በፈተና የፀና ህይወት

 ሕይወት በብዙ ፈተና እና ትግል ውስጥ የምናልፍበት ተግባራዊ ትምህርት ቤት ነው። በዚህ የፈተና ሕይወት ውስጥ ብዙዎች ሲወድቁ አንዳንዶች ግን በድል ይወጡታል። የሕይወት ፈተና ወደ መሬት ሲጥለን በወደቅንበት ቦታ ሆነን ማማረር፤ ማጉረምረም፤ ለመውደቁ ፤ ለመደናቀፉ ምክንያት የሆኑትን ሰዎች ሁኔታዎች እና እድለቢስነቱን ማማረር ሳይሆን ከወደቁበት ለመነሳት መሻት ብቸኛው መፍትሔ ስለመሆኑ እሙን ነው።

የዚህች ዓለም ውጣ ውረድ፣ ቁልቁለት እና አቀበቱ፣ የሕይወት ውስብስብ ፈተና አያልቅም። ሁሌም ቢሆን በሕይወት ውስጥ ክፍተት አለ። ሁልጊዜ ደስተኛ መሆን አይቻልም። አንዳንዴ መከፋት፣ ሀዘን ይኖራል፤ አንዳንዴም ማጣት ይከሰታል፣ ሁሉም ነገር አይሰጥም ሁሉም ነገር ደግሞ አይታጣም። በሕይወት ውስጥ ሁሌም ክፍተት አለ፤ ሕይወት ያመጣችውን ፈተና ተጋፍጦ ውጤታማ መሆን ለብርቱዎች የተሰጠ ፀጋ ነው።

ጋዜጠኛ ፍሬሕይወት ትባላለች። ተወልዳ ያደገችው በጅማ ከተማ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በትውልድ ከተማዋ ጅማ ተከታትላለች። በመቀጠልም ከቤተሰቦቿ ጋር ወደ ወለጋ ጊምቢ በማምራት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን መከታተል ችላለች። በትምህርት አቀባበሏ በመካከለኛ ደረጃ ከሚመደቡ ተማሪዎች መካከል እንደነበረች የምትናገረው ፍሬሕይወት በጊምቢ የጀመረችውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በአዲስ አበባ ከተማ በመጠናቀቅ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም በመቀላቀል በኮምፒውተር ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪ ማግኘት ችላለች።

በጅማና ጊምቢ ቆይታዋ በከተሞቹ ባሉ የሰርከስ የስፖርት ቡድኖች ውስጥ ንቁ ተሳታፊ የነበረችው ፍሬሕይወት በአዲስ አበባ ከተማም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እየተከታተለች በሙዚቃ፣ በቴሌቪዥን ድራማና በሬዲዮ ፕሮግራሞች ላይ ትሰራ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ በነበረችበት ወቅት በ2001ዓ.ም በአዳማ ከተማ ወይዘሪት ሚሊንየም ተብላ የቁንጅና ውድድር አሸናፊ መሆን ችላለች።

ለጋዜጠኝነት ያላት ፍቅር ከፍተኛ እንደሆነ የምትናገረው ፍሬሕይወት ይህንን ህልሟን ለማሳካት ጠንክራ በመሥራት ወደ ኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (ኦ. ብ. ኤን) ተቀላቅላ ሪፖርተር፣ ዜና አንባቢ፣ ብሎም ፕሮግራም አዘጋጅ በመሆን በምትወደው ሙያ ጥቂት ለማይበሉ ዓመታት አገልግላለች። ከጋዜጠኝነት ሥራዋ ጎን ለጎን በድራማ፣ በማስታወቂያ፣ በመድረክ ትርኢት እና በሞዴሊንግ ለረዥም ጊዜ መሥራት ችላለች።

የፍሬሕይወትን የሕይወት አቅጣጫ የቀየረው ክስተት የተከሰተው በ2006 ዓ.ም ለሥራ ጉዳይ ከአዳማ ወደ አዲስ አበባ ከተማ መጥታ የነበራትን ሥራ አጠናቅቃ ወደ አዳማ ከተማ በመመለስ ላይ ሳለች የመኪና አደጋ ይደርስበታል። በደረሰባት የመኪና አደጋ አንድ እግሯን ያጣችው ጋዜጠኛ ፍሬሕይወት በወቅቱ የተፈጠረውን አጋጣሚ ስታስታውስ ሁኔታው እጅግ አስቸጋሪ እንደነበር ትናገራለች፤ “አብረውኝ የነበሩ ጓደኞቼ እንዲሁም አንድ የ8 ወር ነፍስ ጡር ሴት ምንም አልሆነችም ሁሉም ጭረት አልነካቸውም ነበር” ትላለች።

