በልጆቻቸው አደራ ተረካቢነት የዘመነው የአባት የሽመና ሙያ

ወጣት ሃያት ጀማል ትባላለች፡፡ ትውልድና እድገቷ በጎንደር ከተማ ነው፡፡ በሀገር ባህል አልባሳት ሥራ ላይ የተሰማራችው ሃያት ሙያውን ከአባቷ ነው የቀሰመችው። አሁንም ከአባቷ እና ከወንድሟ ጋር በመሆን ሙያውን በማዘመን ለማሳደግ ጥረት እያደረገች ትገኛለች፡፡ ‹‹ሃያት እና አብዱልቃድር ዘመናዊ የሽመና ሥራ›› የተሰኘ ድርጅት በመክፈት ከአባቷና ከወንድሟ ጋራ ባሕላዊ አልባሳትን እያመረቱ ይገኛሉ፡፡

የእነ ሃያት አባት በሙያው ላይ ረጅም ጊዜ ቆይተዋል፤ በሽመና ሥራዎች አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎችን በመሥራት የተለያዩ ባህላዊ አልባሳትን በተለያዩ ዲዛይኖች ሲሠሩ እንደነበር ሃያት ታስታውሳለች። ‹‹የኛን ቤተሰብ ለየት የሚያደርገው የምንጠቀመውን እያንዳንዱን ልብስም ሆነ ቁሳቁስ ራሳችን የምንሰራቸው ናቸው›› የምትለው ሃያት፤ ተማሪዎች እያሉ አባታቸው የትምህርት ቤት የደንብ ልብስ (ዩኒፎርም) ሳይቀር ከሸማ ውጤቶች ያዘጋጁላቸው እንደነበር ታስታወሳለች፡፡ አልባሳቱን ከትምህርት ቤቱ የደንብ ልብስ ጋር እንዲመሳሰሉ አድርጎ ከነቦርሳው ጭምር በሽመና ይሠራልን ነበር›› ስትል ትገልጻለች፡፡

እነ ሃያት የሽመና ሥራውን ከ12 ዓመታት በላይ ቆይተውበታል። ከአባታቸው የወረሱትን ይህን የሽመና ሥራ በማስቀጠል ዘመናዊ አድርገው እየሠሩ እንደሆነ ሃያት ትናገራለች፡፡ ከልጅነቷ ጀምሮ እያየች ያደገችው የአልባሳት ሥራ ዲዛይነር የመሆን ፍላጎት እንዲያድርባት እንዲመጣም አድርጓል፤ ሙያውን በወረቀት ላይ ሳይሆን በቀጥታ በጨርቅ እየተለማመደች ሙያውን እያዳበረች መምጣቷን ትገልጻለች ፡፡

ሃያት የሽመና ሙያውን በማስቀጠል ከትውልድ ወደ ትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነት እንዳለባት ታምናለች፡፡ ከወንድሟ ጋር በመሆን የአባቷን ሙያ በማስቀጠሏም ደስተኛ ናት፡፡ ‹‹ሙያው ላይ የቆየ ልምድ ያለው አባቴ ቢሆንም፣ እኔና ወንድሜ ደግሞ ወጣቱ ምን ይፈልጋል? በምን መልኩ ቢሠራ ለየት ያሉ የፋሽን አልበሳትን መሥራት ይቻላል? የሚለው ላይ ትኩረት አድርገን አብረን ሆነን እንሠራለን፤ ለዚህም እኛ የምንለብሳቸው ልብሶች ሁሉ ዘመኑን የተከተሉ የፋሽን አልባሳት ናቸው›› ትላለች፡፡

‹‹በባህላዊ ሽመና የተዘጋጁ አልባሳት ሲባል ቶሎ ብሎ ወደ አእምሮአችንን የሚመጣው በዓላትን ጠብቀን የምንለብሳቸው የሀበሻ ልብሶች ናቸው›› የምትለው ሃያት፤ የሸማ አልባሳትን ለሁልጊዜም እንዲሆኑ አድርጎ በዘመናዊ መልኩ መሥራት እንደሚቻልም  ጠቁማለች፡፡ ድርጅታቸው በአሁኑ ወቅት አልባሳት፣ ቦርሳዎች፣ አልጋ ልብሶች፣ መጋረጃዎች፣ የጠረጳዜ ልብስ፣ የመኪና ወንበር ልብስ እና ጫማዎችም በዘመናዊ መልኩ እየሠራ ለገበያ ያቀርባል፡፡

