ኤች አይቪ ኤድስ ዛሬም ልዩ ትኩረትን ይሻል!

 የኤች አይቪ ኤድስ ቫይረስ ዛሬም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ስጋት ሆኖ ቀጥሏል። በሁለት አስርት ዓመታት ብቻ በዓለም የ40 ሚሊዮን ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው ኤች አይ ቪ ኤድስ፤ በኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከጫፍ ጫፍ አካልሎ 134 ሺህ ሰዎችን ህይወት አሳጥቷል።

ቫይረሱ በኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደተገኘ በይፋ ከተነገረ አራት አስርት ዓመታት ተቆጥረዋል። በእነዚህ ዓመታትም እስከ 2014 ብቻ ከ744 ሺህ በላይ ሕፃናትን ያለወላጅ ያስቀረው ይሄው በሽታ በኢትዮጵያ የቫይረሱ የስርጭት ፍጥነት ጣሪያ የነካው በ1988 ነበር።

የስርጭቱ ፍጥነት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለተወሰኑ ዓመታት የመቀነስ አዝማሚያ ማሳየቱን ቢነገርም፤ አሁን ላይ ከ610 ሺህ በላይ ዜጎች ከቫይረሱ ጋር እንደሚኖሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በቫይረሱ እየተያዙ ካሉት ዜጎች 70 መቶ የሚሆኑት ደግሞ አምራች ኃይሎች መሆናቸው ችግሩን እጅግ አሳሳቢ ያደርገዋል ።

በአዲስ መልክ ከሚያዙት የኅብረተሰብ ክፍሎች ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 30 ያሉ ዜጎች 70 በመቶውን መያዛቸው ወጣቱ ትውልድ ምን ያህል እንደተዘናጋ ማሳያ ነው። ስርጭቱን ይበልጥ አስከፊ ያደረገው ደግሞ ሴቶች ለዚሁ ችግር ይበልጥ ተጋላጭ መሆናቸው ነው። የቅርብ ጥናቶች የሚጠቁሙት ስርጭቱ 1 ነጥብ4 በመቶ በሴቶች፤ 0.8 በመቶ በወንዶች መሆኑ ነው።

ከ15 እስከ 19 ዓመት እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሴቶች 0.2 በመቶዎቹ ቫይረሱ በደማቸው ይገኛል። በተመሳሳይ የእድሜ ክልል የሚገኙ ወንዶች በአንፃሩ ተጋላጭነታቸው ዜሮ ነው። በወጣትነት እድሜም ቢሆን በሴቶች የሚጎላው የቫይረሱ ስርጭት ከ25 እስከ 29 የእድሜ ክልል ያሉ ወጣት ሴቶች ላይ ሲሆን፣ 2.9 በመቶዎቹ ቫይረሱ በደማቸው እንዳለ ሲረጋገጥ በተመሳሳይ እድሜ በወንዶች የታየው ስርጭት መጠን 0.9 በመቶ ነው።

በኢትዮጵያ ቫይረሱን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ባለፉት 30 እና 40 ዓመታት ብዙ ሥራዎች ተሰርተዋል። በተሠራው ሥራ ልክም ስርጭቱን መቀነስ ቢቻልም በአሁኑ ወቅት ቫይረሱ እንደጠፋ የሚያስበው በተለይም የወጣቱን መዘናጋት ለማመላከት ከተጠቀሰው ቁጥር የበለጠ ማሳያ አይኖርም። የቫይረሱ ስርጭት ወጣት እና አፍላ እድሜ ላይ የሚገኙ ዜጎች ላይ እየጨመረ የመጣበት ዋነኛ ምክንያትም መዘናጋት ነው።

የቫይረሱ ሥርጭት በሀገር ደረጃ ከአንድ በመቶ በታች መሆኑን የሚጠቁሙ መረጃዎች ቢኖሩም በአንዳንድ ክልሎች ስርጭቱ እያደገ መጥቷል። ስርጭቱ አምራች ዜጎችና ሴቶች ላይ መጨመሩ እንዲሁም ወደፊት እንደ ወረርሽኝ መልሶ እንዲያገረሽ ይበልጥ ዕድል መስጠቱ አስከፊው ጉዳይ ነው።

