ተመድ በሶማሊያ ላይ የጣለውን ለ30 ዓመታት የዘለቀ ማዕቀብ ሊያነሳ ነው

የተመድ የጸጥታው ም/ቤት በሶማሊያ ላይ የጣለውን ለ30 ዓመታት የዘለቀውን ማዕቀብ ለማንሳት ድምጽ ሊሰጥ ነው።

የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ለሶማሊያ መንግሥት እና የጸጥታ ኃይሎቹ የጦር መሳሪያ እንዳይሰጥ የሚከለክለውን ማዕቀብ ለማንሳት ድምጽ እንደሚሰጥ ሮይተርስ ዘግቧል። የጸጥታው ም/ቤት በፈረንጆቹ 1992 በሶሚሊያ ላይ የጦር መሳሪያ ማዕቀብ የጣለው፣ የሀገሪቱን መሪ መሀመድ ሲያድ ባሬን ያስወገዱት ተቀናቃኝ ታጣቂዎች መሳሪያ እንዳይደርሳቸው ለማድረግ ነበር።

 15 አባላት ያሉት የጸጥታው ምክር ቤት በእንግሊዝ የቀረቡለትን ሁለት የውሳኔ ሃሳቦች ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል። በሶማሊያ ላይ ተጥሎ የነበረው ሁሉም ዓይነት የጦር መሳሪያ ማዕቀብ እንዲነሳ እና በአልሸባብ ላይ የጦር መሳሪያ ማዕቀብ እንዲጣል የሚሉ የውሳኔ ሃሳቦች ናቸው በእንግሊዝ የቀረቡት።

በሶማሊያ መንግሥት ላይ ምንም ዓይነት የጦር መሳሪያ ማዕቀብ መኖር እንደሌለበት በአንደኛው ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ላይ ተጠቅሷል። በሀገሪቱ ደህንነቱ የተጠበቀ የመሳሪያ ማከማቻ ቦታ ቁጥር ላይ ስጋቱን የገለጸው የውሳኔ ሃሳቡ ግንባታ እንዲደረግ እና ሌሎች ሀገራት ርዳታ እንዲያደርጉ ጠይቋል።

ሶማሊያን በእስላማዊ የሼሪአ ሕግ ለማስተዳደር የሚፈልገው አልሸባብ ከፈረንጆቹ 2006 ጀምሮ ደምአፋሳሽ ግጭት ውስጥ ከቷታል። የሶማሊያ መንግሥት ማዕቀቡ እንዲነሳለት ለረጅም ጊዜ ሲጠይቅ ቆይቷል።

የጸጥታው ም/ቤትም ከ2013 ጀምሮ ማዕቀቡን በከፊል ማንሳት ጀምሯል። የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼህ መሀመድ ባለፈው ሳምንት እንደተናገሩት ሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ከሚወጣበት በፊት አልሸባብን ለማጥፋት አንድ ዓመት ብቻ ነው የቀራት ሲሉ ተናግረዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘም ህዳር 22/2016

Recommended For You