።

ኢትዮጵያ ምንም እንኳ በተፈጥሮ፣ ሰው ሰራሽ፣ ባህላዊ መስህቦቿ በአለም ብትታወቅም፣በርካታ መስህቦችን በዩኔስኮ ብታስመዘግብም ፣በዘርፉ ከአፍሪካ ቀዳሚ ስፍራ ላይ ብትሆንም፣ ከዚህ ሁሉ ጸጋዋ ግን የሚገባትን ያህል ጥቅም እያገኘች አይደለችም። ሀገሪቱ ከዚህ ቁጭት በመውጣት ይህን ሁኔታ የሚቀይር ከቱሪዝም ዘርፍ ተገቢውን ተጠቃሚነት የሚያመጣ ተግባር እያከናወነች ትገኛለች። በቱሪዝም ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ ተግባሮችና እየታዩ ያሉ ለውጦችም የዚህ ፍሬዎች ናቸው።

የቱሪዝም ፋይዳ በሚገባ ተለይቷል፤ ተለይቶ ብቻም አልተቀመጠም፣ እንደ ሀገር የቱሪዝም ዘርፉን በአዲስ መልክ የማደራጀት ሥራ ተሰርቷል፤ የቱሪስት መሠረተ ልማት ግንባታ፣ መስህቦችን ለማስተዋወቅና ለመሸጥ የሚያስችሉ አውደ ርዕዮችና ኢግዚቢሽኖች በውጭ ሀገርም በሀገር ውስጥ እየተካሄዱ ናቸው፤ ፋይዳቸውን ማጣጣም የተቻለ በመሆኑም የተመሳሳይ መድረኮች መምጣት አስፈላጊ መሆኑ በተለይ በሳይንስ ሙዚየም በተካሄደው አውደ ርዕይ ተሳታፊዎች ታምኖበታል።

መንግሥት ዘርፉን በማስተዋወቅ፣ በማልማትና ለመሸጥ የሚያስችል መደላድል በመፍጠር እያከናወነ ያለውን ተግባር እንዲሁም ዩኔስኮ የሀገሪቱን መስህቦች በዓለም ቅርስነት እየመዘገበ ያለበትን ሁኔታ በመጠቀም መስህቦችን ማልማት፣ ማስተዋወቅና መሸጥ ከሁሉም ዜጋ ይጠበቃል።

ኃይሉ ሣህለድንግል

አዲስ ዘመን   ኅዳር 29  ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You