
ኢትዮጵያ በአሏት ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ሀብቶች በዓለም ላይ ተመራጭ ከሆኑ የቱሪስት መዳረሻ ሀገራት አንዷ ናት፡፡ ያሏትን ሀብቶች በአግባቡ በመንከባከብና በማልማት ለተቀረው ዓለም በማስተዋወቅና ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ጥቅም እያገኘች አይደለችም፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለቱሪዝም ዘርፉ ትኩረት በመሰጠቱ የተለያዩ ፕሮጀክቶች በመገንባታቸው ለዘርፉ እድገት ትልቅ ሚና ይጫወታሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡ በተለይ ተሰርተው ለአገልግሎት ክፍት የሆኑ እንደ ሀላላ ኬላን ያሉ የቱሪስት መዳረሻ ፕሮጀክቶች ቱሪዝም እንዲያንሰራራ በር ከፍተዋል።
በዚህም ሳያበቃ የገበታ ለሀገርና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡ በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ጎርጎራ፣ ወንጪና ኮይሻ ላይ የቱሪዝም ልማት መዳረሻዎች ስራቸው ተጠናቆ ለምርቃት ዝግጁ ሆነዋል፡፡ ታዲያ እነኝህ ፕሮጀክት ለቱሪዝም ዘርፉም እድገት ምን አስተዋጽኦ ያደርጉ ይሆን? ፕሮጀክቶቹን እንዴት በአግባቡ መጠቀም ይቻላል? በሚሉ ጉዳዮች ላይ የዘርፉ ባለሙያዎች ሃሳብ ሰጥተዋል።
የቱሪዝም ሀብት ልማት ባለሙያ አቶ ቃለዓብ በላቸው ለኢፕድ እንደሚናገሩት፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመላው ሀገሪቱ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው በመሰራት ላይ መሆናቸው ለቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃት አዲስ ዕይታን የሚፈጥር ነው ሲሉ ያስረዳሉ።
የቱሪዝም ዘርፉ ሀገሪቱ ያላትን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ከመፍታት አንጻር የራሱን ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ ከዚህ ቀደም ያልተሞከሩ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ማልማት በስፍራው ለሚገኙ የአካባቢው ማህበረሰቦች የመሰረተ ልማት እድገትን በመደገፍና የሥራ እድልን በመፍጠር ጠቀሜታዎች እያስገኙ ነው ይላሉ፡፡
እንደ ጎርጎራ፣ ወንጪ፣ ኮይሻና ሌሎችም በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ስር በተለያዩ አካባቢዎች የለሙ መዳረሻዎች ከቱሪዝም ጋር ብቻ ሳይሆን ከግብርናው፣ ከትራንስፖርት፣ ከሆቴልና ሌሎችም ዘርፎች ጋር የሚገናኙ በመሆናቸው ሰፊ ለውጦችን እንደሚያመጡ ይጠበቃል ሲሉ አቶ ቃለዓብ ይናገራሉ፡፡
የቱሪዝም መዳረሻዎች ማስፋት ከተቻለ ለዜጎች የሥራ እድልን በመፍጠር ከቦታ ወደ ቦታ የሚደረገውን ፍልሰት ይቀንሳል የሚሉት ባለሙያው፤ የቱሪዝም ዘርፉ ሰው ተኮር በመሆኑ ተገልጋዮች ወይም ጎብኚዎች ጥሩ አገልግሎት የሚያገኙ ከሆነ የቱሪዝም ገቢው ዘለቄታዊ እንደሚሆን ያብራራሉ፡፡
በተጨማሪ በቱሪዝም መዳረሻዎቹ አካባቢ የዕደ ጥበብና ሌሎች ምርቶችን በቀላሉ ለገበያ በማቅረብ ዜጎች ገቢ የሚያገኙበት ሁኔታዎች ማሳደግ ይገባል ሲሉ አቶ ቃለዓብ ያነሳሉ።
በየአካባቢው የሚገኙ ቱባ ባህሎችን በየወቅቱ ለሚመጡ ጎብኚዎች በማስተዋወቅና ኢንቨስትመንቱን መደገፍ እንደሚገባ ባለሙያው ያስረዳሉ።
በተጨማሪ በየወቅቱ የሚነሱ የተለያዩ ችግሮችን በመፍታት ወቅታዊ የሰላም ሁኔታው ሊታሰብበት እንደሚገባም አቶ ቃልዓብ ይጠቁማሉ፡፡
የሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ ከዚህ ቀደም የቱሪስቶች የቆይታ ጊዜ አነስተኛ መሆን ችግር ሆኖ ቆይቷል። ቱሪስቶች የሰሜኑን ወይም የምስራቁን የሀገሪቱን ክፍል በሚጎበኙበት ወቅት በአማካይ እስከ 15 ቀናት ይቆያሉ ተብሎ ቢጠበቅም ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ በየመዳረሻዎች ሰፊ ክፍተቶች እንደነበሩ ያወሳሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት በመሰራት ላይ የሚገኙና ለምርቃት ዝግጁ የሆኑ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ከዚህ ቀደም በየመዳረሻዎች ላይ በቂ የመሰረተ ልማት፣ ዘመናዊ የማረፊያ ስፍራና ሌሎች በአቅራቢያቸው ሊጎበኙ የሚችሉ ስፍራዎችን ከግምት ውስጥ ያስገቡ በመሆናቸው የቱሪስት ቆይታን በማራዘም ረገድ ተመራጭ ይሆናሉ ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
ለአብነትም በጎርጎራ ሰፊና እምቅ ሀብት በመኖሩ የጣና ሀይቆችን፣ ጎንደርንና ሌሎች በክልሉ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን ጎብኝቶ የሚመጣ ሰው ተጨማሪ የሚቆይበትን ስፍራ ያገኛል ይላሉ።
ወንጪ፣ ኮይሻና ሌሎች ፕሮጀክቶች ላይም በተመሳሳይ የቱሪስት ቆይታ የሚጨምር አማራጭ በመኖሩ ፕሮጀክቶቹ ለሀገርና ለማህበረሰቡ የሥራ ዕድል በመፍጠር የውጭ ምንዛሬን በማስገኘት ረገድ ወሳኝ ሚና እንደሚኖራቸው ያመለክታሉ።
በዘርፉ እየመጣ ያለው ለውጥ አካታችነትና ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ ከአየር መንገድ ጀምሮ እስከ ቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች ድረስ ቱሪዝምን ትኩረት ያደረገ ልዩ አገልግሎት መዘርጋትና የተሻለ ገቢ መሰብሰብ ይገባል ሲሉ ያስረዳሉ።
በገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ተምሳሌትነት በሁሉም ክልሎች የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን ይበልጥ ማልማትና የሀገሪቷን የቱሪዝም ገቢ ለማሳደግ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይገባል ሲሉ ሙያዊ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።
ቃልኪዳን አሳዬ
አዲስ ዘመን ኅዳር 23 ቀን 2016 ዓ.ም