ኢትዮጵያ ውስጥ በመንግሥት ከሚተዳደሩና ስኬታማ ከሆኑ ድርጅቶች መካከል ግንባር ቀደሙ ነው። ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ላይ በማስተዋወቅም እንዲሁ ይጠቀሳል፡፡ በዓለም የአቪየሽን ኢንዱስትሪ አየር መንገዱ በሚሰጣቸው ቀልጣፋና ምቹ አገልግሎቶቹ የተነሳ ተፈላጊነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፤ የተሰጡት እውቅናዎችና ሽልማቶችም እንዲሁ በርካታ ናቸው፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፡፡
የኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ኩራት የሆነው ይህ አየር መንገድ አገሪቱ አሉኝ ከምትላቸው አንጡራ ሃብቶቿ መካከል አንዱና ትልቁ ሀብቷ ነው። በሚሰጣቸው አገልግሎቶቹ ከኢትዮጵያም አልፎ በአፍሪካ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን በቅቷል፡፡ በየጊዜው በሚያስመዘግበው ውጤትም ከስኬት ማማ ላይ በመውጣት አይነ ግቡ መሆኑን ቀጥሏል፡፡
ከሰባት አስርት ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው አንጋፋው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጉዞው የተሳካ፣ የተቃናና ትርፋማነቱም አስተማማኝ በሚባል ደረጃ ላይ ስለመሆኑ ያለፉት ዓመታት አፈጻጸሞቹ ይመስክራሉ፡፡
ከፍተኛ ዕድገት የማስመዝገብ አቅም እንዳለው በተጨባጭ ማሳየት የቻለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስም ሲነሳ ለኢትዮጵያውያን በሙሉ መኩሪያና መመኪያ መሆኑም አብሮ ይነሳል፡፡ በሚሰጣቸው ቀልጣፋ፣ ምቹና ዘመናዊ አገልግሎቶቹ የኢትዮጵያን ስም በመላው ዓለም በበጎ እንዲነሳ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ሊጠቀስ ይገባዋል፡፡
ይህ በአፍሪካም በዓለም አቀፍ ደረጃም ታዋቂ የሚባሉ አየር መንገዶችን በመወዳደር ታዋቂ መሆን የቻለው ግዙፍ ተቋም በአስገራሚ የዕድገትና የለውጥ ግስጋሴ ላይ ስለመሆኑ ሌሎች ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ አየር መንገዱ የአቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ እና ብዙ ቢሊዮን ብር አውጥቶ የገነባው ዘመናዊ ሆቴል ባለቤትም ነው፡፡ የካርጎ አገልግሎት በመስጠትም ይታወቃል፡፡ በአሁኑ ወቅትም አየር መንገዱ ፈተናዎችን ተቋቁሞ ግስጋሴውን በድልና በትርፋማነት የቀጠለ ሲሆን፤ በአፍሪካ ያለውን የቀዳሚነት ስፍራ ማስጠበቅ የሚያስችሉ በርካታ ስኬቶችንም እያስመዘገበ ይገኛል፡፡
ይህ በስኬት ጎዳና ላይ መረማመድን በእጅጉ የተለማመደ ተቋም፣ በቅርቡም በአየር መንገዱ ታሪክ ትልቁ የተባለውና በአፍሪካ አቪዬሽን ታሪክም የመጀመሪያ የሆነውን 67 ቦይንግ ጀት አውሮፕላኖች ለመግዛት ከቦይንግ ኩባንያ ጋር ስምምነት ፈርሟል። በተመሳሳይም ኤር ባስ ከተባለው ኩባንያ ጋርም እንዲሁ 11 ኤር ባስ አውሮፕላኖችን ለመግዛት ስምምነት ተፈራርሟል፡፡ እነዚህ ስምምነቶች አየር መንገዱ በ2035 አሳካዋለሁ ብሎ የያዘውን ራዕይ ለማሳካት ትልቅ ግብዓት በመሆን እንደሚያገለግለው ታምኖበታል፡፡ ስምምነቱ በአፍሪካ ቀዳሚነቱን አጠናክሮ ማስቀጠል የሚያስችለው እንደሆነም ከአየር መንገዱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
