መነሻ ምክንያት
አቶ ፀጋዬ ሽኩሬ ይባላሉ፤ ነዋሪነታቸውና እድገታቸው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 ነው። በዚህ ወረዳ ሲኖሩ በአባታቸው አቶ ሽኩሬ እጄ ስም ሰፊ የእርሻ መሬት እንደነበራቸውና በዚህም ለዘመናት ቤተሰባቸው እና እርሳቸው ሲተዳደሩበት እንደነበር ይጠቁማሉ። ቦታቸው ሰፋ ያለ እና ለበጋ እርሻ፣ ለመስኖ፣ ለጓሮ አትክልትና ልማትም ይውል የነበረ፤ ዛፎችም የተተከሉበት እንደነበር ያስታውሳሉ።
ይሁንና ይህ ሁሉ ቦታ ለልማት በሚል ሰበብ እንደተወሰደባቸው የሚገልጹት አቶ ፀጋዬ፤ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ተገቢው ካሣ እንዳልተከፈላቸው ይናገራሉ። በዚህ መልኩ የተነፈጉትን መብታቸውን ለመጠየቅ በርካታ የመንግሥት ተቋማትን ደጅ ቢጠኑም እንዳልተሳካላቸው፤ በወጉ እንኳን ቅሬታቸውን ማቅረብ እንዳልቻሉ ይገልፃሉ።
“በደሌ ካሣ መከልከል ብቻ ሳይሆንም ሌላ ብዙ ችግር አለ” የሚሉት አቶ ፀጋዬ፤ ከእነዚህ መካከል የቤት ግንባታ ፈቃድ መከልከል አንደኛው መሆኑን ይናገራሉ። ከዚህ ባሻገር በአሁኑ ወቅት በሚኖሩበት ቤት የቤት ካርታ ማውጣት እንደተከለከሉ የመብት ጥያቄ ጠይቀውም ምላሽ መከልከላቸውን፤ በሚኖሩበት ክፍለ ከተማ እና ወረዳ እንደ ዜጋ አገልግሎት ማግኘት እንዳልቻሉ ነው ቅሬታቸውን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የመልካም አስተዳደርና ምርመራ ዝግጅት ክፍል የተናገሩት።
ይሄን መነሻ በማድረግም የመልካም አስተዳደርና ምርመራ ቡድኑ ጉዳዩን ይዞ ወደ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ያመራ ሲሆን፤ ክፍለ ከተማውም የበኩሉን ምላሽ ሰጥቷል። በዚህም ምንም እንኳን አቶ ፀጋዬ በዚህ ደረጃ በደል እየደረሰብኝ ነው ቢሉም፤ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ግለሰቡ የሚያነሷቸው ቅሬታዎች በሙሉ ውሃ የማይቋጥሩ ብሎም ከሚገባቸው በላይ ጥቅም ከመፈለግ የመነጨ መሆኑንና እንደ ዜጋም መብታቸው አለመነፈጉን ይነገራል።
የዝግጅት ክፍላችንም እነዚህ ከሁለት ወገን የተነሱ ሀሳቦችን ከባለቤቶቹ አንደበት፣ ከሰነድና ማስረጃዎች፣ ከሰዎች እና ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ለማጣራት፤ መረጃዎችንም ለመተንተን ሞክሯል። በዚህ ሂደት የተገኙ ሃሳቦችና ማስረጃዎችን መነሻ በማድረግም የሚከተለውን ዘገባ አቅርቧል።
የአቶ ፀጋዬ ሽኩሬ ቅሬታና አቤቱታ
አቶ ፀጋዬ ሽኩሬ፣ ለዝግጅት ክፍላችን ባቀረቡት ቅሬታ እንደገለጹት፤ በ2004 ዓ.ም የእሳቸው እና የቤተሰቦቻቸው ቦታ ለልማት ሲወሰድ ቅድመ ውይይት ተደርጓል። በዚህ ወቅትም ቦታው ለውሃና ፍሳሽ ለልማት እንደሚፈለግ ሲነገራቸው፤ ኤርትራውያን ጥለውት የሄዱት ባዶ ቦታ እንዳለ በመጠቆም እዛ ቢያለሙ የሚል ሀሳብ አቀረቡ። ሆኖም ተቀባይነት አላገኙም።
በወቅቱ የነበራቸው የመሬት ስፋት 3ሺ300 ካሬ ሜትር ሲሆን፤ በአጠቃላይ ከአባታቸው ጋር ሲደመር 7ሺ780 ካሬ ሜትር መሬት ነበር። ሆኖም ቦታው ለልማት እንዲውል ሲደረግና የካሣ ክፍያ ሲፈጸም ግን ተጉላልተዋል፤ ይህም አካሄዱ ግልጽነት የጎደለው ስለነበር ነው። ምክንያቱም ክፍያው ሲፈጸም በመጀመሪያ ዙር ካሬው ባልተገለጸ መልኩ እንዲሁ ውሰዱ ተብለው 89ሺ ብር ገደማ በ2004 ዓ.ም ወስደዋል።
ይሄን ገለጻ ተከትሎ ግን የዝግጅት ክፍሉ “ካሬው ባልገለጸበት መንገድ እንዴት ካሣ ልትወስዱ ቻላችሁ?” ሲል ጠይቋል። በምላሻቸው ‹‹ቀሪውን እረሱ፤ ለልማት የተወሰደውን ለክተን እናያለን እናሳያችኋለን›› አሉን። ቀሪውን በእርሻ መልኩ ስንጠቀም ነበር። ከተዘራ በኋላ በ2005 ዓ.ም መስከረም ወር ላይ በግሬደር መጥተው አረሱት። በተመሳሳይ በ2006 ዓ.ም ውሃ ልማት በግሬደር ለማረስ ሲመጡ አታርሱም ብለው በማስቆማቸው ድጋሚ ልኬት እንዲለካ ስለመደረጉም ተናግረዋል።
በዚህም ለ3ሺህ ካሬ ሜትር መሬት አንድ መቶ 29ሺ ብር አካባቢ ካሣ ተቀበሉ። ይህ ሲሆን ስህተት ነው፤ በ2006 ዓ.ም በወጣው መመሪያ እንዲከፈለን ተስማተናል፤ የባሕርዛፍ፤ የአትክልትና የአዝዕርት ቦታ ላይ ከአዝዕርት የሚገኘው ካሣ እንደሚከፈል፤ ብቻ ሳይሆን እንደ ጌሾ፣ ባሕር ዛፍ ያሉ አትክልቶችን ቆርጣችሁ ትወስዳላችሁ ተብለናል። ይህ ባልተፈጸመበት ሁኔታ መብታችን ሊጣስ አይገባም፤ በግሬደር አታርሱም ብለው እንደከለከሉ ያስረዳሉ።
ከዚህ በኋላም እንደገና ይታያል፤ ጥያቄያችሁ ትክክለኛ ስለሆነ ልማት መቋረጥ የለበትም በመባሉ ሥራ እንዲጀመር እና ሥምምነቱም የ10 ዓመት በመሬቱ ባለው አትክልት በዓመት ስንት ጊዜ የሚለውን ጥናት እየተጠና ስለሆነ እያንዳንዳችሁ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ታገኛላችሁ ሲሉ የውሃ ልማት ኃላፊው በቃል እንደገለፁላቸው ተናግረዋል። ሆኖም ይህ እልባት ሳያገኝ በ2007 ዓ.ም ግንባታው ተጠናቀቀ። በ2008 ዓ.ም መጥተው ክፍለ ከተማ ከጻፈላችሁ እኛ እንከፍላለን ተብለን ነበር።
ነገር ግን ይህ ባለመደረጉ በ2009 ዓ.ም ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ድረስ በማመልከት የከተማ ማደስ አመራር የነበረ ከባለሙያ ጋር ቦታው ድረስ በመምጣት ካሣው የተሠራበት ስህተት መሆኑ፤ እንደገናም ነዋሪነታችን ወረዳ 08 መሆኑ፤ እና ቦታው በቋሚነት መወሰዱ በፎቶግራፍ የተደገፈ መረጃ ይዘው መበደል የለባቸውም በማለት ካሣ እንዲከፈል ቢደረግም፤ እስካሁን ማግኘት አልቻልንም ይላሉ። አሁንም ድረስ መሬቱን መለካት ይቻላል፤ ለልኬት የሚያዛባ ሁኔታ የለውም፤ ስለዚህ ተለክቶ ትክክለኛ ካሣ ቢሰጠን ሲሉ ይጠይቃሉ።
