የአርሶና አርብቶ አደሩን አቅም ለማሳደግ ከፍተኛ ድጋፍ ከሚያደርጉ ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት አንዱ ነው። ተቋሙ ለምርትና ምርታማነት ዕድገት እንዲሁም የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከሚሠራቸው ሥራዎች መካከል ለአርሶ እና አርብቶ አደሩ የሚሰጠው የምክር አገልግሎት አንደኛው ነው። ተቋሙ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለአርሶ አደሩ የሚሰጠውን የምክር አገልግሎት ቀልጣፋ፣ ቀላልና ምቹ ማድረግ የሚያስችለውን ‹‹8028›› የተባለ የስልክ ጥሪ አገልግሎት መስጫን ተግባራዊ አድርጓል።
አርሶና አርብቶ አደሩ በእጅ ስልኩ ወደ ‹‹8028›› እየደወለ በግብርና ሥራው እና ከግብርና ጋር ተያይዞ ለሚገጥመው ማንኛውም ችግር መፍትሔ እያገኘ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የሠጠው መረጃ ያመለክታል። ከእርሻ ጋር ተያይዞ በሰብል ምርት ሂደት ላይ ብቻ ሳይሆን በአሁን ወቅት ደግሞ የገበያ መረጃን ለማካተትና ለአርሶና አርብቶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችለውን ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ይፋ አድርጓል።
በተጨማሪ ከገበያው ባሻገር በሰብል ምርቶች ላይ ብቻ የነበረውን የምክር አገልግሎት በእንስሳት ሃብትም ለማስፋት እየሠራ እንደሚገኝ ይፋ አድርጓል። እስከ አሁን በተለይም በአፋርና በሶማሌ ክልሎች 130 ሺ የሚደርሱ አርብቶ አደሮች በዚህ መረጃ እየተጠቀሙ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፤
ሌላው የኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት በግብርና ግብዓት አቅርቦት ላይ ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ያስችላል የተባለለትን ዲጂታል የክፍያ ሥርዓት ላይም ከክፍያ የፋይናንስ ቴክኖሎጂ ተቋም ጋር በመተባበር በጋራ ለመሥራት ሰሞኑን ተፈራርሟል። በዚህ እና በሌሎችም በአጠቃላይ ተቋሙ በሚሠራቸው ሥራዎች ዙሪያ ከኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሤ (ዶ/ር) ጋር ቆይታ አድርገን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል። መልካም ንባብ፡-
አዲስ ዘመን፡- የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ምን እየሠራ ነው ከሚለው እንጀምርና እንቀጥል?
ዶ/ር ማንደፍሮ፡- ትልቁ ሥራችን በአራት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፈላል። አንደኛው የግብርና ዘርፉ ላይ ትላልቅ ማነቆ የሚባሉ እና ለረዥም ጊዜ አስቸጋሪ የሆኑ ጉዳዮችን መለየት እና ለችግሮቹም የመፍትሔ ሃሳብ ማመንጨት ነው። ለዚህ ጥናት እና ምርምር የሚሠራ አንድ የሥራ ክፍል እና ቡድን አለ። በጥናት ክፍሉ የሚመጣው ምክረሃሳብ በቀጥታ በሚመለከታቸው አካላት እንዲተገበር ይሠራል። ተግባሪዎች የምንላቸው የግብርና ሚኒስቴር፣ በክልል፣ በዞን እና በወረዳ ደረጃ ያለ የግብርና ቢሮዎች በቀላሉ ሊተገብሩት የሚችሉት ከሆነ የጥናቱ ምክረ ሃሳብ እንዲተገበር ይደረጋል።
