የቀትሯ ፀሀይ ‹‹አናት ትበሳለች›› ይሏት አይነት ከእግር እስከ ግንባር ዘልቃለች ። በዚህ ሰአት ርቆ ለሚሄድ እግረኛ መንገዱ ፈተና ነው ። በዚህ ሰአት አንዳች የምህረት ንፋስ ‹‹ሽው›› ይል አይመስልም ። የበጋው ሙቀት ደርሶ መላ አካልን ያስጨንቃል።
በዕለተ ቅዳሜ ተሲያት ሰፈረ መገናኛ ልቡ ላይ ደርሻለሁ ። በዚህ ቦታ ትርምሱ ይለያል ። ኪስ ዳባሹ፣ ጎሽሞ አላፊው ይበረታል። የመንገድ ገበያው ለእግረኞችና ለመኪኖች ምቹ አይደለም። እዚህም እዚያም የተዘረጋው የጎዳና ላይ ንግድ መሄጃ መራመጃ እያሳጣ ነው። እንዲያም ሆኖ የሚጠይቅ፣ የሚገዛው ጥቂት አይደለም።
ከዚህ ተቃርኖ ስፍራውን የለወጡት ትላልቅ ህንፃዎች በዘመናዊ ዕቃዎች ተውበው እይታን ይማርካሉ። በነዚህ ቦታዎችም ገዥና ጎብኚው በእኩል ይጋፋል። አይቶ የሚወጣው ፣ ገዝቶ የሚያስጭነው፣ ዕለት በዕለት ይጎርፋል። መገናኛ የብዙ እይታዎች ፣ የበርካታ ትርምሶች ስፍራ ነው።
የሐረሯ እማማ …
ዓይን ከምትወጋው ደማቅ ፀሀይ ሳልሸሽ ለወጉ ከቆምኩበት አንድ ጥግ የሰአቱን መድረስ እጠብቃለሁ ። የእግሬ መምጣቱ አጋጣሚ ከእንግዶች ጋር የነበረኝ ቀጠሮ ነው። አሁንም ከትርምሱ መሀል ቆሜያለሁ። አስተውሎቴ በአግራሞት እንደቀጠለ ነው ። ለደህንነቴ ስል ሀሳቤን አልጣልኩም። የትከሻ ቦርሳዬን እንዳጠበኩ ከወዲያ ወዲህ እቃኛለሁ።
ዓይኖቼ አያዩት የለም። የመገናኛ ጎዳና በመልከ ብዙ ገጽታ መገለጡ እንዳስገረመኝ ቀጥሏል ። በድንገት እይታዬ ከአንዲት እናት ላይ አረፈ። ዕድሜቸው ገፍቷል። አለባበሳቸው ለየት አለብኝ። አንገታቸው ላይ ‹‹ጉፍታ›› የሚባለውን ሻሽ ጣል አድርገዋል። እሱም እንደሳቸው እድሜ በልቶታል።
ልብሳቸው ከማርጀት አልፎ በላያቸው ቆሽሿል። ይህ ሁሉ ለተመልካቹ እንጂ ለእሳቸው ምንም ማለት አይደለም ። ለአቀማመጣቸው ቦታ አይመርጡም ። አፈሩ አቧራውና ጠጠሩ ደንታ አይሰጣቸውም። ባገኙበት ስፍራ አረፍ ይላሉ።
እማማ አሁንም ለአፍታ ቁጭ ካሉበት ተነስተው አለፍ ብለው ተራመዱ። ብዙ አልቆዩም። ተመልሰው መጡና ከነበሩበት ቦታ ተቀመጡ። ነገሩን ሲደጋግሙት ዓይኔ ተከተላቸው። ካሉበት ሆነው የአንድን መንገደኛ ወጣት እጅ እየሳሙ ሲያመሰግኑት፣ ሲመርቁት አየኋቸው። ጉዳዩ የገባኝ ዘግይቶ ነበር ።
አሁን አጠገቤ ደርሰው ጭውውት ጀምረናል። ብስል ቀይ ናቸው። ቀረብ ሲሉኝ የአዳፋ ልብሳቸውን መልክ አየሁት። ቀለል ያለ ሺቲ ነው። እሳቸው እያወሩኝ ገጽታቸውን አስተዋልኩ ። ግንባራቸውን ይዞ መላ ፊታቸውን የከበቡ ቀጫጭን መስመሮች ብዙ ይናገራሉ። ዘለግ ያለ ቁመናቸው ፣ አሳዛኝ አንደበታቸው፣ ጎስቋላው ማንነታቸው ብዙ ይናገራል።
ለጊዜው ስማቸውን አልጠየኩም። እሳቸውም ለዚህ ትውውቅ አልፈጠኑም። ሊያወጉኝ የፈለጉት ጉዳይ እንዳለ አውቄአለሁ። ውስጤ ሊያዳምጣቸው ቸኩሏል። ከእጃቸው የገቡትን ጥቂት ብሮች ከሳንቲሙ እየለዩ ወደ ጉያቸው ቋጠሩ ። ሄድ ብለው ያመጡት ምንዳ መሆኑን ተረዳሁ። አሁንም ዓይናቸው ከላይ ታች ያማትራል። ደግነቱ ያየ አያልፋቸውም። የእጁን እየጣለ ፣የአቅሙን ያደርጋል። የሰጣቸውን ይመርቃሉ፣ያመሰግናሉ።
እማማ የሐረር ሴት ናቸው። ተወልደው ያደጉት፣ ትዳር ይዘው የከበዱት እዛው መሆኑን አወጉኝ። ጨዋታ ሲጀምሩ ንግግራቸው ቀለል ይላል። እየሰማኋቸው መሆኑን ሲያውቁ የልባቸውን እውነት ቀጠሉ። የሐረር ኑሯቸው ከቤተሰብ ጋር ነበር። ዓመታትን በገፉበት አገር ክፉ ደግን አልፈዋል። ከልጅነት እስከ ሽበት የበቁበት ስፍራ ለእሳቸው የማንነት አሻራ ነው።
እማማ የሐረሯ ባገር በቀያቸው ያሻቸውን ቢሆኑ ከብዷቸው አያውቅም። እንዲህ እንደዛሬው ዕድሜ ሳይጫናቸው ጉልበታቸው የፈቀደውን ሰርተው አድረዋል። ቢቸገሩ፣ ቢያጡ፣ ቢነጡ ደግሞ ከወዳጅ ዘመድ የጠየቁትን አያጡም። ማንነታቸውን የሚያውቁ ሁሌም ከጎናቸው ይሆናሉ ። ዕድሜያቸውን በገፉበት ሐረር ህይወት ዓለማቸውን ትተውት ወጥተዋል። ዛሬ በአዲስ አበባ ሰማይ ስር ባቆማቸው አጋጣሚ ክፉ ደጉን ቢያዩም ከአንደበታቸው ምስጋና አይጠፋም። ሁሌም ‹‹ተመስገን›› ማለት ልምዳቸው ነው ።
ከሁለት ዓመት በፊት…
እማማ ራሳቸውን አዲስ አበባ ሳያገኙት በፊት ከሐረር የሚወጡበት ምክንያት አልነበረም ። ቢሾፍቱ የሚኖረው ልጃቸው የአቅሙን እየረዳ ‹‹አለሁሽ›› ሲላቸው ቆይቷል ። ልጃቸው መተዳደሪያው የግንባታ ስራ ነው። የሚሻውን ባገኘ ጊዜ ሙያውን እየከፈለ የወር ደሞዝ ያገኛል። ከሚከፈለው ገንዘብ ለእናቱ አይሰስትም ። ሲሰጠው እየሰጠ ከምርቃቸው ይቀበላል ።
ከቀናት በአንዱ የለመደውን የግንባታ ሥራ ሊከውን ከአንድ ህንጻ ላይ ተገኘ። እንደወትሮው ከመወጣጫው ደርሶ የሙያው ድርሻውን ሊወጣ ከላይ ታች አለ። ዕለቱ ከወትሮው የተለየ አልነበረም። ሌሎች ሰራተኞች ልክ እንደሱ በስራ ገበታቸው ውለዋል። ከደቂቃዎች በኋላ የሆነው እውነት ግን ብዙ ታሪክ ቀየረ። የእማማ ልጅ የቆመበት እንጨት ድንገት ከእግሩ ከዳው። ራሱን ማዳን፣አካሉን መጠበቅ አልቻለም። እየተምዘገዘገ ወደ ታች ወረደ። ከመሬት ሲደርስ የተቀበለው ብረት አልማረውም። ከላዩ ሲወድቅበት ከግራ ጎኑ ጠልቆ ተመሰገ።
አወዳደቁን ከላይ ከታች ሆነው ያዩ ሊያነሱት ተጣደፉ። በደም የራሰው ተጎጂ አስትንፋሱ ይሞቃል። ህይወቱ እንዳለ ሲታወቅ ለህክምና ርዳታ ሩጫው ፈጠነ። ቁስለኛው ዕለቱን አፋጣኝ እርዳታ አገኘ። ሀኪሞቹ ተስፋ አልቆረጡም ። ለቀጣይ ክትትል አልጋ ይዞ እንዲታከም ወሰኑ ።
እናትና ልጅ…
ከቀናት በኋላ እናቱ ከሐረር ተጠርተው አዲስ አበባ ገቡ። ልጃቸው ዘንድ ሲደርሱ መላ አካሉ ተጎድቷል ። ውስጣቸው እያነባ ጎንበስ ቀና ብለው አስታመሙት ። ጥቂት የጭንቅ ቀናቶች አለፉ። የእማማ ልጅ ቁስል በዋዛ አልሻረም። ውሎ አድሮ ህመሙ ባሰ ። ጎኑን አልፎ ኩላሊቱ የዘለቀው ብረት መጨረሻውን አሳዛኝ አደረገው። ታታሪው የግንባታ ሰራተኛ ህይወቱ አልተረፈም።
እንግድነትን በሀዘን …
የእማማና የአዲስ አበባ አጋጣሚ መልካም አልሆነም። ልጃቸውን ቀብረው በሀዘን አንገታቸውን ደፉ። ታሪካቸውን የሰማ ሁሉ ከልብ አዝኖ ደገፋቸው። የዕድሜያቸው መግፋት ከዕውቀት ማነስ ተዳምሮ ስለልጃቸው መብት አልጠየቁም። አንዳንዴ አንዳንዶች የልጃቸውን በአደጋ መሞት እያስታወሱ አሰሪውን በህግ እንዲጠይቁ ይመክሯቸዋል። መውጫ መግቢያውን ለማያውቁት አቅመ ደካማ ይህን ማሰብ ከባድ ነበር ።
ቀን አልፎ ቀን ሲተካ ብቸኝነት ዋጣቸው ። በልቶ ለማደር እጅ አነሳቸው። የሚሰጣቸውን ጥሪት ይዘው ቀናት ቆጠሩ። እማማ ተመልሰው አገራቸው አልገቡም። እንደዋዛ የለመዱት እጅ መዘርጋት ከብዙዎች አስተዋውቆ ምጽዋዕት መቀበሉን ተለማመዱት ።
ዛሬ ኑሯቸው ሀና ማርያም በተባለ ሰፈር ነው። ጎዳና ላለመውደቅ የተከራይዋት ትንሽዬ ቤት ለጎን ማረፊያ አትበቃም። እስከዛሬ በልመና ከሚያገኙት ገንዘብ የአቅማቸውን ከፍለው ኖረዋል። በቅርቡ ግን አከራዮቻቸው ቤቱን አንድ ሺህ አምስት መቶ ብር አድርገውታል።
ውሏቸው መገናኛ፣ አዳራቸው ሀና ማርያም የሆነው ትልቋ ሴት ዛሬ ልመናን መተዳደሪያ አድርገው ህይወትን መግፋት ይዘዋል። ቀርቦ ላናገረ ላዋያቸው ሁሉ የልጃቸውን ታሪክ ይመዛሉ። ዛሬ ላሉበት የከፋ ህይወት የዳረጋቸው የእሱ ድንገቴ ሞት መሆኑን ሲያወጉ ፊታቸው ይጠይማል፣ በጎደጎደ ዓይናቸው ዕንባ ይሞላል ።
ከእማማ ጋር የነበረኝ ቆይታ አጭር የሚባል ነው። በዚህ አፍታ ግን ማንነታቸውን አውቄአለሁ። አሁንም ውስጤ ማዘኑን ቀጥሏል። ዕድሜያቸውን ከቀደመ ኑሯቸውና አሁን ካሉበት ህይወት እያነጻጸርኩ አርቄ አሰብኩ። ብዙ ቢያወሩኝ እወድ ነበር ። ሥራ አስፈትቼ ራታቸውን ላሳጣቸው አልፈለኩም። ተሰናብቻቸው ተለያየን።
ሌላው ጥግ…
ቀጠሮዬን አልረሳሁም ። አሁንም ግን ወደ እንግዶቼ እንዳልሄድ ካስገደደኝ ሌላ አጋጣሚ ጋር ተፋጠጥኩ። እማማ የሐረሯን ተሰናብቼ ራመድ ከማለቴ ዓይኖቼ በአንዲት ወይዘሮ ዓይኖች ላይ አረፉ። በንጹህ ልብሳቸው ቆሸሽ ያላየውን ንጹህ ነጠላ ደርበዋል። ጸአዳነታቸውን እያየሁ ውስጣቸውን አጤንኩት። ተክዘዋል ። ካፋቸው ጣል ያደረጉት መሸፈኛ ማስክ የፊታቸውን ገጽታ አልደበቀውም።
በአንድ ታዋቂ የገበያ ማዕከል ደረጃ ስር የተቀመጡትን ወይዘሮ በሀዘኔታ ማየት ቀጥያለሁ። ሁኔታቸው አሳዝኖኛል። እየለመኑ ነው ለማለት ግን ፈጥኜ አልደፈርኩም ። ሳላስበው አጠገባቸው ደርሻለሁና በእጄ ያለውን ጥቂት ብር በእጃቸው ላይ አኖርኩ ። ምስጋናውን ያደረሱኝ ከማቋርጥ ዕንባ ጋር ሆነ። ወትሮም ሁኔታቸው ገርሞኝ ነበርና ቀርቤ ላወጋቸው አልዘገየሁም።
በትካዜ የተዋጡት ወይዘሮ የሰውን ፊት ለማየት እየሸሹ ነው ። እጃቸውን በልመና መዘርጋት እንደተሳቀቁ ተረዳሁ። ከበረከቱት እግረኞች መሀል ጥቂቶቹን እየለዩ ‹‹እርዱኝ ›› ይላሉ ። የደከመ ድምጻቸው እምብዛም አይሰማም። ብርድ ከሀሩር የማያውቅ ፊታቸው ውሎውን የቻለው አይመስልም ። መጥቆርና መጎሳቆል ይዟል። በአናታቸው የዘለቀችው የቀትር ፀሀይ አላዘነችላቸውም። ያለአንዳች ከለላ አግኝታ እያንገላታቻቸው ነው።
ወይዘሮዋን ስመለከት ለልመና ህይወት አዲስ መሆናቸው ገባኝ። ልቀርባቸው አልቸገረኝም። አጠገባቸው ሆኜ ገና ጨዋታ ስጀምር ዳግም በዓይናቸው ውሀ ሞላ ። በነጠላቸው ጫፍ የሚሞዥቁት ፊት ከትኩስ ዕንባ ተዳምሮ ገጽታቸውን ለወጠው። እንዳሻቸው እንዲሆኑ ተውኳቸው።
ወይዘሮዋ የአዲስ አበባ ላይ ኑሮ ዓመታት አስቆጥሯል። አብራቸው የምትኖረው ልጃቸው ጤና አጥታ ከእጃቸው ከወደቀች ቆይቷል ። እሷን በማስታመም የቆየ አቅማቸው ዛሬ ከእሳቸው አይደለም። እግራቸውን፣ ወገባቸውን ያማቸዋል።
ህይወትን ለመግፋት ብዙ ሲደክሙ ቆይተዋል። በቤት ኪራይና በብቸኝነት ህይወት ያላዩት ፈተና የለም። አሁን እጃቸው ቢያጣ ቢነጣ የሰውን ፊትን ሊያዩት ግድ ሆኗል። እንደአባባሉ ደግሞ ‹‹የሰው ፊት እሳት ነው›› ይፋጃል፣ያስፈራል። ቀናትን የቆጠረው የእሳቸው ውሎ ከዚህ እውነታ እየታገለ ነው ።
አሥመራ ላይ …
ወይዘሮዋ ራሳቸውን በጎዳናው ልመና ከማግኘታቸው በፊት መልካም ህይወት ነበራቸው። አስመራ ላይ ከዶክተሩ ባለቤታቸው ጋር በደስታና በክብር ኖረዋል። ባለቤታቸው በጦር ሰራዊቱ ከሚታወቁት ሀኪሞች መሀል አንዱ ነበሩ። ዛሬ በህይወት የሉም። ከዓመታት በፊት በነበረው ውጊያ መሰዋታቸውን ወይዘሮዋ በሀዘኔታ ያወሱታል።
ይህ እውነት የሆነው ደርግ ሥልጣን ለቆ መንግሥት በተለወጠበት ጊዜ ነበር። የዛኔ እሳቸውን ጨምሮ በርካቶች ከአገረ- ኤርትራ በስደት ሊወጡ ተገደዋል። በጦርነቱ አምስት ወንድሞቻቸውን በሞት የተነጠቁት ወይዘሮ የጊዜው መዳረሻቸው አዲስ አበባ ሆነ ።
ሀኪሙ ባለቤታው ሀገራቸውን በሙያቸው አገልግለዋል ። ካለፉ በኋላ ግን ለጡረታ እንኳን የሚተርፍ ታሪክ አላገኙም ። የወቅቱ ለውጥ የነበረውን እንዳልነበር አድርጎ በእሳቸው ህይወት ጭምር ጥቁር አሻራውን አኖረ ።
ዛሬ ወይዘሮዋን በመሀል መገናኛ ለልመና ያስቀመጣቸው አንዱ ምክንያት ይኸው ሆኗል። እድሜ ሲገፋ፣ አቅም ሲደክም ማንነት ይንገዳገዳል፣ ዙሪያው ገደል ይሆናል። እንዲህ እንደአሁኑ ኑሮ ሰማይ ሲነካ ደግሞ ለእንዲህ አይነቶቹ ነፍሶች መከራው ይለያል።
የእናቶቹ ነገር …
ዛሬ ሁለቱን እናቶች ከቤት አውጥቶ ጎዳና ያዋላቸው በህይወታቸው ያለፉት ጠመዝማዛ መንገድ ነው። ልክ እንደነሱ ሁሉ ትናንትን የተደላደ ኑሮ የነበራቸው ወገኖች ፣ በተለያዩ ክፉ አጋጣሚዎች የሌላውን እጅ ለማየት ይገደዳሉ። ቀን ሲጎድል፣ ዕድሜ ሲያዘነብል ደግሞ ‹‹ አለሁ ››የሚል ወዳጅ ዘመድ ፣ደጋፊ የሚሆን አጋር ያስፈልጋል ።
በዕድሜ ማምሻ ፣ በማረፊያ ዘመን የሚያጋጥም የህይወት ስብራት በቀላሉ አይጠገንም ። ወድቆ ላለመቅረት ተረስቶ ላለመተው የሁሉንም ወገን ትብብር ያሻል። የቀድሞውን ማክበር ለነገ ማንነት መሰረት ነውና ።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘም ህዳር 22/2016