አብዛኞቹ ፖለቲከኞች የፖለቲካ ‹‹ሀሁ››ን የሚጀምሩት በሕዝብ ስም በመማል ነው። መነሻም ሆነ መድረሻቸው ሕዝብ እንደሆነና ለሕዝብ ጥቅም ሲሉም ሕይወታቸውን አሳልፈው እንደሚሰጡ ሲምሉና ሲገዘቱ መስማት አዲስ አይደለም፡፡ እንደውም የጀማሪ ፖለቲከኛ መለያ እስከመሆን ደርሷል፡፡
ከየትኛውም ፖለቲከኛ አንደበት ከማይጠፉ ቃላት ውስጥ ሕዝብ የሚለው ተጠቃሽ ነው፡፡ ሕዝቡ ከእነዚህ ፖለቲከኞች የተጠቀመው ነገር ባይኖርም ፖለቲከኞቹ ግን በሕዝብ ስም ብዙ ተጠቅመዋል። አንዳንዶቹ የኑሮ መሰረታቸው አድርገው ስለሚወስዱትም የዕለት ኑሯቸውን ከመምራት አንስቶ ሕይወታቸውን እስከመለወጥ ያስቻለ ሃብት ለማፍራት በቅተዋል፡፡
ትላንት በባዶ እግሩ ሲኳትን የምናውቀው ፖለቲከኛ የሕዝብን ስም ጠርቶ ዘመኑ ባመጣው አውቶሞቢል ሲንፈላሰስ በአይናችን በብረቱ ተመልክተናል፡፡ በተለይም የአሁን ዘመኖቹ ፖለቲከኞች ሕዝብ የሚለው ጥቅል መጠርያ አንሶባቸው ብሔርን እና ኃይማኖትን ጭምር ደርበው የበለጠ ሕዝባዊነታቸውን ሲያፋፍሙ እየተመለከትናቸው አንዳንዴም እየታዘብናቸው ነው።
ሆኖም እነዚህ ሕዝበኞች ያሰቡትን እስኪያሳኩ እና የማይጠረቃ ፍላጎታቸውን እስኪሞሉ ድረስ ትዝብትም፤ ወቀሳም የሚበግራቸው አይደለሉም። ጭራሽ እራሳቸውን የሰቀሉበት ማማ የትየለሌ ስለሆነ እነሱ ተነኩ ማለት ሕዝብ ተነካ ማለት ነው። ማንን ሳይሾማቸውና ሳይቀባቸው የሕዝብ መሪ፤ ጠበቃና ተሟጋች አድርገው እራሳቸውን ስለፈረጁ እነሱን መንካት ማለት ምልዓተ ሕዝቡን እንደመንካት ይቆጥሩታል፤ ወይንም እንዲቆጠር ይፈልጋሉ፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከሚታወቅባቸው አኩሪ ባሕሪያቶቹ መካከል የሚጠቀሱት፣ ሕግ አክባሪነቱና ሰላም ወዳድነቱ ናቸው፡፡ ከሕግ አክባሪነቱና ከሰላም ወዳድነቱ ጋር ደግሞ ለዘመናት በጋራ የገነባቸው ትውልድ ተሻጋሪ ማኅበራዊ እሴቶቹ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጣቸው ናቸው፡፡ እርስ በዕርስ በሚያደርጋቸው የዕለት ተዕለት መስተጋብሮቹ ተዋዶና ተከባብሮ መኖር ብቻ ሳይሆን፣ የብሔርና የሃይማኖት ልዩነቶች ሳይገድቡት በጋብቻ ጭምር የተሳሰረ ነው፡፡ ሆኖም እነዚህ ሕዝበኞች ዛሬ ተነስተው ሕዝቡን ስለበዳይና ተበዳይ በትርክት፤ ስለልዩነት፤ ስለመጠፋፋትና መለያየት ሊመክሩት ሲሞክሩ ይደመጣል፡፡
እነሱ የሚያውቁትና የሚያዋጣቸውም ክፉ ምክርና ሃሳብ ስለሆነ በጠበበ ጭንቅላታቸው ጠባብ ሃሳብ ቀን ከሌት ሲተፉ ይደመጣሉ፡፡ አንደበታቸው ላይ የተገጠመው ክፉ ጋኔል ስለሆነ ቆሌያቸው የሚፈልገው ሞት፤ ዕልቅት፤ መፈናቀል እና ስደት የመሳሰሉትን ነው፡፡ ለሺ ዘመናት አብሮ ኖረውን ሕዝብ እርስ በእራሱ እንዲራጠር፤ እንዲገፋፋና ብሎም እንዲገዳዳል በሕዝብ ስም እየማሉ ሴራ ይሸርባሉ፡፡
ከኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ አኩሪ መገለጫዎች መካከል የብሔር፣ የእምነት፣ የቋንቋ፣ የባሕልና ሌሎች ልዩነቶችን ዕውቅና በመስጠት ተሳስቦና ተከባብሮ መኖር ትልቁ እሴት ነው፡፡ የዘመኑ ፖለቲከኞችና አጋፋሪዎቻቸው ግን ለዘመናት የተገነባውን የአብሮነት እሴት በመናድ፣ አንዱ በሌላው ወገኑ ላይ ጭካኔ የተሞላበት ወንጀል እንዲፈጽም መገፋፋት ትልቁ ተግባራቸው ሆኗል፡፡ ልዩነቶችን ጌጦቹ አድርጎ ሳያፍር ለዘመናት አብሮ የኖረ ሕዝብ ውስጥ ጥላቻ በመዝራት ቅራኔ መፍጠር፣ የዘመኑ ትውልድ ባልኖረበት ዘመን ትርክት መወንጀል፣ የገዛ ወገንን መጤና ባለቤት በማለት መከፋፈል፣ ተፈጥሯል ለተባለ ክስተት ዕዳ መክፈያ ይመስል በጭካኔ መጨፍጨፍና ለማመን የሚከብዱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መፈጸም ተለምዷል፡፡
አሁን አሁን ልብ ብሎ ለተመለከተው ለሞት፤ ለአካል መጉደል፤ ለስደትና ለመፈናቀል መንስኤ እየሆኑ ያሉት በሕዝብ ስም በሚምሉ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች አማካኝነት ነው፡፡ እገሌ ብሔር እገሌን በደለ፤ የእገሌ ብሔር የእገሌን ይዞታ ወሰደ፤ የእገሌ ብሔር እገሌን ጨፈጨፈና መሰል የእልቂት እወጃዎች በየቀኑ ሲነዙ ቢውሉም የተባሉት ግፍና ሰቆቃዎች ግን በገሃዱ ዓለም የሉም፡፡
ከራሳቸው ጥቅምና ፍላጎት ውጪ የሕዝብ ጉዳይ ዴንታም የማይሰጣቸው እነዚህ በሕዝብ ስም የሚምሉና የሚገዘቱ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ከአጃቢዎቻቸው ውጪ ማኅበረሰቡ ውስጥ የሚታወቅ ጠብም ሆነ ጥላቻ ባይኖርም የኑሮ መሰረታቸው ነውና እንደዕድር በጡሩንባ ነፊ ሌሊት ተነስተው መርዶ መንገር እንጀራቸው ነው፡፡ የነሱ ኪስ የሚደልበው፤ የኑሮ መሰረታቸው የሚደላደለውና ሕልውናቸው የሚረጋገጠው በሚለፍፉት የመርዶ መጠን ነው፡፡
እንዲህ ዓይነቶቹ ከራሳቸው በፊት ለአገርም ሆነ ለሕዝብ ምንም ደንታ የሌላቸው ስለሆኑ፣ የእነሱ ፍላጎት እስካልተሳካ ድረስ ሚሊዮኖች ቢያልቁ ደንታቸው አይደለም፡፡ እንኳንስ ለወጣቱ መማርና መለወጥ፣ ለአጠቃላይ ሕዝቡ የኑሮ ዕድገት ቀርቶ ለአገር ሕልውናም ደንታ የላቸውም። እነሱ ቀንና ሌሊት የሚማስኑት ለሥልጣንና ይዞት ለሚመጣው ጥቅም ብቻ ስለሆነ፣ የእነሱን ፍላጎት እስካረካ ድረስ ሕዝብና ሀገር ላይ ስለሚመጣው ጉዳት ለአፍታም አይጨነቁም፡፡ አዋጭ ሆኖ ካገኙትም የሽንሸናው ዋና መሐንዲስ ከመሆን አይመለሱም፡፡ በዚህም ምክንያት በሕዝብ ስም እየነገዱ ፍላጎታቸውን ለማርካት ማንኛውንም ወንጀል ይፈጽማሉ፡፡
የብዙዎችን የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም ቡድኖች አመሰራረት ስንመለከተው ከተጠና አመላከት ይልቅ በስሜት ወይም በግብታዊነት የተመሰረቱ ናቸው። የግል ጥቅማቸው አልከበር ሲላቸው፤ ከወቅቱ የፖለቲካ አካሄድ ጋር ሲኳረፉ፤ ሰርቶ ከመለወጥ ይልቅ በአቋራጭ መበልፀግ ሲከጅሉና አንዳንድ ጊዜም እጅ ሲያጥራቸው በድንገት ተነስተው የፖለቲካ ፓርቲ የመሰረቱ ሰዎችን ወይም ቡድኖችን እናውቃለን፡፡
አንዳንዶቹም የቤተሰብ አባሎቻቸውን አስተባብረውና ወደ ምር ቦርድ አቅንተው የፖለቲካ ፓርቲ የመሰረቱና ኑሯቸውን ለመደጎም የተጠቀሙበት ግለሰቦች መኖራቸው ጭምርም በየሚዲያው ሲገለጽ የኖረ ነው፡፡ አንዳንዶቹ አሁን የት እንዳሉ ባይታወቅም ከቀድሞው መንግስት እህል እየተሰፈረላቸው ፖለቲካ ማድመቂያ ሆነው መኖራቸው ከሕዝብ የተሰወረ አይደለም፡፡