አንዳንዴ ምክረ ሃሳቡን ለመተግበር ተጨማሪ ዕውቀት እና ክህሎት የሚያስፈልግበት ጊዜ ያጋጥማል። በዛ ጊዜ የትግበራ ድጋፍ እንሠጣለን። እንዲተገበር አጋዥ ኃይል ማለትም ባለሙያዎችን እናስቀምጣለን። አፈር ላይ፣ ውሃ ላይ፣ የኅብረት ሥራዎች አሠራር ላይ ምርምር የሚያካሒዱ ብቻ ሳይሆኑ እንዲተገበር የሚያግዙ ባለሙያ እናስቀምጣለን። እነርሱ ምክረሃሳቡ እንዲተገበር አጋዥ ኃይል ይሆናሉ ማለት ነው። ባለሙያ በሚያስፈልግበት ቦታ ዕውቀታቸውን ተጠቅመው እንዲተገበር ያደረጋሉ።
ስለዚህ ምክረ ሃሳቡን በመስጠት ብቻ ሳይሆን አንዳንዴ ባለሙያም አብሮ ሠርቶ አሳይቶ መረጃ ሰብስቦ ከዛ ወደ ትግበራ የሚገባበት ሁኔታ ይኖራል። በተጨማሪነት ግን ባለሙያ ገብቶበትም የማይተገበርበት ሁኔታ ያጋጥማል።
በዚህ ጊዜ የሚመለከታቸው አካላት ይሳተፋሉ ማለት ነው። ለምሳሌ የግብርና ግብይት ሥርዓት ይኖራል። የአርሶ አደርን መሬት ኩታ ገጠም አድርጎ በመካናይዜሽን በትራክተር እንዲታረስ፣ በትራክተር እንዲዘራ፣ በኮምባይነር እንዲታጨድ ይፈለጋል።
አርሶ አደሮች ሰብስበው ለቤተሰብ ብቻ የሚበቃውን አስቀርተው፤ ቀሪውን ለገበያ እንዲያቀርቡ ማድረግ ላይ የሚሠራ ሲሆን፤ ሥራው ምርታቸውን ሲሸጡ የመደራደር አቅማቸውን ማሳደግንም ያካትታል። በዚህ ጊዜ ውጣ ውረድ ያለው ምርትም ሆነ ገበያ አይኖርም። ሁሉም የምርምር ውጤት ስለሚጠቀሙ ምርታማነታቸው ከፍተኛ ይሆናል። ይህ ደግሞ እንደሀገርም ምርታማነታችንን በከፍተኛ ደረጃ ይጨምረዋል።
የኢንስቲትዩቱ ሥራ አርሶ አደሩ ምርታማነቱ ጨምሮ ከራሱ አልፎ ለገበያ አቅርቦ ኑሮውን እንዲያሻሽል ነው። ያ ማለት ኑሮ ሲሻሻል ከግብርና አልፎ ወደ ሌላ ኢንቨስትመንት ይገባል። በዛ ክላስተር የተደራጁ አርሶ አደሮች ወደ ፊት ወደ ቢዝነስ ኢንተርፕራይዝ ይቀየራሉ። እርሻው ላይ መቆየት የሚፈልግ ሰው እዛው እርሻው ላይ ይሠራል። የማይፈልግ ሰው ደግሞ በኩታ ገጠም አንድ ላይ ኢንተርፕራይዝ አቋቁሞ ቀጥሮ ሊያሠራ ይችላል። ይህንን በማድረግ ወደ መካናይዜሽን ሲሸጋገር፤ በርካታ ሰዎችን የያዘው የግብርናው ዘርፍ የሰው ኃይሉ ወደ ኢንዱስትሪ ይሸጋገራል። በዚህ ጊዜ ወደ ኢንዱስትሪ ሽግግር የምንለው ዕውን ይሆናል ማለት ነው። ይሔንን በምናደርግበት ጊዜ የግብርና ትራንስፎርሜሽንን እውን ስናደርግ አብዛኛው ሰው ካመረተው ውስጥ 75 በመቶ የሚሆነውን የሚሸጥ ከሆነ የግብርና ትራንስፎርሜሽን እውን ሆኗል ማለት ነው።
ከ75 በመቶ በታች ከሆነ ገበያው አላደገም ማለት ነው። ለገበያ የሚሔደው እየበዛ በሔደ ቁጥር ግን ወደ ኢንዱስትሪ እና ወደ አግሮ ፕሮሰሲንግ ለመሔድ ያስችላል። ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ሽግግር ይፋጠናል ማለት ነው። ለምሳሌ አርሶ አደሮች ተደራጅተው የብቅል ገብስ እያመረቱ፤ የብቅል ገብስ ያቀርባሉ። አርሶ አደሮች ተደራጅተው አኩሪ አተር አምርተው ዘይት ለሚጨምቅ ኩባንያ ያቀርባሉ። አርሶ አደሮች ተደራጅተው አቮካዶ አምርተው ወደ ውጪ ለሚልክ ድርጅት ያቀርባሉ። አቮካዶ ተመርቶ ዘይት እና ጁስ እየተዘጋጀ ነው። ይህ እየቀጠለ ሲሔድ ግብርና ኢንዱስትሪውን እየመገበ ኢንዱስትሪው ይበልጥ እየተስፋፋ፤ ግብርና ላይ የሚኖረው የሰው ኃይል ደግሞ በመካናይዜሽን እየተተካ እየቀነሰ ወደ ኢንዱስትሪው መሔድ ይችላል። ስለዚህ ግብርናን እንደ ቢዝነስ ኢንተርፕራይዝ እያዩ በክላስተር የተደራጁ አርሶ አደሮች ሕጋዊ ሰውነት እንዲኖራቸው መበደርም ማበደርም እንዲችሉ ሥራውን ማፋጠን የኛ ተግባር ነው።
