‹‹በሰላም ስለ ሰላም እንመካከር!››  የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች ድምጽ፤

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የአባል ቤተ እምነት ተወካዮች ኅዳር 19 እና 20፤ 2016 ዓ.ም ለሁለት ቀናት በአዳማ ሲመክሩ የሰነበቱት ወቅታዊውን የሀገራችንን የሰላም ህመም መንስኤና መፍትሔው ምን እንደሆነ በመፈተሽ ነበር። በዋናነትም ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል አሳታፊ እንደሚሆን ተስፋ የተጣለበት ብሔራዊ የመመካከሪያው ውጥን በስፋት ተዘርግቶ የምንመኝለትንና የምንጓጓለትን “ጣፋጭ ፍሬ” በማዝመር ለብሔራዊ እፎይታችን የማያዳግም ፈወስ እንዲገኝ የየሃይማኖቱ ተቋማትና ቤተሰቦች ምን ድርሻና ሚና እንደሚጫወቱም በግልጽነት የተመከረበት ውሎ ነበር።

በሁለቱ ቀናት ቆይታ “በሀገራዊ ምክክር ከሃይማኖት ተቋማት ምን ይጠበቃል?” በሚል ርዕሰ ጉዳይ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት ዶ/ር ዮናስ አዳዬ የመጀመሪያውን የመወያያ ሃሳብ ካቀረቡ በኋላ በተከታታይም ለሀገራዊ የሰላም ጽናትና በምክክሩ ሂደት ከሃይማኖት ተቋማትና ከምእመናኑ ምን እንደሚጠበቅ ከሃይማኖታዊ መጻሕፍታቸው፣ ከግል ተሞክሯቸውና ከንባብ ትሩፋታቸው ካካበቱት ሰፊ እውቀት እየቀዱ ያስተማሩት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጠበብት ዘውገ አስራት እና ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት የፈትዋ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ሸኽ ሙሐመድዘይ ዛህረዲን ነበሩ።

ይህ አምደኛም “የሃይማኖት ቤተሰቦች የሰላማዊ የሚዲያ አጠቃቀምና የኮሚዩኒኬሽን ልምምድና ባህላቸውን ከፍ በማድረግ ለሀገራዊ ምክክሩ ላቅ ያለ ሚናቸውን ሊወጡ በሚያስችላቸው” ሰፋፊ ጽንሰ ሃሳቦች፣ ሀገራዊና ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ላይ አጽንኦት በመስጠት በሦስተኛነት የጥናት ጽሑፉን አቅርቧል።

ጉባኤው ወትሮ ሲደረግ እንደኖረው በጸሎት ተከፍቶ የመንፈሳዊ ድባብ በሰፈነበት አኳኋን ተጀምሮ ብቻ የተደመደመ አልነበረም። “ስለምን ሀገራዊ ሰላማችን ሊታወክ ቻለ? እውክታውስ ስለምን ፋታ ነስቶን መፍትሔው እስከ መወሳሰብ ደረሰ? ከጅማሬውስ ቢሆን ለሰላሙ መደፍረስ ዋነኛ ሰበበ ምክንያቱ ማንና ምን ነበር?”

“ስለ ሰላም የሚሰብኩና የሚያስተምሩ የሃይማኖት ቤተሰቦችና የየቤተ እምነቱ መሪዎችና ምእመናንስ በዚህ ጥፋት ውስጥ ምን ድርሻ ነበራቸው? ውስብስብ ባህርይ ያለው የሰላም ርሃባችን ጠልቆ ሥር እስኪሰድ ድረስስ የሰላም ሰባኪያኑ ተቋማት ምን ሲሰሩ ነበር? ችግሮቹ ከተከሰቱ በኋላስ “የደጀ ሰላሞቹ” ባለቤቶች ምን ሙከራ አድርገዋል? ምንስ ባለማድረጋቸው ሊወቀሱ ይገባል? ወዘተ.” በጉባኤተኛው የተጠየቁትና በጎርፍ ሊመሰሉ የሚችሉ አስተያየቶችና ሃሳቦች ነበሩ።