የደረሰባትን አደጋ ስትገልጽ “ህልም ነበረ የመሰለኝ” የምትለው ፍሬሕይወት፤ በወቅቱ ከአደጋው ትንሽ ቆይቼ ስነቃ እኔ ብቻ ነኝ ከመኪና ስር ያለሁት ከውጭ ፍሬሕይወት የሚል የለቅሶ ድምጽ ሰማሁ። እንደምንም ብዬ ልወጣ ስል አንድ እግሬ ከፊት ወንበር ስር አስገብቼ ነበረና እግሬ ተጎድቷል። ሳየው አንድ እግሬ ተንጠልጥሎ አገኘሁት። ስትል እጅግ አስቸጋሪና መጥፎ የነበረውን አጋጣሚ ታስታውሳለች።

ይህንን አደጋ አሸንፈ ዛሬ ላይ ውጤታማ መሆን እንድትችል ስላደረጋት የሕይወት ሚስጢር ስትናገር፤ “ምንም ነገር በሕይወቴ ሲከሰት ለበጎ ነው የሚል እምነት አለኝ። በተጨማሪም በፈጣሪ ላይ ትልቅ እምነት አለኝ። ተስፋ ስለመቁረጥ አስቤ አላውቅም። ምንም ነገር በሕይወቴ ስመጣ ለመልካም ነው የሚሆነው የሚል አመለካከት ከድሮ ጀምሮ ስላለኝ ነው። ከዚህ በሻገር በደረሰው አደጋ የተጎዳሁት እኔ ብቻ መሆኔ ይህ በእኔ ላይ የደረሰው ፈጣሪ የሆነ ምክንያት ስላለው ነው ብዬ ለመቀበል ብርታት ሆኖኛል” ትላለች።

ሰው ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ የሚገነባበት የተለያየ መንገድ አለ የምትለው ፍሬሕይወት፤ ከቤተሰብ፣ ከማህበረሰብ፣ ከትምህርት ቤት፣ ከውሎ ብዙ መማር ይቻላል፤ ትላለች። ከልጅነት ጀምሮ ፈተናዎችን አልፈው ስኬታማ መሆን የቻሉ ሰዎችን ታሪክ ማየት እንደሚያስደስታት ፈተና ገጥሟቸው ያንን ፈተና እንዴት አለፉ ብላ እንደ ሰዓሊ ብሩክ የሺጥላ፣ የትነበርሽ ንጉሴ፣ መጋቢ ሀዲስ እሸቱ ዓይነት በሕይወታቸው ፈተና ገጥሟቸው በፅናት ታግለው አሸናፊ መሆን የቻሉና ስኬት ያስመዘገቡ ኢትዮጵዊያንን ሕይወት መከታተሏ ለሰው ልጅ ከአካል በላይ ትልቁ ነገር አዕምሮና ስብዕና ነው የሚል መረዳት ፈጥሮ በሕይወቷ ውስጥ የተከሰተውን ፈተና ማለፍ እንድትችል ብርታት እንደሆናት ትናገራለች።

ምንም ነገር በሕይወት ስመጣ ፈጣሪ ፈቅዶ የሚሆን ነው ብላ እንደምትቀበል የምትናገረው ፍሬሕይወት፤ ነገሮችን ለበጎ ነው ብለን ካሰብን ለበጎ ይሆናሉ። ሕይወት ያስተማረችንም ይህንን ነው ትላለች። ትላንትና ሙሉ አካል ነበርኩኝ ዛሬ አካሌ ጎድሎ እንዴት ጓደኞቼ ጋር እቀርባለሁ? እንዴት ወደ ሥራዬ እመለሳለሁ? ቤተሰቦቼስ ምን ይላሉ? የሚሉ አሉታዊ አስተሳሰቦችን መጋፈጥ የግድ ነው። በሕይወት ውስጥ መቀየር የማንችላቸው ነገር ወደ ሕይወታችን ሲመጣ ያንን ነገር በማዘን፣ በመጨነቅ እንዴት ይህ ነገር በእኔ ላይ ሆነ እያሉ መለወጥ የማይችሉት ነገር ውስጥ ከልቆዩ የትኛውንም ፈተና ማሸነፍ ይቻላል ትላለች።

ፍሬህይወት እንደምትናገረው፤ “እግሬ መቆረጡን አምኜ ስወስን ወደ እኔ ሊመጡ የሚችሉ ሃዘኔታ የሚመስሉ ግን እኔን የሚሰብሩ ወይም መንገድ ላይ የሚያስቀሩ ንግግሮችን ከንፈር መጠጣን ጨምሮ መዝጋት እንዳለብኝ እራሴን በማሳመን ሆስፒታል በነበርኩ ሰዓት አንድም ቀን ለሰከንድ ፈገግታ ከፊቴ ተለይቶ አያውቅም። አዝነው ለጥያቄ የሚመጡ ቤተሰቦቼን፣ የሥራ ባልደረቦቼን ሁሉ እግር ነው ያጣሁት እስትንፋሴን አለጣሁም፤ እግር ደግሞ የሚተካ ነገር ነው፤ ምንም ማለት አይደለም እያልኩ ቀላል አድርጌ እነግራቸዋለሁ። አልቅሰው የመጡ ሰዎች እኔን ስያዩ እንባቸውን ይገቱ ነበር” ስትል ትናገራለች።