ከመካናይዜሽን ክላስተር ወደ ኩታ ገጠም የግብርና ምርት ክላስተር ያሸጋገርናቸው አርሶ አደሮች አሉ፡፤ ከዚህ ደግሞ በቀጣዮቹ ሁለት እና ሦስት ዓመታት ወደ ኢንተርፕራይዝ የምናሸጋግራቸው አሉ። በዚህ የሽግግር ሒደት ውስጥ በርካታ ፕሮጀክቶች አሉ። አንደኛው ምርታማነትን ለመጨመር ወሳኙ ዘር ነው። ስለዚህ ዘር የሚያባዙ አርሶ አደሮችን በኅብረት ሥራ አደራጅተን ኅብረት ሥራን መሠረት ያደረገ ዘር እያመረቱ አሽገው ለሌሎች አርሶ አደሮች እየሸጡ ነው። ስለዚህ በልዩ ሁኔታ አጠቃላይ ምርት ከማምረት ወደ ዘር ማምረት የቀየርናቸው አርሶ አደሮች አሉ ማለት ነው።
የመካናይዜሽን አገልግሎት ሰጪዎች አሉን። አሥር የመካናይዜሽን ማዕከላትን አቋቁመናል። እነዚህ የራሳቸው ትራክተር አላቸው፤ አርሶ አደሮች ትራክተር መግዛት አይጠበቅባቸውም። መከራየት፣ መጠቀም እና መክፈል ይችላሉ። ይህ አገልግሎት በመሰጠቱ ግብርናው በጣም ይዘምናል። የሚባክን እህል አይኖርም። እንደአሁኑ ማለትም ዝናብ ሲያጋጥም በአንድ ቀን ውስጥ አጭዶ ወደ ማከማቻ ማስገባት ይችላል ማለት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹የእናንተን ትራክተር አልፈልግም፤ ሠልጥኜ ኦፕሬተር መሆን እፈልጋለሁ።›› የሚሉ ወጣቶችም ካሉ፤ ማዕከሉ ያሰለጥናል፤ ብቁ ያደርጋቸዋል። ይህ በማዕከል የሚሠራ ሲሆን፤ አርሶ አደር በግሉ ገዝቶ አሠርቶ ሲበላሽበት ደግሞ ከተማ ውስጥ የጋራዥ አገልግሎት እንደሚሠጠው ሁሉ የጋራዥ አገልግሎት እና የመለዋወጫ አቅርቦት ሥራም ይሠራል። ማዕከላቱ ከውጪም አስመጥተው መለዋወጫ ያቀርባሉ። እነዚህን የመካናይዜሽን አገልግሎት የሚሠጡ ማዕከላት ሁለተኛ ፕሮጀክቶቻችን ናቸው።
ሦስተኛው የኢንስቲትዩቱ ሥራ ግብዓት ነው። አሁን መንግሥት እያመጣ መንግሥት እያሠራጨ ነው። በእኛ በኩል በየወረዳው 325 ሱቆችን አቋቁመናል። ሱቆች ግብዓቶችን ይገዛሉ፤ ለአርሶ አደሩ ይሸጣሉ። እነዚህ ሁሉን በአንድ የሚይዙ ሲሆን፤ ዘር፣ ማዳበሪያ፣ የግብርና ኬሚካል እና የእንስሳት መድኃኒት እንዲሁም ሁሉም ነገር አላቸው። አርሶ አደሩ መድኃኒትን ያለአግባብ እንዳይጠቀም ማሠልጠኛ አላቸው። ስለዚህ አርሶ አደሩን የሚደግፉ 325 ሱቆች እና 10 የመካናይዜሽን አገልግሎት ማዕከላት አሉን። በሞዴላችን 70 በመቶውን እኛ እንሸፍናለን። 30 በመቶ እነርሱ ይሸፍናሉ።
የመካናይዜሽኑን ሥራ ከዩኒየን ጋር አያይዘነዋል። ሱቆቹ ደግሞ የግለሰቦች ሲሆኑ፤ የሚያገኙት ተወዳድረው ነው። አራተኛው ፕሮጀክታችን ደግሞ የገበያ ክላስተሮቹ ዝናብን መሠረት ያደረጉ ናቸው። ስለዚህ የሚያመርቱት አንድ ጊዜ ነው። በእኛ በኩል ሁለት ጊዜ ማምረት እንዲችሉ የመስኖ አውታር መዘርጋት፤ በተለይም በፀሐይ ብርሃን (በሶላር) እንዲዘረጋ እየሠራን ነው። ይህም በእያንዳንዱ ግለሰብ በበርካቶች ቤት እየገባ ይገኛል። ይህ የኮሪያ ሞዴል ሲሆን፤ አሁን ከግለሰብ ቤት ወደ ማኅበረሰብ ደረጃ እያደገ ይገኛል።
ከፀሐይ ኃይል በተጨማሪ ውሃው ለመጠጥ፣ ለንጽሕና መጠበቂያ (ሳኒቴሽን) እና ለመስኖ እንዲሁም ለብዙ አገልግሎት ይሆናል። ከፀሐይ ብርሃን የሚገኘው ኃይል ውሃ እንዲገኝ የሚረዳ ሲሆን፤ በሌላ በኩል በገጠር ለመብራት አገልግሎትም ይሆናል። በዚሁ መልክ በኮሜርሻላይዜሽን ክላስተር ውስጥ አስራ አምስት ፕሮጀክቶች አሉን። የምንሠራው ይሔንን ሲሆን፤ ከዛ በተጨማሪ የኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓት ሽግግር (ኢትዮጵያን ፉድ ሲስተም ትራንስፎርሜሽን) ላይም እንሠራለን። እዚህ ላይ በርካታ ሚኒስትሮች የሚገኙበት ሲሆን፤ እርሱንም እናግዛለን።
የዲጂታል ግብርናን እናስተባብራለን። የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ እርሱንም ለማስተግበር፤ እያስተባበርን እና ሁሉንም አካላት እያሳተፍን አዋጅ ደንብ እና መመሪያዎች እንዲወጡ እያደረግን ነው። ስለዚህ በአጠቃላይ ችግር ከመለየት ጀምሮ መፍትሔ እስከ ማመንጨት በማገዝም ሆነ በመሞከር እንዲሁም በማስተባበር እንሠራልን። ሥራችን እና ኃላፊነታችን ከግብርና በላይ ሰፊ ነው። ማምረት ብቻ ሳይሆን ገበያንም አካቶ ይይዛል። ኢንዱስትሪ እና መስኖን የሚይዝ ሲሆን፤ እነዚህ በሚኒስትር ደረጃ ከሚታዩት በተጨማሪ፤ ኅብረት ሥራ ላይ፤ ኢንቨስትመንት ላይ እንሠራለን። እነዚህን ሁሉ አንድ ላይ በማቀናጀት ከግብርና ምርት ግብዓት ጀምሮ እስከ ሸማቹ ጠረጴዛ ድረስ እናስተሳስራለን። ለዚህ ደግሞ የተለያዩ መድረኮች አሉ።
አዲስ ዘመን፡- ጥናት እናደርጋለን ብላችኋል። ከግብርና ጋር ተያይዞ በዋናነት ያጠናችኋቸውን ይግለፁልን?
ዶ/ር ማንደፍሮ፡- ለማምረት ሁለት ነገሮች ወሳኝ ናቸው። አንደኛው አፈር ሲሆን፤ ሁለተኛው ውሃ ነው። አጠቃላይ የሀገሪቷን የአፈር መዋቅር ለይተናል። አጠቃላይ የአፈርን ለምነት እና አሲዳማነት አውቀናል። የትኛው ቦታ ምን ዓይነት አፈር እና ምን ዓይነት ማዳበሪያ ይፈልጋል የሚለውን በጥናት ለይተን በዛው ልክ ምክረ ሃሳብ አስቀምጠን እና በምርምር ለክተን እየሠራንበት ነው። በውሃ በኩልም ጥናት ላይ ተመሥርተን ሠርተናል።
ከመሬት በላይ የሚታየውን ውሃ ሳይሆን የማይታየውን የከርሰ ምድር ውሃ ላይ ጥናት በማድረግ የት ቦታ ምን ያህል ውሃ አለ? በውሃ አማካኝነት ምን ያህል መሬት ማልማት ይቻላል? የሚለውን ማወቅ ወሳኝ ነው። በተጨማሪ ፖሊሲ ላይ እና ስትራቴጂ ነደፋ ላይ ጥናት እናደርጋለን።
የመሥሪያ ቤቶች አቅም ማለትም ግብርና ላይ ለሚሠሩ፣ ኢንቨስትመንት ላይ የሚሠሩ ተቋማትን ምን ይመስላሉ? የት ቦታ ምን ችግር አለባቸው? ክልሎች እና ኅብረት ሥራዎችም አደረጃጀታቸውም ሆነ አተገባበራቸው ላይ ምን ቢደረግ ይሻላል? ብለን እናጠናለን፡፡ የመንግሥት ተቋማት ብቻ ሳይሆኑ የግል ተቋማትንም እናግዛለን፡፡ የእኛ ፍላጎት ለውጥ ነው፡፡ ሀገሪቷ መድረስ ያለባት ቦታ ላይ እንድትደርስ የግብርናም ሆነ ሌሎች ተቋማት እናጠናለን። ለምሳሌ ዘር ላይ የሚሠራ ተቋም ምን መምሰል አለበት? የፌዴራል እና የክልል እንዲሁም የግል ዘር ላይ የሚሠሩ ሁሉንም ተቋማት እንተነትናለን፡፡ የማንገባበት የለም፡፡ በሁሉም በኩል እናግዛለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ጥናቶች ካጠናችሁ በኋላ ትግበራው እና ምክረ ሃሳብ ተቀብሎ ተግባራዊ በማድረግ ዙሪያ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?
