የባህር በር/ወደብን ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገትን ሆነ የተሟላ ሉአላዊ ሀገር ለመፍጠር የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብም እንደ አንድ አቅም ይወሰዳል። ከዚህ የተነሳም የባህር በር ያላቸው ሀገራት ከሌላቸው 20 ከመቶ እድገት እንደሚኖራቸው ጥናቶች ያመላክታሉ።
ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ካሉ የአፍሪካ ሀገራት አንዷ ስለመሆኗ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሳይቀር እያረጋገጡት ያለው እውነታ ነው፤ ይህም ሆኖ ግን የባህር በር አልባ መሆኗ ዜጎቿ በሚመኙት ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ላይ ሆነ በሉዓላዊነቷ ላይ ተግዳሮት ከሆነ ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል።
ሀገሪቱ በሕዝብ ብዛታቸው ቀዳሚ ከሆኑ / ከ120ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት / እና የባህር በር ከሌላቸው የዓለም ሀገራት የመጀመሪያ እንደሆነች መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህም በሀገሪቱ ዛሬዎች ሆነ ነገዎች ላይ ሊኖረው የሚችለው አሉታዊ ተጽእኖ መላውን ሕዝብ አደጋ ውስጥ ሊከት እንደሚችል ይታመናል።
የባህር በር አልባ መሆን ሀገራትን ከውሃ አካላት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያገል ፤ በአቅራቢያቸው ከሚገኙ ትላልቅ የንግድ መዳረሻዎች ተጠቃሚ እንዳይሆኑ የሚያደርግ ነው፤ ከዚህ ባለፈ የኢኮኖሚ ነጻነት እንዲያጡ በማድረግ ረገድ ቀዳሚውን ድርሻ እንደሚይዝ ጥናቶች ያመለክታሉ።
ይህ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በማደግ ላይ ያሉ እና የህዝብ ብዛታቸው ከፍተኛ የሆኑ ሀገራትን በእጅጉ የሚፈትን ስለመሆኑ ብዙም ለጥያቄ የሚቀርብ አይሆንም። “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው ባልተመጣጠነው የወጪ እና ገቢ ንግድ ላይ ተዳምሮ ሀገራዊ ኢኮኖሚው እንዳይረጋጋ ማድረጉ የማይቀር ነው።
አሁን ላይ ሀገሪቱ ወደ ውጪ ከምትልካቸው ምርቶች ይልቅ ከውጪ የምታስገባቸው ምርቶች ከፍተኛውን ቦታ ይይዛሉ፤በዚህ ላይ ለወደቦች ኪራይ ልታወጣው የምትችለው ወጪ ሲታከል እንደ ሀገር በዜጎች የእለት ተእለት ሕይወት ላይ ሊፈጥር የሚችለው ጫና እጅጉን ከፍተኛ ነው።
ሀገሪቱ የጅቡቲን ወደብ በኪራይ መጠቀም ከጀመረች ሶስት አስርት ዓመታት ተቆጥረዋል። በነዚህ ዓመታትም ለጅቡቲ በበርካታ ቢሊዮን ዶላሮች እየከፈለች ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥና ወደ ውጪ ስታጓጉዝም ቆይታለች። ይህም በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ /በተለይም ኢኮኖሚዋ እያደገ በመጣ ቁጥር እያስከተለ ያለው ጫና ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ ነው።
አሁን በተጨባጭ ሀገሪቱ ለወደብ ኪራይ በቀን 3 ሚሊዮን ዶላር ለጅቡቲ ትከፍላለች። ይህ ደግሞ በዓመት ሲሰላ ወደ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ገደማ ይሆናል። ይህ ለአንድ ወደብ ኪራይ የሚከፈል ገንዘብ በውጪ ምንዛሬ መሆኑ ደግሞ ችግሩ የቱን ያህል የከፋ ስለመሆኑ ማሳያ ነው።