አቤቱታ አቅራቢው ይሄን ሃሳባቸውን ለማጠ ናከር፣ በቀን 29/10/ 2009 ዓ.ም ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማት እና ማደስ ኤጀንሲ በመሬታቸው በብዙ መልኩ ተጠቃሚ እንደሆኑ፤ ቦታው ለልማት ሲወሰድባቸው በቦታው ለነበረ ሰብል እንደሚከፈላቸውና በዓመት ከሚያገኙት በ10 ተባዝቶ ክፍያ እንደሚፈጸም ነበር። ነገር ግን በልማት ምክንያት መሬቱ ሲወሰድ በወቅቱ የነበረ አትክልት፤ ባሕር ዛፎችና ሌሎች ችግኞች ያለምንም ክፍያ በግሬደር እንደታረሰና በወቅቱ የተከፈለን በካሬ 37 ብር ከ45 ሳንቲም ነው። ይህም የተከፈለው ብር ግልጽነት የጎደለው በመሆኑ ሕጉና መመሪያው በሚያዘው መሠረት እንዲከፈላቸው የጠየቁበትን ሰነድ እንደ ማሳያ አቅርበዋል።
አቶ ፀጋዬ፤ በካሳ ጉዳይ ፍርድ ቤት ድረስ ሄጄ መብት እንዳለኝና ያቀረብኩት ቅሬታ አግባብ መሆኑ የታመነበት ቢሆን መፍትሔ ለመስጠት ፍቃደኛ ያልሆኑት ክፍለ ከተማው እና ወረዳው ናቸው ይላሉ። ይህ የሆነው በየጊዜው አመራር ስለሚቀያየር ጉዳዩን በጥልቀት አለመረዳት ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ እዛው ወረዳ እና ክፍለ ከተማ ላይ ለዘመናት የቆዩ እና የእኔን ጉዳይ የሚያውቁ ግለሰቦች እና አመራሮች አሉ። እዚህም የእጅ መንሻ የሚፈልጉ በመሆናቸው እኔን ለማስተናገድ ፈቃደኛ አይደሉም ሲሉም ይወቅሳሉ።
የእኔ በደል ይህ ብቻ አይደለም የሚሉት አቶ ፀጋዬ፤ በክፍለ ከተማው ነዋሪ ሆኜ የምኖርበት ቤት እንኳን ዲጂታል ካርታ እንዳይኖረኝ ተከልክያለሁ። ይህ ሲሆን ግን ከእኔ ግራ ቀኝ ያሉት ጎረቤቶች ወይንም የአካባቢው ሰው ግን ካርታ በእጃቸው ይዘዋል። ከዚህም በተጨማሪ እኔ እድሳት ማድረግ ሆነ አዲስ ግንባታ ማከናወንም አልችልም ሲሉ የበደላቸውን ሁኔታ ያስረዳሉ።
የክፍለ ከተማው ምላሽ
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ተካ እና በክፍለ ከተማው የወሰን ማስከበር ባለሙያ የሆኑት አቶ አበባው ዳዊት በጋራ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት መረጃ፤ አቶ ፀጋዬ ሽኩር በተደጋጋሚ በአቡጨፌ የፍሳሽ ማጣሪያ ካሳ ሳይከፈለኝ መሬት ተወስዶብኛል፤ የቋሚ ተክል በተለይም የባሕርዛፍ ካሣ ሳይከፈለኝ ቀርቷል ወዘተ የሚል ቅሬታ፤ ገቢዎች እና ጉምሩክ ፕሮጀክት ላይ ካሣ በአግባቡ አልተከፈለኝም የሚል ቅሬታ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
ላቀረቡት ቅሬታ የክፍለ ከተማው የመሬት ልማት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በየጊዜው ምላሽ ተሰጥቷቸዋል። በውሃና ፍሳሽ ፕሮጀክት በአቶ ፀጋዬ ሽኩር ስም የተለካ ይዞታ የለም። በፕሮጀክት ዘመኑ ማለትም በ2004/2005 ዓ.ም ግለሰቡ በፕሮጀክቱ ክልል ውስጥ መሬት አልነበራቸውም። ከዚህ ይልቅ በአባታቸው በአቶ ሽኩሬ ሄጂ ስም የተለካ 5ሺህ 906ነጥብ55 ካ.ሜ መሬት ነበረ። ይሄም የቋሚ ተክል ያረፈበት እና የመስኖ መሬት ነው። ለዚህ መሬት ደግሞ በሦስት ዙር በድምሩ 239ሺ212ነጥብ28 ብር ለአቶ ሽኩሬ ሄጂ ሕጋዊ ተወካይ ለሆኑት ለባለቤታቸው ለወይዘሮ ሐብታሟ ከበደ ተከፍሏል።
የካሣ ክፍያውም በሦስት ዙር የክፍያ ማስተርሊስት ክፍያ ተፈፅሞላቸዋል። ሰነዶቹም ፋይል ላይ ተያይዘው ይገኛሉ። ተወካዩዋም ይሄንን መውሰዳቸውን አልካዱም። በወቅቱ የነበሩ ኮሚቴዎች እና የአቶ ፀጋዬ ሽኩር ወንድሞች ሁሉ በቦታው ላይ ካሣ ስለመከፈሉ በተደጋጋሚ መስክረዋል። በውሃና ፍሳሽ ፕሮጀክት ምክንያት የተቆረጠውን የባሕርዛፍ ተክል በተመለከተ በወቅቱ በነበረው የካሣ መመሪያ ቁጥር 3/2002 መሠረት አንድ አርሶ አደር ዛፉን ቆርጦ ማንሳት ከፈለገ ካሣ ሳይከፈለው ዛፉን እንዲያነሳ እና እንዲጠቀምበት ማድረግ ይችላል፤ ስለሚል በዚሁ አግባብ የአቶ ፀጋዬ አባት ዛፉን ቆርጠው በማንሳታቸው ካሣ አልተከፈላቸውም። ይህ ደግሞ በወቅቱ የነበረው መመሪያ የሚያዘው አሠራር በመኖሩ ነው።
የገቢዎች እና ጉምሩክ ፕሮጀክትን በተመለከተ የፕሮጀክቱ ልኬት በተወሰደበት በቀን 04/10/2012 ዓ.ም ሳይት ላይ በተወሰደው ልኬት መሠረት በመስኖ ተጠቅመው ያለሙት የነበረውን የመስኖ ካናል (ቦይ) የነበረበትን አንድ ሺ 18ነጥብ95 ካሬ ሜትር መሬት በመስኖ የተከፈላቸው ሲሆን፤ ከወንዝ ራቅ የሚለውን ምንም ዓይነት የመስኖ ካናል የሌለበትን መሬት ደግሞ መሬት በሚል አንድ ሺ 513 ካሬ ሜትር በወቅቱ በዝናብ የሚለማ እርሻ በነበረው የካሣ ተመን መሠረት በመጀመሪያ ዙር የካሣ ክፍያ አንድ ሚሊዮን 468ሺህ 458ብር ከ94 ሳንቲም፤ በሁለተኛ ዙር በልዩነት ክፍያ ደግሞ አንድ ሚሊዮን 633ሺህ 13 ብር ከ82 ሳንቲም፤ በድምሩ 3ሚሊዮን 101ሺህ 472 ብር ከ76 ሳንቲም ካሣ ክፍያ ተፈጽሞላቸዋል።
ይሁንና ቅሬታቸው ሙሉ ለሙሉ ለምን በመስኖ አልተለካልኝም የሚል መሆኑ ግልጽ ሲሆን፤ በወቅቱ ሳይት ላይ የተገኘው ግን ከፊሉን መሬት በመስኖ ይጠቀሙበት እንደነበረ ቀሪውን ደግሞ በክረምቱ ዝናብ ተጠቅመው ያለሙት የነበረ መሆኑን ከመተማመኛ ቅፁ ላይ ተረጋግጧል። ግለሰቡም በወቅቱ በተሞላው የልኬት መተማመኛ ቅጽ ላይ ተስማምተው ፈርመዋል። ወረዳውና ኮሚቴዎችም መተማመኛውን አጽድቀውታል።
በዚህ ረገድ ለሁለቱም ፕሮጀክቶች የተሰጣቸው ምላሽ አግባብነት ያለው ነው። የውሃና ፍሳሽ ፕሮጀክት ለአባታቸው ሕጋዊ ተወካይ ለሆኑት በ2004/2005 በጀት ዓመት በነበረው መመሪያ ቁጥር 3/2002 መሠረት፤ የገቢዎችና ጉምሩክ ፕሮጀክት ደግሞ ለራሳቸው በመመሪያ ቁጥር 19/2006 መሠረት በወቅቱ በነበረው አሠራርና መመሪያ መሠረት ተገቢው አገልግሎት በመጀመሪያ ዙርና በሁለተኛ ዙር በልዩነት ካሣ ክፍያ ተፈፅሞላቸዋል፤ ይህም በገንዘብ ተቀባዩ ወይንም ካሣ በወሰደው አካል ፊርማ የተረጋገጠ ነው።
የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የወሰደውን መሬት በተመለከተ የእርሻና መስኖ መሬት እንዲሁም የቋሚ ተክል ካሣ ክፍያ አልተከፈለኝም በሚል ክስ ያቀረቡ ቢሆንም እንኳ፤ ፍርድ ቤቱ ግን አስፈላጊውን ማጣራት አድርጎ በመሬቱ ላይ በወቅቱ በነበረው መመሪያ እና አሠራር መሠረት ካሣ ክፍያ ለአባታቸው እንደተከፈላቸው በማረጋገጡ ክሱ አግባብነት የለውም በሚል በ16/04/2012 በመዝገብ ቁጥር 014/10 በተሰጠው ውሳኔ ክሳቸውን ውድቅ አድርጎባቸዋል።
ስለሆነም ከፍርድ ቤት ውሳኔ በኋላ አስተዳደራዊ ቅሬታ ማቅረብም ይሁን በየመገናኛ ብዙኃን (ሚዲያው) እየሄዱ የተቋሙን ስም ማጥፋታቸው ተገቢነት የለውም። ምናልባትም በፍርድ ቤቱ ብይን ቅሬታ ካለባቸው እንኳን ይግባኝ መጠየቅ ሲገባቸው፤ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ ሽራችሁ ተጨማሪ ክፍያ ክፈሉኝ ማለት አግባብነት የሌለው መሆኑን ለማጣራት መቻላቸውን ነው ለዝግጅት ክፍላችን ያስረዱት።
ይሄንን የሚመለከቱ አስረጂ ሰነዶችም በውሃና ፍሳሽ በሦስት ዙር ካሣ ክፍያ የተፈፀመበት የክፍያ ማስተርሊስት ቃለ ጉባኤ እና ሰርተፊኬት ፋይል ላይ ተያይዟል። በተደጋጋሚ ያቀረቡት ቅሬታ እና የተሰጣቸው ምላሽ ፋይል ላይ ተያይዟል። ፍርድ ቤት ክስ መሥርተው ብይን የተሰጠበት የፍርድ ቤት ውሳኔ ፋይል ላይ ይገኛል። በገቢዎችና ጉምሩክ ልኬት የተወሰደበትና አርሶ አደሩም በልኬቱ አምነው የፈረሙበት ወረዳውና ኮሚቴዎች ያረጋገጡት መተማመኛ ቅፅ ፋይል ላይ ተያይዟል። በገቢዎችና ጉምሩክ ካሣ ክፍያ በሁለት ዙር የወሰዱበት የክፍያ ማስተርሊስት እና ሰርተፊኬት ፋይል ላይ ተያይዟል።
አቶ ፀጋዬ ሽኩር ለሚያቀርቡት ቅሬታ በተደጋጋሚ ጊዜ ተገቢና በቂ ምላሽ የተሰጣቸው መሆኑን ያነሱት ምላሽ ሰጪዎቹ፤ ግለሰቡ ግን ሆን ብለው በተቋማችን ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ በማካሄድ በተቋሙ ላይ በተለያየ ወቅት ቅሬታ በማቅረብ ለዚህ ምላሽ ለመስጠት ሲባል ተቋማችን ባለሙያዎችን በመመደብ በሚያደርገው የማጣራት ሥራ ከፍተኛ የሥራ ጫና በመፍጠር ላይ ይገኛሉ ሲሉ አብራርተዋል።
ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስደውት የነበረም በመሆኑ የግለሰቡ ቅሬታ እና ክስ አግባብነት የሌለው መሆኑ ፍርድ ቤቱ በውሳኔው ስላሳወቀ ከፍርድ ቤት ውሳኔ በኋላ የሚሠራ ምንም ዓይነት አስተዳደራዊ ሥራ የሌለ በመሆኑ፤ በየተቋሙ እየዞሩ የሚያቀርቡት ቅሬታ አግባብነት የሌለው መሆኑን ሁሉም የሚመለከተው አካል ሊያውቀው ይገባል በሚል አጠቃላይ የማጥራት ሂደቱን ማጠቃለሉን ክፍለ ከተማው አሳውቋል።
በተመሳሳይ መልኩ ምላሽ የሰጡን የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ አሕመድ በበኩላቸው፤ አቶ ፀጋዬ አንደ ዜጋ የክፍለ ከተማችን ነዋሪ ናቸው። ይህም በመሆኑ መብታቸውን በተለየ ሁኔታ የሚቀማቸው ወይንም ደግሞ የተለየ መብት እንደ ግለሰብ እንዲያራምዱ ወይንም እንዲጠቀሙ በተለየ ሁኔታ የሚስተናገዱበት አግባብ የለም። ይሁንና እኝህ ግለሰብ ቅሬታቸውን በየተቋማቱ እየዞሩ ያስገቡ ቢሆንም በየደረጃው ምላሽ መሰጠቱን ይናገራሉ።
እውነታው አቶ ፀጋዬ ሽኩሬ የሚጠይቁት የመብት ጉዳይ ሳይሆን፤ ‹‹የሚያቀርቡት ቅሬታ ሁሉም ከእውነት የራቀ እና ከሚገባው በላይ ጥቅም ፈላጊነት ነው›› ብለዋል። በተለይም በተለያዩ ወቅቶች፣ ሙስና አለ፤ የመልካም አስተዳደር ችግር እየተፈጠረ ነው በሚሉ እና ሌሎች መረጃዎችን ይዘው ወደ ጽሕፈት ቤቱ ይምጡ እንጂ፤ ይሄ ክሳቸው ግን መሬት ላይ የሌለ እውነት ነው። አብዛኛው ፍላጎታቸውም ሕጋዊ አሠራርን የተከተለ ሳይሆን የግል ጥቅማቸውን በማሰብ የሚደረግ ነው። በተለይም ደግሞ ከካሣ ጋር የሚያነሷቸው ቅሬታዎች በራሳቸው ፊርማ አረጋግጠው የወሰዱት ሆኖ ሳለ፤ ካሣ አልተከፈለኝም የሚለው አካሄዳቸው የማጭበርበር እና መንግሥትን የማታለል ሙከራ እንደሆነ አረጋግጠዋል።
እንደ አቶ መሐመድ ገለፃ፤ ግለሰቡ ከቤት ዕድሳት፣ ግንባታ ወይንም ግብር ጋር በተያያዘ የሚያነሷቸው ነጥቦች ብሎም የቤት ካርታ ባለቤትነት መብትም እንደ ግለሰብ ሆን ተብሎ ተለይቶ በደል የማድረስ ወይንም የማጉላላት ዓላማ ያለው ተቋምም ሆነ ግለሰብ የለም። ይህ ከሆነም በሕግ አግባብ እርምጃ ይወሰድበታል። ግለሰቡም ሕጋዊ መስፈርቶችን ካሟሉ መብታቸው የሚነፈግበት ምንም ዓይነት ሕጋዊ መሠረት የለም። ግለሰቡ እንደ ዜጋ አልተቆጠርኩም እያሉ ወቀሳ የሚያቀርቡት በማይመለከታቸው የፓርቲና የወጣት አደረጃጀቶች ስብሰባ ልግባ ሲሉ ይህ እርስዎን አይመለከትም ሲባሉ ልክ መብታቸው እንደተነፈጉ አስመስለው ይከሳሉ። በተጨማሪም የቤት ዕድሳት አስፈላጊውን መስፈርት አሟልተው ከመጡ የማይስተናገዱበት መንገድ የለም።
ከዚህም በተጨማሪ አቶ ፀጋዬ መብቴን ተነፈግሁ ብለው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ክስ መሥርተው እንደነበር አስታውሰው፤ በዚህም ክርክር በፍርድ ቤት የተሸነፉ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የሰነድ ማስረጃዎች
