ራስን መሆን

መቼም በዚህ ምድር ላይ ራስን እንደመሆን የሚያስደስት ነገር የለም። የብዙ ሰዎች ችግር ግን ራስን አለመሆን ነው። ራስን መሆን ቢያቅት እንኳን ራስን ለመሆን የሚደረግ ብርቱ ጥረት በብዙ ሰዎች ዘንድ አይታይም። ብዙዎችም ራስን ከመሆን ይልቅ ሌላውን መምሰል የሚፈልጉት በደፈናው ነው። ራስን ከመሆን ይልቅ ሌላውን ለመምሰል የሚደረገው ጥረትም ቢያንስ ያ ሰው እንዴት ራሱን መሆን እንደቻለና የራሱን ስብእና እንደገነባ ጥያቄ ውስጥ ባስገባ መልኩም አይደለም።

ስለዚህ አንተም ‹‹እኔስ መቼ ነው እንደራሴ የምሆነው? እንደልቤ የአዕምሮ ነፃነት ኖሮኝ ሕይወቴን እንደፈለኩ የምመራው እንዴት ነው? መቼ ነው ሰዎች ምን ይሉኝ ይሆን፣ ሰዎች ስለኔ ምን ያስባሉ የሚለውን የማቆመው?›› እያልክ ይሆናል። ያንተን መኪና የሚነዳው ማነው? ቤተሰብ ነው? ጓኛህ ነው? ወይስ በዙሪያህ ያለ ሰው ነው? በርግጥ መኪና ለሁለት አይነዳም። መኪና ማለት ሕይወትህ ነው። ሕይወትህን ለሁለት የምትመራው ከሆነ፣ በሌሎች አስተሳሰብ የምትመራው ከሆነ ወደ ገደል ነው የምትገባው።

ስለዚህ በአንተ ሕይወት የሚያዘው ማነው? ገንዘብህንና ጉልበትህን የሚያዝበት ማነው? አንተና ፈጣሪህ ካላዘዛችሁበት ሰዎች እንደጥላ ናቸው፤ ፀሐይ ሲገባ ይሰወራሉ። አንተ ስትደምቅና ሲኖርህ ነው የሚከተሉህ። ከሌለህ አጠገብህ ማንም የለም። ስለዚህ በራስህ ላይ አንተ ራስህ እዘዝበት። ራስህን ሁን። እንዴት? ካልክ ጥሩ ጥያቄ አንስተሃል። እነሆ መልሱ።

ሰዎች የሚወዱህ ጥንካሬ አስካለህ ድረስ ብቻ ነው። ምን ይሉሃል መሰለህ? እሱ እኮ ያመነበትን ነው የሚያደረርገው ይሉሃል። ለምን? ስትጠነክር፤ ራስህ ላይ ስታተኩር ሁሉም ያከብሩሃል። ባይወዱህ እንኳን በልባችው እነርሱም እንዳንተ መሆን ይፈልጋሉ። ለራስህ ቅድሚያ ስጥ። እሳቱ ላይ የምትጣደው እኮ አንተ ነህ። ምንም ቢሆን ብትታመም፣ ችግር ቢደርስብህና ብትከስር ቤተሰብና ጓኛህ አይዞህ ሊልህ ይችላል እንጂ ሕመምህን አብሮ አይታመምም። አብሮህ ገደል አይገባም። ግን አይዞህ ይልሃል። እንዴ! ሬሳ መቃብር ሲገባ አብሮ የተቀበረ ሰው አይታችሁ ታውቃላችሁ? ማንም አብሮ አልተቀበረም። ይሸኛል እንጂ አብሮ ማንም የሚቀበር ሰው የለም። የሞተ ሰው ከትንሽ ጊዜ በኋላ ይረሳል።

ስለዚህ ለራስህ መኖር መጀመር አለብህ። ለራስህ የምትሰጠውን ቦታ መቀየር አለብህ። ቅድሚያ ለራስህ ስጥ። የምታደርገውን ነገር ታምንበታለህ? ለሕይወትህ በጣም ወሳኝ ነው? አንተ ካመንክበት ሌሎች ምንስ ቢሉህ! አላማህን ካላወክ ግን ሰዎች ይነዱሃል። ወደፈለጉበት አቅጣጫ ይመሩሃል። በቃ ስላንተ አያስቡም። ዞር ብለው አያዩህም። አየህ! ሰዎች የሚወዱህ ጥንካሬህን አይተው ነው። ምን ዓይነት ጎበዝ ነው፣ ምን ዓይነት ደፋር ነው ሲሉ ይሰይሙሃል፣ ያከብሩሃል፣ ለራስህ የምትሰጠውን ቦታ ያዩና እነሱም መልሰው አንተን ያከብሩሃል። ያመንክበትን እንድታደርግ እድል ይሰጡሃል። አንተ ግን ለራስህ የምትሰጠው ቦታ መቀየር ይኖርበታል።