የጥያቄዎቹ ዓይነትም ሆነ የጠያቂዎቹ ቋንቋና ስሜት ከአሁን ቀደም ከነበረውና እንደ ባህል ተወስዶ ከዳበረው “የትህትናና የመሽኮርመም ልምምድ” በእጅጉ የተለየና ጠጠር ያለ ነበር። “ታሟል እየተባለ የሚወቀሰው አንካሳው ፖለቲካ ለጊዜው እዚያው በህመም አልጋው ላይ እያቀሰተ እንደ ቢጤቱ ይሁን ‹እኛ› ስመ ፈጣሪ ከአፋችን የማይለየው የየሃይማኖቱ ቤተሰቦች ምን እየሠራን ቆየን? ኢትዮጵያ ጨንቋት ስትቃትት በጸሎታችን ‹ይማርሽ!› እያልን ከመማለድ ውጭ እንደ ሀገር ዜጎች ምን መፍትሔ አመንጭተን ከህመሟ ለመፈወስ ግንባር ቀደም ነበርን? በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የሰላም መልእክተኛነታችንን ዋነኛ ተልእኳ ዘንግተን እንደሆነስ?”

“በዚህ ጉባኤ ላይ ስለ ሰላማችን ስብራት ተሰባስበን የምንወያየው ነገሮችን ሳንሸፋፍን ራሳችንን በፈጣሪ ፊት አራቁተን ስለሆነ ብርታታችንን በማወደስ ‹እንዲህ ነበርን! ነንም› በማለት ብቻ ሊሆን አይገባም። “ተሞክሯችን እንዲህ ነበር፣ የቅዱስ መጻሕፍቱ ትምህርትም እንዲህና እንዲያ ስለሚል…” ማለቱ መልካም ቢሆንም ከዚህ እልፍ ብለን ግን ራሳችንና ቤተ እምነቶቻችን ባልተወጡት ጉዳዮች ላይ ጨክነን ልንመክርበትና በጎ በጎውን ልንወስን ይገባል። ”

“እውነት እውነቱን በመነጋገርና ችግሮቻችንን በማፍረጥ የመፍትሔው ቀዳሚ ምክንያት እንድንሆንም እንደ ሃይማኖታችን ቀኖና በንስሃ ወደ ፈጣሪ በመማለድ፣ እንደ ሀገር ልጅነታችንም በግላችን በመጸጸት ራሳችንን አጽደተን ለተግባር እርምጃ መጨከንና መረባረብ ይኖርብናል። ” የሚሉት ሃሳቦች በየትምህርቶቹና በውይይቶቹ ክፍለ ጊዜያት ጎልተውና ከፍ ብለው የተደመጡ ‹አስገምጋሚ› ቁጭት የወለዳቸው ድምጾች ነበሩ።

“ራሳችንን ብንመረምር ባልተፈረደብን” ምን ያህሉ የኢትዮጵያ ዜጋ በአንድም ይሁን በሌላ ጎራ ከአንድ ቤተ እምነት ተጠግቶ “ምእመን” የሚሰኝ ቅጽል እንዳተረፈ ለጊዜው የቅርብ ጊዜ “የሕዝብ ቆጠራ” ውጤት እጃችን ላይ ስለሌለ ይህን ያህል ለማለት ያዳግታል። አዘውትረው የሚጠቀሱ ግምታዊ አሀዞችን እንደ መነሻ እንውሰድ ከተባለ ግን ምናልባትም ከአጠቃላይ የሀገሪቱ ዜጎች ወደ 98% የሚጠጋው ሕዝባችን በየራሱ ዐውደ ምህረት ሥር ተጠልሎ “የእከሌ ቤተ እምነት ምእመን” እንደሚባል ደፍረን ለመናገር አፋችንን አይዘንም።

የሁሉም የሀገራችን ዋና ዋና ሃይማኖቶች ማዕከላዊ ትምህርት ከሰላም ጋር የተያያዘ መሆኑ ተደጋግሞ ተተርኳል። ክርስቶስ በምድር ላይ የኖረው ሰላምን ለሰው ልጆች እየሰበከ መሆኑ በየምስባኮቻችን ሳይሰበክ ውሎ ማደሩ ያጠራጥራል። የኢስላም መሠረታዊ አስተምህሮም እንዲሁ በሰላም ላይ የተመሠረተ ነው። የአይሁድ እምነትም ቢሆን የሚያስተምረው ያህዌ የሰላም ምንጭና አምላክ መሆኑን ነው።

እውነታውም ሆነ ሃይማኖታዊ ትምህርቶች ዋና ትኩረታቸው ይህን መሰሉ የሰላም ጉዳይ ከሆነና አብዛኛው ሕዝብ የሃይማኖቶቹ ቤተሰብ ነው ብለን የምንናገር ከሆነ ስለምን የሰላም ርሃብተኛ ልንሆን ቻልን? የችግሩ መንስኤስ ምንድን ነው? ችግር ፈጣሪውስ ማነው? ነባሩ ብሂላችን እንደሚያስተምረን የኢትዮጵያ ችግር፡- “ሀዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽ አልወጣ፤ የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ” ይሉት ብጤ ሊሆን የቻለውስ ስለምንድን ነው?

ጦር ይዞ የሚፋለመውም ሆነ ጋሻ ወድሮ የሚመክተው ያው ከኢትዮጵያ ማህጸን ወጥቶ አንድም “የክርስትናን ስመ ጥምቀት የተቀዳጀ”፣ አንድም ሙስሊም ተብሎ “የተለየ”፣ አንድም አይሁድ ተብሎ “የተባረከ”፣ ወይንም በባህላዊ እምነት “የታቀፈ” ዜጋ እንጂ ባዕድ ወራሪ ሳይመጣብን ስለምን እርስ በእርስ ቃታ እየሳብን እንድንተላለቅ በራሳችን ፈረድን? እንዲህ ዓይነቱ መራራ ጥያቄ መጠየቅ ያለበት በገደምዳሜ ጎንዮሽ ሳይሆን ጨከን ብለንና ደፍረን ራሳችንን በራሳችን ልንሞግትበት የሚገባ መራራ ሐቅ እንደሆነ በተጠቀሰው ጉባኤ ላይ በስፋት ተንጸባርቋል።

በጋራ ከሚጠቀሱት የየሃይማኖቶቹ ብርቱ አስተምህሮች መካከል አንዱ “እውነት ሳትድበሰበስ በፍቅርና በጥበብ መገለጥ ይገባታል” የሚለው አገላለጽ በየቅዱሳት መጻሕፍቱ ውስጥ የተሰመረበት በጉልህ “ቀለማት” ነው። እናስ “አጥፊን ገስጾ፤ ተጎጂን አጽናንቶ ወደ ሰላም ለማምጣት ቤተ እምነቶች ስለምን ጉልበታቸው ላላ? በምን ምክንያትስ አቅማቸው ዛለ? ይህ ጉዳይ በጉባኤተኞቹ ውይይት ላይ በተለያየ መልኩ ተደጋግሞ የተንሸራሸረ መሪ ሃሳብ ነበር።

ሌላውና በቁጭት ሲሰነዘር የነበረው “የማሕበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምን” የተመለከተው ሃሳብ ነበር። በየማሕበራዊ ሚዲያዎች ላይ ጦርነት እየጫሩ ሕዝብን ለቁጣና ለበቀል የሚያነሳሱትን “አፋላሚ ፊት አውራሪዎች” ሕግ አውጥቻለሁ ያለው መንግሥታዊ ተቋም ስለምን ዝምታን መርጦ “በተው ቻለ ሆዴ” መርህ ሊረጋጋ ቻለ? የሚለው አስተያየት የቀረበው “የሚመለከተው” አካል ያስብበት በሚል ምክረ ሃሳብ ብቻ ሳይሆን “የሚመለከተው አካል ራሱ ግዴታውን ባለመወጣቱ ሊጠየቅ ይገባል” የሚል ውሳኔ በማሳለፍ ጭምር ነበር።

የብሔራዊ ምክክር አደረጃጀቱ ላይ የጎደለ ነገር እንደነበርም በግልጽ ተመክሮበታል። በጉባዔው ላይ መልእክት ላስተላለፉት ኮሚሽነርም በግልጽ ተነግሯቸዋል። ቀደም ሲል እንደተገለጸው ወደ መቶ ፐርሰንት የሚጠጋ ሕዝቧ በአንድም ይሁን በሌላ በየሃይማኖቱ ጥላ ሥር የተሰባሰበ ነው በሚባልባት ሀገር ኮሚሽነሮች ሲሾሙና ቢሮው ሲደራጅ “ሕገ መንግስቱን ከጨበጡ ብቻ ይበቃል” ከማለት ይልቅ ቅዱሳት መጻሕፍትን በልባቸውና በእጃቸው የያዙ መካሪና አስተማሪ አባቶች፣ በጸሎትና በዱዓ ደጋፊ ተወካይ መሪዎች ስለምን እንዲኖሩ አልታሰበም? የሚለውም ጥያቄ ተነስቶ ውይይት መደረጉ አልቀረም።

በተለይም የእርቅና የሰላም ጉዳይ ሲታወስ “የጥንቱን ዘመን አስታውስ፤ የብዙ ትውልድንም ዓመታት አስተውል፤ አባትህን ጠይቅ ያስታውቅህማል፤ ሽማግሌዎችህንም ጠይቅ ይነግሩህማል” (ዘዳግም 32፡7) የሚለው የቅዱስ መጽሐፍ እውነታ በምክክር ኮሚሽኑ አደረጃጀት ላይ ቢታወስ ኖሮ መልካም አልነበረምን? ይህስ ባለመደረጉ አልተጎዳንምን? ጥያቄዎቹ የተቋጩት ሌላ ጥያቄ አስከትለው ስለነበር ከዚህ በዘለለ ብዙ ለማለት ያዳግታል።

ብዙ ሃሳቦች የተንሸራሸሩበት የሃይማኖት ቤተሰቦቹ ጉባኤ የተጠናቀቀው በአንድ የጋራ ሃሳብ ላይ ተደርሶ ነበር። ያለፈው አልፏል፤ የሆነውም ሆኗል። የትናንቱ ጉዳትና ዘርፈ ብዙ ስብራት ለምን ተፈጸመ? ብሎ መቆዘሙ ብቻ ውጤት የለውም። በዋናነት ሊታሰብ የሚገባው ጉዳይ የዛሬው ህመምተኛ የሰላም ስብራት እንዲፈወስ የሃይማኖት ቤተሰቦች ምን ሚና ሊጫወቱ ይገባል? ነገስ የዛሬው አበሳ ጎልብቶና የከፋ አሳር ወልዶና ተዋልዶ ዝቀን የማንጨርሰው፣ ገፍተን የማናስወግደው መከራ እያሳጨደን እንዳይሰነብት ምን እርምጃ ሊወሰድ ይገባል? የሚሉት ጥያቄዎች ብዙ ተመክሮባቸዋል ተዝክሮባቸዋልም።

የሃይማኖት መሪዎች፣ መምህራንና የምእመናን እረኞች የሀገሪቱ ሰላም ተፈውሶ ሕዝቡ በሰላም ውሎ እንዲያድር በጸሎትም ሆነ በዱዓ፣ በጾምም ሆነ በእግዚኦታ ሕዝባቸውን እያበረታቱና አብረውም ፈጣሪን እየተማጸኑ ከሚፈጽሙት መንፈሳዊ ኃላፊነትና ተጋድሎ ጎን ለጎን አጥፊዎችን ለመገሰጽ፣ እምቢተኞችን ለማለዘብና ግትር ሃሳብ ያላቸውን ለማብረድ ሥልጣነ ክህነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ ጉባኤተኞቹ በአሜንታ ተስማምተዋል። ይህንኑ የአደራ መልእክትም ወክለው ለላኳቸው መሪዎቻቸው ለማድረስ በይሁንታ ፈቃደኝነታቸውን አረጋግጠዋል።

በዚህ አምደኛ ትኩረት የተሰጠበት የሚዲያ አጠቃቀም አቅርቦትም በተዋያዮቹ በስፋት ተመክሮበታል። ቢያንስ እያንዳንዱ ቤተ እምነት ለራሱ ምእመን በተለይም በሶሻል ሚዲያ አጠቃቀም ላይ ገንቢ እንጂ አፍራሽና አደፍራሽ መልእክቶችን ከማስተላለፍ እንዲታቀቡ በየመንፈሳዊ ጉባዔዎቻቸው ላይ በዘርፉ ባለሙያዎች ትምህርትና ምክር መሰጠቱ አግባብ እንደሆነ ተማምነውበታል።

በመጨረሻም፡- “በሰላም ስለ ሰላም እንመካከር!” በሚለው የማጠቃለያ ሃሳብ ላይ ሁሉም የጉባኤው ተሳታፊያን ስምምነታቸውን አረጋግጠው እንደተለመደው ለሀገራቸው ሰላም፤ ለሕዝባቸውም በጎ ፈቃድ ተመኝተው ስብሰባቸውን አጠናቀዋል።

 (በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)

gechoseni@gmail.com

አዲስ ዘም ህዳር 22/2016

Recommended For You