ድርጅታቸው የሀበሻ አልባሳትን ዘመናዊ ሆነው ሁሉም ሰው ወዶ የሚለብሳቸው እንዲሆኑ በማድረግ ይሰራቸዋል፡፡ ሙሉ ቀሚስ፣ ጉርድ፣ አጭር ቀሚስ፣ ሱሪ፣ የእስልምና እምነት ተከታዮች የሚለቡሷቸው ጀለቢያና ሙሉ ለሙሉ ጀለቢያ፣ ፓኪስታን ሻል የሚባል ሙስሊም ወንዶች ከጀለቢያ በላይ የሚለብሱት ልብስና የመሳሰሉትም ድርጅቱ ከሚያመርታቸው መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

በድርጅቱ ጥራት ያላቸው የሽመና ምርቶች እንደሚሠሩ የምትገልጸው ሃያት፣ እነዚህም ምርቶቹ የፋብሪካ ምርቶችን ሊተኩ የሚችሉ እንደሆኑ ነው የተናገረችው፡፡ ጥራታቸውን የጠበቁ መሆናቸው ከሀገር ውስጥ ገበያም አልፎም ተርፎ ለውጭ ገበያ እንደሚመጥኑ ትገልጻለች፡፡

አባታቸውም ወደ ሙያው ሲገቡ የሽመናና የልብስ ስፌት ሥልጠና ወስደው እንደነበር አስታውሳ፣ ይህም አዳዲስ የፈጠራ ሃሳቦችን እያፈለቁ የተለያዩ የፋሽን ዲዛይን ያላቸው እልባሳት እንዲሠሩ እንዳስቻላቸው አመልክታለች፡፡ የሽመናውና የልብስ ስፌቱን ሥራ በአንድ ላይ ይዘው ሲሠሩ እንደነበርም ጠቅሳ፣ እስካሁንም ራሳቸው የሸመኑትን ልብስ ራሳቸው ሰፍተው እየለበሱ እንደሆነ ትናገራለች፡፡

ቀደም ሲል በጎንደር በነበራቸው የመሸጫ ሱቅ በተለያዩ ዲዛይን የሚሠራቸው አልባሳት ለውጭ ሀገር ዜጎች ጎብኚዎች ይሸጡ እንደነበር ገልጻ፤ በአሁኑ ወቅት የሚያመርቱት መጠንና የገበያ ሁኔታው ስላልተመጣጠነላቸው ሥራቸውን ለማስፋፋት በማሰብ ሰፊ ፍላጎት ወደአለበት አዲስ አበባ መምጣታቸውን ትናገራለች፡፡

እሷ እንደምትለው፤ የእነርሱን የሽመና ሥራ ከሌላው ይለያል፤ ለእዚህም ምክንያቱ ለሽመና ሥራው የሚጠቀሙበት ማሽን ልዩ ነው፤ ይህ ማሽን ዲዛይን ተደርጎ የመጣው ከጀርመን ሀገር ቢሆንም፣ ለኢትዮጵያ ሽመና በሚመች መልኩ አባቷ ማሻሻያዎች አድርገውለታል፡፡ የማሽኑ ስፋቱ 2 ሜትር በ10 ሳንቲ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ደረጃ የመጀመሪያው ነው፡፡ በዚህም በሦስት ሸማኔ የሚሠራውን የሽመና ሥራ በዚህ ማሽን በአንድ ሸማኔ መሥራት ያስችላል፡፡ ይህ ደግሞ ጊዜንና ጉልበትን ለመቆጠብ ይጠቅማል፡፡

“የሰው ፍላጎት የተለያየ ነው፣ በጣም የሚጮህ ልብስ የሚፈልግ እንዳለ ሁሉ ዝም ያለ ቀለም ያለው ልብስ የሚመርጥም አለ” የምትለው ሃያት፤ ድርጅታቸው የሁሉንም ሰው ፍላጎት ሊያሟሉ የሚችሉ አልባሳትን ዲዛይን አድርጎ እንደሚያቀርብ ጠቁማለች፡፡

ሃያት እንደምትለው፤ ምርቶቻቸውን በአብዛኛው በውጭ ሀገር ዜጎች ተፈላጊና ተወዳጅ ናቸው፡፡ ለየት ያሉ ጥራት ያላቸው ምርቶች መያዛቸውም ገበያው ጥሩ እንዲሆን አድርጎላቸዋል። ድርጅቱ ጀሞ አካባቢም የማምረቻ ቦታ አለው፤ ሥራዎችን በትዕዛዝ የሚሠራ ሲሆን፣ ምርቶቹን በባዛርና በኢግዚቢሽኖች ላይ ያቀርባቸዋል፡፡

የድርጅቱ ምርቶች ጥራት የተጠበቀ መሆኑን ገልጻ፣ ልምዳቸውን የሚያጋሩበት የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ወደ ተለያዩ ሀገራት እንደሚሄዱም አስታውቃለች፡፡ ይህንን ሙያ ለመማር ለሚፈልጉ ብዙ ሰዎች ሥልጠና መስጠታችውን ጠቅሳ፤ ሥልጠናውን ከወሰዱት ውስጥ በአብዛኛው ሴቶች መሆናቸውን ትናገራለች፡፡ ከሥልጠናው በኋላ ብዙዎቹ በራሳቸው እያመረቱ መሸጥ ውስጥ መግባታቸውንም ጠቅሳለች። እነ ሃያት ሙያውን የበለጠ ለማሳደግና ባሕላዊ ልብሶች ይዘታቸውን ሳይለቁ እንዲዘምኑ ለማስቻል ከሥራቸው ጎን ለጎን ራሳቸውን በትምህርት እያበቁ ናቸው፡፡

እነ ሃያት የፋሽን አልባሳቱን ከሠሩ በኋላ ማህበራዊ የሚዲያ አማራጮችን (ፌስቡክ፣ ቴሌግራም፣ ኢንስታግራም፣ ቲክቶክ) በመጠቀም ያስተዋውቃሉ፡፡ ቀደም ሲል ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ ያቀርቡ የነበረው በትውውቅ ነበር፤ የገበያ መዳረሻዎቻቸውም ካናዳ፣ አሜሪካና ፈረንሳይ ነበሩ፡፡ አሁን ላይ ግን ለሀገር ውስጥ ገበያ ብቻ ያቀርባሉ፡፡

ምርቶቻቸው ከጥራቱ አንጻር ዋጋቸውም ቢሆን ተመጣጠኝ የሚባል እንደሆነ የምትናገረው ሃያት፣ አልባሳቱ ከሚፈጁት ጊዜና ከሚወጣባቸው ጉልበት እንዲሁም ከጥሬ እቃው አቅርቦት አንጻር ዋጋቸው እንደሚሰላም ገልጻለች፡፡ የእያንዳንዱ ምርት ዋጋም እንደወቅቱ ሁኔታ እንደሚለያይ አስታውቃለች፡፡

“የሀገራችንን ምርቶች እኛ ለብሰን ካልደመቀንባቸው፣ ካልኮራንባቸውና ካላስተዋወቅናቸው ማን ሃላፊነቱን ይወስድልናል” የምትለው ሃያት፤ ሙያው እንደ ሙያ፤ ባለሙያው እንደ ባለሙያ ተከብሮ እንዲኖር ሁሉም የበኩሉን ኃላፊነት መወጣት አለበት ስትል ታስገነዝባለች፡፡ ወጣቱም በዚህ ሙያ ተሰማርቶ የሀገሩን ምርት በማምረት ለራሱም ለሀገሩም መትረፍ ይችላል ስትል ምክረ ሃሳቧን ለግሳለች፡፡

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን   ኅዳር 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You