በቅርቡ ዱባይ በተካሄደው የ2023 የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ ዓውደ ርዕይ ላይ የተገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ በአንድ ሳምንት ውስጥ 78 አውሮፕላኖችን ለመግዛት ነው ከአሜሪካዎቹ ቦይንግ እና ኤር ባስ ኩባንያዎች ጋር ስምምነት ያደረገው። ከኤር ባስ ኩባንያ ጋር ያደረገው ስምምነት 11 “ኤርባስ ኤ350-900ኤስ” አውሮፕላኖችን ለመግዛት ያስችለዋል። ስምምነቱ እንደ አስፈላጊነቱ ተጨማሪ ስድስት አውሮፕላኖችን ማዘዝ የሚያስችል ዕድል የተካተተበት ነው፡፡ “ኤ350 ኤር ባስ” አውሮፕላን ዘመናዊ እና ቀልጣፋ ሰፊ ሰው ጫኝ እና ከ300 እስከ 410 መቀመጫዎች ያለው የረጅም ርቀት አውሮፕላን ነው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦይንግ ኩባንያ ጋር ባሰረው ውል ለመግዛት ከሚያዛቸው 67 አውሮፕላኖች መካከል 11 ዱ “787 ድሪምላይነር” እና 20ዎቹ “737 ማክስ” አውሮፕላኖች ሲሆኑ፣ 36ቱ ደግሞ ሌሎች አውሮፕላኖች ናቸው፡፡
አውሮፕላኖቹ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ አየር መንገዱ እጅ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። አዳዲሶቹ አውሮፕላኖች የተሻሻሉ ሞዴሎች መሆናቸውና የነዳጅ አጠቃቀማቸው ውጤታማነት ከቀደሙት አውሮፕላኖች አንጻር 20 በመቶ የበካይ ጋዞችን ልቀት እንደሚቀንሱ፣ 50 በመቶ የድምፅ ብክለትን እንደሚያስቀሩም መረጃዎች ያመለክታሉ።
የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ከሁለት ወራት በፊት በቱርክ የኢኮኖሚ መዲና ኢስታምቡል በተካሄደው የዓለም አቪዬሽን ጉባዔ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2035 ላይ የአውሮፕላኖቹን ቁጥር 271 የማድረስ እቅድ እንዳለው ማስታወቃቸው ይታወሳል። የ 130 አውሮፕላኖችን ግዢ እንደሚፈጸምም ገልጸው ነበር። ሁለቱ ስምምነቶች አየር መንገዱ በ2035 ለመድረስ ያስቀመጠውን ራዕይ መሠረት ያደረጉ ስለመሆናቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።
አየር መንገዱ በቅርቡ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች በተገኙበት ከፍተኛ እምርታ ያስመዘገበበትን የካርጎ ደንበኞች ቀንንም አክብሯል። በዕለቱ የተገኙት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ67 በላይ በሆኑ መዳረሻዎቹ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የካርጎ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭ የካርጎ አየር መንገድ መሆን ችሏል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ካርጎ አገልግሎት በአፍሪካ ትልቁ የአየር ጭነት አጓጓዥ ነው። 16 አውሮፕላኖችን ለካርጎ አገልግሎት መድቦ አስተማማኝ የካርጎ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን፣ በካርጎ አገልግሎቱ ባለፈው ዓመት ብቻ 740 ሺህ ቶን ጭነት አጓጉዟል።
በተያዘው በጀት ዓመትም የካርጎ አገልግሎቱን ወደ አንድ ሚሊዮን ለማሳደግ እየሠራ ነው። አየር መንገዱ የካርጎ ደንበኞች ቀንን ሲያከብር በዘጠኝ የኤክስፖርት ምድቦች ከፍተኛ አፈፃፀም በማስመዝገብ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ለያዙ 27 ኤክስፖርተሮች እውቅና ሰጥቷል። ዕውቅና የተሰጣቸው ኤክስፖርተሮችም ዕውቅናው በቀጣይ ተግተው መሥራት የሚያስችላቸው እንደሆነና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በካርጎ አገልግሎቱ አመርቂ ውጤት እያስመዘገበ እንደሆነ አስታውቀዋል። በዚህም የሀገሪቱ የወጪ ንግድ እንዲያድግ በማድረግ የውጭ ምንዛሬ ግኝቱን ማሳደግ የሚያስችል እንደሆነም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ወቅት 147 አውሮፕላኖች ያሉት ሲሆን፣ ከቦይንግ እና ከኤር ባስ የታዘዙት 78 አውሮፕላኖች ሲጨመሩ የአውሮፕላኖቹ ቁጥር ወደ 225 ከፍ ይላል። የአየር መንገዱ የግዢ ስምምነት የደንበኞቹን ምቾትና ፍላጎት በመጠበቅ ተመራጭነቱን ለማሳደግና ተደራሽነቱን ለማስፋት ከአፍሪካ ቀዳሚ አየር መንገድ ሆኖ መዝለቅ እንዲችል እንደሚያግዘው ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለደረሰበት ለእዚህ ሁሉ ስኬት የበቃው በበርካቶች አስተዋጽኦ እንደሆነ የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው በአንድ ወቅት ከፋና ብሮድካስቲንግ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ አየር መንገዱ እንደ ዕድል ሆኖ ጥሩ ጥሩ ሥራ አስፈጻሚዎች ገጥመውታል፡፡ በተለያየ ጊዜ አየር መንገዱን የመሩ የሥራ ኃላፊዎች በሙሉ ድርጅቱ እንዲያድግ፣ ትርፋማና ተወዳዳሪ እንዲሆን ከፍተኛ ድርሻ ነበራቸው፡፡ በተለይም መሰረተ ልማቶችን በማሟላት የሰው ኃይሉን በዕውቀት፣ በችሎታ ሲያንጹና ሲቀርጹ ኖረዋል፡፡ በመሆኑም በእነዚሁ ትጉህ አመራሮች አማካኝነት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሁልጊዜም ቀዳሚና ተመራጭ ሆኖ በድልና በስኬት ወደፊት እንዲጓዝ አስችሎታል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድን ስኬታማ እንዲሆን ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ሌላው የአገሪቷ መልከዓምድራዊ አቀማመጥ ስለመሆኑም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ኢትዮጵያ ለአረቡ ዓለም ለአውሮፓም ጭምር በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኝ መሆኗ እንዲሁም በአሜሪካና በቻይና መካከል መገኘቷ አየር መንገዱ ትርፋማ እንዲሆን ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ መሆኑም ይገለጻል፡፡
እንደ ሌሎች የአየር መንገዶች ሁሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ፈተናዎች አጋጥመውት እንደነበረ ያስታወሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ያም ቢሆን ጥንካሬውን ይዞ መቀጠል እንደቻለ ነው የተናገሩት፡፡ ሌሎች አየር መንገዶች የሚገጥማቸውን ፈተና መቋቋም ሳይችሉ በመቅረታቸው ሲንኮታኮቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን በተለይም አፍሪካ ውስጥ ካሉ አየር መንገዶች በብዙ መንገድ ቀዳሚ መሆን ችሏል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አንድ አይነት አውሮፕላን ሲገዛ አቅም አብሮ የሚገነባ መሆኑንም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ለእዚህ አብነት አንስተዋል። የጥገና አቅም፣ የበረራ አቅም፣ ፓይለቶችን በራሱ አቅም የማሰልጠን አቅም መገንባቱን ጠቅሰው፣ ቴክኒሻኖችንም እንዲሁ በውስጥ የማሰልጠን አቅም ያለውና ከዚህ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን አቅም በመገንባት ጭምር ወደፊትም የዕድገት ግስጋሴውን የሚቀጥል እንደሆነ ነው ያረጋገጡት፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪውን ጠንቅቆ እንደሚያውቅ የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ከሌሎቹ አየር መንገዶች ለአብነትም ከሉፍታንዛ፣ ከኤምሬትስና ከሌሎቹም ባልተናነስ መልኩ ኢንዱስትሪውን እንደሚያውቀው ገልጸዋል፡፡ ይህ ሁሉ አየር መንገዱ ወደ ጎን የሚተው እንዳይሆን እንዳደረገው አስታውቀዋል፡፡ በዚህ የተነሳም አየር መንገዱ ከቦይንግ ኩባንያ ጋር ያለው ግንኙነት እጅግ ጥብቅ የሆነና በከፍተኛ ጥንካሬ፣ በዕውቀትና በአቅም ላይ የተመሰረተ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የአየር መንገዱ ፈተናዎችን ተረማምዶ ማለፍ ሲነሳ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ዓለምን ከእንቅስቃሴ ባቀበበት ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያስችሉ መዳህኒቶችን በማጓጓዝ፣ አየር መንገዶች ሁሉ በተዘገቡት በዚያ ወቅት አገልግሎት በመስጠት መላ ዓለምን ከክፉ ቀን የታደገ በመሆኑም ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያም አልፎ ለአፍሪካውያን ኩራት መሆን የቻለ ግዙፍ ተቋም እንደሆነ በብዙዎች ዘንድ የሚታመን ሃቅ ነው፡፡ በመሆኑም አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርጉትን ዘመናዊ መሰረተ ልማቶችና አገልግሎቶች በማሟላት እንዲሁም ባለሙያዎችን በዕውቀት በማነጽ ከአገር ልጆች አልፎ የውጭ ዜጎችን ጭምር በማሰልጠን ሁለንተናዊ በሆነ መንገድ ከከፍታው ከፍ እያለ መብረሩን የቀጠለ ስኬታማ ተቋም መሆን የቻለ አንጋፋና ግዙፍ ተቋም ነው፡፡
ከቀድሞው ትራንስ ወርልድ ኤር ዌይስ ጋር የተመሰረተው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ተመራጭና አሉ ከሚባሉ አየር መንገዶች መካከል መጠቀስ ችሏል፤ በአፍሪካ ቀዳሚው አየር መንገድ መሆን ችሏል፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ አየር መንገዱ ሲመሰረት ከአሜሪካ ወታደራዊ ኃይል የተገዙና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ያገለገሉ አምስት ዲሲ አውሮፕላኖች ብቻ ነበሩት፡፡ የመጀመሪያ በረራውንም አሀዱ ያለው ከአዲስ አበባ ወደ ግብጽ ካይሮ በመብረር ነው፡፡ ይህም በ1938 ዓ.ም መጋቢት 30 ቀን የተደረገ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ በአፍሪካ፣ በእስያ፣ በአውሮፓና በአሜሪካ ክፍለ አጉራት በ127 መዳረሻዎቹ የመንገደኛና የጭነት አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፣ በአገር ውስጥ ደግሞ 22 መዳረሻዎች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የራሱ የአውሮፕላን አብራሪዎች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ሲኖረው የግል አብራሪና የግል አውሮፕላን አብራሪ ፈቃድ በመስጠት የአገር ልጆችንም ሆነ የውጭ ዜጎችን በማሰልጠን የ40 ዓመታት ልምድ እንዳለውም ይታወቃል፡፡
ለበርካታ የአፍሪካ አገራት ብሔራዊ አየር መንገዶች እና የግል አውሮፕላኖች የጥገና አገልግሎት ይሰጣል፡፡ የናይጄሪያና አንዳንድ አገራት አየር መንገዶችን ደግሞ በሼር ያስተዳድራል፡፡ የኢትዮጵያውያን ሃብት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመንገደኞች አገልግሎት የሚውል አዲስና ዘመናዊ ቦይንግ 787 ድሪም ላይንር አውሮፕላን በማዘዝና ጥቅም ላይ በማዋል ከአፍሪካ የመጀመሪያው አየር መንገድ በመሆን ይጠቀሳል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ሽልማቶችና እውቅናዎች በማግኘትም ይታወቃል፡፡ በአቬየሽን ኢንዱስትሪው በየዓመቱ በሚደረጉ የእውቅናና የሽልማት ስነስርዓቶች ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አይታጣም። ለእዚህም ከአውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር 2020 ጀምሮ እስካሁን ድረስ “የአፍሪካ ምርጡ አየር መንገድ” የሚል ሽልማት “Business Traveller Awards” ማግኘቱን በአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ህዳር 15/2016