በራስ አቅም መፍታት የማንችለው ችግር ሲያጋጥመን ከዛ ነገር ቶሎ አዕምሮን ማውጣት አስፈላጊ ነው የምትለው ፍሬሕይወት፤ “በማዘን፣ በመቆጨት፣ በማላዘን፣ በማልቀስ እራሳችንን ብሎም በዙሪያችን ያሉ ሰዎችን ሁሉ ስለሆነ የምንጎዳው ወዲያው ከዛ ስሜት ወጥቶ ቀሪ ሕይወትን ለማስተካከል መጣር ተገቢ ነው። እኔም የገጠመኝን ፈተና ተሻግሬ ዛሬ ላይ መቆም የቻልኩት ይህንን የሕይወቴ መርህ ስላደርኩት ነው” ትላለች።

ፈተናዎች ቢገጥሟትም የጽናት እና የቁርጠኝነት ምስክር ሆነ በጋዜጠኝነት መሰል ሥራዎች እና ችግሮችን

 ለማሸነፍ ባላት አቅም ሌሎችን ማነሳሳቷን የቀጠለችው ፍሬሕይወት፤ በቅርቡ፣ በአውስትራሊያ ውስጥ በተካሄደው (focus on ability) በተሰኘው ዓለም አቀፍ የአጭር ፊልም ፌስቲቫል ላይ ተሳትፋ፤ ስለ ሕይወቷ ታሪኳ ባሳየችው የሁለት ደቂቃ ከ40 ሰከንድ ቪዲዮ (አጭር ፊልም) የ5,000 የአሜሪካን ዶላር ሽልማት አግኝታለች። በተጨማሪም አምስት ነፃ የበይነ መረብ የትምህርት እድሎች ማግኘት ችላለች። ሽልማቷን በቅርቡ በኢትዮጵያ በድርጅቱ ተወካዮች በኩል ትቀበላለች።

የአጭር ፊልም ውድድሩ ትኩረት የሚያደርገው በአካል ጉዳተኞች አለመቻል ላይ ሳይሆን መቻላቸው ላይ ነው የምትለው ፍሬሕይወት፤ አካል ጉዳት ከዓላማ ማስቀረት እንደማይችል እና አካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎች መሥራት እንደሚችሉ ማሳያ የሚሆን ፊልም ነው ለውድድር የሚቀርበው ትላለች።

የአጭር ፊልም ውድድሩ የዛሬ ዓመት አካባቢ በኢትዮጵያ የተዘጋጀ ጊዜ በተጋባዥነት ተገኝቼ ነበር የምትለው ጋዜጠኛ ፍሬሕይወት፤ ይህ ነገር የእርሷንም ታሪክ የሚወክል በመሆኑ በዚህ ዓመት በተካሄደው ውድድር አጭር ቪዲዮ ለውድድር አዘጋጆቹ በመላክ ተሳትፎ እንዳደረገች ታስረዳለች።

ድምፅ እንዲሰጥባቸው ከመላው ከተመረጡ 134 አጭር ፊልሞች ውስጥ አንዱ መሆን የቻለው የፍሬሕይወት ፊልም በአንድ ሳምንት ውስጥ ድምፅ እንዲሰጥበት ተደርጎ በአብላጫ ድምፅ ዓለም አቀፍ አሸናፊ መሆን እንደቻለ ትናገራለች። የፊልሙ የግምገማ መስፈርት የበይነ መረብ ላይ የሕዝብ ድምፅ ብቻ ሳይሆን እንደ ቀረጻ፣ አርትዖት እና ሌሎች ጉዳዮችን የሚያካትት በባለሙያዎች የሚመረጥ እንደሆነ በውድድሩ ላይ ያሳየችው የሕይወት ታሪኳ ተፅእኖ ፈጣሪ ሆኖ አሸናፊ ስለመሆኑ ገልፃለች።

