በአገሪቱ በቀጣይ ለሚገነቡ መናኸሪያዎች ሞዴል ተደርጎ በዘመናዊ መልኩ እየተገነባ የሚገኘው የቃሊቲ መናኸሪያ፣ በአንድ ጊዜ ከ120 በላይ አገር አቀፍ አውቶቡሶችን እንዲያስተናግድ ተደርጎ እየተገነባ ነው። አጠቃላይ ግንባታው በሶስት ነጥብ ዘጠኝ ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ሲሆን፣ የመናኸሪያ ተርሚናሉ ዘመናዊ ሕንፃ ግንባታ ብቻ በአምስት ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ነው፡፡ ሕንፃው አምስት ወለሎችም (G+4) አሉት፡፡
የመናኸሪያ ግንባታው ውል የተገባው ሚያዝያ 6 ቀን 2011 ዓ.ም ቢሆንም፣ ግንባታው በተለያዩ ምክንያቶች ተጓትቶ ቆይቷል፡፡ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ባለቤትነት እና በኤፍኢ (EFE) ኮንስትራክሽን ደረጃ አንድ የሀገር ውስጥ ተቋራጭ ተቋራጭነት በአንድ ነጥብ አንድ ቢሊየን ብር እየተገነባ የሚገኘውን የዚህን መናኸሪያ ግንባታ በመጪው ጥር ወር መጨረሻ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው፡፡
በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የመሠረተ ልማት ማስፋፊያ ባለሙያ እና የቃሊቲ መናኸሪያ ግንባታ ፕሮጀክት መሪ መሀንዲስ አቶ ሚኪያስ ታደሰ እንደሚሉት፤ ፕሮጀክቱ 540 የመጀመሪያ የውል ቀናት የነበሩት ሲሆን፣ በመስከረም 14 ቀን 2014 ዓ.ም ለማጠናቀቅ ታቅዶ ነበር የተጀመረው፡፡ ይሁንና በዲዛይን ለውጥ እና በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ግንባታው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ሊጠናቀቅ አልቻለም።
አጠቃላይ የፀደቀ የውለታ ጊዜ ማራዘሚያ 682 ቀናት እንዳሉት የጠቀሱት መሪ መሀንዲሱ፣ የግንባታ ማጠናቀቂያ ጊዜውም ሕዳር 12 ቀን 2015 ዓ.ም እንደነበረም አስታውሰዋል። ይሁንና ሌላ የዋጋ ማሻሻያ እንደተደረገለት ተናግረዋል፤ በዋጋ ማሻሻያው ጊዜ ተሰጥቶት ተቋራጩ እስከ ጥር 30 ቀን 2016 ዓ. ም የፕሮጀክቱ የመጨረሻ ቀሪ ስራዎችን አጠናቆ እንዲያስረክብ የጊዜ ሰሌዳ መቀመጡንም አስታውቀዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ የመናኸሪያ ሕንጻ ግንባታው አሁን ላይ የፊዚካል አፈፃፀሙ 78 በመቶ ደርሷል፤ እስካሁን የፈጀው ጊዜም 125 በመቶ ነው፣ ግንባታው ክረምት ላይ ተቀዛቅዞ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ከለቀማና ከማጠናቀቂያ ስራዎች በቀር አብዛኛው የግንባታ ስራ እየተጠናቀቀ ይገኛል። የመናኸሪያ ሕንፃው ግራውንድ + ሚዛኒ + አራት ሲሆን፣ ለቢሮ፣ ለሱቅ፣ ለካፍቴሪያ፣ ለመሠብሰቢያ አዳራሽ፣ ለትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ የሚውሉ ቢሮዎችንም አካቶ ይዟል። አገልግሎቱም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን ተደርጎ እየተገነባ ይገኛል፡፡