ዶ/ር ማንደፍሮ፡- እስከ አሁን ካጠናናቸው ጥናቶች እና ካቀረብናቸው የመፍትሔ ሃሳቦች መካከል 65 በመቶ አካባቢ ተግባር ላይ ውሏል፡፡ ጥናቱ ለአንዳንድ ተቋማት አሠራራቸውን እንዲከልሱ አድርጓቸዋል። ተግባራዊ የማያደርጉት ጥቂቶች ናቸው፡፡ የምንነሳው ከተግባራዊ ችግር እና ከእነርሱ ጥያቄ ስለሆነ ወዲያውኑ ጥናቱ ላይ በመመሥረት ወደ ተግባር ይገባል፡፡ አሁን የባሕሪ (ካራክተራይዜሽን) ጥናት እያደረግን ነው። የሶማሌ እና የደቡብ ምዕራብ ክልሎች የግብርናው ዘርፍ ውጤታማ የሚሆንላቸው በምን መልክ ነው? ብለን ጥናት አጥንተናል። ለሲዳማ አሁን እየሠራን ነው። ለብዙዎች ሠርተናል፡፡ በተለይ የቴክኒክ ድጋፍ ለሚፈልጉ ክልሎች እናግዛለን፡፡ የት ቦታ ትኩረት ቢያደርጉ የተሻለ እንደሚሆን እና አሁን በሚሠሩት ሥራ ምን ዓይነት መሰናክል እንደሚያጋጥማቸው እንጠቁማለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሥራችሁ ሒደት ግብርና ዘርፍ ላይ አለ የምትሉት ትልቅ ችግር ምንድን ነው?
ዶ/ር ማንደፍሮ ፡- ትልቁ ለማንኛውም ችግር መፍትሔ ማግኛ ቁልፉ ፋይናንስ ነው፡፡ ፋይናንስ ለእኛ አይደለም። ይህንን ሥራ ለማስኬድ የብድር አቅርቦት ይፈልጋል፡፡ ሁሉም አርሶ አደር አቅም የለውም፤ ወይም አቅም አለው ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን በግለሰብ ደረጃ አንድ አርሶ አደር ትራክተር ይገዛል ማለት ከባድ ነው። አርሶ አደሮችን አሰባስቦ ትራክተር እንዲገዙ ማድረግ ይቻላል። ነገር ግን ይህንን የመሥሪያ የሕግ ማዕቀፍም ሆነ ምንም ዓይነት መንገድ የለም፡፡ ስለዚህ የብድር አቅርቦት ይፈልጋሉ። እንኳን ትራክተር ዘርም ሆነ ማዳበሪያ ለመግዛት ብድር የሚፈልጉ አርሶ አደሮች አሉ፡፡ ምንም ብድር የማይፈልጉም አሉ፡፡ ነገር ግን አብዛኛው አርሶ አደር ብድር ይፈልጋል፡፡ ይህ ትልቅ ችግር ነው፡፡
ከፋይናንስ አቅርቦት ቀጥሎ የግብርናው ዘርፍ ትልቅ ችግር የማከማቻ መዋቅር አለመኖር ነው፡፡ ሰው ያመርታል፤ ብዙ ጊዜ እና ጉልበት ፈሶበት የተመረተው ምርት በአንድ ቀን ዝናብ ከጥቅም ውጪ ይሆናል፡፡ ተሰብስቦ ሜዳ ላይ ቢደረግ በአንድ ቀን ሌሊት ብዙ የተለፋበት የሚበላሽበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ስለዚህ በየገጠሩ የማከማቻ መጋዘን ያስፈልጋል። አንዳንዴ መጋዘን ቢኖርም በየቦታው ባሉ መጋዘኖች ለማስቀመጥ ዋስትና የለም፡፡ አላየሁም ቢባል ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ አብዛኛው ሰው በሃይማኖት ውስጥ በመታሠሩ እና እምነት ስለሚዘው እንጂ ወንጀል የሚሠራበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ መፍትሔው ሰዎች በከተማ ቡና እና ሻይ ቤቶች ወይም ሆቴሎች ለመሥራት ከመረባረብ ይልቅ፤ ገጠር መጋዘን ቢሠሩ ለዛም ሥርዓት ቢበጅ በአገሪቱ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡
ምርት ሲበላሽ የሚጎዳው አንድ አርሶ አደር ብቻ አይደለም፡፡ ምርቱ በመበላሸቱ አቅርቦት ያንሳል፤ በዚህ ጊዜ ሸማቹም ላይ የሚሸምተው ምርት ዋጋ የተጋነነ ይሆንበታል። ስለዚህ ትርጉሙ ትልቅ ነው፡፡ ይህንን ችግር መቅረፍ እንዲቻል ገጠር ውስጥ እንደዛ አይነት መጋዘኖች ቢሠሩ መልካም ነው። አነስተኛ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያዎችም ቢሠሩ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ግን የብድር አቅርቦት ወሳኝ ነው። ትልቅ የእህል ማከማቻ መጋዘን ለመሥራት አቅም ላይኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን ብድር ቢኖር ተበድሮ በየወሩ ከሚገኘው ገንዘብ ላይ ብድሩ ሊመለስ ይችላል፡፡
የኢትዮጵያ ባንኮች ሲታዩ በአጠቃላይ ስሪታቸው ከተማ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ለገጠር እና ለረዥም ጊዜ የሚሆን ገንዘብ አያበድሩም፡፡ ዋስትና ይፈልጋሉ፡፡ በሬ ተቆጥሮ ዋስ አይሆን፤ ያለው ቤት ብቻ ነው፡፡ ቤቱም ቢሆን የሣር ይሆናል፡፡ ዋጋ ላያወጣ ይችላል፡፡ ስለዚህ አርሶ አደሩ ለብድር የተለየ መንገድ ይፈልጋል፡፡ እነዚህ ሁለት ችግሮች ከተቀረፉ ትራክተሩ ይመጣል፤ እሴት የሚጨምር አግሮ ኢንዱስትሪው ይመጣል፡፡ በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥም ጥሩ ተወዳዳሪ እንሆናለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ግብርናውን እያስተጓጎሉ ካሉ የተለያዩ ምክንያቶች መካከል አንዱ የግብዓት አቅርቦት ነው፡፡ ለግብዓት አቅርቦት 325 ሱቆች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ ሱቆቹ ራሳቸው በእርግጥ ለአርሶ አደሩ በቂ ግብዓት ማቅረብ ይችላሉ?
