ሥርዓተ-ምግብ፡- ለሠብዓዊ ርዳታ፣ ልማትና ሰላም

ምግብ መሠረታዊ ከሆኑ የሰው ልጅ ፍላጎቶች ውስጥ አንዱ ነው። ያለ ምግብ መኖር አይቻልም። ምግብ የሰው ልጆች መሠረታዊ ፍላጎት የመሆኑን ያህል ግን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎች ባሉባቸው ሀገራት ውስጥ አሁንም ቅንጦት ነው። የምግብ ዋስትናቸውን ያላረጋገጡ በርካታ ሀገራት ዛሬም አሉ። በኢትዮጵያም ቀላል የማይባሉና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች አሁንም የምግብ ዋስትናቸውን አላረጋገጡም። በሴፍቲኔት የሚረዱትም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። በድርቅ፣ ጦርነትና በሌሎችም ተፈጥሯዊ አደጋዎች ምክንያት የእለት ምግብ ተረጂ የሆኑትም የዛን ያህል ቁጥራቸው ከፍ ያለ መሆኑ ይነገራል።

ከዚህ በተቃራኒ ባደጉት ሀገራት ምግብ ጥያቄ የሚነሳበት ጉዳይ አይደለም። ማንም ዜጋ ከምግብም የተሻለ ምግብ ተመግቦ የማደር ዋስትናው ተረጋግጦለታል። እንደውም በአብዛኛዎቹ ያደጉ ሀገራት ራሱን የቻለ የሥርዓተ ምግብ ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ዜጎች ጤናማና የተስተካከለ የአመጋገብ ሥርዓት እንዲኖራቸው ሁኔታዎች ተመቻችተዋል። የሥርዓተ ምግብ አመራር ፈጥረውና በዚህ ዙሪያ የሚታዩ ችግሮችን ፈተው ዜጎቻቸው የተሻለ ምግብ ተመግበው በጤና እንዲኖሩ ሰፊ ሥራ ሠርተዋል።

በኢትዮጵያም በሥርዓተ ምግብ ዙሪያ ያለውን ችግር በማየትና በተደጋጋሚ የሚከሰተውን ረሃብ ለመቅረፍ ጠንካራ መሠረት ያለው የሥርዓተ ምግብ አመራር አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት በበጎ ፍቃደኛ የምግብ ባለሙያዎች የኢትዮጵያ የሥርዓተ ምግብ መሪዎች ኔትዎርክ /ጥምረት/ ተመሥርቷል። አምስተኛ ጉባዔውንም ‹‹የሥርዓተ ምግብ አመራር ለተፋጠነ ሠብዓዊ ርዳታ፣ ልማትና ሰላም የሶስትዮሽ ጥምረት በኢትዮጵያ›› በሚል መሪ ቃል ከሰሞኑ በአዲስ አበባ አካሂዷል።

ወይዘሮ እስራኤል ሃይሉ የኢትዮጵያ የሥርዓተ ምግብ መሪዎች ኔትዎርክ /ጥምረት/ መሥራችና ሰብሳቢ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፣ ሁሉም የጥምረቱ አባላት በነፃ የሚችሉትን አገልግሎት እንዲሰጡና የሥርዓተ ምግብ አመራር በኢትዮጵያ እንዲዳብር ለማስቻል ብሎም ሀገሪቱ ካለችበት የሥርዓተ ምግብ በተለይ ደግሞ ከርሃብ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመቅረፍ ጥምረቱ ተመሥርቷል። በአምስት ዓመታት ጉዞውም ጥምረቱ በርካታ አባላትን ማሠልጠን ችሏል። አባላቱም የነፃ አገልግሎቱን እየሰጡ ይገኛሉ። በሥርዓተ ምግብ ዙሪያ በጥምረቱ አባላትና አጋር አካላት ጋር የሚደረጉ ግንኙነቶች አሉ። ይህንኑ ግንኙነት የማጠናከር ሥራም ይሠራል።

ሥርዓተ ምግቡን ለማጠናከር መደበኛ አባላት በወር ከሚሰጡት የስምንት ሰአት ነፃ አገልግሎት በተጨማሪ ሥራውን የሚደግፉ በርካታ ወጣቶችና የተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች አሉ። ከነዚህ ውስጥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ረጂ ድርጅቶች፣ የግል ሴክተሮች፣ ምርምርና የአካዳሚክ ተቋማት፣ ከፌዴራልና ከክልል የተውጣጡ ምግብና የሥርዓተ ምግብ ፈፃሚዎችና ሌሎችም ይገኛሉ። እነዚህ አካላት ካላቸው መደበኛ ሥራ በተጨማሪ በትርፍ ጊዜያቸው የኢትዮጵያን ሥርዓተ ምግብ ለማሻሻል የሚሠሩ ናቸው።

