ለኮፕ28 ስብሰባ የዓለም መሪዎች ወደ ዐረብ ኢምሬትስ እያመሩ ነው። በፕሬዚዳንት ሼህ መሐመድ ቢን ዛይድ አልነሀያን የቀረበላቸውን ጥሪ ተከትሎ በኮፕ28 የአየር ንብረት ለውጥ ስብሰባ ለመሳተፍ የዓለም መሪዎች እና ተወካዮቻቸው ወደ ዐረብ ኢምሬትስ እያመሩ ይገኛሉ።
የቶጎ ፕሬዚዳንት ዶክተር መሐመድ ፋኡሬ ጊናስንግቤ፣ የጉያና ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ዶክተር መሐመድ ኢርፋን አሊ እና የኮትዲቭዋር ፕሬዚዳንት አላሳኔ ኦታራ ከትናንት በስቲያ ዐረብ ኢምሬትስ ገብተዋል።
በተጨማሪም የጊኒ ቢሳው ፕሬዚዳንት ጀኔራል ኦማር ሲሶኮ ኢምባሎ፣ የጋቦን የሽግግር ፕሬዚዳንት ጀኔራል ንጉይማ እና የፓኪስታን የሽግግር ጠቅላይ ሚኒስትር አኑዋር ሀቅ ካካርም ዐረብ ኢምሬትስ ደርሰዋል።
በዱባይ ከኖቬምበር 30 እስከ ዲሴምበር 2 ለሚካሄደው የአየር ንብረት ጉባኤ መሪዎች መምጣታቸውን ቀጥለዋል። ዐረብ ኢምሬትስ ኮፕ 28 በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ የተቀመጡ ግቦችን በማሳካት በዓለም ስኬታማ የሆነ ስብሰባ ይሆናል የሚል ተስፋ አላት።
በስብሰባው ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የሠሯቸውን ሥራዎች ሪፖርት ያቀርባሉ። ከፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስብሰባ ቀጥሎ በሚካሄደው በዚህ ትልቅ ስብሰባ ከሀገራት መሪዎች በተጨማሪ ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ወኪሎች በመገኘት መግለጫ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ህዳር 21/2016