በጣም ታዋቂው ባለሀብት ቢል ጌትስ ‹‹ራስህን መናቅ የጀመርከው ከሰዎች ጋር መወዳደር ስትጀምር ነው›› ይላል። ለማን ብለህ ነው ራስህን የምታወዳድረው? ራስህን እንዳትንቀው። ካወዳደርከው ራስህን እየናከው ነው። አንተ እኮ ትልቅ ህልም ነው ያለህ፤ ትልቅ ፍላጎት ነው ያለህ። ጊዜያዊ ነገር እያየህ እኔ እኮ ከእሱ አንሻለሁ ወይም ከእሱ በልጫለሁ አትበል። ትልቅ ህልም ካለህ መወዳደር ላንተ አይገባም። ላንተ ማንንም ማነፃፀር የለብህም። ሕይወትህን ከራስህ አንፃር ቃኘው። ከራስህ አንፃር እየው። ትልቅ ህልም ካለህ ራስህን በፍፁም ከሰዎች ጋር አታነፃፅር።

ራስህን ማነፃፀር አቁም! ይህን ካደረክ በፍፁም ሰላም አይኖርህም። ከሰዎች ጋር ሕይወትን እያወዳደርክ ልትደሰት አትሞክር። ብትበልጣቸው ራሱ ገና መቼ መጥተው በለጡኝ ብለህ ስትሰጋ ነው የምትኖረው። ሲበልጡህ ደግሞ መቼ ነው የምበልጣቸው ብለህ ትጨነቃለህ። ውድድርና ንፅፅር ውስጥ ከገባህ ያ ሰው ምን ያስባል ምን ያደርጋል ብለህ የሰው ኑሮና ውድድር ውስጥ ነው የምትገባው። ለማን ብለህ ነው ታዲያ ራስህን የምታወዳድረው?

ሰዎችን ማስደሰት አቁም! ሁሉንም ማስደሰት አትችልም። መጀመሪያ ራስህን አስደስት። ከዚህ በተቃራኒ ግን ሁሉንም ሰዎችን አስደስታለሁ ብለህ ስትጋጋጥ እነሱ ብቻ ሳይሆኑ አንተ ራሱ መደሰት ታቆማለህ። ሀዘንተኛ ትሆናለህ። ባዶ እጅህን ትቀራለህ። መጀመሪያ አንተ በሕይወትህ ተደሰትበት።

ሁሉንም ስለማስደሰት አታስብ። ራስህን የማትሆነው እኮ ለዛ ነው። እንዲህ ባደርግ ሰዎች ያዝኑብኝ ይሆን? ይከፉ ይሆን? ስትል መቼም ደስተኛ አትሆንም። ሕይወት ትከብድሃለች። ለምን? አንተ ለሰዎች ደስታ መስዋትነት እየከፈልክ ነዋ! ነገር ግን አንድ ነገር አትርሳ። ለምትወዳቸው ስትል የምትከፍለው መስዋትነት ድንበር ያስፈልገዋል። ‹‹በቃ! ከዚህ በላይ ዋጋ አልከፍልም›› ማለት አለብህ። ‹‹ለራሴ ነው ዋጋ የምከፍለው፤ ለራሴ ነው የሆነ ነገር የማደርገው›› ብለህ ራስህን ማስቀደም አለብህ።

እንደውም ይህ የማደግ ምልክት ነው። ከፍ ስትል ዓይን ውስጥ ትገባለህ። ‹‹ሰዎች ምንድን ነው እሱ›› ይሉሃል። ይበሉህ! ችግር የለውም ከፍ ባልክ ቁጥር እነሱን ማስደሰት አይጠበቅብህም። ሊጠሉህም ይችላሉ። ይጥሉህ! ችግር የለውም። አንድ የዛፍ ችግኝ መሬት ላይ እያለ ማንም ሰው ዞር ብሎ አያየውም። ሲያድግ፣ ዋርካና ጥላ ሲሆን ግን ሁሉም ቀና ብሎ ያየዋል። የሚወድ ይወደዋል፤ የሚጠላው ይጠላዋል። መብታቸው ነው መውደድም መጥላትም። አንተ ግን ዝቅ ማለትን አትውደድ። ይወዱኛል ብለህ ዝቅ አትበል። አንተ ደስ ያለህንና የምታምንበትን አድርግ። ከዛ እነሱ ቢወዱህ፤ ቢጠሉህ የእነርሱ ምርጫ ነው።

ማጨድ የምትፈልገውን ብቻ ዝራ። ስንዴ ከዘራህ ስንዴ ነው የምታጭደው። ጤፍ ከዘራህ ጤፍ ታጭዳለህ። ምንም ካልዘራህ ግን አረም ታበቅላለህ። ሰዎች እንዲያከብሩህ ከፈለክ ራስህን አክብር። አንተ ራስህን ስታከብር አይተው እነሱም መልሰው ያከብሩሃል። በሕይወትህ እነዚህን ነገሮች ቀይር። ለራስህ የምትሰጠውን ቦታ መቀየር አለብህ። ጊዜና ገንዘብህን የምታጠፋበትን ሁኔታ መቀየር አለብህ። ውሎህን መቀየር አለብህ። ከነተረቱ ‹‹አንድ ዓይነት ቀለም ያላቸው ወፎች አብረው ይበራሉ›› ይባል አይደል።

‹‹ባለቤቱ የናቀውን አሞሌ ማንም አይገዛውም›› ይባላል። አዎ! የራስህን ሕይወት ማራከስና ዝቅ ማድረግ የለብህም። ‹‹ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ›› የሚባልም ተረት አለ። አዎ! ሰዎች ባንተ ሕይወት ጣልቃ የሚገቡት ለራስህ የምትሰጠውን ክብር አይተው ነው። ራስህን ከናክ ሌሎች ሰዎችም ይንቁሃል። ራስን ካከበርከው እነርሱም ያከብሩሃል። ለራስህ የምትሰጠው ቦታ ከፍ ማለት አለበት። ራስህን አክብረው። የዘራኸውን ነው የምታጭደው። ለራስህ ክብር ከዘራህ ክብር ታጭዳልህ።

ከሚንቁህ፣ ከሚተቹህና እንደማትችል እየደጋገሙ ከሚነግሩህ ሰዎች ጋር ለምን ትውላለህ? ለዛ እኮ ነው እየደጋገምክ እንዲህ ባደርግ ምን ይሉኛል? ያዝኑብኝ ይሆን? ይስቁብኝ ይሆን? ይቀልዱብኝ ይሆን? የምትለው ውሎህ ከማይጠቅሙ ሰዎች ጋር ስለሆነ ነው። የበታችነት እንዲሰማህ ከሚያደርጉህ ሰዎች ጋር አትዋል። ማጨድ የምትፈልገውን ብቻ ዝራ። መከበር ከፈለክ ራስህን ብቻ አክብር።

ነገሮችን አክብደህ የምታያቸው በጣም ከባዱ ስላልገጠመህ ነው። የዛሬ ሳምንት ትሞታለህ ብትባል አሁን የሚያስጨንቅህ የሰዎች ምን ይላሉ፣ ምን ያስባሉ የሚለው የሚያሳስብህ ይመስልሃል? የዛሬ ሳምንት እንደምትሞት ባሰብክ ቁጥር ‹‹እንዴት ልደሰት፣ እንዴት አድርጌ ወደፈጣሪዬ ልቅረብ?›› ነው የምትለው። አየህ! ከትልቁ ችግር አንፃር ይህ በጣም ቀላል ነው። ሰዎች ስላንተ የሚያስቡት ነገር አንተን ሊያሳስብህ አይገባም።

መሳሳትን አትፍራ። ምንም ካልሞከርክ፤ ቁጭ ካልክ የማሳካት እድልህ ዜሮ ነው። ከሞከርክ ግን የሆነ እድል ይኖርሃል። የሆነ እጣ ፈንታ ይኖርሃል። መጥፎውን አስብና ተነስ። ‹‹ደሃ ሆኜ ከምቀር ቢዝነሱን ሞክሬ ብከስር አይሻልም? እንደዚህ ስሜቴ እየተጎዳና ውስጤ እያዘነ ከምቀጥል የልቤን ተናግሬ እፎይ ብል አይሻልም? እንደዚህ ሆኜ እስከመቼ እቀጥላለሁ?›› ብለህ ማሰብ መጀመር አለብህ። ሕይወትህ ውስጥ ጥያቄ ማንሳት አለብህ። እስከመቼ ሰዎች እንደፈለጉ ያሽከረክሩኛል? እስከመቼ ይጠቀሙብኛል? እስከመቼ ገንዘቤን ለእነሱ እየሰጠሁ እነሱን ብቻ አስደስታለሁ? ….. እስከመቼ?? ማለት አለብህ።

ለአንተ አርአያ የሚሆንህ፣ የምታከብረው፣ የሆነ ነገር ከሕይወቱ የምትኮርጅለት፣ የምታደንቀው፣ አንተ የምትፈለገውን ነገር ቀድሞ ያሳካና የምትማርበት ሰው ያስፈልግሃል። ምክንያቱም እርግጠኛ ሁን ያ ሰው ራሱን ነበር። ለሰዎች ደስታ ሳይሆን ለራሱ ደስታ ሲል ሲሮጥ ነበር። እርሱን ባየኸውና ስለርሱ በሰማህ ቁጥር አንተም ለራስህ መሆን እንዳለብህ ይሰማሃል። ከሰዎች ኮርጅ። ከሰዎች የሆነ የሚጠቅምህን ነገር ስረቅ። ለራስህ አድርገው። እመንበት። ከዛ ራስህን ሁን።

የሰዎችን አድናቆት እንደትልቅ መስፈርት መውሰድ ከጀመርክ ባንተ ላይ ሙሉ ሥልጣን እየሰጠሃቸው ነው። ዛሬ የሰጡህ አድናቆት በደስታ ሰማይ ድረስ ሊያንሳፍፍህ ይችላል። ነገ ግን ከባድ ትችት ሊያጋጥምህና ስድባቸው ሞራልህን መሬት ሊፈጠፍጠው ይችላል። ራስህን እንድትጠላ ሊያደርግ ይችላል። ስለዚህ ሰዎች አደነቁህ አላደነቁህ ቦታ አትስጠው። የእነሱ አድናቆት የእነርሱ ምልከታ እንጂ አንተ ያለህበትን ትክክለኛ ቦታ አያሳይም። አስተያየቶችን ግን ራስህን ለማሻሻል ልትጠቀምባቸው ትችላለህ። ነገር ግን አምነህ አትደገፍባቸውም።

አንተ ድንቅ እንደሆንክ መጀመሪያ ለራስህ ንገረው። ከዛ ማመን ጀምር። በሂደት ድርጊቶችህ ይቀየራሉ። ማንነትህ የድንቅ ሰዎች ብቻ ይሆናል። አሰታውስ! የትኛውም ስኬታማ ሰው በሰዎች ከመደነቁ በፊት ራሱን ያደንቅ ነበር። አንተም ድንቅ እንደሆንክ ሌሎች እስኪነግሩህ ድረስ አትጠብቅ፤ ራስህን ድንቅ ነኝ በማለት ጀምር። ምክንያቱም ድንቅ ስለሆንክ።

ሰዎች ባንተ ከማመናቸው በፊት አንተ በራስህ ማመን አለብህ። ያኔ ነው ሰዎች የሚደገፉህ። ጠንካራ ካልሆንክ ማንም አይፈልግህም። ዓላማ ከሌለህ፣ ማን እንደሆንክ ለማሳየት እንደምትፍጨረጨር ካላሳየህ ሁሉም ይንቅሃል። እርሱ ምን ቁም ነገር ያውቃል? ስለሕይወት ምን የተሻለ አረዳድ አለው? ሲቀልድ አይደል እንዴ የሚውለው፤ ትባላለህ። ስለዚህ ለራስህ የምትሰጠው ቦታ መቀየር አለበት። ሰዎች የሚሉህን እርሳው። ራስህን ብቻ አድምጥ። ያኔ ሰዎች ያደምጡሃል። አንተን መከተል ይጀምራሉ። ‹‹እርሱ እኮ ዓላማና ልበ ሙሉነት አለው፤ ያመነበትን ያደርጋል›› ይሉሃል።

ሕይወት አጭር ናት። ያለችህ እድሜም እንደዛው። ሰዎች ታዲያ ይህችን አጭር እድሜ እንደፈለጉ ሲነዷት ዝም ብለህ ልታያቸው ነው የፈለከው? አንድ ዓይን ያለው በአፈር አይጫወትም። አንተ እኮ አንድ ሕይወት ነው ያለህ። አንተ ከሌለህ እኮ ምንም የለም። ለማን ብለህ ነው ለዚች አጭር እድሜ ለሰዎች ደስታ ብለህ የምትሮጠው? ሰዎችን ላለማስከፋት ብለህ የማታምንበትን ነገር የምታደርገው?

ስለዚህ የምትፈልገውን ዓይነት ሰው ሁን። የሚያስደስትህን ኑር። ለማንም ስትል ያላመንክበትን ነገር አታድርግ። ሕይወትህ የሚቀየረው ራስህን ከሆንክ ብቻ ነው። ሕይወትህ እንዲቀየር ታዲያ መጀመሪያ አንተ መቀየር አለብህ። በዚህ ዓለም የሚገጥሙህ ማንኛውም ነገሮች የአንተና የአመለካከትህ ነፀብራቅ ናቸው። ደስ የሚለው ግን ያለንበት ክፍለ ዘመን አመለካከታችንን በመቀየራችን ብቻ ሕይወታችንን እንድንቀይር ያስችለናልና አንተም አመለካከትህን ለመቀየር ተዘጋጅ፤ ከዛም ራስህን ሁን፤ ያኔ ሕይወትህ ይቀየራል።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘም ህዳር 22/2016

Recommended For You