ሰብሳቢዋ እንደሚናገሩት፣ ጥምረቱ ሥራውን ሲጀምር በስምንት ሰዎች ነበር። ይሁንና በአሁኑ ጊዜ ከ400 በላይ አባላት አሉት። በአምስት ዓመት ጉዞው ጥምረቱ ገና ከምሥረታው እንደሀገር ሊያኮራ የሚያስችለውን ‹‹የኢትዮጵያ የሥርዓተ ምግብ ፖሊሲን›› ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ህዳር 15 ቀን እንዲወጣና እንዲፀድቅ አድርጓል። ፖሊሲው ከፀደቀም በኋላ የሥርዓተ ምግብ መሪዎች ሀገሪቱ ያስቀመጠቻቸውን ፕሮግራሞች በመደገፍ፣ በፖሊሲው ላይ የተቀመጡ ዓላማዎች እንዲፈፀሙ ለማድረግ ሰፊ ሥራ ሲሠሩ ቆይተዋል።

በተለይ ከርሃብና ከሥርዓተ ምግብ መጓደል ጋር የተያያዙ ችግሮችን ዜሮ ለማድረስ፣ የምግብና የሥርዓተ ምግብ ፖሊሲን፣ የምግብና የሥርዓተ ምግብ ስትራቴጂንና የሰቆጣ ቃልኪዳንን ለመተግበር የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ይገኛሉ። ከነዚህ ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሰው የምግብና የሥርዓተ ምግብ ፖሊሲው ነው። ፖሊሲውን ተከትሎ የአስር ዓመት የምግብና የሥርዓተ ምግብ ስትራቴጂ ተዘጋጅቷል። በዚህም ሁሉም ሴክተሮች ስትራቴጂውን በፕሮግራማቸው ውስጥ አካተው እንዲተገብሩ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ተደርጓል። ከአምስት ዓመት በፊት ደግሞ የሰቆጣው ቃልኪዳን የትግበራው ምእራፍ በሚመለከታቸው 240 ወረዳዎች እንዲዳረስ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። ከዚህ ባለፈ ሁሉም ወረዳዎች ይህን ሥራ በተሳለጠ መልኩ እንዲያከናውኑ ቅድመ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል። የሥርዓተ ምግብ ሽግግር ፍኖተ ካርታም ተዘጋጅቶ ወደሥራ ተገብቷል። ይህም በተለይ የግብርናው ሴክተር መሪ ሆኖ የጤናውም ሴክተር አጋዥ ሆኖ ለመሥራት የሚያስችል ነው።

እንደሀገር ለመጀመሪያ ጊዜ የአመጋገብ ሥርዓት መመሪያም ተዘጋጅቷል። የሥርዓተ ምግብ መሪዎች ፕሮግራም እንዲኖርም ተደርጓል። በዚህም ከዚሁ ጋር የተያያዙ ሥልጠናዎች እንዲሰጡና ሁሉም ባለሙያዎች፣ በምግብና በሥርዓተ ምግብ ዙሪያ እየሠሩ ያሉ ባለሙያዎች ተሳታፊ የሆኑበት እስከታችኛው ቀበሌ ድረስ የሚወርድ ሥራ ለመሥራት በርካታ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ይገኛሉ።

እንደሰብሳቢዋ ማብራሪያ፣ ኢትዮጵያ ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት የሥርዓተ ምግብ ፖለሲን ካፀደቀች በኋላ በሥርዓተ ምግብ ዙሪያ በተበጣጠሰ መልኩ ሲሰራ የነበረውን ሥራ በተናበበና አንድ ወጥ በሆነ መንገድ እንዲሠራ አድርጓል። ይህ ሲባል ግን በሥርዓተ ምግብ ዙሪያ አሁን እየተሰራ ያለው ሥራ በቂ ነው ማለት አይደለም። በአሁኑ ጊዜ ሥርዓተ ምግቡን እየደገፉ ያሉት ከአስራ አራት በላይ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች እንደመሆናቸው ሥራው የሁሉንም ቁርጠኝነትና ድጋፍ ይሻል።

በሥርዓተ ምግብ ዙሪያ የተጠናከረ ሥራ ከመሥራት አንፃር በርካታ ለውጦች አሉ። በዚህ ረገድ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለይ በቅርቡ የተቋቋመውና የተለያዩ ሚኒስትሮችን ያካተተው ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆነ የሥርዓተ ምግብና የምግብ ስትሪንግ ኮሚቴ ይጠቀሳል። በቀጣይ ደግሞ የሥርዓተ ምግብና የምግብ ካውንስል እንዲመሠረት ጥረት እየተደረገ ይገኛል። ይህ ካውንስል ከፌዴራል በጠቅላይ ሚኒስትሩ አልያም እርሳቸው በሚወክሉት፤ በክልል ደግሞ በክልል ርእሰ መስተዳድሮች የሚወከልና እስከታችኛው የቀበሌ እርከን ድረስ ባለው አደረጃጀት ሁሉ የሚያስተባብር እንዲሆን ሥራዎች እየተሠሩ ነው።

በሕግም ተጠያቂነት ያለው አደረጃጃት እንዲኖር ተመሳሳይ ሥራ እየተሠራ ይገኛል። ይህም ትልቅ ውጤት ነው። ምክንያቱ ደግሞ እንደሀገር ከዚህ ቀደም እንዲህ አይነት ተጠያቂነትን የሚያሰፍን አሠራር የነበረ ባለመሆኑ ነው። ከዚህ ባሻገር ተጠሪነቱ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የሆነ በጤና ሚኒስቴር የሥርዓተ ምግብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት እንዲቋቋም ተደርጓል። ይህም እንደሀገር በሥርዓተ ምግብ ዙሪያ ትልቅ ውጤት የመጣበት ነው። በክልልም በመሳሳይ አደረጃጀት አስከታችኛው መዋቅር ድረስ እንዲወርድ ትልቅ ሥራ እየተሠራ ነው።

ሥርዓተ ምግብ ዙሪያ በተበጣጠሰ መልኩ የሚሠራውን ሥራ ወደ አንድ ለማምጣት በቅርቡ በሀገር የሥርዓተ ምግብ አመራር ለተፋጠነ ሠብዓዊ ርዳታ ፣ልማትና ሰላም የሶስትዮሽ ጥምረት በኢትዮጵያ ይፋ ተደርጓል። ይህም እንደሀገር በሥርተ ምግብ ዙሪያ የሚሠራውን ሥራ ወደ አንድ በማምጣት የተጠናከረ ሥራ ለመሥራት ያስችላል። ከድርቅ፣ ኮቪድ፣ ዓለም አቀፍ የዋጋ ንረት፣ ጦርነትና ከሌሎችም ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ጋር ተያይዞ የሚመጡ አደጋዎችንና ችግሮችን ለመቋቋምና ለነዚህ ጫናዎች የማይበገር ዜጋ እንዲኖር ለማስቻልም የጥምረቱ ይፋ መሆን ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል።

በጤና ሚኒስቴር የሥርዓተ ምግብ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ሕይወት ዳርሰኔ እንደሚናገሩት፣ አምስተኛው የኢትዮጵያ የሥርዓተ ምግብ መሪዎች ኔትዎርክ ዓመታዊ ጉባዔ የሚካሄደው ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት የፀደቀውን የምግብና የሥርዓተ ምግብ ፖሊሲን ለማክበርና ሥርዓተ ምግብ የብዙ ሴክተር መሥሪያ ቤቶችና የብዙ ባለድርሻ አካላት በትብብር የሚሠሩት ሥራ በመሆኑ ነው። በዚህ ዓመት የጥምረቱ ጉባዔም ‹‹የሥርዓተ ምግብ አመራር ለተፋጠነ ሠብዓዊ ርዳታ፣ ልማትና ሰላም የሶስትዮሽ ጥረት በኢትዮጵያ›› በሚል መሪ ቃል ተካሂዷል። ይህም የሥርተ ምግብ አመራሮች ያላቸውን ድርሻ ለማጉላትና የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ያስችላል።

የሥርዓተ ምግብ ፕሮግራም የሚከናወነው በጤና ሚኒስቴር ብቻ ሳይሆን ግብርና ሚኒስቴርን ጨምሮ በሁሉም ባለድርሻ አካላት ነው። ከዚህ አኳያ በሥርተ ምግብ ዙሪያ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ የተለያዩ ሥራዎች ሲሠሩ ቆተዋል። በዚህ ሂደትም ሀገሪቱ በተለያዩ ግጭቶችና የተፈጥሮ አደጋዎች ውስጥ አሳልፋለች። በተለይ ደግሞ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የነበረው ጦርነት፣ የኮቪድ 19 ወረርሺኝ፣ ዓለም አቀፍ የምግብ ዋጋ ንረት፣ ድርቅ ከፍተኛ የምግብ እጥረት አስከትለዋል።