ዶ/ር ማንደፍሮ፡– በእርግጥ አቅርቦቱ ከአንድ ቋት ነው። የሚከፋፈል እንጂ ራሳቸው የሚያመጡት አይደለም፡፡ አሁን ከተመሳሳይ ቦታ እየመጣ ነው፡፡ እኛ ግን የምንፈልገው ራሳቸው አስመጥተው እንዲያከፋፍሉ ነው፡፡ ነገር ግን ያንን ለመሥራት አቅም የላቸውም። እነዚህ ሱቆች ለየብቻ ሳይሆን ማኅበር ፈጥረው ተደራጅተው አስመጥተው እንዲያከፋፍሉ እንፈልጋለን፡፡ በጋራ ሲሠሩ የራሳቸው መገናኛ መሥመር ይኖራቸዋል፤ ማለት ነው፡፡ ከመንግሥት ብቻ አይጠብቁም። የግል ዘርፉ መጠናከር ይፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በመካናይዜሽን እርሻን ማከናወን ላይ እያጋጠመ ያለው ችግር ምንድን ነው ?
ዶ/ር ማንደፍሮ፡- ዋናው የኦፕሬተር ችግር ነው፡፡ አርሶ አደር ወይም የአርሶ አደር ልጆች በዛ ላይ ዕውቀቱም ክህሎቱም የላቸውም፡፡ ይህ ትልቅ እንቅፋት ነው፡፡ ነገር ግን ለእዚህ ችግር መፍትሔው ማሠልጠኛ ማዕከላትን አቋቁመናል፡፡ ስለዚህ በአጭር ጊዜ ብዙ ሠልጣኝ በማፍራት ኦፕሬተሮች እና ቴክኒሻኖች እንዲኖሩ እየሠራን ነው፡፡ በዛ አካባቢ የእውቀት ችግር መኖሩ የሚካድ አይደለም፡፡
አዲስ ዘመን፡- የእናንተን ሥራ የሚያከናውኑ ብዙ ተቋማት አሉ፡፡ ደጋፊው ማን ነው?
ዶ/ር ማንደፍሮ፡– እምንደግፈው እኛ ነን። መሠረት እንጥል እና በዛ መሠረት ላይ እንዲሠሩ እናደርጋለን። ለምሳሌ የአፈር ምርመራ እናካሂዳለን፡፡ ከዛ ለአፈር ምርምር ተቋም የተመረመረውን ለኩ እንላለን ከዛ ምርምሩ ልክ ነው ወይ? በዝቷል ወይስ አንሷል? የሚለውን ይለካሉ፡፡ በዚህ መልክ ወደ 500 አካባቢዎች ሠርተዋል፡፡ ሌሎችም ተቋማት መሠረት ስንጥልላቸው ማረጋገጡን ደግሞ እነርሱ እየሠሩ ይሔዳሉ፡፡ ስለዚህ ሥራችን ተቋማትን ማብቃት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሰሞኑን የዋጋ መረጃ ማሳወቅ የሚያስችል ቴክኖሎጂ አርብቶ አደሩ በስልኩ የሚያገኝበት ሁኔታ ላይ ለመሥራት ስምምነት ፈርማችኋል፡፡ እስኪ ስለዚህኛው ጉዳይ በደንብ ያብራሩልን?