ስለቫይረሱ ሁለገብ እውቀት በበቂ ሁኔታ አለመዳረስ ለስርጭቱ ማገርሸት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። ለዚህም ኤች አይ ቪን በተመለከተ በቂ የሚባል ግንዛቤ እና እውቀት ያላቸው ሴቶች ከጠቅላላው ቁጥራቸው 19 በመቶ ብቻ መሆኑን ልብ ይላል። ልቅ የግብረ ስጋ ግንኙነት ፣ ኮንዶምን ሁልጊዜና በአግባቡ አለመጠቀም ብዙዎችን ለቫይረሱ ተጋላጭ አድርጓል። በሴተኛ አዳሪዎች የቫይረሱ ስርጭት 25 በመቶ የደረሰ ሲሆን፤ አሁንም ግብረስጋ ግንኙነት ከሚፈፅሙ ወንዶች መካከል 64 በመቶዎቹ ሴተኛ አዳሪዎችን እንደሚጎበኙ በጥናት የተደገፉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ኤች አይ ቪ በኢትዮጵያ መልሶ ሊያገረሽ ወደማይችልበት ደረጃ አልወረደም። ለዚህ ደግሞ ወጥ የኮንዶም ማሰራጨት አሰራር አለመዘርጋት እና የማሰራጫ ጣቢያዎች የክትትል ሥርዓት አለመኖር ችግሩን በበቂ መንገድ መከላከል እንዳይቻል አድርጓል።

በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የምርመራ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቁጥር አነስተኛ መሆንና የፀረ ኤች አይቪ መድኃኒት ከሚያስፈልጋቸው ለ13 በመቶዎቹ ብቻ መድረስ የቫይረሱን ተጠቂነት ችግር እንዳይቀረፍ ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው።

ዛሬ ላይ ተጋላጭነቱ እየጨመረ የሚገኘውን ወጣቱን ትውልድ ለማንቃት የግንዛቤ ማስጨበጫና የባህሪ ለውጥ ሥራዎች በተለያዩ ጊዜና በተለያዩ አካባቢዎች በልዩ ሁኔታ መስጠት የግድ የሚልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። ከዚህ ቀደም ማኅበረሰቡን በማንቃት ረገድ ከሚሰራው አንጻር አሁን ላይ በጣም ተቀዛቅዟል። በመሆኑም የመንግሥት ተቋማት፣ ኅብረተሰቡና የሚዲያ አካላት ከጤና ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ጋር በመሆን ከምርመራ ባሻገር የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎችን በስፋት ሊሰሩ ይገባል!

በተለየ ሁኔታ ለቫይረሱ ተጋላጭ ናቸው በተባሉት ዜጎች ማለትም ሴተኛ አዳሪዎች፣ አደንዛዥ ዕጽ ተጠቃሚዎችና የረጅም ርቀት ሹፌሮች ላይ የሚያተኩር ሥራ ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል። ቫይረሱ ያለባቸውን ሰዎች በምርመራ የመለየት፣ ተገቢውን ሕክምና እንዲያገኙ የማድረግና የቅድመ-መከላከል ሥራዎች ይበልጥ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።

ፍትሐዊ የኤች አይቪ ሕክምና አገልግሎትን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግም ከመቼውም ጊዜ በላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል። ጥቂት መዘናጋት እኤአ በ2030 ኤች አይ ቪ ኤድስ የጤናና የማህበራዊ ችግር እንዳይሆን የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት እንቅፋት ይሆናል። መዘናጋትም እንደ ሀገር ትልቅ ዋጋ ያስከፍላልና ዛሬም ትኩረት ለኤች አይቪ ኤድስ!

አዲስ ዘም ህዳር 22/2016

Recommended For You