በአሁኑ ወቅት ፍሬሕይወት በግሏ በተለያዩ የሙያ ሥራዎች ላይ ተሳትፎ እያደረገች ትገኛለች። ከቀድሞ የሥራ ባልደረቦቿ ጋር በመተባበር (ማይሎ) የተባለ የግል የመልቲሚዲያ ኩባንያ በመቋቋም፣ በዛ ውስጥ የማስታወቂያ ሥራዎችን፣ የፌስቲቫል ፕሮግራሞችን፣ ዘጋቢ ፊልሞችን፣ የመድረክ ዝግጅቶችን እና ሌሎችንም ሥራዎች በኦሮምኛ እና በአማርኛ ቋንቋዎች በማዘጋጀት ላይ ትሰራለች። ፍሬሕይወት (ከማይሎ) ጋር ከምትሰራው ሥራ በተጨማሪ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎችን በመስጠት እየሰራች ትገኛለች።

ፍሬሕይወት የወደፊትን እቅዷን ስትናገር፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቀው እንደተከፈቱት ዓይነት የተለያዩ የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው

 ሕፃናትና ዜጎች የሚሆኑ ድጋፍ ሰጪ ተቋማትን ለማቋቋም በትጋት ለመሥራት እቅድ እንዳለት ትገልፃለች። በትጋት በመሥራት እነዚህ ልጆች በአካል ጎዶሎነት ያጡትን እድል ዳግም የዕድሉ ባለቤት በማድረግ እና የተለያዩ የግንዛቤ መስጫ መድረኮችን በመዘጋጀት ለመሥራት የረዥም ጊዜ እቅድ እንዳላት ትናግራለች።

በተጨማሪም ፍሬሕይወት የሰው ሠራሽ የሰውነት ድጋፍን እንዴት መጠቀም እንደሚገባ ስላለውም ጥቅም ግንዛቤዎችን ለማህበረሰቡ ለማስጨበጥ፤ ሥልጠናዎችን በማዘጋጀትና እና ያሉትን የሕይወት ልምድ ለወጣቶች ለማካፈል በቁርጠኝነት እንደምትሰራ በአፅንዖት ትናገራለች። በተጨማሪም ከእሷ የሕይወት ተሞክሮ በመነሳት ታሪኳን በማካፈል ሌሎች ሰዎች መሰናክሎችን እንዲያሸንፉ እና ግባቸውን እንዲያሳኩ የማድረግ አላማ እንዳላት ትገልፃለች።

ወጣቶች ሊያጋጥሟቸው የሚችሏቸው ተግዳሮቶች እና ማዘናጊያዎች ቢኖሩም፣ ጠንክሮ እንዲሰሩ እና ተስፋ እንዳይቆርጡ በአፅንኦት የምትናገረው ጋዜጠኛ ፍሬሕይወት፤ በተለይ ወጣቶች የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማቸው ለራሳቸው ጥንቃቄ የተሞላበት መሆን እንዳለበት ተናግራ፤ ለማህበረሰቡ የሚጠቅመውን ብቻ በመውሰድ በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማቸው አስተዋይ እንዲሆኑ ትመክራለች። እራስን ጠንካራ መሠረት መጣል ከልጅነት ጀምሮ እንደሚጀምር የምትናገረው ፍሬሕይወት፤ ነገ በባከነ ትላንትናቻው ላለመቆጨት ወጣቶች ጊዜያቸውን በአግባቡ ተጠቅመው ውጤታማ ለመሆን ነገ ሳይሉ ዛሬ ላይ ጠንክረው መሥራት እንዳለባቸው ትናገራለች።

ፍሬሕይወት በተጨማሪ ስትናገር፤ ወጣቶች ከእርሷ ተሞክሮ በመውሰድ መማር እና ምንም ነገር ላለመሳካቱ ሰበብ ባለመስጠት ጠንክሮ መሥራትን ብቻ አማራጭ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተናግራ፤ ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥማቸው ማንኛውንም ሁኔታና መሰናክል ማሸነፍና ለስኬት መብቃትን የሕይወት መርህ በማድረግ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ትናገራለች።

ሁሉም ሰው በሕይወት ሲኖር የሚያልፈው የተለያየ የሕይወት ምዕራፍ አለው የምትለው ፍሬሕይወት፤ ከደረሰባት አደጋ የተማረችው ነገር ቢኖር በሕይወት ውስጥ ነገ የሚባል ቀን እንደሌለ ነው። የተሰጠን ቀን ዛሬ በመሆኑ ነገ በእኛ እጅ ስላይደለ ዛሬን በአግባቡ መጠቀም እንዳለብን ነው። ስለዚህ ዕድሜያችንን በአግባቡ ሰዓት እንጠቀም ፣ ቀናቶቻችንን ባለማባከን ለጥቅማችን ማዋል አለብን ከምንም በላይ ደግሞ በፈጣሪ ላይ ትልቅ እምነትና ተስፋ ሊኖረን ይገባል ስትል መልዕክቷን አስተላልፋለች።

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን   ኅዳር 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You