“የሰው ገጽ” እፍታዎች

አትጠይቁኝ

የት አለሽ አትበሉኝ ድንገት ተነስታችሁ፤

ከተዋችሁኝ ስፍራ ከጣላችሁኝ ቦታ አጣናት ብላችሁ፤

የት ጠፋሽ አትበሉኝ ብዙ ጠብቃችሁ፤

ከትልቁ ስፍራ ከማማው ወጥቼ ስላልታየኋችሁ፤

በፊት ጅማሪዬን ዕቅድና ትልሜን አባሪ አድርጋችሁ፤

እንቅፋት፣እሾሁን፣ ምቹ፣ ሾተላዩ አልታይ ብሏችሁ ፤

ስለምን ዘገየሽ? የት ቀረሽ ? እያላችሁ፤

የተዳፈነውን የውስጤን ሽፍንፍን ትነካካላችሁ።

አለሁኝ አለሁኝ በቆምኩበት ስፍራ

ሁሉም ሳይቀርብኝ እያየሁ በተራ

ተቸገርኩኝ እንጂ በወይኑ እርሻዬ እሾህ እየፈራ።

አንጠይቅም…ደግሞ ከወዴት እንዳለች ከማወቅም አንቆጠብም፡፡ ቅሉ እርሷ አትጠይቁኝ ብትለንም፤ ወዴት እንዳለች ግን ሳንጠይቅም ደርሰንበታል። ድሮስ ጥበበኛ ከወዴት ሊሆን ይችላል?… ከጥበብ መንደር፤ ከብዕር ዋርካ ጥላ ሥር ካልሆነ በቀር። ዳሩ የእርሷ መልዕክት፤ ከሰው ገጽ የምናብ ባሕር ውስጥ ሳለች ከሕይወቷ ግዙፍ መርከብ ላይ፤ በሀሳብ እያቃጨሉ እረፍትን ለነሷት የሀሳብ ተውሳኮች ቢሆንም፤ እኛ ግን ለኛም ይድረስ ብለን ከወዴት አለሽ ልንል የግድ ሆኗል። እንግዲህ ጥበብን ተከትለን እርሷን…እርሷንም ተከትለን “የሰው ገጽ”ን አግኝተናል። “የሰው ገጽ”ስ ምንድነው? በወፍ በረር…በረን በአውሎ ንፋሱ እንዳንሳፈፍ፤ በጠሊቁ ሰምጠንም በጊዜና አየር እጥረት የፊታችንን እንዳንተፋው ከሁለቱም መሐል ሆነን “የሰው ገጽ”ን ከእፍታ መሶብ ወርቁ ላይ ቆርሰን ልንቃመስ ያስመኘናል። የእፍታ ታህል ከምናነሳባት ከዚህቹ መሶብ ወርቅ ውስጥ፤ ለዛሬው ደርሶን ባናገኘውም ሌላ እንጎቻ ስለመኖሩም እንዳንዘነጋ፤ እኛም…ደራሲዋም ታስገነዝበናለች።

እንግዲህ ሰሞነኛ ጥበብ ማደሪያዋን ከወዲህ አድርጋለች፤ ከየት ካላችሁ ዘንድ…ካለችበትና ጥበብ ከተሰናዳችበት። ጥበብ ጥበብ ሲሸተን፤ የጥበብ የእግሯን ኮቴ፤ የጠረንዋን መዓዛ ተከትለን በስተመጨረሻም ከብሔራዊ ቲያትር አድርሳ አገናኘችን። እዚህ መክተሟ በምክንያት ነው። እሷን ፍለጋ ወጥቶ ከዚያ የተገኘውም አንድ ጉዳይ ሽቶ ነው። ጉዳዩም “አትጠይቁኝ” ስትል ከስንኞቿ ጋር በመግቢያችን የሞገተችን ደራሲና ጋዜጠኛ ፍሬዘር ዘውዴ፤ ሁለተኛውን የጥበብ ልጇን ወልዳለችና ‘እንኳን ጥበብ ማረችሽ’ ስንል የመጽሐፍ ልጇን ለመሳምና ከቀለም ጠብታ እንትፍ ብለን ለመመረቅ ነው። ደራሲና ጋዜጠኛ ፍሬዘር ዘውዴ፤ በብዙ የምናብ ምጥ ተጨንቃ የወለደችውን “የሰው ገጽ” የተሰኘውን የግጥም መጽሐፏን ከእንጎቻ ወጎች ጋር በእቅፍ አነባብራ፤ በጥበብ ታጅባ ከብሔራዊ ቲያትር መገኛዋን አድርጋለች። ምስጋና ለደራሲያን ማኅበር ይግባና በተንጣለለውና የጥበብ ናርዶስ በፈሰሰበት፤ በግዙፉ የብሔራዊ ቲያትር አዳራሽ ለመታረስም በቅታለች። የደራሲያን ማኅበርን ማንሳታችን፤ ደራሲዋ የዚህ ማኅበር አባል በመሆኗም ነው። እንግዲህ ማኅበሩም የልጅነት ፈቃድ ለሰጣቸው አባላቱ አለኝታነቱን ከሚያሳይባቸው ጉዳዮች መካከል አንደኛው፤ አባላቱ በሚከትቧቸው የመጽሐፍ ሥራዎች ውስጥ ከጎናቸው በመሆን ከግባቸው እንዲደርሱ ማድረግ ነው። ዛሬም ለደራሲዋ ደጀን ቆሞ ያማረውን ልጇን ባማረ መልኩ እንድታስመርቅ ሆኗል።

እንዲህ አይነት ማኅበራት በሁሉም ዓለማት የሚገኙ ቢሆንም፤ እንደ አፍሪካ ብሎም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ላሉ ደራሲያን ያለው ሚና አለ የማይባል ነው። የእጦት ችንካር በተቸነከረባቸው ሀገራት ውስጥ በምጥ የሚሞቱት እናቶች ብቻ ሳይሆኑ ጠቢባንም ጭምር ናቸው። ከማህፀን ምጥ የባሰው ምጥ፤ ምናባዊ የአዕምሮ ምጥ ነው። ላይገላገሉት እድሜ ዘመናቸውን ጥበብን በምናብ እያማጡ ኖረው እንዳማጡ ይሞታሉ። በእድልህ እደግ ተብሎ አይወለድ ነገር ጭንቅ ነው። ልጅ በድሉ፣ ሀብታሙ…ወዘተርፈ ተብሎ ስሙን መልአክ አያወጣለት ነገርም እዳ ነው። ብቻ ግን ከአፈር በላይ የሚውሉትን ዘለዓለማዊ የጥበብ ልጆቻቸውን ወልደው ስመው ለወግ ለማዕረጉ የሚያሳኩበትን ገንዘብ ከማጣት የተነሳ፤ ሳይወልዱም ሳይስሙም፤ ቀና ያላለች ቀናቸው ደርሳ ከነምጣቸው ተፈግመው አፈር ይለብሳሉ። ስማቸውን በሥራዎቻቸው ለዘለዓለሙ ሕያው አድርገው ማኖር የሚችሉ ስንቶቹ መወለድ፤ መሞታቸውንም ሳናውቅ አፈር ታቅፈው ለአፈር ግብር ውለዋል። የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ካለው አጭር እድሜና የቅርብ ጊዜ ታሪክ አንጻር በብዙ ሀገራት እንደምንመለከተው አይነት፤ እጁን በችሮታ ዘርግቶ ለአባላቱ ከኪሱ ገንዘብ ለመስጠት አልታደለም። ይልቁኑ ነብሱን የሚያቆየውም ከአባላቱ የሚሰበሰበውን ገንዘብ እየቀማመሰ መሆኑ ነው። በአሁኑ ሰዓትም ለአባላቱ ካለው ኃላፊነት መሐከል ዓበይቱ፤ ደራሲያኑ ያሰቡት ተሳክቶ፤ ሕልማቸው እውን ይሆን ዘንድ በሥራዎቻቸው ከጎናቸው በመቆም፤ አጋር ሊሆኑ የሚችሉ አካላትን ከመፈለግና ሁኔታዎችን ከማመቻቸት ጀምሮ የአቅሙን ይጥራል። እንግዲህ አንድ ቀን ያጠረው እጁ እረዝሞ፤ ማድጋ ወጭቱ ሞልቶ፤ ከአቁማዳውም ተትረፍርፎ እንመለከተው ይሆናል በማለት በእፍታ እንለፈው።