እነዚህና መሰል የተበላሸ የፖለቲካ መስመር የሚከተሉ ሰዎችና ቡድኖች በሕዝብ ላይ ኑሯቸውን ለመመስረት አስበው የተነሱ ቢሆንም ከአፋቸው ግን ለሕዝብ ሲሉ እንደተቋቋሙ ከመናገር ቦዝነው አያውቁም፡፡ በንግግሮቻቸው መሀል ያለመታከት ለሕዝብ ያላቸውን ተቆርቋሪነት በመግለጽ አቻ የላቸውም፡፡ ሆኖም ለሕዝብ አንድ ጠብ ያለ ነገር ሲሰሩ አይታዩም፡፡ ሁልጊዜ መውቀስ፤ መተቸት፤ ማብጠልጠል እና ማጠልሸት መለያቸው ነው። ሲያጠለሹና ሲያብጠለጥሉም በበቂ መረጃ ላይ ተመስርተው አይደለም፡፡
ትችታቸውና ማብጠልጠላቸው የተበላሸውን ለማስተካል የፈሰሰውና ለማፈስ፤ የጎበጠውን ለማቅናት ሳይሆን የመቃወምና የማጠልሸት ሱሳቸውን ለመወጣት ነው፡፡ ይህ አካሄድ ደግሞ ከ1960ዎቹ ጀምሮ እንደ ባህል የተያዘና ኢትዮጵያም በሰለጠነ መንገድ በሃሳብ ሙግት የፖለቲካ ስርዓት እንዳትገነባ እንቅፋት ሆኖባታል፡፡
በ21ኛው ክፍለ ዘመን በሥልጡን የፖለቲካ መንገድ ቢጓዙ የሚጠየቁት አንድ ነገር ብቻ ነው። እሱም የሕዝብን ቀልብ የሚስብ አጀንዳ ነው። ሕዝብ የሚፈልገው ሰላሙን በዘለቄታዊነት የሚያረጋግጥለት፣ ከድህነት አረንቋ ውስጥ የሚያወጣውና ነገን ብሩህ የሚያደርግለት ፖሊሲ ነው፡፡ ይህ ነው የሚባል አማራጭ ፖሊሲ ሳያቀርቡ መፎከር ዋጋ የለውም፡፡ አንዴ ቢሳካ እንኳ መድገም አይቻልም፡፡ ዘለቄታዊና አስተማማኝ የሆነ የሕዝብ ተቀባይነት ማግኘት የሚቻለው ግን ለውይይት፣ ለድርድርና ለመተማመን ዝግጁ የሆነ አደረጃጀትና ሥምሪት ሲኖር ነው፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎችም ሆኑ በዙሪያቸው ያሉ ወገኖች ከተራ ብሽሽቅ፣ እሰጥ አገባ፣ ሐሜት፣ አሉባልታና ለትዝብት ከሚዳርጉ ድርጊቶች መታቀብ ይኖርባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያን ታላቅ አገር አድርጎ በሰላም፣ በነፃነት፣ በፍትሕና በእኩልነት ለመኖር የሚያስችል ሥርዓት ዕውን ማድረግ የዘመኑ ትውልድ ኃላፊነት ነው፡፡
ይህንን ኋላ ቀር የፖለቲካ ምህዳር ለመለወጥ በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት ተፈርጀው የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ፍረጃው ተነስቶላቸው በአገሪቱ የፖለቲካ መጫወቻ ሜዳ ላይ ተሠልፈዋል፡፡ ከእነዚህ ድርጅቶች መካከልም የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ)፣ አርበኞች ግንቦት ሰባት፣ እንዲሁም የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ሆኖም አንዳንዶቹ ቡድኖች አሁንም በድሮው መንገድ በመጓዝ በየጫካው ነፍጥ ማንሳቱንና መንግስትን በኃይል ለመቀየር ሲጣጣሩ እየተመለከትን ነው፡፡ ሆኖም ይህ የ1960ዎቹ አካሄድ ዘመኑን የሚዋጅ ካለመሆኑም ባሻገር ለሕዝብና ለሀገር ያለማሰብም ጭምር ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከፊቷ የተጋረጡ በርካታ ችግሮች ያሉባት አገር ናት፡፡ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ ለመነጋገርና ለመደማመጥ ጊዜ መስጠት አለባቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የጸጥታ ችግር አለ፡፡ ድርቅ፤ ጎርፍ፤ መፈናቀል በየጊዜው ይከሰታል፡፡ የኑሮ ውድነቱ እየባሰበት ነው። የወጣቱ ቁጥር በየጊዜው እያደገ ስለሚመጣ የሥራ አጥነቱ መጠን በፍጥነት እያሻቀበ ነው፡፡
ለዘመናት ሳይከፈሉ የቆዩ የአገሪቱ የዕዳ ጫና ከባድ ነው፡፡ ጥራት ያለው የትምህርትና የጤና አገልግሎት ተደራሽነት በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ በገጠርም ሆነ በከተማ የሚኖሩ በርካታ ሚሊዮኖች ከድህነት ወለል በታች ይኖራሉ፡፡ በሀገር ውስጥ ካለው አለመረጋጋትና ግጭት ባሻገር በተለያየ መልኩ የኢትዮጵያን ውድቀት የሚሹ የውጭ ጠላቶች እያደቡ ኢትዮጵያን ማድማታቸው አልቀረም፡፡
ስለዚህም በዚህ ወሳኝ ጊዜ ከግል ፍላጎት ወጥቶ በሰከነ መንገድ መነጋገርና መደማመጥ ያስፈልጋል። ፖለቲከኞች ምኅዳራቸው በሥርዓት ተመሥርቶ ሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር እንዲፈጠር፣ ልዩነቶቻቸውን አስታርቀው በጋራ መሥራት አለባቸው፡፡ በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ምሁራንና ልሂቃን ለፖሊሲዎች ግብዓት የሚሆኑ ድጋፎችን የማበርከት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ መንግሥት ግብዓቶችን ተቀብሎ ተግባራዊ እንዲያደርጋቸው ተደራጅተው ጫና ማሳደር ይጠበቅባቸዋል፡፡
ለአገራቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችሉ ልምድ ያካበቱ ወገኖች በማሰባሰብ ጭምር አገራዊ ኃላፊነት መወጣት ግዴታቸው ነው፡፡ በተጨማሪም በአገሪቱ የመነጋገርና የመደማመጥ፣ እንዲሁም የመተማመን ባሕል እንዲጎለብት ግፊት ማድረግ አለባቸው፡፡
በሌላ በኩል ባሉት ችግሮች ላይ ተጨማሪ ችግሮች በመቀፍቀፍ ላይ የተጠመዱ ወገኖችም፣ አንድ ጉዳይ ላይ አጽንኦት ቢሰጡ መልካም ነው፡፡ የሚፈልጉትን ዓላማ ለማሳካት ሲነሱ፣ የሕዝብን ሕይወትና የአገርን ሕልውና አደጋ ውስጥ ከሚከት ድርጊት መታቀብ አለባቸው፡፡ በእነሱ ምክንያት ንፁኃን ሲገደሉ፣ ንብረታቸው ሲዘረፍና ሲወድም፣ ሲፈናቀሉና የአገር ሰላም ሲታወክ ለጊዜው ከሕግ ተጠያቂነት ቢያመልጡም፣ ከታሪክ ተጠያቂነት የሚታደጋቸው ግን የለም፡፡ ከሕግ ለጊዜው ቢሰወሩም ቆየት ብሎ ፍትሕ ደጃፍ ላይ መገተራቸውም አይቀሬ ይሆናል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን ግን ለሀገር እና ለሕዝብ ሰላም ሲባል የተጀመሩ የሰላም ጥረቶች ሁሉ መቀጠል አለባቸው። ሕዝብም ሰላም ወዳዱን እና ለሰላም ጀርባውን የሚሰጠውን ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ነገ ከነገወዲያ ከሰላም ርቀው ግጭትና ሁከትን መተዳደሪያቸው ያደረጉትን እንዲሁም በሕዝብ ስም እየማሉ ሕዝብን የሚገሉ፤ የሚያቆስሉ፤ የሚያፈናቅሉና የሚያጎሳቁሉ ወገኖች በሕዝብ ክንድ የእጃቸውን ማግኘታቸው አይቀሬ ነው፡፡
አሊ ሴሮ
አዲስ ዘመን ኅዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም