የዘንድሮ የአስራ ሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች ሆይ! መቼም በ2015 ዓ.ም የመልቀቂያ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎችን ውጤት ሰምታችኋል፡፡ እጅግ አስደንጋጭ ነበር፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ 3 ነጥብ 2 ከመቶ ያህሉ ብቻ ተማሪዎች ነበሩ ፈተናውን ማለፍ የቻሉት፡፡ ይህ የሆነው ታዲያ አንድም የፈተና ቁጥጥሩ ከዚህ ቀደም ከነበረው ጠንካራ በመሆኑና በተማሪዎች በኩል ለፈተናው የተደረገው ዝግጅት በቂ ባለመሆኑ ነው፡፡ እናም ዘንድሮ ደግሞ እናንተ ይህንን የመልቀቂያ ፈተና ለመውሰድ ተረኞች ናችሁ።
ምንም እንኳን በ2015 ዓ.ም የተመዘገበው ውጤት አስደንጋጭ ቢሆንም እናንተ በዚህ ውጤት መደንገጥ የለባችሁም፡፡ ይህን ውጤት እንደመማሪያ እንጂ ተስፋ መቁረጫ አድርጋችሁ መውሰድ አይጠበቅባችሁም፡፡ ብልህ ተማሪ ከሌሎች ውድቀት ነው የሚማረው፡፡ ጎበዝ ተማሪ ራሱን የሚያዘጋጀው ገና ከአሁኑ ነው፡፡ ጎበዝ ገበሬ ቀደም ብሎ ማሳውን በሚገባ ስለሚያዘጋጅና ወቅቱን ጠብቆ ስለሚዘራ ነው መልካም አዝመራን የሚያጭደው፡፡ ጎበዝ ተማሪም ጥሩ ውጤት ማምጣት ከፈለገ ገና ከአሁኑ ነው ራሱን ማዘጋጀት የሚጠበቅበት፡፡
እናም ተማሪዎች ዓላማችሁን ስታውቁት ከእናንተ በላይ ጎበዝ የሚሆን፤ የሚፈልገውን የሚያሳካ የለም፡፡ አይደለም ለራሳችሁ ለማንም ትተርፋላችሁ፡፡ ለቤተሰቦቻችሁ ኩራት መሆን ትችላላችሁ፡፡ ሕልማችሁን መኖር ትችላላችሁ፡፡ ማንም ከእናንተ ብዙ ነገር ቢጠብቅ አትፍረዱበት። ጎበዝም ብትሆኑ፤ ዩኒቨርሲቲ እንድትገቡ ቢጠብቅ እናንተ አትፍረዱበት፡፡ ስለሚገባችሁ ነው፡፡ በቃ ትልቁ ቦታ ይገባችኋል፡፡ ለዛ ነው ሕይወታችሁን መቀየር ያለባችሁ፡፡
አንድ ምሳሌ ልንገራችሁ! ሁለት ወንድማማቾች ናቸው፡፡ የአንድ እናትና የአንድ አባት ልጆች። አንደኛው ሰካራም፣ ተደባዳቢ፣ ሌባ፣ ቀማኛና ወንበዴ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ጠበቃ ነው፡፡ የሕግ ሰው፣ የተከበረ፣ ሰዎች የሚወዱት ትልቅ ተከፋይ ጠበቃ ነው፡፡ እርሱን ጥብቅና ያቆመ ድርጅትና ግለሰብ የማይረታው ጉዳይ የለም፡፡ በጣም ስኬታማ ጠበቃ ነው፡፡ ሁለቱ ወንድማማቾች ተጠየቁ። እንዴ! አንድ ቤት ነው ያደጋችሁት፡፡ ወንድምህ ነው፣ ያውም የሥጋ፡፡ አንተ እንዴት ጠበቃ ልትሆን ቻልክ? አንተኛውስ እንዴት ዱርዬና ሰካራም ልትሆን ቻልክ? ተባለ፡፡
ሰካራሙ ‹‹አባቴ ነዋ! አባቴ እኮ ሰካራም ነው። ማታ ጠጥቶ እየመጣ እናቴን ይደበድባታል። ታዲያ እሱን እያየሁ አድጌ እንዴት ነው ሰካራም የማልሆነው›› ሲል መለሰ፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አንተስ ምን ብታደርግ ነው ጥሩ ጠበቃ ልትሆን የቻልከው? ከአንድ ቤት ወጥተህ ያውም ወንድምህ ሰካራምና ሌባ ሆኖ ተብሎ ሲጠየቅ ‹‹አባቴ ነዋ!›› አለ፡፡ እንዴት? ሲባል ‹‹አባቴ እናቴን ማታ ጠጥቶ ገብቶ ሲደበድባት እያየሁ እንደእሱ አይነት ሰው አልሆንም ብዬ ለራሴ ቃል ገባሁ፡፡ በፍፁም እንደሱ አልሆንም ብዬ ቃል ገባሁ፡፡ ራሴን ለውጥኩኝ›› አለ፡፡
ሁለቱም ልጆች የገጠማቸው ችግር ተመሳሳይ ነው፡፡ ሁለቱም በከባድ ሁኔታ ውስጥ ሆነው በአንድ ቤት ውስጥ ነው ያደጉት፡፡ አንደኛው ጠበቃ ሆነ፡፡ ሌላኛው ደግሞ ሌባ፡፡ ስለዚህ ሕይወትን የሚቀይረው ምርጫ ነው፡፡ ሕይወትን የሚቀይሩት ሁኔታዎች አልያም ደግሞ ሰዎች አይደሉም የሚቀይሩት፡፡ ተማሪዎች ቁርጣችሁን እወቁ! አስማሪዎቻችሁን ጎበዝ ማድረግ አትችሉም፡፡ የአስራ አንደኛና አስራ ሁለተኛ ክፍልን ብቻ ነው የምፈተነው ማለት አትችሉም፡፡ ከዘጠነኛ እስከ አስራ ሁለተኛ የክፍል ደረጃ ያለውን ነው የምትፈተኑት፡፡
ስለዚህ መቀየር የማትችሉትን ነገር መቀበል ነው ያለባችሁ፡፡ ዝናቡን ልታቆሙት አትችሉም። ዣንጥላ ግን ትዘረጋላችሁ፡፡ ቢደበድባችሁ ተጠያቂው እናንተ ናችሁ፡፡ ለምን ዝናብ ዘነበ ማለት አትችሉም፡፡ ለምን አልተጠለልንም ነው መልሱ።አያችሁ! አሁን በዚህ ሰዓት ከባድ ሁኔታ ውስጥ እንዳላችሁ ሁሉም ይረዳችኋል፡፡ ጥሩ አድርጋችሁ አልተማራችሁም። አንዳንዴ መሸፈን የሚገባችሁን ያህል ምዕራፍ ጨርሳችሁ ላይሆን ይችላል፡፡
ከዛም ወደ ፈተና ትገባላችሁ፡፡ ከባድ ነው፡፡ ከዛ ደግሞ ዩኒቨርስቲ እንድትገቡ ትጠበቃላችሁ፡፡ ለጥቆ ደግሞ የሆነ ቦታ እንድትደርሱ ትፈለጋላችሁ፡፡ ነገር ግን በዚህ ሁኔታ ውስጥ መቀየር የማትችሉትን መቀበል አለባችሁ። ‹‹በቃ! አዎ እውነት ነው፡፡ እኔ የቤተሰቦቼን አስተሳሰብ መቀየር አልችልም። አስተማሪዬን መቀየር አልችልም፡፡ ሁኔታዎችን መቀየር አልችልም፤ መቀየር የምችለው አንድ ነገር ነው እርሱም ራሴን ነው›› ማለት አለባችሁ፡፡
ራሳችሁን ለመቀየር መነሳት አለባችሁ፡፡ ለምን መሰላችሁ መቀየር የምትችሉት ራሳችሁን ነዋ! ያላችሁ እድል እሱ ነው፡፡ እጃችሁ ላይ ላለው መታመን ያለባችሁ ራሳችሁ ናችሁ፡፡ ምንድን ነው ማድረግ ያለብኝ ታዲያ ጎበዝና ውጤታማ እንድሆን?፣ ቤተሰቦቼን እንዳስደስት ምንድን ነው ማድረግ ያለብኝ? ከኔ ምን ይጠበቃል? ካላችሁ….