ወደ ዋነኛው ርዕሰ ጉዳያችን እምብርት ሰትረን ከመግባታችን በፊት ጥቂት ስለ ደራሲዋ እንበል። ፍሬዘር ዘውዴ ውልደትና እድገት እዚሁ ከአዲስ አበባዋ ክንፍ ቀራኒዮ መድኃኒዓለም መንደር ውስጥ ነው። አዲስ ከተማ ትምህርት ቤት፤ በእውቀት የተለወሰውን የፊደል ማር የበላችበት፤ ሀሁ የቆጠረችበትና ዛሬም ድረስ ከትዝታዋ ማህደር ያልተፋቀ የሕይወት ብርሃን ያየችበት ነው። አብዝታም ስሙን መጥራት ትወዳለች። ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የእውቀት መንገድ ተዋውቃበታለች። ከልጅነቷ ጀምሮ በአንቀልባዋ አዝላ ያኖረችውን ሥነ ጽሑፍ፤ በተለይም የግጥም ፍቅሯ ከፍቅርነት አልፎ የመጀመሪያውን ፍሬዋን የተመለከተችውም በዚሁ በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ ነበር። ከዩኒቨርሲቲው የባሕልና የኪነት ቡድን አባላት ከነበሩ ጓደኞቿ ጋር በመጣመር የግጥም መድብል አሳትማለች። በሥራው ዓለም ሳለችም፤ በግሏ የመጀመሪያ የሆነውን “የፍቅር ገጽ” የተሰኘ የግጥም መድብል ለጥበብ አፍቃሪያኑ አቋድሳለች። ከ”የፍቅር ገጽ” የቀጠለው ሁለተኛው ሥራዋ ደግሞ ከሰሞኑ ለምርቃት የበቃው “የሰው ገጽ” የተሰኘው ይሄው ድንቅ የግጥም ሥራዋ ነው።

ኅዳር 15 ቀነ ቀጠሮውን ቆርጦና ቆጥሮ በብሔራዊ ቲያትር ይህን ሊያስመለክት ከልበ ደጋጎቹ ዘንድ ደርሷል። ኪነ ጥበብ፤ የጥበብ ገብረዲኑን ለብሶ ካማረ ሸማው ጋር በፍቅር ከትሟል። ለጥበበኞች ጥበብን ለጀግኖቹም የክብርን ዘውድ ሊደፋ በግርማው ተገልጧል። ጠቢባን፣ የጥበብ አፍቃሪያን፤ እንዲሁም ጀነራል ካሳዬ ጨመዳን ጨምሮ የጦር ሜዳው ሊህቀ ህሩያን ከአዳራሹ ተንቆጥቁጠዋል። “እናንተ ልበ ጥሩዎች..እናንተ ደጋጎች…እናንተ መልከ መልካም የሀገሬ ልጆች..” በማለት ጀመረች፤ የመድረኩን የመግቢያ መጋረጃ የገለጠችው ደራሲና ጋዜጠኛ እንዲሁም በእለቱ በጥበብ ያጌጠችው የጥበብ ባለጸጋ፤ ፍሬዘር ዘውዴ…ጸጋዋ የሥነ ጽሑፍ ብቻም አይመስልም፤ ብዙዎቻችን የጎደለንን የአመስጋኝነትን ጸጋም የተቸረች ትመስላለች። የምስጋናን ማር ካንደበቷ ታፈልቃለች። ለኛ የዛሬ ማንነት መሻገሪያ ድልድይ የሆኑትን በሕይወት ሳሉ የሚገባቸውን ሳንሰጥ፤ ከሞት ወዲያ መገነዣ ከፈን አድርገን ብናቀርበው ለሄደው ከሞት አንቂ ስሜት አይሰጠውም። ሀገርና ሕዝቧን የምትወድ፤ በእናትና አባቶቻችን ወግና ሥርዓት ተቀርጻ ያደገች ስለመሆኗ የእለቱ ዝግጅት ፍንትው አድርጎ ለማሳየትም ይዳክራል።

“የሰው ገጽ” የተሰኘው መጽሐፍ ግጥሞችን ብቻም ሳይሆን እንጎቻ ወጎችንም አካቶ የያዘ ነው። በግጥሙ፤ ስብጥር ስሜቶች እና እሱና እሷ የሚሉ ክፍሎች አሉት። እሱና እሷ እውነተኛ የታሪክ ቅምሻዎች ስለመሆናቸው ደራሲዋ ትናገራለች። በዚህም 5 አጫጭር ታሪኮች ተካተውበታል። “የሰው ልጅ ልክ እንደ ሽንኩርት የተለያየ ንብብር ስሜት፣ ማንነት፣ እውነት እና አመለካከትን የያዘ ደግሞም እያንዳንዱ ንብብር በተነሳ ቁጥር ሌላ ከቀደመው ተቃራኒ የሆነ አዲስ ገጽ የሚገኝበት ነው፡፡ ይሄ በሽንኩርት ገላ የተመሰለው ማንነት ግን፤ ልክ ሽንኩርት እያንዳንዱ ንብብር በተነሳ ቁጥር እየኮሰሰ ከዛም እንደሚያልቀው ሳይሆን ዘመን እስከፈቀደ ዝም ብሎ የሚገለጥ የማያልቅ ንብርብር ነው፡፡ እናም በዚህ መጽሐፌ እጅግ በጣም ጥቂት የሰው ገጾች ቀርበዋልና እርስዎም ይግለጧቸው…” ትለናለች። ፍቃዷ ሆኖ ግለጡት ካለችን ዘንድ፤ እኛም ይሄን የሰው ገጽ ገልጠን ወርቁንም፤ ሰሙንም…ቅኔውንም ሆነ ግጥሙን ለመመልከት አይሰለቸንም፡፡ በጥበብ መታቀፊያ እያኖርን ዳግም እንኳን ጥበብ ማረችሽ እያልን ስመን ለመመረቅ እንወዳለን።