መናኸሪያው በኢትዮጵያ ሞዴል መናኸሪያ ሆኖ እየተገነባ ነው፡፡ የእቃ ማጓጓዣንና የሕዝብ ማጓጓዣን በመለየት የማጓጓዝ ሂደቱን ከመግቢያው አንስቶ እንዲዘመን ይደረጋል፤ የተሳፋሪዎች እና የተሽከርካሪው እንቅሰቃሴ በማይጋጭበት ሁኔታ መናኸሪያው የራሱ የሆነ ከፀሐይ እና ከዝናብ መከላከያ ሼድ ይኖረዋል። የቲኬት መቁረጫ ፋሲሊቲዎችን ጨምሮ የመቆያ ቦታዎች እና አውቶብሶቹ የት እንዳሉ መረጃ የሚሰጡ ሲስተሞች ይገጠሙለታል፡፡ አውቶቡሶቹ ሲገቡም ሆነ ሲወጡ ዘመናዊ የሆነ እና በካርድ የታገዘ የመቆጣጠሪያ የክፍያ እና የደህንነት ሲስተሞች አሉት። የፓርኪንግ ካርድ ከፍለው በሲስተም የሚገቡበት እና የሚወጡበት አሰራር ይተገበርበታል፤ ይህም ሕገወጥ ስምሪትን ለመከላከል ያስችላል፡፡
ተቋሙ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድር እንዲሆን ታስቦ መናኸሪያው እየተገነባ መሆኑንም ጠቅሰው፣ ከትራንስፖርት አገልግሎት ውጪ ያሉ አገልግሎቶችን እንዲሰጥ ተደርጎ እየተገነባ እንደሚገኝ ተናግረዋል፤ ለዚህም በሞል ደረጃ የሚገነባ ሲሆን፣ ሱቆች፣ ባንኮች፣ ካፍቴሪያዎች እና ለመሳሰሉት አገልግሎቶች የሚውሉ ክፍሎች ይኖሩታል፡፡ አገልግሎቶቹም ከትራንስፖርት አገልግሎቱ ጋር እንዳይቃረኑ ተደርገው የሚሰጡ ይሆናሉ፡፡ ሁለት አሳንሰር ወይም ሊፍት የሚኖረው ሲሆን፣ በሶስት ቦታዎችም ደረጃዎች ይኖሩታል።
ከመናኸሪያው ሕንፃ ፊት ለፊትም ለከተማ አውቶብሶች እንዲሁም ሌሎች የግል መኪና እና የታክሲ ማቆሚያ ሰፊ ቦታም አለው። በምድረ ግቢው ዶክ የሚባለው እና ከሕንፃው ጋር የሚገናኘው ተሳፋሪዎች ጸሀይና ብርድ ሳያገኛቸው የሚያርፉበትና ወደ መኪና የሚገቡበት ቦታ ተያይዞ ተገንብቶለታል፡፡ ግቢው ሶስት መውጫና መግቢያ በሮች የሚኖሩት ሲሆን፣ በቂ ጥበቃ ማድረግ የሚያስችሉ የጥበቃ ቤቶች ይኖሩታል፡፡
የምድረ ግቢው የአስፓልት ስራ እየተካሄደ መሆኑን አቶ ሚኪያስ ጠቁመው፣ ግንባታው አስፋፓልት እና ሰብ ኮርስ የሚባሉ ሁለት ንብርብር ስራዎች እንደሚቀሩት አቶ ሚኪያስ ተናግረዋል፡፡ የግቢ ስራው ብዙም እንደማያቆይ ጠቅሰው፣ ትልቁን ስራ የሚይዙት የሕንፃ ለቀማ እና የማፅዳት ስራዎች መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የግንባታው ሂደት እንዲዘገይ ዋነኛው ምክንያት በስፍራው የነበረውን የፖሊስ ካምፕ ለማንሳት ጊዜ መውሰዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ የአየር ፀባይ፣ የዋጋ ማሻሻያ ሂደቶች እና በመሀል የነበሩ የዲዛይን ጉዳዮች ለግንባታው መጓተት ሌሎች ምክንያቶች መሆናቸውንም አመልክተዋል። ለተቋራጩ ክፍያ በወቅቱ አለመፈፀሙም የተወሰነ መዘግየት እንዲከሰት ምክንያት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ሁሉም የመፍትሔ አቅጣጫዎች ተሰጥቷቸው በአሁኑ ወቅት ግንባታው ወደ ማጠቃለያ ምዕራፍ መግባቱንም ገልፀዋል።
በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የመሠረተ ልማት መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ሰይፉ ክንፉ በበኩላቸው እንደገለፁት፤ የቃሊቲ ዘመናዊ መናኸሪያ ተርሚናል ግንባታ ዘመናዊ አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ እየተገነባ የሚገኝ ሲሆን፣ ከዲዛይን ጀምሮ መሟላት ያለባቸው አስፈላጊ ፋሲሊቲዎች ተለይተው የተካተቱበትም ነው፡፡
አየር መንገድን ከመሣሠሉ አንጋፋ ተቋማት ተሞክሮ በመውሰድም የጉዞ ፕሮግራም ማሳያ ስክሪኖች ጭምር እንደሚኖሩትም አቶ ሰይፉ ገልጸዋል፡፡ አውቶቡሶቹ በተመደበላቸው ሰዓት መሰረት ወደ አገልግሎቱ እንዲገቡ የሚደረግበት ሁኔታ እንደሚኖርም ጠቁመዋል። ተሳፋሪው መናኸሪያው ውስጥ ጓዙን ተሸክሞ የሚንቀሳቀስበት ሁኔታ እንደማይኖርና ለእቃው ደረሰኝ ተሰጥቶት ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ እቃው ለብቻው ተጭኖ ወደ አውቶብሱ የሚጓጓዝበት ዘመናዊ አሰራር የሚተገበርበት ነው ብለዋል።
ውጫዊና ውስጣዊ ችግሮች ባያጋጥሙ ፕሮጀክቱን መስከረም 30 ቀን 2016 ለማጠናቀቅ ታቅዶ እንደነበረ አቶ ሰይፉም ገልፀው፣ በዝናብ ወቅት መራዘም ምክንያት በሳይት ስራው ላይ የደረሰውን ብልሽት ለማስተካከል ግንባታው በአዲስ መልኩ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል። ይህ በራሱ የፈጠረው ጫና እንዳለም ጠቅሰው፣ ጥራቱን አስጠብቆ መስራቱ ለድርድር እንደማይቀርብ ገልጸዋል። አሁን ባለው የስራ መርሀ ግብር መሠረትም ጥር 30 ቀን 2016 ዓ.ም ግንባታውን ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በፕሮጀክቱ ስራ ካጋጠሙት ችግችሮች መካከል የአየር ፀባይ አንዱ መሆኑን አቶ ሰይፉም ይገልጻሉ፡፡ ሁለተኛውም ችግር ለግንባታው የሚያስፈልገውን ገንዘብ በተፈለገው መጠን አለማግኘት መሆኑንም ተናግረዋል። ከፋይናንስ ጋር የተያያዘውን ችግር መንግሥት ፕሮጀክቱ ሞዴል መናኸሪያ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት በሰጠው ትኩረት ችግሮቹ መፈታታቸውን ገልጸዋል፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴር የአገር ፕሮጀክት መሆኑን በመረዳት በቅርበት እገዛ እያደረገ መሆኑንም አመላክተዋል።
መናኸሪያው በዋናነት ታሳቢ ተደርጎ እየተገነባ የሚገኘው አገር አቋራጭ አገልግሎትን እንዲሰጥ ተደርጎ ነው ያሉት አቶ ሰይፉ፣ አሁን በአገራችን ከሚታዩ ተሽከርካሪዎች ውጪ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ መሥሪያ ቤት በሕዝብ ትራንስፖርት በኩል በርካታ ሰዎችን በአንድ ጊዜ ለሚያንቀሳቅሱ አገልግሎቶች አቅዶ እና ፖሊሲ ቀርፆ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የቃሊቲ መናኸሪያም አገር አቋራጭ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ እና ሌሎች ጎን ለጎን የሚሰሩ ሥራዎች መኖራቸውንም ገልፀዋል። 