አሁን በዚህ ሰዓት እጃችሁ ላይ ያለው ነገር ትምህርታችሁ ነው፡፡ ሌላ እጃችሁ ላይ ምንም ነገር የለም፡፡ ትምህርታችሁ ላይ ጎበዝ ከሆናችሁ ነገ በምትፈልጉት ጉዳይ ስኬታማ ትሆናላችሁ። ትንሹ ላይ ስትታመኑ ትልቁ ላይ ትሾማላችሁ፡፡ ለምሳሌ ትምህርት አልወድም ልትሉ ትችላላችሁ። ማን ይወዳል? ማንም እኮ አይወድም፡፡ ግን ምን ታደርጉታላችሁ የግድ መማር አለባችሁ፡፡ እንቁራሪት መብላት ግዴታችሁ ቢሆን ምን ታደርጋላችሁ? የምትወዷቸውን ሰዎች አጠገባችሁ አስቀምጠው ይህን እንቁራሪት ካልበላችሁ እጨረሳችኋለሁ ብትባሉ ምንድን ነው የምታደርጉት? ምርጫ የላችሁም ትበሉታላችሁ፡፡
እንደውም ብራያት ሬሲ የተሰኘ አንድ ታላቅ ደራሲ ‹‹Eat That Frog›› የሚለው መጽሐፉ እንቁራሪት መብላት ግዴታችሁ ከሆነ ሁለት ነገር ከሆነ ሁለት ነገር እመክራችኋለሁ ይላል፡፡ የመጀመሪያው መጨፈን ነው፡፡ ከዚያም ትልቁን አስቀድማችሁ ብሉት፡፡ ይህ ማለት አንዳንድ ግዜ መብላት ያላባችሁ ግዴታ የሆነ እንቁራሪት በሕይወታችሁ አለ፡፡ ከዚህ ውስጥ አንዱ ትምህርት ነው፡፡ ትምህርት ስትማሩ ደስ ላይል ይችላል፡፡ ግን ደግሞ መማር ግዴታ ነው፡፡ አሁን ከተወጣችሁት ግን ነገ የምትስቁት እናንተ ናችሁ፡፡
ለማንኛውም አሁን በዚህ ሰዓት እናንተ በትምህርታችሁ ደስተኛ ላትሆኑ ትችላላችሁ። ‹‹እዚህ ትምህርት ቤት የምመጣው እኮ ለእናቴና ለአባቴ ብዬ ነው፤ ለማን ብዬ ነው›› እያላችሁ ሊሆን ይችላል፡፡ ችግር የለውም ወደ ትምህርት ቤት ኑ፡፡ ምንም ችግር የለውም ተማሩ፡፡ እጃችሁ ላይ ላለው ለትምህርታችሁ ታመኑ፡፡ አሁን በዚህ ሰዓት ፊዚክስ ከብዶህ ሊሆን ይችላል፡፡ ከገባውና ከጎንህ ካለው ጎበዝ ተማሪ ተረዳ፡፡ ሂሳብ ከብዶሽ ሊሆን ይችላል። ቆንጆ አድርጎ የሚያስረዳ መምህር ካለ እርሱን ተከታታይ፡፡ ዛሬን ታመኑ፡፡ መማር ምን ይጠቅማል መሰላችሁ? አሁን ተምራችሁ የት ልትደርሱ ነው የሚሉትን ተዋቸውና የምትወዱትን የምትማሩ ከሆነ ማንም አይደርስባችሁም፡፡
አንድ ምሳሌ እንካችሁ፡- አስር ሰዎች ናቸው፡፡ አንድ ቤት ውስጥ ለጥ ያለ እንቅልፍ ወስዷቸዋል። እዛ ቤት ውስጥ ለአንድ ሰው ብቻ የሚበቃ ምግብ አለ፡፡ ዝም ብላችሁ አስቡት፡፡ ማን የሚበላ ይመስላችኋል? ቀድሞ የተነሳው ነው ምግቡን ሊበላ የሚችለው፡፡ እንግዲህ መማር ማለት በተኙት መካከል መንቃት ነው፡፡ ስለችግሩ አብዝቶ ማውራት መፍትሔ አያመጣም፡፡ ‹‹አስተማሪው እንዲህ አድርጎኝ፣ ከባድ ነው ትምህርቱ›› ብትሉ ማንም አይሰማችሁም፡፡ ችግሩን አትፈቱትም፡፡ ጨለማን እየተራገማችሁ ብርሃን አታመጡም፡፡ ስለብርሃን ማሰብና ወደተግባር መግባት ነው የሚያስፈልገው፡፡
‹‹ራሴን የምቀይረው እኔው ነኝ ማንም አይደለም የኔን ሕይወት ሊቀይር የሚችለው›› ማለት አለባችሁ፡፡ ደሞም ፈጣሪ በሁላችሁም ውስጥ አንድ ትልቅ ኃይል አስቀምጧል፡፡ ቆፍራችሁ እስክታወጡት ድረስ ነው፡፡ ትንሽ ሰነፍ እንደሆንን የምናስበው አንዳንዴ ‹‹እኔ እኮ እጥራለሁ፤ አነባለሁ ግን ጥሩ ውጤት አላመጣም፣ ቤተሰቦቼ አይረዱኝም አስተማሪዎቼ አይረዱኝም ምን ላድርግ፤ መለወጥ እኮ እፈልጋለሁ›› ትሉ ይሆናል፡፡ እናንተ ውስጣችሁ ያለውን ነገር አልገባችሁም፡፡ ከቻላችሁ ‹‹ምንድነው የምፈልገው?›› ብላችሁ ማሰብ ጀምሩ፡፡ ምንድን ነው የምትፈልጉት? ዓላማችሁን ለማወቅ ሞክሩ፡፡ ዓላማን ማወቅ ጎበዝ መሆንን አይጠይቅም፡፡ ከእናንተ የሚጠበቀው ዓላማችሁን ለማወቅ ፍቃደኛ መሆን ነው፡፡
‹‹የዛሬ አስር ዓመት ከእንቅልፌ ስነቃ ምን አይነት ቦታ ላይ ነው ራሴን የማገኘው?›› ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ፡፡ የዛሬ ዓመት፣ አምስትና አስር ዓመት የት ነው የምደርሰው? ምን አይነት ቦታ ላይ ራሴን ባገኝ ነው ደስ የሚለኝ?›› በሉ፡፡ ዝም ብላችሁ አስቡት፡፡ ‹‹ቤተሰቦቼን ማስደሰት የምችለው ምን አይነት ቦታ ላይ ስደርስ ነው? ከአስር ዓመት በኋላ ምን አይነት ሁኔታ ላይ ብሆን ነው እኔስ ደስተኛ የምሆነው?›› ብላችሁ አስቡ፡፡ ዓላማን ማወቅ ጉብዝና፣ ጥበብ፣ ችሎታና ክሂል አይጠይቅም፡፡ ቁጭ ብሎ ራስን መጠየቅ ነው፡፡
አንድ ታሪክ እንካችሁ፡- የአስራ ሦስት ዓመት ታዳጊ ነው፡፡ እግር ኳስ ለመጫወት ሁሌም ወደ ሜዳ ይሄዳል፡፡ ሁሌም ቢሆን ልምምድ ቦታ አይቀርም፡፡ ግን ኳስ አይችልም፡፡ እንዲሰለፍም አይፈቀድለትም። ሁሌ ወደ ሜዳ መጥቶ ይለማመዳል፡፡ ጥግ ላይ ሆኖ አባቱ ያየዋል፡፡ የሆነ ግዜ ግን ልጁ ጠፋ፡፡ ለአራት ቀን ወደ ሜዳ አልመጣም፡፡ በአምስተኛው ቀን ልጁ እዛ ሜዳ ተከሰተ፡፡ ልክ ሲመጣ የእርሱ ቡድን ግጥሚያ ነበረው፡፡ ከዛም ወደ አሠልጣኙ ጠጋ ብሎ አሰልፈኝ አለው፡፡ አሠልጣኙም እየሳቀ ‹‹አንተ ትቀልዳለህ እንዴ የት ኳስ የምትችለውን ነው የማሰልፍህ፤ ደሞም የት ጠፍተህ ነው የመጣኸው በል ዞር በል አለው፡፡
ልጁ ግን ካላስገባኸኝ ብሎ ድርቅ አለ። ከዛም አሠልጣኙ ‹‹ይሄ ልጅ ምን ታይቶት ነው እንደው አስገብቼ ልሞክረው እንዴ›› ብሎ አሰለፈው። ያ የማይችለው ልጅ ወደ ሜዳ ገብቶ ተጫወተ። በእርሱ ምክንያት ቡድኑ አሸነፈ፡፡ ብዙ ጎሎች አገባ። አሠልጣኙም ደነገጠ፡፡ ጨዋታው ሲያልቅ ልጁን ጠርቶት ‹‹አንተ እስከዛሬ ድረስ ለምንድን ነው ያልተጫወትከው፤ ዛሬ ምን አግኝተህ ነው?›› ብሎ ጠየቀው፡፡ ልጁ መለሰ … አባቴ ስለሚያየኝ ነው አለ። አሠልጣኙ ገርሞት ዞር ዞር ብሎ ሲያይ ማንም የለም። ‹‹ምንድን ነው የምትዋሸው ማንም የለም እኮ›› አለው፡፡ ልጁም ቀጠለና ሁልጊዜ ለልምምድ አንተ ጋር ስመጣ አባቴ እዛ ጋር ቁጭ ብሎ ያየኛል፡፡ ግን ዓይነ ስውር ነበር፡፡ ከአራት ቀን በፊት ግን ሞተ፡፡ ዛሬ ከላይ ሆኖ እንደሚያየኝ እርግጠኛ ስለሆንኩ ነው እንደዚህ የተጫወትኩት›› አለው፡፡
አስባችሁታል ይህ ልጅ ሰነፍ ስለሆነ አይደለም። ግን አባቴ ካላየኝ ለምን እጫወታለሁ ብሎ ስለሚያስብ ነው በደምብ ያልተጫወተው፡፡ ዛሬ ግን ሲሞት ከላይ ሆኖ ያየኛል ብሎ እርግጠኛ ሆኖ ከልቡ ተጫወተ። እናንተም ተማሪዎች ሁላችሁም የሚገርም አቅም አላችሁ፡፡ አይደለም ለራሳችሁ ለማንም ትተርፋላችሁ፡፡ ለቤተሰቦቻችሁ ኩራት መሆን ትችላላችሁ፡፡ ሕልማችሁን መኖር ትችላላችሁ፡፡ ማንም ከእናንተ ብዙ ነገር ቢጠብቅ አትፍረዱበት። ጎበዝ እንድትሆኑና ዩኒቨርስቲ እንድትገቡ ቢጠብቅ አይግረማችሁ፡፡ ትልቁ ቦታ ስለሚገባችሁ ነው፡፡ ለዛ ነው ሕይወታችሁን መቀየር ያለባችሁ፡፡ ለዛ ነው ሰበብ መደርደሩን ማቆም ያለባችሁ፡፡
ከዚህ በኋላ ሰበብ አልደረድርም ማለት አለባችሁ። ከዛሬ ጀምሮ በትንሹ ለራሳችሁ ትታመናላችሁ፡፡ በየቀኑ በትንሹ ታጠናላችሁ። ተራራ የሚወጣ ሰው ቢያንስ አንድ እርምጃ እየተራመደ ነው፡፡ ተራራውን ሳይወጣ እንዲሁ ሽቅብ እያየ ይህን ተራራ እንዴት ልወጣ ነው በዛ ላይ ፀሐዩ እያለ ሰበብ ከደረደረ ተራራውን አይወጣውም፡፡ የሚያመነታ ሰው ከመንገድ ይቀራል። እንዲያ ከሆነ ደግሞ እንዲህ አይነት ሰው ለማንም አይሆንም፤ እናንተም እንደዛው፡፡ ምክንያት ስታበዙ ከመንገድ ትቀራላችሁ፡፡ ያኔ ማንም በእናንተ ደስተኛ አይሆንም፡፡ በራሳችሁ ታዝናላችሁ፡፡ ስለዚህ ከዛሬ ጀምሮ ራሳችሁን ቀይሩ፣ በትንሹ ለራሳችሁ ታመኑ፣ ጣሩ ከዛም ዓላማችሁን ቁጭ ብላችሁ አስቡ፡፡ ከዚህ ውጪ ከእናንተ የሚጠበቅ ምንም ነገር የለም፡፡
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ህዳር 15/2016