“የሰው ገጽ” ሰው የመሆንን ሚስጥር፤ ከሰውም ኢትዮጵያዊ የመሆንን ምስጢር በስንኞች እየቋጠረ መልክና ወዘናውን እጹብ ድንቅ ጣዕሙን ያጠግበናል። ግን…ሰው ማለት ምንድነው? የሰው ገጽስ? ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትስ… ማናቸው? ቅኔ ፍጡር…ቅኔ ሀገር…ቅኔ ሕዝብ ሁሉም በግጥም ቅኔ ውስጥ ተቃኝተዋል። ደራሲዋ ፍሬዘር ዘውዴ፤በዚህ “የሰው ገጽ” በተሰኘው በሁለተኛው ልጇ ውስጥ ሁሉንም ለማየት ታትራበታለች። “ግጥም እኮ ማብራሪያ አይሻም። ምክንያቱም ግጥም ጥያቄ እንጂ ምላሽ አይደለም። ግጥም ትንቢት ተናጋሪ እንጂ ሁነትን አብራሪ አይደለም” በማለት የዚህ መጽሐፍ አርታኢ የነበሩት መምህር መሠረት አበጀ፤ የግጥምን ገጽ ገልጠው ለማሳየት ሲሞክሩም ሰምተን ነበር። እውነት ነው፡፡ የሰው ልጅ ገጽና የግጥም መጋረጃ፤ ውስጡ በማብራሪያ የሚገለጥ አይደለም። ግጥምም ለአይን የቀረበ የቅኔ ወሰን የለውም። የሰው ልጅም የማንነትና የምንነት መለኪያ ቁና የለውም። የግጥም ቅኔ ጥልቀትና የሰው ልጅ ገጽ ስንት ነው ተብሎ ተቆጥሮ አይደረስበትም። ነጭ ሲሉት ጥቁር፤ ቢጫ ሲሉት ግራጫ፤ መልአክ ሲሉት ሰይጣን፤ ሲኦል ሲሉት ገነት ነው። “የሰው ገጽ” ደራሲዋ ጥላቻና ፍቅርን፣ እውነትና ውሸትን፤ ትላንትናና ዛሬን እንዲሁም ሀገርና ሕዝብን በሰው ልጅ ገጽ ውስጥ እየሾረች፤ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በተካተቱ የግጥምና የወግ ሥራዎች ውስጥ ለመደወር ሞክራለች።

የኅዳር 15ቱ የብሔራዊ ቲያትር የረፋድ ቆይታ ሀገር ሀገር እንዲሸት ካደረጉት ነገሮች አንደኛው፤ በምስጋና የታጀበው የሀገር ባለውለታ ጀግኖች የእውቅና አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት ዋነኛው ነበር። በዚህ መሠረትም ይህቺን ሀገር ከትውልድ እስከትውልድ ጠብቀው ያስረከቡን የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ግንባር ቀደሙ ነው። ማኅበሩ ዛሬ ላይ ለዛሬ የተመሠረተ ሳይሆን ፋሽስቱ ድባቅ የተመታበትን ጊዜ መነሻውን በማድረግ በትውልድ ሐረግ ሽቅብ እየተምዘገዘገ ዛሬና ዘንድሮን ደርሷል። እኚያ ታላላቅ አባቶች እኛን ከአፈር በላይ አኑሮው እነርሱ ግን ከአፈር በታች ናቸው። ይህ ማኅበር ዛሬ ብዙ የጦር ሜዳ ጀግኖችን ያቀፈ ቢሆንም፤ በብዛት ግን ለዚሁ ቅርብ በሆኑ በአርበኛ ልጆችና የልጅ ልጆች ጭምር የቆመ ነው። “የእናንተና የኛ አባቶች፤ እናትና አጎቶች እንዲሁም ዘመዶች…አጥንታቸውን ከስክሰው፤ ደማቸውን አፍሰው ይቺን የማትበገር ኢትዮጵያን ሰጥተውናል። እኛ ደግሞ የነገሩንና ያየነውን፤ የሰማነውንም እውነተኛ ታሪክ ለልጅ ልጆቻችን እናወርሳለን። የኛ ማኅበር ዛሬ ላይ ልክ እንደቀደምቶቻችን ሁሉ በጦር አውድማ ላይ ባይጋደልም፤ ተጋድሎው ከታሪክ ጋር ነው። በአንዳንድ አላዋቂዎች ምክንያት እየተበረዘ ያለውን ታሪካችንን በማንጻት እውነተኛዋን ኢትዮጵያን እንድንመለከታት ለማድረግ ይሠራል” ሲሉም የማኅበሩ ፕሬዚዳንት የሆኑት ልጅ ዳንኤል መስፍን(ጆቴ) የእውቅናና የምስጋና ሰርተፊኬታቸውን በተቀበሉበት ጊዜ ተናግረዋል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ለአበርክቶው እውቅና የተበረከተለት ሌላኛው ደግሞ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጽሐፍት አገልግሎት(ወመዘክር) ነበር። በእርግጥም ተቋሙ እውቅናም ሆነ ሽልማት የሚያንስበት እንጂ የሚበዛበት አይደለም። ዓላማው ትውልድን በእውቀት መቅረጽና በጽሑፍ የሠፈሩ የሀገር ሀብትና ንብረቶችንም መጠበቅ ነው። ተቋሙ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ በዩኔስኮ ያስመዘገበቻቸውን 12 የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን እንዲሁም በርካታ የሆኑ የጥንት መጽሐፍት፣ አዲስ ዘመንን ጨምሮ ቀደም ሲል የነበሩ ጋዜጦች፣ መነን መጽሔትና ሌሎች ኅልቁ መሳፍርት ጽሑፎችን አካቶ ይዟል። ከዚህ ባሻገርም የንባብ ባሕል ይዳብር ዘንድ በየሳምንቱ በሀገራችን ልዩ ልዩ ክፍሎች የንባብ ሳምንትንም ያዘጋጃል።

እንግዲህ እፍታ… ኩሬና ባሕር፤ ትንሽና ትልቅ የለውምና ካየንና ከሰማነው ብዙ ነገር፤ ያወቅነውንና የተረዳነውን ጥቂት ነገር አንዲህ ባለ መልኩ አወሳናችሁ። ከጥበብ ባሕር እየቀዳች፤ ከሰው ገጽ ባሕሪ እየጨለፈች፤ ከፍቅር ሸማ እየፈተለች “የሰው ገጽ” የተሰኘውን የግጥም መድብሏን የደወረችው ደራሲና ጋዜጠኛ ፍሬዘር ዘውዴ፤ ከምናባዊው ፀአዳማ ሰማይ፤ ከምድራዊው የገነት ልምላሜ፤ ነፋሻማውን አየር ለመኮምኮም እየተመኘች፤ በመጨረሻም በስንኞቿ እንዲህ ትላለች።

ና ኮከብ እንቁጠር!

ና ኮከብ እንቁጠር በጭፍን ሰማይ ላይ፤

ባዶ በሚመስለው ከደመናው በላይ፤

ኮከብ አልባ የሆነ ከጥቅል ጢስ መሳይ፤

ጨረቃን ካፈነ የጉም ጥቅጥቅ ፍታይ፡፡

ምንም ከሌለበት እንዳልነበር ሆኖ፤

ክዋክብት እንቁጠር እኛ በተቃርኖ፡፡

በዚህ አይነት ምሽት በእንዲህ አይነት ሰማይ፤

ጨረቃና ኮከብ ለእኛ ብቻ እንዲታይ፤

ልባችን ሰሌዳ እንዲወክል ሰማይ፤

አይናችን ከኮከብ ደምቆ አምሮ እንዲታይ፡፡

ሁሉን የፈጠረ በሩህያችን ፅፎ፤

ያኖረ ይመስለኛል ጊዜን አስደግፎ፡፡

ና ኮከብ እንቁጠር በጭፍን ሰማይ ላይ፤

ሁሉ ተቀምጧል ለእኛ ብቻ እንዲታይ፡፡

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You