120 አገር አቋራጭ አውቶቡሶች አንድ ጊዜ የሚንቀሳቀሱበት መሆኑን ጠቅሰው፣ በመጠባበቂያ ያሉትን ያካተቱ ተጨማሪ መሠረተ ልማቶች ተሰርተው እስከ 30 እና 40 ዓመታት ሊያገለግል እንዲችል ተደርጎ እየተገነባ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በቅርቡም ለማሕበረሰቡ ተጨማሪ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ እና ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የተያያዙ ግንባታዎችን ለማድረግ የማስፋፊያ ቦታ ከከተማ አስተዳደሩ መጠየቁንም አቶ ሰይፉ ገልጸዋል፡፡ ለእዚህም ምላሽ ከተገኘ በኋላ ተጨማሪ ስራዎችን በማካተት የሕብረተሰቡን የአገልግሎት ፍላጎቶች ለመመለስ እንደሚሰራም አመልክተዋል።
አሁን እየተሰራ የሚገኘው በየሰዓቱ እና በየደቂቃው ለሚንቀሳቀሱ አውቶቡሶች መሆኑን ገልፀው፣ በዚያው አካባቢ በሚደረገው ተጨማሪ ማስፋፊያም ተገልጋዮች ርቀው ሳይሄዱ ሌላ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚጠብቁበት ቦታ መዘጋጀት አለበት በሚል የቦታ ጥያቄው መቅረቡን ጠቁመዋል። መንግስትም ሆነ ከተማ አስተዳደሩ ይህንን እንደሚደግፉ ጠቅሰው፣ በቅርቡ አካሄዱን ጠብቆ ጥያቄው ምላሽ ያገኛል የሚል ተስፋ እንዳላቸውም አስታውቀዋል፡፡ አካባቢው የሕዝብ አገልግሎት መስጫ መሆኑን ጠቅሰው፣ የፍሳሽ መልሶ ጥቅም ማዋያ መሰረተ ልማት /ሪሳይክል ማድረጊያ/ መስሪያ ቦታ መጠየቁንም አስታውቀዋል።
አቶ ሰይፉ እንዳሉት፤ የትራንስፖርት አገልግሎትን ለማዘመን መሠረተ ልማት ላይ ትኩረት መስጠት ይገባል። እስከ አሁን የሚሰጠው አገልግሎት ማንንም እያረካ አይደለም። ተገልጋዩን ብቻ ሳይሆን አገልግሎት ሰጪውን አካል ጭምር እያረካ አይደለም። በመሆኑም ይህ ዘመናዊ መናኸሪያ አንድ ዘመናዊ መናኸሪያ ሊሰጥ ከሚገባው አገልግሎት እና አቅርቦት አኳያ ተገልጋዩ ሳይጉላላ የሚፈልገውን ምቹ አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል ነው።
የመናኸሪያው አገልግሎት የውጭ ዜጎችንም ታሳቢ እንደሚያደርግ አቶ ሰይፉ ጠቁመዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ በመናኸሪያዎች አካባቢ የሚሰጡ አገልግሎቶች ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን አገራችን በትኩረት እየሰራችበት የምትገኘውን የቱሪዝም ዘርፍንም ታሳቢ ማድረግ አለባቸው፡፡ ይህ አይነቱ አገልግሎት የአገሪቱን ገፅታ በከፍተኛ ሀኔታ የሚቀይር ከመሆኑም ባሻገር፣ ቱሪስቶች ኢትዮጵያ ውስጥ በሕዝብ ትራንስፖርት ለመንቀሳቀስ ሲፈልጉ ልዩ አገልግሎት ለመስጠት በሚቻልበት ደረጃ እና በሚፈልጉት ልክ እንዲዘምን የመናኸሪያው ፋይዳ ከፍተኛ ይሆናል፡፡
እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገዱ ሁሉ ደረጃውን የጠበቀና የአፍሪካ ኩራት የሆነ ዘመናዊ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ታሳቢ ያደረገ ስታንዳርድ ለማምጣት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ላይ ሕብረተሰቡ ሳይጉላላ እና ሌሊት ተነስቶ መሠለፍ ሳይኖርበት በኦንላይን ቲኬት የሚያገኝበት አሰራር ተዘርግቶ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል። ይሄንን ምቹ በማድረግም ማንም ሰው ሰዓቱን አስተካክሎ እና ቲኬቱን በእጁ ይዞ ሊሳፈር የሚችልበትን አሰራር በመዘርጋት ተገልጋዩን ማርካት እና የአገርንም ገፅታ መገንባት ታሳቢ ተደርጎ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ ብቻውን በቂ እንዳልሆነም አቶ ሰይፉ ተናግረዋል፡፡
በነባሩ የአውቶቡስ ተራ ትልቁ እና ትንሹ መናኸሪያም እንዲሁ አዲስ እና ልዩ ግንባታ እንደሚካሄድም አቶ ሰይፉ ጠቁመዋል፡፡ የዚህ ግንባታ የዲዛይን ስራ አልቆ ወደ ተግባር እንደሚገባ ጠቅሰው፣ ግንባታው የከተማዋን ገፅታ እንደሚቀይረውም ተናግረዋል፡፡ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም በሕዝብ ማመላለሻ መናኸሪያዎች ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በደረቅ ጭነት እና ፈሳሽ ጭነት ላይም እንዲሁ ደረጃዎችን አዘጋጅቶ ከየክልል አስተዳደሮች ጋር ግንባታዎችን እያካሄደ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የኮንስትራክሽን ዘርፉ ከግብርና ቀጥሎ በአገር ላይ ከፍተኛ የሥራ እድል እየፈጠረ እንደሚገኝ አመልክተው፣ የቃሊቲ መናኸሪያ ግንባታው ለበርካታ ሰዎች የስራ እድል መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ግንባታው ለ228 ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠሩ ተጠቁሟል፡፡ በየዓመቱ በአማካይ ለአንድ ሺ 392 ሰዎች ደግሞ ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠሩም ተገልጿል፡፡ ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ስራ ሲጀምርም በተመሣሣይ በርካታ ቋሚና ጊዚያዊ የሥራ እድሎችን አንደሚፈጥርም አቶ ሰይፉ አስታውቀዋል።
በሌሎች መናኸሪያዎችም ዘመናዊ አገልግሎቱን ለማስፋት እንደሚሰራ ጠቁመው፣ በተመሳሳይ ደረጃ በላምበረት፣ በአየር ጤና እና አስኮ መናኸሪያዎች ትልቅ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገለፀዋል። በዚህም ሕብረተሰቡ ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት እንዲያገኝ ለማድረግ ፕሮጀክት ተቀርፆ እና ጨረታ ወጥቶ ለትግበራ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም መናኸሪያዎቹን ወደ ቃሊቲ መናኸሪያ ስታንዳርድ በሂደት የማምጣት ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
የአገር አቋራጭ ትራንስፖርት ተጠቃሚው በማለዳ የሚነሳ መሆኑን አቶ ሰይፉ ተናግረው፣ በመናኸሪያዎች አካባቢ ያለው የመብራት አገልግሎት ስታዲየም ላይ በማታ እንደሚታየው ያህል የደመቀ እንዲሆን እንደሚደረግም አስታውቀዋል። ሕብረተሰቡ የሚፈልጋቸውን አገልግ ሎቶች እንዲያገኝ በሚያስችል መልኩ መናኸሪያዎቹ አንደሚዘጋጁም ጠቁመዋል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ህዳር 15/2016