ዶ/ር ማንደፍሮ፡- ሥራችን እስከ ግብይት ድረስ የዘለቀ ሲሆን፤ መረጃው ግብይትን የተመለከተ ብቻ ሳይሆን ከእንስሳት ጋር ተያይዞ ብዙ መረጃዎችን የሚሠጥ ነው። ገበያዎች ባሉበት ቦታ ላይ በየወረዳው የእኛ ባለሙያዎች በመኖራቸው የገበያ ጥናት ያካሒዳሉ፡፡ ያንን ካካሄዱ በኋላ መረጃ ሲያቀብሉ በዋናው የመረጃ ማዕከላችን ይታያል። ማንኛውም ሰው በ‹‹6077›› ደውሎ እነዚህን መረጃዎች ያገኛል፡፡ በእኛ በ157 ወረዳዎች ውስጥ በየገበያ ማዕከላት መረጃ ይሰበሰባል፡፡ ይኸው መረጃ ተመልሶ ይሠራጫል፡፡ የሚሰራጨው ለአርብቶ አደር ለከፊል አርብቶ አደር ወይም ለአርሶ አደር ብቻ ሳይሆን ለሚገዛ ሸማችም ጭምር ነው። የቄራ አገልግሎት ለሚሰጡ ሁሉ ነው፡፡ የት ቦታ በምን ዓይነት ዋጋ እንደሚሸጥ ያንን ያሳያል፡፡
ሰብል የሚመረትባቸው ቦታዎች ላይ የሰብሎቹን ዓይነት ጥራት እና ዋጋቸውን እንሠበስባለን፤ ይህንኑ መረጃ እናሰራጫለን ማለት ነው፡፡ ይሄ አርሶ አደሮች ያለአግባብ ምርታቸውን እንዳይሸጡ፤ ሸማቾችም ምርቶችን ያለአግባብ ዋጋ እንዳይከፍሉ ያደርጋል፡፡ ይሔ ለአምራቹም ለሸማቹም የመረጃ ሥርዓት የመገንባት እና አገልግሎት የመስጠት ሒደት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ይህ ሥራ እስከ አሁን ነበረ፤ ወይስ አሁን ገና አዲስ ነው?
ዶ/ር ማንደፍሮ፡- አይ የአሁኑ ስምምነት ሥራውን ለማስፋት ነው እንጂ፤ እስከ አሁንም እየሠራን ነበር። ለረዥም ጊዜ ተሠርቶባቸዋል፡፡ ‹‹8028›› ላይም አርሶ አደሮች እንዲያመርቱ እንስሳትን እንዴት እንደሚያደልቡ፤ ጤናቸውን እንዴት እንደሚጠብቁ አገልግሎት ይሠጣል። በቀጣይ ደግሞ ተጨማሪ ቦታዎችን እንድንሸፍን ስምምነት ላይ ደርሰናል። አዲሱ ስምምነት የአፋርን ክልል የሚጨምር ነው። ይህ ከቋንቋ ጋር ይገናኛል፡፤ ለምሳሌ ደጋ ላይ ላሞች በጎች ፍየሎች ሲሆን፤ ቆላ ሲኬድ ደግሞ ግመል እና ሌሎችም የጋማ ከብቶች ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ አካባቢ ሲቀየር ቋንቋ ብቻ ሳይሆን የእንስሳ አይነቶቹ፤ የባለሙያ አይነቶ፣ ምክሩም ይቀየራል። መጀመሪያ ሲደወል ቋንቋ ይመረጣል፤ ከዛ እንስሳም ሆነ ሰብል ምን ዓይነት እንደሆነ እና በየት አካባቢ እንዳሉ ሲገልፁ ማማከሩ ይቀጥላል፡፡
ይህንን በጋራ ከሌሎች ጋር የምንሠራው ሲሆን፤ ቀደም ሲል ከሜሪሲ ጋር በጋራ ሶማሌን አካተናል፡፡ ይህ ከአርብቶ አደሮች ጋር በጋራ እንድንሠራ የሚያደርገን ሲሆን፤ ፊድ ዘፊውቸር ከተሰኘ ድርጅት ጋር ያደረግነው ስምምነት ደግሞ ገበያን በተመለከተ በጋራ ለመሥራት ነው፡፡ ከእነርሱ ጋር አሁን ያሉንን 157 ወረዳዎች ወደ 250 ወረዳዎች ከፍ ማድረግ የሚስችለን ነው፡፡ ይህ ተደራሽታችንን እያሰፋን እንድንሔድ የሚያስችል ስምምነት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- አርብቶ አደሩ አካባቢ በእርግጥ ምን ያህል በስልክ ጥሪ ወይም በዲጂታል መንገድ ተደራሽ መሆን ይቻላል?
ዶ/ር ማንደፍሮ፡- ደጋ ላይ ከምናገኛቸው አርሶ አደሮች የበለጠ ለመረጃ ቅርብ የሚሆኑት አርብቶ አደሮች ናቸው። ዲጂታል መድረክ ስንከፍት ፈጥነው የማግኘት እና የመጠቀም ሁኔታቸው በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ አርሶ አደሮች በተለያየ መንገድ በማኅበራዊ ግንኙነታቸው በቤተክርስቲያን፣ በመስኪድ እና በዕድር በመሳሰሉት በተለያዩ የመገናኛ አጋጣሚዎች መረጃ ይለዋወጣሉ። አርብቶ አደሮች ግን ተራርቀው ስለሚኖሩ የሚገናኙት በዲጂታል መንገድ ነው። ለመረጃ በጣም ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጡ ሲሆን፤ በሁለት ዓመት ውስጥ 350 ሺህ አካባቢ ደርሰዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡-በዲጂታል ወይም በሞባይል አገልግሎት የምትሰጡባቸው ክልሎች ስንት ነበሩ?
