
አዲስ አበባ:- የደብረብርሃን ከተማ መዋቅራዊ ፕላን ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ተመራጭና የኢንቨስትመንት መዳረሻ ማድረግ የሚያስችል አቅም የሚፈጥር ነው ሲል የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር ገለጸ፡፡
የደብረ ብርሃን ሪጂኦ-ፖሊታን ከተማ መዋቅራዊ ፕላን፣ የዝግጅት ሂደትና የስማርት ሲቲ ጽንሰ-ሃሳብ ላይ ያጠነጠነ የምክክር መድረክ ትናንት ተካሂዷል፡፡
የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት በውይይት መድረኩ ላይ እንዳስታወቁት፤ ከተማዋ የዕድገት ምሳሌ እየሆነች በመምጣቷ ስፋትና ዕድገቷን የሚመጥን የዘመናዊ ስማርት ሲቲ ግንባታ መዋቅራዊ ፕላን ዝግጅት እየተደረገ ነው። ከተማዋን ወደ ስማርት ሲቲ የመቀየሩ ሂደት ኅብረተሰቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠትና የመንግሥት አገልግሎቶች ለማሻሻል ያስችላል፡፡
እንደ አቶ በድሉ ገለጻ፤ የሚዘጋጀው ስትራቴጂክ ፕላን መሰረት የደብረ ብርሃን ከተማን ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ተመራጭና የኢንቨስትመንት መዳረሻ ማድረግ የሚያስችል አቅም ይፈጠራል፡፡
የስማርት ሲቲ ግንባታ ሂደቱ ከተማዋን ወደ ተሻለ ደረጃ የሚወስዳትና የማኅበረሰቡ ፍላጎትን መሰረት ያደረገ ነው ያሉት አቶ በድሉ፤ የፕላን ዝግጅቱ 50 በመቶ መጠናቀቁንና በ2017 ዓ.ም ወደ ሥራ እንደሚገባ አመልክተዋል።
በመድረኩ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ከተሞች ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪና የከተማ መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አህመዲን ሙሀመድ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ የከተሞች መዋቅራዊ ፕላን ሲዘጋጅ ለቀጣዩ ትውልድ መሰረት የሚጥል እንዲሁም አረንጓዴ ኢኮኖሚን ማረጋገጥ በሚችል መልኩ መሆን አለበት፡፡
ለመጪው ትውልድ አሻራ ለማስቀመጥ የሚያስችል ውጤታማና ተሻጋሪ መዋቅራዊ ፕላን መዘጋጀት አለበት ያሉት አህመዲን (ዶ/ር)፤ ከከተሞች ማደግ ጋር ተያይዞ የሚፈጠረው የኢንዱስትሪ ዕድገት የሚመጥን የፕላን ዝግጅት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ደብረ ብርሃን ከተማ የኢንዱስትሪና የዕውቀት ማዕከል በመሆኗ የስማርት ሲቲ መዋቅራዊ ፕላን ያስፈልጋታል ያሉት አህመዲን (ዶ/ር)፤ በዓለም ላይ ካለው የቴክኖሎጂና የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዕድገት አንጻር ከተሞችን ወደ ስማርት ሲቲ መቀየር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
ስማርት ሲቲ የነዋሪዎች አገልግሎት ለማሻሻልና የመንግሥት አሰራርን ለማሳደግ እንደሚረዳ ጠቁመው፤ ከከተሜነት ጋር ተያይዞ የሚመጡ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመቀነስ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።
እንደ አህመዲን (ዶ/ር) ገለጻ፤ የከተማ መዋቅራዊ ፕላኖች ነገ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችንም ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ሊዘጋጁ ይገባል።
የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ንጉስ ታደሰ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ላለፉት ሶስት ዓመታት የከተማዋን የስማርት ሲቲ መዋቅራዊ ፕላን ዝግጅት ጥናት ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል።
ዘመኑን የዋጀና የቀጣዩን ትውልድ ከግምት ውስጥ የሚያስገባ መዋቅራዊ፣ እስትራቴጂክ ፕላን ያለው ማዘጋጀት ያስፈልጋል ያሉት ንጉስ (ዶ/ር)፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ ዕድገትና ስፋት እያሳዩ ከሚገኙ ከተሞች መካከል ደብረ ብርሃን አንዷ መሆኗን ተናግረዋል።
በውይይት መድረኩ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን፤ ስትራቴጂክ ፕላኑ የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር ከደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ በመሆን እንዳዘጋጁት በመድረኩ ተገልጿል፡፡
ልጅዓለም ፍቅሬ
አዲስ ዘመን ኅዳር 23 ቀን 2016 ዓ.ም