ትኩረት ለፍትህ ስርዓቱ

 ፍርድ ቤቶች ሕግን የመተርጎም ሕገመንግስታዊ ተልዕኮ የተሰጣቸው አካላት ናቸው፡፡ ከሕግ ውጪ ተፈጽመዋል ለሚባሉ ድርጊቶችም ሕግንና ማስረጃን መሰረት በማድረግ በነጻነትና በገለልተኝት ፍትህ/ዳኝነት ይሰጣሉ፡፡ የዜጎችን የፍትህ ጥማት ያረካሉ፡፡ ዜጎች በሕግ ስርአቱ ላይ ያላቸውን እምነት እንዲያጎለብቱም ሌት ተቀን ይሰራሉ፡፡

እንደ አጠቃላይም ሕዝብ በፍትህ አካላት ላይ የጠነከረ እምነት ሲይዝ የሕግ የበላይነት ይረጋገጣል። በውጤቱም የሀገርና የሕዝብ ደህንነት ዋስትና ያገኛል፡፡ ሰላም ይሰፍናል፤ ፍትህ ይነግሳል፡፡ ለሀገር ኢኮኖሚያዊ፤ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ዕድገት ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ሕዝቡንም ፍትሃዊ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች ይኖራሉ፡፡

በኢትዮጵያ ከፍተኛ የፍትህ ፍላጎት አለ። የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዛኛውን ጊዜ በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ በመሬት፣ በተለያዩ ወንጀሎች፣ ከጎረቤትጋር በሚኖሩ ያለመግባባቶች፣ ከቤተሰብ እና ከቤት ውስጥ ጥቃት ጋር በተያያዙ ችግሮች፣ ከገንዘብ ጋር በተያያዙ አለመግባባቶች እና ከሥራ ጋር በተያያዙ የሕግ ጉዳዮች ያጋጥሙታል። ሆኖም እነዚህን ችግሮች በሕግ አግባብ ለመፍታት የሚሄድበት መንገድ አታካች ከመሆኑም በላይ በሕግ አግባብ እልባት የሚያገኙት ጥቂቱ ብቻ ናቸው፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩትም በየዓመቱ 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሰዎች የሕግ ጉዳይ አጋጥሟቸው ወደ ፍርድ ቤቶች ቢሄዱም ከእነዚህ ውስጥ መፍትሄ የሚያገኙት ከ30 በመቶ በታች ናቸው፡፡ 70 በመቶ የሚሆኑት በወቅቱ ሕጋዊ መፍትሄ ካለማግኘታቸውም በላይ በሚኖራቸው ምልልስ የጊዜና የኢኮኖሚ ኪሳራ ያጋጥማቸዋል፡፡ በየዓመቱ የሚተላለፉ መዝገቦች መብዛት አንድን ጉዳይ እልባት ለመስጠት የሚወስደውን ጊዜ የተራዘመ በመሆኑ የዜጎችን ፍትህ በጊዜው የማግኘት መብትን የሚጥስ ጉዳይ ሆኗል፡፡

የዘገየ ፍትህ እንደተነፈገ ይቆጠራል እንደሚባለው የሕግ ጉዳይ አጋጥሞት ወደ ፍርድ ቤቶች የሄደ ሰው ጉዳዩ እስኪፈጸምለት በርካታ ዓመታት ይቆጠራሉ፡፡ በዚህም ሕዝብ በፍትህ ስርዓቱ ላይ እምነት እንዲያጣ አድርጓል፡፡ እንደ አጠቃላይም ፍትህ ለዲሞክራሲ ግንባታ፣ ለሰላም እና ለልማት ሊወጣ የሚገባውን ሚና እንዳይወጣ አድርጎታል፡፡

ፍርድ ቤቶች ለዘመናት የተከማቹ ችግሮች ያሉባቸው የፍትህ ተቋማት ናቸው፡፡ መጓተት፣ የጥራት አለመኖርና ውስን ተደራሽነት የፍርድ ቤቶቻችን መለያ ከሆኑ ቆይተዋል፡፡ በሙስና፤ በምልጃ እና በትውውቅ ጉዳይን ማስፈጸምም በፍርድ ቤቶች አካባቢ ስለመኖሩም ብዙዎች ሲናገሩ ይሰማል፡፡

በሌላም በኩል የባለሙያዎች የአቅም ክፍተት፤ ብቁ ባለሙያዎችን ወደ ፍትህ ስርአቱ ለመሳብና ለማቆየት አለመቻል፤ የምርምርና የማሰልጠን አቅም ያለመዳበር፤ ዘመናዊ ቴክኖሎጂና ሌሎች መሰረተ ልማቶች አለማሟላት የፍትህ ስርዓቱ ማነቆዎች ናቸው፡፡ ስለዚህም በስነምግባርም ሆነ በአቅም ግንባታ ረገድ የሚታዩ ክፍቶችን መሙላትና እንደ አጠቃላይ ለፍትህ ስርዓቱ በቂ ትኩረት መሰጠት የጊዜው ጥያቄ ሊሆን ይገባል፡፡

በፍርድ ቤቶች የሚስተዋሉ የስነ-ምግባር ችግሮችን ያለ ርህራሄ ማስወገድ ወይም መታገል ያስፈልጋል። በዳኞችም ይሁን በድጋፍ ሰጪ ሠራተኞቻችን አካባቢ በሚስተዋሉ እና እያደጉ የመጡ የስነ-ምግባር ችግሮች በጊዜ ካልተቀረፉ የፍርድ ቤቶች ፍትህ/ዳኝነት የመስጠት የሞራል ልዕልና ሊኖረው አይችልም፡፡

በማኅበረሰብ ደረጃ ሰፊ የፍትህ ተደራሽነትን በሚያረጋግጥ እና አስፈሊጊ በሚሆንበት ጊዜም መደበኛ የፍትሕ አሰጣጥ ዘዴዎችን ተደራሽ በሚያደርግ መልኩ በኢ-መደበኛ እና በመደበኛ ፍትሕ መካከል ድልድዮች መዘርጋት እና ዜጎች ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች ጎን ለጎን በየአካባቢቸው በባሕላዊ መንገዶች ፍትህ እንዲያገኙ ማድረግን እንደ አንድ አማራጭ አድርጎ መውሰድ ይገባል፡፡

ሥር ነቀል የፍትሕ ለውጥ ሂደትን በኢ-መደበኛ እንዱሁም በመደበኛ፣ በክልል እንዲሁም በፌዴራል ደረጃዎች ማስጀመር እና የፍትህ ስርዓቱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማገዝና ሰዎች ያለብዙ ውጣ ውረድ የሕግ ጉዳዮቻቸውን እንዲፈጽሙ ማድረግ የፍትህ ስርዓቱ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ሌላው ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የዳኝነት አገልግሎቱን ነጻነትና ተጠያቂነት የሚያጠናክሩ፤ ጥራትን የሚያሻሽሉ እና ተደራሽነትን የሚያጎለብቱ ሥራዎችን በማከናወን በፍትህ ስርዓቱ ላይ ሕዝቡ እምነቱን እንዲጨምር ማድረግ ያሻል፡፡

በአጠቃላይ የዜጎች በተቀላጠፈ ሁኔታ ፍትህ የማግኘት መብት በምንም ምክንያት ሊሸፋፈን የማይገባው ከመሆኑም በላይ እንደ ሀገር የዴሞክራሲና የልማት ጉዳይ ስለሆነ መንግስት የፍትህ ስርዓቱ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጥ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል!

አዲስ ዘመን   ኅዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You