ዶ/ር ማንደፍሮ፡- አራቱ ዋና ዋና የተሰኙት ክልሎች ላይ ብቻ ነበር፡፡ አሁን ሰባት ደርሰዋል፡፡ አሁንም በዚያ አይገደብም፡፡ የትም ቦታ ሆኖ ኔትወርክ ባለበት ‹‹8028›› ላይ ቢደወል መረጃ ማግኘት ይቻላል፡፡ ነገር ግን አሁን መረጃ የምንሰበስበው ከሰባቱ ክልሎች ነው፡፡ አሁን ግን ከእዛ ወጥተን ወደ አርብቶ አደሩም እየገባን ነው፡፡
የኢንስቲትዩቱ የመጨረሻ ግቡ ምርታማነትን ማሳደግ ነው፡፡ ምርት የሚቀንሰው በተባይ ወይም በበሽታ ከሆነ ምርቱ ሳይበላሽ ወይም ሳይቀንስ አስቀድሞ የሚከላከልበት ምክረ ሃሳብ ይሰጣል፡፡ ሥራው ምርት ከፍተኛ እንዲሆን ማድረጊያ እና ገቢ ማሳደጊያ ነው፡፡ ስለዚህ የመጨረሻ ግቡ የአርሶ አደሩን ምርታማነት እና ገቢ መጨመር ነው፡፡ እነዚህ ሁለቱ ሲጨምሩ የአርሶ አደሩ ሕይወት የተሻለ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የገጠሩን ማኅበረሰብ ኑሮ ማሻሻል ላይ እየሠራን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እስከ አሁን አገልግሎት እያገኙ ያሉ ምን ያህል አርሶ አደሮች አሉ?
ዶ/ር ማንደፍሮ፡– እስከ አሁን ‹‹ 8028 ›› ላይ በመደወል ብዛት ላለፉት ሦስት ዓመታት ወደ 50 ሚሊዮን አካባቢ የስልክ ጥሪዎች የተስተናገዱ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል በተደጋጋሚ የሚደውሉ እና መረጃ እያገኙ ሥራቸውን የሚያሻሽሉ ወደ ስድስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ቋሚ ደዋይ አርሶ አደሮች አሉ። ከንግድ ጋር በተያያዘ ‹‹6077›› ላይም አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን አካባቢ ደዋይ አለ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ክፍያ ከተሰኘ ተቋም ጋርም ስምምነት አድርጋችኋል፡፡ ስምምነቱ ምንድን ነው?
ዶ/ር ማንደፍሮ፡- ስምምነቱ የገቢ ደረሰኝ ሥርዓት (ኢንፑት ቮቸር ሲስተም) ላይ ያተኮረ ነው፡፡ አርሶ አደሮች ማዳበሪያ ሲገዙ በብሔራዊ ደረጃ ግብርና ሚኒስቴር ማዳበሪያ ይገዛል፡፡ የገዛውን ማዳበሪያ ለዩኒየን ወይም ለኢትዮጵያ ኅብረት ሥራዎች ኮርፖሬሽን ያደርሳል፡፡ አርሶ አደሩ ጋር እስከሚደርስ ድረስ የሚሔደው በዱቤ ነው። ዩኒየኖቹ ገንዘቡን ሲሰበስቡ አንዳንዴ ቶሎ ይገባል። አንዳንዴ ሌላ ነገር ይሠሩበታል፡፡ የገንዘብ ብክነት እና መዘግየት ነበር፡፡ ስለዚህ አሁን ክፍያ የሚደረገው ለፋይናንስ ድርጅቶች ለባንክ ወይም ለቁጠባ ድርጅት እንዲሆን እየተስማማን ነው፡፡ ይሔ ሲደረግ ክፍያው መፈፀሙን በራሪ ደረሰኝ ይሰጣቸዋል፡፡
አርሶ አደሮች ደረሰኙን ይዘው ወደ ዩኒየን ይሔዳሉ። ዩኒየኑ ደረሰኙን አይቶ ማዳበሪያ ይሠጣቸዋል፡፡ ስለዚህ ዩኒየኑ በማዳበሪያ ዙሪያ ከገንዘብ ንክኪ ነፃ ይሆናል። ይህንን በቅድሚያ በወረቀት ሠርተን ጨረስን፤ ወደ ሰባት ሚሊዮን አርሶ አደሮች ይጠቀሙበታል፡፡ የገንዘብ እንቅስቃሴው ወደ 32 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ሲሆን፤ ይህንን ዲጂታል ለማድረግ አቅደን ሠርተናል፡፡
ከዚህ በኋላ አርሶ አደሩ በቅርብ ርቀት ባለ የገንዘብ ተቋም በባንክ ወይም በአንድ ሌላ የገንዘብ ድርጅት ይከፍላል፤ ደረሰኙን ሲይዝ በዲጂታል መንገድ ዩኒየኑ መከፈሉን ያረጋግጣል፡፡ አርሶ አደሩ ዩኒየኑ ቅርብ ከሆነ ሄዶ ይወስዳል፡፡ ቅርብ ካልሆነ ቤቱ ድረስ ይመጣለታል።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ?
ዶ/ር ማንደፍሮ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ኅዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም