ቀነኒሳ በቀለ በቫሌንሲያ ማራቶን ፈጣን ሰዓት ለማስመዝገብ ይሮጣል

በዓለም አትሌቲክስ የፕላቲኒየም ደረጃ ከተሰጣቸው የማራቶን ውድድሮች መካከል የፈረንጆቹ ዓመት የመጨረሻ ውድድር የሆነው የቫሌንሲያ ማራቶን ከነገ በስቲያ ይካሄዳል። በስፔን ከሚካሄዱ የጎዳና ሩጫዎች በግዝፈቱ ቀዳሚ በሆነው በዚህ ውድድር ላይ ታዋቂ አትሌቶችን ጨምሮ 30ሺ ሰዎች ይሳተፋሉ። በሁለቱም ጾታዎች በውድድሩ ተሳታፊ መሆናቸው ያረጋገጡ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶችም ፉክክሩን ይበልጥ አጓጊ አድርገውታል።

በተለይ በወንዶች መካከል በሚካሄደው ውድድር በማራቶን ዓለምን ካስደመሙ አትሌቶች ሶስተኛውን ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበው ጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በቀዳሚነት ትኩረት አግኝቷል። በረጅም ርቀት የመም፣ በሀገር አቋራጭ እንዲሁም በማራቶን ውድድሮች ተደራራቢ ስኬቶችን ማጣጣም የቻለው አንጋፋው አትሌት የሰው ልጅ 42 ኪሎ ሜትርን ከ2ሰዓት በታች መሮጥ ይችላል የሚለውን ሳይንሳዊ እሳቤ እውን ያደርጋሉ ተብሎ ተስፋ ከተደረገባቸው አትሌት አንዱ ነው። የኦሊምፒክና የዓለም ቻምፒዮና የበርካታ ድሎች ባለቤት የሆነው ቀነኒሳ በተደጋጋሚ በሚገጥመው ጉዳት ምክንያት ሙሉ ብቃቱን ማሳየት ባይችልም ይህ ውድድር ግን አዲስ ነገር ሊያሳይበት እንደሚችል ብዙዎች ገምተዋል።

በዓለም አትሌቲክስ ታሪክ ከታዩ እጅግ ድንቅ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች መካከል ቀዳሚ የሆነው ቀነኒሳ፤ በሁለት ኦሊምፒኮች እንዲሁም በአራት የዓለም ቻምፒዮና መድረኮች በ5ሺ እና 10ሺ ሜትር ርቀቶች 8 የወርቅ፣ 1የብር እና 1 የነሃስ በጥቅሉ 10 ሜዳሊያዎችን ማጥለቅ ችሏል። በሀገር አቋራጭ ውድድርም የእሱን ያህል በድል የተንቆጠቆጠ አትሌት የለም። ወደ ማራቶን ከተሸጋገረም በኋላ በለንደን እና በርሊን ማራቶኖች ተደጋጋሚ ፉክክር በማድረግ በርቀቱ ክብረወሰኑን ለማሻሻል ከጫፍ ደርሶ እንደነበር አይዘነጋም። እአአ በ2019 የበርሊን ማራቶን ያስመዘገበው 2:01:41 የሆነ ሰዓት በወቅቱ የዓለም ክብረወሰን ባለቤት ከነበረው ኬንያዊው አትሌት ኢሉድ ኪፕቾጌ በ2 ሰከንዶች ብቻ የዘገየ ነበር። በቅርቡ የርቀቱ አዲስ ፈጣን ሰዓት መመዝገቡን ተከትሎም የቀነኒሳ ሰዓት ሶስተኛው ሊሆን ችሏል።

በመሆኑም ከቆይታ በኋላ በድጋሚ በሚታይበት በእሁዱ የቫሌንሲያ ማራቶን ፈጣን ሰዓት ወይም ለታሪስ 2024 ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን መወከል የሚያስችለውን ውጤት ለማስመዝገብ ተዘጋጅቷል። ቀነኒሳ ለረጅም ዓመት ሲሰለጥን ከቆየበት የማኔጅመንት ቡድን ተለይቶ የቻይናውን ‹‹ANTA›› ከተቀላቀለ የመጀመሪያው ውድድሩ ነው። በመሆኑም በማሸነፍ ታሪኩ የሚታወቀው አትሌቱ በውድድሩ ከባድ ፉክክር ቢገጥመውም ውጤታማነቱን ያስቀጥላል የሚለው የስፖርት ቤተሰቡ ግምት ነው። አትሌቱም በይፋዊ ማህበራዊ ድረ ገጹ ‹‹ከጉዳት በኋላ ብቃቴን ለመፈተን የምሳተፍበት ውድድር እንደመሆኑ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ እንደመሆኔ ውጤታማ ለመሆን ተዘጋጅቻለሁ›› በማለት አስተያየቱን አስፍሯል።

ቀነኒሳ በውድድሩ ላይ ጠንካራ ፉክክር ይገጥመዋል ተብሎ ይጠበቃል። ለዚህም በርካታ የሀገሩ ልጆች እና የጎረቤት ሀገራት ጠንካራ ተቀናቃኝ አትሌቶች በውድድሩ መሳተፋቸው አንዱ ምክንያት ነው። በቡዳፔስት የዓለም ቻምፒዮና በማራቶን የነሃስ ሜዳሊያ ያስመዘገበው አትሌት ልዑል ገብረሥላሴ እና የዘንድሮው ቶኪዮ ማራቶን አሸናፊው ጫሉ ዴሶም ለአሸናፊነት ከሚጠበቁ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል ይገኛሉ። የታንዛኒያ እና ኬንያ አትሌቶችን ጨምሮም ከ2ሰዓት ከ5ደቂቃ በታች ፈጣን ሰዓት ያላቸውም ናቸው። በሌላ በኩል በ10ሺ ሜትር ወንዶች ከቀነኒሳ ቀጥሎ አስደናቂ ጉዞ በማድረግ ላይ የሚገኘው የ5ሺ እና 10ሺ ሜትር የዓለም ክብረወሰን ባለቤቱ ኡጋንዳዊ አትሌት ጆሽዋ ቺፕቴጌ በቫሌንሲያ ማራቶንን ለመጀመሪያ ጊዜ ይሮጣል። በዶሃ፣ ዩጂን እና ቡዳፔስት የዓለም ቻምፒዮናዎች የበላይነትን ያስመዘገበው ጠንካራው አትሌት ቺፕቴጊ በጎዳና ላይ ሩጫም ስኬታማ የመሆን ተስፋውን የሚለካበት ውድድር እንደሚሆን ይጠበቃል።

እንደወንዶቹ ሁሉ በሴቶች ውድድርም ኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች የማሸነፍ ግምት ያገኙ ሲሆን፤ በተለይም አትሌት አልማዝ አያና የአሸናፊነት ቅድመ ግምቱን ልትቀዳጅ ችላለች። በሪዮ ኦሊምፒክ የ10ሺ ሜትር አስደማሚ ድሏ የምትታወሰው አልማዝ እአአ ከ2022 ወዲህ ማራቶንን ተቀላቅላለች። በአምስተርዳም ማራቶን አሸናፊ በመሆን ስኬትን ያጣጣመችው አልማዝ 2:17:20 የሆነ ፈጣን ሰዓት ባለቤትም ናት። ሌላኛዋ ባለፈጣን ሰዓት ኢትዮጵያዊት አትሌት ፀሐይ ገመቹም ለአሸናፊነት ፉክክር የምታደርግ አትሌት ናት። በቡዳፔስቱ የዓለም ቻምፒዮና በአስደናቂ የቡድን ሥራ የተመሰገነችው አትሌቷ የቶኪዮ ማራቶን ተሳትፎዋን በሁለተኛነት ነበር ያጠናቀቀችው። በወቅቱ የገባችበት 2:16:56 የሆነ ሰዓትም የግሏ ፈጣን ሆኖ ተመዝግቦላታል። ወርቅነሽ ደገፋ እና ሕይወት ገብረኪዳንም በውድድሩ የሚሳተፉ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ናቸው።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ህዳር 21/2016

Recommended For You