የሐምሌ 19ኙ ተስፋለም ታምራት

በ1992 ዓ.ም በአንደኛው ሰንበት ማለዳ ላይ፤ በአዲስ አበባ ከተማ የአዲሱ ገበያ መንደር አብዛኛው ነዋሪ ጆሮውን ከኢትዮጵያ ሬዲዮ ደግኖ የሚተላለፈውን “የማዕበል ዋናተኞች” የተሰኘውን ተከታታይ ድራማ እስኪጀምር በጉጉት በመጠበቅ ላይ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ከድራማው ተወዳጅነት ባሻገር፤ ከልጅነቱ ጀምሮ በርታ ሲሉ ያሳደጉትና የሰፈራቸው ልጅ የሆነው ተስፋለም ታምራት፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ድራማ አማካኝነት ሊተውን በመሆኑ በትወናው ድምጹን ለመስማት ነበር። ለሰፈሩ ሰው፤ የድራማው ሰዓት አልደርስ ብሎት ከወትሮው የራቀ ቢመስለውም በተለመደው ሰዓቱ ጀመረ። በጉጉት ሲጠብቁት የነበረው ተስፋለምም፤ የማተሚያ ቤት ባለቤት ሆኖ ከተፍ አለ:: “እናቴ ወይዘሮ ማናለብሽ ተበጀ ለመጀመሪያ ጊዜ ድምጼን በራዲዮ ስትሰማ የጮኸችውን የደስታ ጩኸትና እልልታዋን እስካሁን ድረስ አስታውሰዋለሁ” ይላል ዝነኛው አርቲስት ሲያስታውስ።

የማዕበል ዋናተኞች ከአድማጩ ጋር ያስተዋወቀው ተስፋለም ታምራት ሲፈጥረው ጀምሮ ተዋናይ ነበር:: በተማረበት ሐምሌ 19 ትምህርት ቤት ባሉ ክበባት ላይ የነቃ ተሳትፎ ያደርግ ነበር። ትወናን የእለት ተእለት ተግባሩ አድርጎትም ነበር:: በትምህርት ቤቱ ድራማ ይሠራል። የተለያዩ መድረኮችን በግሩም ሁኔታ ይመራል:: በትምህርት ቤቱ ለሚደረጉ የጥበብ ክዋኔዎች የሚሰጠው አትኩሮትም ከቀለም ትምህርቱ በላይ እንደነበር ያስታውሳል:: ይሁን እንጂ በጊዜው የእለት የጥበብ ፍቅሩን ከማስታገስ በዘለለ የወደፊት የሕይወት መንገዴ ነው ብሎ ጥበብን የሙጥኝ ስለማለት ብዙ አላሰበም:: ሁሌ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ከአፉ የማትጠፋው የአማርኛ አስተማሪው መምህር አበበች ግን እንቅስቃሴውን አጥንታ “ወደፊት አንተ ተዋናይ ነው የምትሆነው” ትለው ነበር::

በተማሪዎች መካከል በሚካሄዱ የክርክር መድረኮች፤ ከሌሎች በተለየ ተስፋለም የሚመራበት መንገድና እዛው በሚዘጋጁ ድራማዎች ላይ የሚያሳየው የትወና አቅም ለመምህሯ የወደፊቱን ለመተንበይ ብዙም አልከበዳትም ነበር። ሆኖም ግን ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ለተወሰኑ ጊዜያት ያህል የእርሷ ትንበያ የተሳሳተ መስሎ ይታይ ጀመር። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የትምህርት ቤት ቆይታውን ካጠናቀቀ በኋላ፤ ነገረ ዓለሙን ትቶ ከጥበብ ጋር ተቆራርጦ ኑሮውን እየገፋ ስለነበረ ነው።

በ1992 ዓ.ም ያኔ በትምህርት ቤት ቆይታው አብሮት ስለጥበብ ይጨነቅ ከነበረውና በአሁኑ ሰዓት በሕይወት ከሌለው ዳንኤል ሹመቴ ጋር በድንገት መንገድ ላይ ተገናኙ። ዳንኤል በወቅቱ የማዕበል ዋናተኞች ላይ ይተውን ነበርና ‹‹አንተም እንድትሳተፍ ለምን ከደራሲና አዘጋጁ ኃይሉ ጸጋዬ ጋር አገናኝቼህ አታወራውም›› አለው:: ይሄ አጋጣሚ ተገኝቶማ እንዲሁ አይታለፍም ሲል ያሰበው ተስፋለም፤ በሃሳቡ ተስማማ:: ከኃይሉ ጸጋዬ ጋር ተገናኝተውም ፍላጎቱንና ችሎታውን አስረዳው። በተስፋለም ብቃት የተደሰተው ኃይሉም የማዕበል ዋናተኞች ላይ እንዲሳተፍ አደረገው። ለመጀመሪያ ጊዜ ስክሪብቱ ተሰጥቶት ጅማ በር ይገኝ በነበረው የኢትዮጵያ ሬድዮ ስቱዲዮ ውስጥ ድምጹ ተቀርጾ እስኪመለስ በጉጉት ትጠብቀው ለነበረችው ለእናቱ እንዲሁም ለመላው የአካባቢው ነዋሪ የሬድዮ ድራማ ሠርቻለሁና ስሙኝ ሲል አወጀ:: ስሙኝ የተባሉት በሙሉ አላሳፈሩትም፤ ከመስማትም አልፈው አስደስተውታል::

ተስፋለም በወቅቱ በርካታ ታዋቂ ተዋናዮች የሚሳተፉበትና በጉጉት ይጠበቅ የነበረ ድራማ ላይ መሳተፍ በመቻሉ የተለየ ስሜት እንደተሰማው ያስታውሳል:: የመጀመሪያው በሆነው የማዕበል ዋናተኞች ላይ ከተሳተፈ በኋላ፤ እሱ ሥራዎችን ለመፈለግ ወደ ሰዎች ከመሄድ ይልቅ ሰዎች ወደ እሱ ሥራ ይዘው መምጣት ጀመሩ። “ድምጽህ በጣም ቆንጆ ነው…ለምን ሌላ የሬድዮ ድራማ አትሰራም?… የመድረክ ቲያትር ብትሠራ…” የሚሉ አስተያየቶች በረከቱ። ወዲያውም ወደ ሌላ የሬድዮ ድራማ ተሸጋገረ::

ከድምጹ በተጨማሪ በስፖርት የዳበረ ተክለ ሰውነቱንና መልከ መልካም ወጣትነቱን የተመለከቱ ሌሎች ደግሞ ለምን የቴሌቪዥን ማስታወቂያ አትሠራም የሚል ጥያቄያቸውን ቀጠሉ። እሱም መቀበሉን ቀጠለ። “የጥበብ ሙያ ግንኙነት ይፈልጋል” የሚለው የጥበብ ሰው፤ መስመሩ ሲበጠስ ደግሞ እንደሚጠፋም ይናገራል። እርሱም ከጠፋበት የጥበብ መንገድ ሲገናኝ ብቃቱን የተመለከቱ ሌሎች ሰዎች ለሥራዎቻቸው ተስፋለምን ማጨት ጀመሩ:: የጥበብን ዓለም በተቀላቀለበት ወቅት “ተስፋ ኢንተርፕራይዝ” ከተሰኘ ድርጅት ጋር በስፋት ይሠራ ነበር:: ወቅቱ ኤች አይቪ ኤድስ የተስፋፋበት ነበርና በየአካባቢው፣ በትምህርት ቤቶች እንዲሁም በትልልቅ ተቋማት ቫይረሱን ለመከላከል የሚያግዙ ድራማዎችን ይሠራሉ::

በማስታወቂያ ሥራዎቹ ከሁሉም በበለጠ ከሀሌታ የማስታወቂያ ሥራ ጋር በርካታ ማስታወቂያዎችን መሥራት መጀመሩን ያስታውሳል:: ከኪነ ጥበብ ባሻገር ስፖርትና ተስፋለም የሚዋደዱ ነበሩ:: በተለይ ቴኳንዶ አብዝቶ የሚወደው ስፖርት ነበር:: ወደ ጥበቡ ዓለም ከመቀላቀሉ በፊት የወወክማ ውድድሮች ላይ ይሳተፍ ነበር። በካራቴው ጎበዝ ስለነበረ በሠፈር ውስጥ ከተማሪነት ወደ አስተማሪነት ሁሉ ተሸጋግሮ ነበር:: ወደ ጥበቡ ዓለምም ሲቀላቀል በስፖርት የዳበረ ሰውነት ያለው እንዲሁም የትወና አቅም ያለው ሆኖ በመገኘቱ የአዘጋጆች ምርጫ ለመሆን ጊዜ አልፈጀበትም::

በትምህርት ቤት ያዳበረው መድረክ የመምራት ችሎታ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ወደ መምራት ለመሸጋገር ጊዜ አልወሰደበትም:: የጥበቡን አለም ተቀላቅሎ ብዙም ሳይቆይ “ደቦ” የተሰኘ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለሚተላለፍ ፕሮግራም አስተዋዋቂነት እንፈትንህ የሚል ጥያቄ ቀረበለት:: በወቅቱ ከሚታወቁ ሰዎች ጋር አብሮ ቢፈተንም ለሥራው ተመርጦ ማስተዋወቅ ጀመረ:: የማስተር ፊልም ፕሮዳክሽን ባለቤት ቢንያም ከበደ በአጋጣሚ ድምጹን ሰምቶ “እንዴ ለመድረክ እኮ የሚገርም ድምጽ ነው ያለህ መድረክ ምራ” አለው:: “ኧረ እኔ መድረክ መርቼ አላውቅም” ቢልም “ችግር የለውም ከእኔ ጋር አብረን እንመራለን” አለው:: የመጀመሪያ መድረኩ ኤግዚቢሽን ማዕከል ነበር:: በአንድ መድረክ ተቀባይነቱ ከፍተኛ ሆነ ፈላጊውም በዛ:: በዚያውም መድረክ የመምራት ሥራውን ቀጠለ:: በመድረክ ያየው ለሌላ መድረክ የመምራት ሥራ እያጨው እስካሁን በመድረክ መሪነቱ ሥራ በተፈላጊነት ቀጥሏል::

‹‹ከፊልም ረገድ የመጀመሪያዬ የቱ እንደሆነ ይምታታብኛል›› የሚለው ዝነኛው ተዋናይ፤ “ከታሰረ ፍቅርና” “ንጉሥ ናሁሰናይ” ከተሰኙት እሱ የተወነባቸው ፊልሞች መካከል ማናቸው እንደሚቀድሙ እርግጠኛ ለመሆን ይከብደዋል:: በ90ዎቹ በሀገራችን ፊልም በብዛት የሚመረትበት ወቅት እንደመሆኑ በርካታ ፊልሞች ላይ ተሳትፏል:: ከተወነባቸው ከ20 በላይ ፊልሞች መካከል የባህር በር፣ መዘዝ፣ የምሽቱ ፍጻሜ፣ ያልረገቡ አይኖች ይገኙበታል:: “ዳና” እና “ዮቶራውያን” በብቃት ከተወነባቸው የቴሌቪዥን ድራማዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው:: በኃይሉ ጸጋዬ የተዘጋጀው “መዘዝ” የተሰኘው ፊልም፤ ቡቻ እያለ በስስት የሚጠራትን የትዳር አጋሩ የሆነችውን ተዋናይት ቃልኪዳን አበራን ለመተዋወቅ ሰበብ ሆኖታል::

ቃልኪዳን አበራ የመጀመሪያ የፊልም ሥራዋ ነበር:: በሰዓቱ እንዳያት ልቡ ቢመኛትም ነገር ግን ደጅ አስጠንታዋለች:: ተስፋለም ከምግብ ፓስታ፣ ቂንጬ ሩዝ ይሉት ነገር ባያይ ደስተኛ ነው:: ታዲያ በአንድ ወቅት ብዙም ፊት ካልሰጠችው ቃልዬ ጋር ምሳ ሊበሉ ሲቀመጡ “ፓስታ ይሁን አይደል?” አለች:: እሷ የመረጠችውን ነገር እጠላለሁ አይል ነገር ግራ ገባው፤ እሷ ፓስታ ስትል ምን ብሎ አልወድም ይበል:: ሲጣፍጥ እያለ አብሯት ፓስታ ሲበላ ከርሞ፤ ልክ ለፍቅር ጓደኛነት እሺ ስትለው እኔ ፓስታ አልወድም ሲል እራሱን ነጻ አወጣ:: ደፍሮ ከመጀመሪያው የምግብ ምርጫውን ቢናገር የእሱ ምርጫ ሥጋ ነበር::

ከቃልኪዳን ጋር ደጅ መጥናቱን አልፎ፣ ጥምረታቸው ከላይ የታዘዘ ሆነና ትዳራቸው ሰምሮ በሁለት ሴት ልጆች ተባርከዋል:: ‹‹ትዳር ትልቅ ኃላፊነት ነው›› የሚለው ተስፋለም፤ አንድ ትዳር ሲበተን ሀገር ይጎዳል ብሎ ያምናል:: ሁለቱ ጥንዶች በልምድ የገቡበትን ትወና ለማሻሻል መማር እንዳለባቸው ስላመኑ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቲያትርን በዲፕሎማ ተከታተሉ:: እዚያው ደግሞ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል:: በመዘዝ ፊልም ትውውቅ አብሮ መስራትን ሀ ብለው የጀመሩት ጥንዶች፤ ፊልምና ቲያትርም ሆነ የቴሌቪዥን ድራማ በጋራ ሠርተዋል::

ይሄ ጥምረታቸው ከሕይወትም ባሻገር ለሥራም አስመርጧቸው የተለያዩ መድረኮችን በጋራ መርተዋል:: ተስፋለም ለመጀመሪያ ጊዜ መድረክ አብሮት ከመራው ቢንያም ከበደና ሌሎችም ባለሙያዎች ጋር በመሆን “አውቶሞቲቭ ጆርናል” የተሰኘ የራዲዮ ፕሮግራም ሸገር ኤፍ ኤም ላይ መሥራት ጀመረ:: ከአድማጭ የሚሰማው አስተያየት መልካም ስለነበረ በራዲዮ ፋና ደግሞ “አዲስ ጣእም” የተሰኘ ሌላ ፕሮግራም ጀመሩ:: ሆኖም በመሀል ይሄ ሙያ የጋዜጠኝነት ሙያ ነው እኔ ለዚህ ሙያ ተሰጥቻለሁ ወይ?… በማለት እራሱን መጠየቁን ያስታውሳል::

ሆኖም ያገኘው መልስ ለጋዜጠኝነት ሙያ እንዳልተሰጠ ነበርና ውስጡ ሲያምን ወዲያው ሥራውን እያከበረው ለሚሰሩ ሰዎች መተዉን መረጠ:: ‹‹እኔ የተሰጠሁት ለትወና ነው›› በማለት ትወናና ከትወና ጋር የተያያዙ ነገሮችን እንጂ የጋዜጠኝነት ሥራ ለእርሱ ከባድና ኃላፊነቱ ትልቅ የሆነ ሥራ ነው ብሎ ስላመነ አቁሟል:: ሆኖም በሀገሬ ቲሌቪዥን “ዘና ሀገሬ” የተሰኘ የመዝናኛ ዝግጅት ከባለቤቱ ተዋናይት ቃልኪዳን አበራ ጋር በመሆን ዘና እያሉ ማስተዋወቅ መጀመራቸውን ይናገራል::

የራሱ የሆነ ቀን ተሰይሞለት፤ ተከብሮና ታስቦ ከመዋል አንጻር በሀገራችን ለኪነጥበብ የተሰጠው ቦታ አነስተኛ ነው:: ለዚህም በ2004ዓ.ም ከሙዚቀኞች ማህበር ጋር በመሆን ድምጻዊ አረጋኸኝ ወራሽንና ሰርጸ ፍሬ ስብሃትን ለምን የሙዚቃ ቀን አይኖርም በማለት ጠየቃቸው:: እውነትም ሊኖረው ይገባል በሚል ሃሳቡ ተንሸራሸረ:: ተስፋለም ቀኑን ለማክበር የሚያስችል ፕሮጀክት ቀረጸ:: የሙዚቃ ባለሙያዎች አስተያየት ቢካተትበት የተሻለ እንደሚሆን በመታመኑ ለባለሙያዎች ጥሪ ተላልፎ በሀርሞኒ ሆቴል ስብሰባ ተደረገ::

በዚህም አንዳንዶቹ ባለሙያዎች እኛን ያከበረና ልንደግፈው የሚገባ ሃሳብ ነው ሲሉ፤ አንዳንዶች ደግሞ ትልቅ የገቢ ምንጭ ነውና አንተ እንደ ግለሰብ ነገ ጠዋት ብር ልትሰበስብ ነው በሚል ተቃወሙ:: ሆኖም በዓላማው ጸንቶ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ፤ የሙዚቃ ቀን በ2004 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተከበረ:: የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቀን ተብሎ በአዲስ አበባ ብቻ መወሰን የለበትም በሚል ቀጣዩን በሃዋሳ፣ በባህርዳር፣ በመቀሌና በአክሱም ከተከበረ በኋላ በአዲስ አበባ ድጋሚ ተከብሯል:: ለስድስት ዓመታት ከዘለቀ በኋላ በዓሉን በክልሎች ለማክበር በሀገራችን የነበረው የሰላም ጉዳይ ባለማስቻሉና በየዓመቱ በዓሉ በመጣ ቁጥር ከተለያዩ አካላት የሚመጣው ቅሬታ ሙዚቃውንና የሙዚቃ ባለሙያዎችን ላክብር ባልኩ እንዴት በሚል ስሜት ማቋረጡን ያስረዳል::

አሁንም ቢሆን የሙዚቃ ቀንን በማክበር ሙሉ በሙሉ ተስፋ አልቆረጠም:: ነገሮች ቢስተካከሉና እንደገና ለማክበር ቢቻል ደስተኛ ነው:: ለዚህም ከተለያዩ አካላት ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ ነው:: በተለያዩ ጊዜያት ለመጀመር ያስብና ያለው ሁኔታ እየከበደው እንደሚተው ያስረዳል:: መከበሩ ይበልጥ ደስ ቢያሰኘውም፤ ያንን ማድረግ ሳይችል ቢቀር እንኳ የሙዚቃ ቀንን በማክበር በሀገራችን የመጀመሪያው መሆኑ ብቻ ደስታን እንደሚሰጠው ይናገራል:: እሱ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቀን ብሎ ካከበረ በኋላ፤ የያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት የዓለም አቀፍ የሙዚቃ ቀን ብሎ ማክበሩን እንዲሁም ደግሞ ብሔራዊ ቲያትርም የቲያትር ቀን ብሎ ማክበር መጀመሩ እንደሚያስደስተው ይናገራል::

ተስፋለም በሌላኛው የሕይወት መስመሩ፤ ለበጎ ዓላማና ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች ቅርብ ከሆኑ ዝነኞች መካከል አንዱ ነው:: ከዚህ ውስጥ በጣም ጠንካራ ሴት በሚላት ሲስተር ዘቢደር የተመሠረተውን የ “ሜሪጆይ” ድርጅትን ዓላማውን በመደገፍ በአምባሳደርነት ያገለግላል:: በተጨማሪ ራዕይ የበጎ አድራጎት ድርጅት ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ህጻናት የሚደግፍ ሲሆን፤ አሜሪካ ሀገር የምትኖረው የድርጅቱ መስራች በምታቅዳቸው እቅዶች ላይ ከጎኗ በመሆን እሱና ባለቤቱ የድርጅቱ የበጎ ፈቃድ አምባሳደር ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ::

ድርጅቱ ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ልጆች በኮምፒውተርና ሌሎችም ሙያ ነክ ሥልጠናዎችን እየሰጠና በልጆቹም ሕይወት ላይ የሚታይ ለውጥ እየታየ መሆኑን ይጠቅሳል:: ተስፋለም ታምራት፤ በቀጣይ ባለው ትልቅ እቅድ መሠረት ከስድስት ዓመታት በኋላ የተቋረጠውን የኢትዮጵያን የሙዚቃ ቀን፤ ኮንሰርትን በማከል በደማቁ የመሥራት ሃሳብ አለው:: በአሁኑ ሰዓት በፊልምና ቲያትሮች ላይ እንደቀድሞው በሰፊው እየተሳተፈ እንዳልሆነ በመናገር፤ ከትምህርቱ በቀሰመው እውቀት መሠረት በቀጣይ የተሻሉ ሥራዎችን ይዞ ለመምጣትም እቅድ አለው::

 ቤዛ እሸቱ

አዲስ ዘመን ህዳር 23/2016

Recommended For You