እንዲያም ሆኖ ግን የሥርዓተ ምግብ ሥራዎች ወደ ማህበረሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ ከጤና ሚኒስቴር አንፃር የተለያዩ ሥራዎች ተሠርተዋል። ሥርዓተ ምግብ በጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጅ ውስጥ ተካቶ ሲሠራበት ቆይቷል። የሥርዓተ ምግብ ሥራው እንዳይቋረጥ ከክልል ጤና ቢሮዎች ጋር መምሪያ የማዘጋጀትና በዛ ልክ ሥራው እንዲደሠራ ተደርጓል። ለህክምና ግብዓት የሚያስፈልጉ፤ በተለይ ደግሞ ለአጣዳፊ የምግብ እጥረት፣ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ህፃናትና ለነፍሰጡር አጥቢ እናቶች ግብዓቶች ሳይቆራረጡ እንዲደርሱ፤ እንዲሁም በትክክል ሥራው እንዲሠራባቸው ጥረት ተደርጓል። ይህ ሲባል ግን ሙሉ በሙሉና በሚፈለገው ልክ በሥርዓተ ምግብ ዙሪያ የሚሠራው ሥራ እየተሠራ ነው ማለት አይቻልም። በተለይ ግጭት ባለባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች ለሥርዓተ ምግብ ህክምና የሚውሉ ግብዓቶች በተለያዩ አካባቢዎች ላልተፈለገ ዓላም ሲውሉም ታይተዋል። በዚህ ረገድ ይህን ለመከላከል ብዙ የተሠሩ ሥራዎች አሉ። ችግሩ በመንግሥት አቅም ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ ለጋሽ ድርጅቶችም በበቂ ሁኔታ መዋዕለ ንዋያቸውን ሊያፈሱ ይገባል።

መሪ ሥራ አስፈፃሚያዋ እንደሚሉት፣ ከአንድ ዓመት በፊት ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በወጣ ጥናት መሠረት የመቀንጨር ምጣኔ 39 በመቶ ሆኗል። ይህ አሃዝ በመቶኛ ሲታይ እ.ኤ.አ በ2019 ከነበረው ጥናት ጋር ሲነፃፀር እ.ኤ.አ በ2023 በ 1 በመቶ ብልጫ አሳይቷል። ኮቪድ 19፣ ዓለም አቀፍ የምግብ ዋጋ መናር፣ ድርቅና ግጭቶች ደግሞ ለዚህ አሃዝ ከፍ ማለት አስተዋፅኦ አድርገዋል። ነገር ግን ከአሃዙ ትንሽነት አንፃር ችግሮ አለመባባሳቸውን ያሳያል። ያምሆኖ በሥርዓተ ምግብ ዙሪያ አሁንም ሰፊ ሥራ መሥራትን ይጠይቃል።

መቀንጨር አሁንም የህብረተሰብ ጤና ችግር ሆኖ ቀጥሏል። ሌሎችም የምግብ እጥረት ችግሮች አሁንም አሉ። ከዚህ አኳያ በተለይ በነፍሰጡር እናቶች፣ በአፍላ ወጣቶችና በህፃናት ላይ ሰፊ ሥራዎችን መሥራት ያስፈልጋል። ከነዚህ ሥራዎች ውስጥ አንዱና ተስፋ የተጣለበት አስራ አራት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ያሉበትና ጤናና ግብርና ሚኒስቴር የሚመሩት የኢትዮጵያ የምግብና የሥርዓተ ምግብ ኢንተር ሚንስቴሪያል ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባት ነው።

ይህ ግን ብቻውን በቂ ባለመሆኑ ከሠብዓዊ ርዳታ፣ ልማትና ሰላም የተያያዙ ነገሮች የማይነጣጠሉና በጋራ መሠራት ያለባቸው በመሆኑ ይህንኑ ከግምት ውስጥ በማስገባት ለዚህ የሚሆን መመሪያና እንደሀገር ደግሞ ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀት የቴክኒክና አማካሪ ቡድን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል። በቀጣይም ሠብዓዊ ርዳታ፣ ልማትና ሰላም የማይነጣጠሉ ጉዳዮች ስለሆኑ በሥርዓተ ምግብ ዙሪያ የሚሠራው ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። በዚሁ ጊዜ ተግባራዊ የሚሆኑ ስልቶችም መቀየስ አለባቸው።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 29  ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You