ገቢ ንግድ ሚዛን ከፍ በሚልባቸው፤ ከዚህም ባለፈ ኢኮኖሚያቸው በግብርና ላይ መሰረት ላደረጉ ሀገራት ዶላር ማግኘት የቱን ያህል ፈተና እንደሆነ ለመግለጽ የሚያዳግት አይደለም። ከዚህ የተነሳም ሀገራችን በየጊዜው የሚያጋጥማትን የዶላር እጥረት እና በወደብ ኪራይ መጨመር የሚመጣውን ጫና ተቋቁማ የ120 ሚሊዮን ሕዝብ ፍላጎትን በቅጡ ማርካት ይቻላታል ብሎ ማሰብ ቀላል አይሆንም።
ከዚህ የተነሳ አሁን ላይ እያነሳች ያለው የአማራጭ ወደብ ጉዳይ፤ የሉአላዊነትና የህልውና ጉዳይ መሆኑን ለመገንዘብ አይከብድም። የወደብ ጥያቄው / የባህር በር / ጦረኛ ሆና ሳይሆን የባህር በር የዜጎቿ የህልውና ጥያቄ በመሆኑ ነው ። ይህን ለመረዳት ደግሞ አለም አቀፉም ህብረተሰብ ሆነ ጎረቤት ሀገራት የሚከብዳቸው አይሆንም።
አሁን ላይ ያለው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ሀገሪቱ ከ90 ፐርሰንት በላይ የሚሆነውን የወጪ ገቢ ንግዷን የምታከናውነው በጅቡቲ ወደብ ላይ ነው። ይህ ደግሞ ለወደቡ ኪራይ ከሚወጣው ከፍተኛ ገንዘብ በተጨማሪ ኢትዮጵያዊያን ላይ ሊፈጥር የሚችለው የደህንነት ስጋት ቀልሎ የሚታይ አይደለም።
ከወደቡ ጋር በተያያዘ ለአንድ ቀን እንኳ ችግር ቢፈጠር፤ በኢትዮጵያዊያን ህልውና ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ የቱን ያህል አደገኛ ሊሆን እንደሚችል ለመገመት የሚከብድ አይደለም፤የተለየ እውቀት የሚጠይቅ አይሆንም።
ይህ ማለት ሌላ አማራጭ ወደብ ባለመኖሩ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ሥራ የሚያቆም ይሆናል ማለት ነው። ከነዳጅ ጀምሮ ኢኮኖሚውን የሚያንቀሳቅሱ ሸቀጦችን በቀላሉ ማግኘት የማይቻል ሁኔታ ሲፈጠር የ120 ሚሊዮኑ ሕዝብ ህልውና ጥያቄ ውስጥ ከመግባትም የሚያልፍ ይሆናል።
ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ የሰላም ዘብ ነች ፤ የራሷንና ጎረቤቶቿን ሰላም ስታስጠብቅ የኖረች የሰላም አምባሳደር ነች ፤ የአማራጭ ወደብ ጥያቄዋም ከዚህ ማንነቷ የሚመነጭና ሰላማዊ አማራጮችን ታሳቢ ያደረገ ነው።
ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር በጋራና በሁለትዮሽ ትብብር አማራጭ ወደቦችን ለማልማት የምታደርገውን ጥረት በአዎንታዊ መልኩ ተረድተው፤የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ ባደረገ መልኩ ምላሽ ሊሰጧት ይገባል።
ከዓለም አቀፍ ህግ አንፃር ኢትዮጵያ የባህር በር ለእድገቷ እና ለልማቷ ከማስፈለጉም በላይ፤ ጉዳዩ የሀገሬው ዜጋ የዳቦ ጥያቄም ጭምር በመሆኑ ሁሉን አቀፍና የሁሉንም ሀገራት ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል።
ለዚህም የወደብ ባለቤት የሆኑ ጎረቤት ሀገራት በቀረበው የውይይት እና የንግግር ጥሪ መሰረት ቁጭ ብሎ በመወያየት ለጥያቄዋ ተገቢውን ምላሽ መስጠት ይኖርባቸዋል። አፍሪካዊ ችግሮችን በአፍሪካዊ መፍትሔ ለመፍታት የተጀመሩ ጥረቶችን በማጠናከር፤አብሮ ለማደግ የቀረበው ጥሪ ለቀጣናው ሀገራት የሚኖረውን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማጤን ፈጥኖ ምላሽ መስጠት ተገቢ ነው።
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘም ህዳር 22/2016