በኬንያ የተንሰራፋው ሥራ አጥነት ለመንግሥትና ለአካባቢው ሠላም የፀጥታ ሥጋት ፈጥሯል፡፡ በተለይ የኬንያ ሥራ አጥ ሴቶች የአልሸባብ መረብ ውስጥ መግባታቸውን የአልጀዚራ ዘገባ ያትታል፡፡ እንደ ዘገባው የምሥራቅ አፍሪካን አካባቢ ፀጥታ እያናጋ የሚገኘው ፅንፈኛው አሸባሪ ቡድን ሥራ አጥ ወጣቶችን እየመለመለ የእኩይ ዓላማው ማስፈፀሚያ እያደረጋቸው ነው፡፡
ከኬንያ ህዝብ ውስጥ ሦስት አራተኛውን የሚይዙት ወጣቶች ሲሆኑ፤ ዕድሜያቸውም ከሰላሳ አይበልጥም፡፡ አብዛኛው ወጣት ሥራ አጥ እና በድህነት ህይወቱን የሚገፋ በመሆኑ ተስፋ የመቁረጥ ሁኔታ ይታይበታል፡፡ ይህም ባለፉት አስርት ዓመታት በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች አልሸባብ የተባለውን ፅንፈኛ የሶማሊያ ታጣቂ ቡድን እንዲቀላቀሉ ምክንያት ሆኗል፡፡ በአገሪቱ ሥራ አጥ ከሆኑት ወጣቶች ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት ደግሞ እንስቶች ናቸው፡፡ በመሆኑም ፅንፈኛውን የአልሻባብ ቡድን በመቀላቀል ከፍተኛውን ቁጥር ይዘዋል፡፡
ሴቶች በአሸባሪነት እምብዛም ስለማይጠረጠሩና የተሰጣቸውንም ግዳጅ በብልጠት የማከናወን ችሎታ አላቸው በሚል የአልሸባብ ቡድን እንስቶችን መመልመልን ተያይዞታል፡፡ በኬንያ የሥራ አጥነት ቁጥር መበራከትም ለቡድኑ ሴቶችን በእጁ ለማስገባት ጥሩ አጋጣሚ ተፈጥሮለታል፡፡ በኬንያ አክቲቪስትና የአልሸባብ ተዋጊዎችን መልሶ በማቋቋም ሥራ ላይ የተጠመዱት ሮበርት ሮቦው አኮላ እንደሚያስረዱት አልሸባብ ሴቶችን በመመልመል እኩይ ተግባሩን ለመፈፀም መረጃ ለመሰብሰብና ለስለላ ተግባር ይጠቀመባቸዋል፡ በኬንያ ትልቅ ችግር የሆነው የሥራ አጥነት መፍትሄ ካልተሰጠው ብዛት ያላቸው ወጣቶች በጥቅማጥቅም ተታለው አልሸባብን እንዲቀላቀሉ የሚያደርግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ማስረጃቸውም ከአልሸባብ ተዋጊዎች አንዷ የነበረችውና አሁን ወደ ቀደመ ህይወቷ የተመለሰችው ፋጡማ የሰጠቸው ምስክርነት ነው፡፡ እርሷ እንደምታስረዳው የአልሸባብ ተዋጊ ሆኜ ከመቀጠሬ በፊት አሁን የምሠራውን ዓይነት ሥራ ቢኖረኝና ምግቤንና መሰል መሰረታዊ ፍላጎቴን ሟሟላት የሚያስችል ገቢ ቢኖረኝ ኖሮ አልሸባብን አልቀላቀልም ነበር፡፡
ፋጡማ እ.ኤ.አ በ2006 አካባቢ አልሸባብ እንደ ተቋቋመ ቡድኑን የተቀላቀለች የመጀመሪያዋ እንስት ወጣት ኬንያዊት ናት፡፡ ዛሬ ግን ወደ ትውልድ አገሯ ተመልሳ የተፈጠረላትን የሥራ ዕድል ተጠቅማ በሠላማዊ መንገድ ህይወቷን በመምራት ላይ ትገኛለች፡፡
ፋጡማ አልሸባብን የተቀላቀለችበትን ሁኔታ ወደ ኋላ ከትዝታ ማህደሯ መዛ እንዲህ ታስረዳለች፡፡ አልሸባብን የተቀላቀልኩት በባለቤቴ ግፊት አማካኝነት ነው፡፡ ከባለቤቴ ጋር የተዋወቅኩት በ17 ዓመቴ ነበር፡፡ በጥያቄው መሰረትም ትዳር መሰረትን፡፡ እርሱ በወቅቱ የአልሸባብ አባል ነበር፡፡ ሆኖም ለእኔ አልነገረኝም፡፡ በተለያዩ ኃይማኖታዊና ማህበራዊ ቀውሶች ምክንያት ባለቤቴ ትምህርቴን እንዳቋርጥ አደረገኝ፡፡ እንግዲህ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለሁ ነበር የአልሸባብ አባል መሆኑን ያሳወቀኝ፡፡
በወቅቱ እርሱ የሚለኝን ከመሆን ውጭ ምንም አማራጭ ስላልነበረኝ አብሬው ለመኖር ተገደድኩኝ፡፡ በእርግጥም ሦስት ዓመታትን አብረን በነበርንበት ወቅት ከበፊቱ የተሻለ ኑሮ እየኖርኩ ነበር፡፡ ቢያንስ ስለሚበላ ነገር አላስብም፤ ምግብ ተዘጋጅቶ ነው የሚቀርብልኝ ስትል ፋጡማ ታስረዳለች፡፡ ሶማሊያ ውስጥ የአልሸባብ ተዋጊ የነበረው ባለቤቷ የውሃ ሽታ ሲሆንባት ቤተሰቦቿን ለመጠየቅ ወደ ትውልድ አገሯ ኬንያ ለመመለስ መገደዷን ታወሳለች፡፡ በትውልድ ቀየዋ የሥራ ዕድል በማግኘቷም የአልሸባብ አባልነቱን ትታ በአዲስ መልክ ህይወቷን መምራት ጀምራለች፡፡
ከአውድ ውጊያ የተመለሱት የቀድሞዎቹ የአልሸባብ ተዋጊዎች በትውልድ አገራቸው የተለያዩ ፈተናዎች እንደ ተጋረጡባቸው ይናገራሉ፡፡ በአልሸባብ ከሚፈፀምባቸው የበቀል እርምጃ ይልቅ ሥራ ላይ በዋለው የአገሪቱ ጠንካራ የደህንነት ሕግ ምክንያት በፀረ ሽብር ቡድኑ አማካኝነት የሚደርስባቸው ወከባ፣ ጥቃትና ግድያ ያማረራቸው መሆኑ ነው የሚናገሩት፡፡
አንድ ሰው የተሰማራበት እኩይ ተግባር ጥሩ እንዳልሆነ ገብቶት አጥፍቻለሁ ማሩኝ ብሎ ወደ አገሩ ሲመለስ ይህን ሰው መርዳት ወይም ማቋቋም ያስፈልጋል፡፡ ፖሊስ ተመላሾቹን የሚያሳድዳቸው፣ የሚያስራቸውና የሚገድላቸው ከሆነ ግን ችግሩ ይባባሳል ሲሉ አክቲቪስቱ ሂደያ ያስረዳሉ፡፡
‹‹እ.ኤ.አ በ2014 ልጄ በሶማሊያ የሃላኔ የጦር ካምፕ ላይ የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት በመሰንዘሩ ምክንያት ሁሉም ሰው እኔን ዓይንህ ለአፈር ብሎኛል፡፡ አንዳዶች እንዲያውም እንደ ሰብዓዊ ፍጡር አይቆጥሩኝም›› ሲሉ በአልሸባብ ቡድን አባል በመሆነው ልጃቸው ምክንያት መገለል የደረሰባቸው አባት ይናገራሉ፡፡ እኔ እንዲህ ከተገለልኩ ተመላሾቹ ምን ያህል በሥጋት ውስጥ መኖራቸውን ያሳያል ይላሉ፡፡
‹‹በእኔ ቤት የተከሰተው ነገር በሌሎችም ቤት ተከስቷል፡፡ የአንድ ሰው ችግር የሌላውም ሰው ችግር መሆኑን አምናለሁ፡፡ ስለዚህ ዘላቂ መፍትሄ የሚሆነን በችግሩ ዙሪያ መመካከር ነው፡፡ በእኔ በኩል ልጆችን እንዴት በኃላፊነት ማሳደግ እንደሚገባን ከእናቶች ጋር እየተሰበሰብኩ መምከር ጀምሬያለሁ›› ሲሉ የችግሩን አሳሳቢነት ያስረዳሉ፡፡
እንደ ራይት ዎች ዘገባ አልሸባብ እ.ኤ.አ በመስከረም ወር 2017 በመቶዎች የሚቆጠሩ ተዋጊ ታዳጊዎች ከአካባቢው የሚመለመሉ መሆኑን ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡ይህን ተከትሎም ብዙ ታዳጊዎች በግዳጅ እንዳይመለመሉ በመሥጋት የትውልድ አገራቸውን ጥለው በመሸሽ ላይ ናቸው፡፡ የኬንያ መንግሥት በጉዳዩ ዙሪያ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ትኩረት ሰጥቼ እየሠራሁ ነኝ ቢልም የኑሮ ደረጃቸው ዝቅተኛ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችንና ተመላሽ የአልሸባብ ተዋጊዎችን መልሶ በማቋቋም ረገድ እዚህ ግባ የሚባል ሥራ እየሠራ አይደለም፡፡
የኬንያ መንግሥት አክራሪነትንና ፅንፈኝነትን አስመልክቶ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ለተቋቋሙ በጎ አድራጊ ድርጅቶች የሚያፈሰውን ከፍ ያለ ገንዘብ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ወጣት ሴቶች ሠርተው እንዲለወጡ የሚያደርግ አሠራር ቢከተል የችግሩን ምንጭ ማድረቅ ይቻላል፡፡ ግን በግንዛቤ ማስረፅ ስም በበጎ አድራጎት ድርጅቶች አማካኝነት በታላላቅ ሆቴሎች የሚባክነው ብር ችግሩን ሊፈታው እንደማይችል ነው ምሁራን የሚናገሩት፡፡ አሳሳቢውን ችግር ለመፍታት ህብረተሰቡ ዘንድ ሄዶ በቅርበት መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ምንም እንኳን አልሸባብ በሶማሊያ ከተቋቋመ ወዲህ በርካታ ኬንያዊያን ሴቶች የአልሸባብን አስተሳሰብ በማስረፅ ረገድ ሚናቸው የጎላ ቢሆንም ፅንፈኝነትንና አክራሪነትን በመከላከል በኩልም ግንባር አስተዋጽኦ አላቸው፡፡
አልሸባብ የሶማሊያ ፅንፈኛ ወጣቶች ክንፍን በማደራጀት የአፍሪካ ቀንድን ለማተራመስ የተቋቋመው እ.ኤ.አ በ2006 ነው፡፡ ይህ ፅንፈኛ ቡድን የሱፊ እስልምና ተከታይ በሆኑት አብዛኛዎቹ ሶማሊያን ላይ የውሀቢ እስልምና እምነትን በግድ በመጫን አገሪቱ በሼሪያ እንድትተዳደር አልሞ የተነሳ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ቡድኑ የአል-ቃይዳን ተልዕኮ ለማስፈፀም በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ኃላፊነትን ወስዶ የሚንቀሳቀስ ሲሆን ከናይጄሪያው ቦኮሃራም እና በስሃራ በረሃ ከሚንቀሳቀሰው የአል-ቃይዳ ክንፍ ጋርም ጥብቅ ትስስር አለው፡፡
አልሸባብ በምሥራቅ አፍሪካ ከፈፀማቸው የሽብር ጥቃቶች መካከል እ.ኤ.አ በ2010 በኡጋንዳ ካምፓላ ራግቢ ክለብ እና ሬስቶራንት፣ በ2013 በኬንያ ናይሮቢ ዌስት ጌት የገበያ ማዕከል፣ በ2015 በኬንያ ጋሪሳ ዩኒቨርሲቲና በ2016 በሶማሊያ ወታደራዊ ካምፕ ይገኙበታል፡፡ በእነዚህ የሽብር ጥቃቶችም በርካታ ንፁሃን ሰዎች ህይታቸው አልፏል፡፡ ለአካል ጎዳት ተዳርገዋል፡፡ በንብረቶች ላይም ጉዳት ደርሷል፡፡
እ.ኤ.አ ከ2017 ወዲህ የአሜሪካኑ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአልሸባብ ላይ ጠበቅ ያለ አቋም በመያዛቸው በአሜሪካን የጦር አውሮፕላኖች፣ በሶማሊያ አፍሪካ ሕብረት ሠላም አስከባሪ ኃይል እና በሶማሊያ መንግሥት ወታደሮች ጠንካራ ዱላ እያረፈበት ይገኛል፡፡ በዚህም አቅሙ በመዳከሙ የተቆጣጠራቸውን የሶማሊያ ግዛቶች እየለቀቀና እየተፍረከረከ ቢሆንም በአልሞትባይ ተጋዳይነት አሁንም እያደፈጠ ጥቃት መሰንዘሩን አላቆመም፡፡
ኢያሱ መሰለ