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ፤ በቀን 3/10/2007 ዓ.ም በቁጥር መልከማኤ1-17/3052/07 በሰጠው የውሳኔ ማሳወቅ በሚለው ደብዳቤ፤ ለአቶ ሽኩሬ ኤጃ አቤቱታ የቀረበበት ቀን- 03/10/2007 ዓ.ም የባሕር ዛፍ ግምት አልተከፈለኝም፤ የአትክልት የካሣ ግምት በአግባቡ አልተሰጠኝም የሚል ነው።
‹‹የአቤቱታው ዝርዝር ሁኔታም በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 ልዩ ስሙ አቡ ጨፌ ነዋሪ የሆንኩኝ በአዲስ አበባ ውሃ ልማት ፕሮጀክት ምክንያት የአትክልት ቦታ ለልማት በመፈለጉ በቦታው ላይ ላለው ባሕር ዛፍ የካሣ ግምት ያልተከፈለኝ ሲሆን፤ ለጓሮ አትክልቱ ደግሞ ተገቢው ካሣ ያልተሠጠኝ ስለሆነ በአግባቡ የካሣ ክፍያ እንዲሰጠኝ›› በማለት ኤጀንሲው የቀረበ አቤቱታ ነው ሲል ግለሰቡ ያቀረቡትን ጭብጥ ሃሳብ አስፍሯል።
የባህር ዛፍን በተመለከተ የወረዳ 08 ሥራ አስኪያጅ ጽሕፈት ቤት በ26/02/05 ዓ.ም ለክፍለ ከተማው መሬት ልማት ባንክና ከተማ ማደስ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በድጋሚ በ29/02/2005 ዓ.ም ለክፍለ ከተማው ለመሬት ልማት ባንክና ከተማ ማደስ ጽሕፈት ቤት ወረዳው በላከው ቃለ ጉባዔ ላይ የተዘረዘረው የባሕር ዛፍ ችግኝ ብዛት 1091፤ መካከለኛ ብዛት 7፤ ትልቅ ብዛት 24፤ በጣም ትልቅ ብዛት 10 ካሣ እንዲከፈላቸው ተብሎ የተላከ ቢሆንም ግለሰቡ ራሳቸው አንስተው እየተጠቀሙበት ስለሆነ የካሣ ክፍያው እንዳይፈጸም ተብሎ የተጻፈ በመሆኑና ራስዎ ባሕር ዛፉን የተጠቀሙበት በመሆኑ የካሣ ግምት እና ምትክ ቦታ አሰጣጥ መመሪያ ቁጥር 3/2002 አንቀጽ 16.5.2 ባለንብረቱ ከካሣ ይልቅ ዛፉን ቆርጠው ለመውሰድ ከመረጡ የካሣ ክፍያ አይሰጣቸውም ሲል ያትታል።
የጓሮ አትክልቱን በተመለከተም፤ በመጀመሪያ ለ2ሺ417 ነጥብ 87 ካሬ ሜትር የካሳ ክፍያ ብር 89ሺ797 የመሬት ልማት ባንክና ከተማ ማደስ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በደብዳቤ ቁጥር አቃ/ቃ/ክ/ከ/መ/ል/ባ/9439/04 በቀን 16/04/2004 ዓ.ም በድጋሚ ለ3ሺ488 ካሬ ሜትር መረጃው ትክክለኛ ስለመሆኑ በ14/02/04 ባለጉዳዩ በቅጽ 002 ላይ ባረጋገጡት መሠረት የካሣ ክፍያ ብር 129ሺ104 የመሬት ልማት ባንክና ከተማ ማደስ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በደብዳቤ ቁጥር አቃ/ቃ/ክ/ከ/መ/ል/ባ/404/05 በቀን 12/04/2005 ዓ.ም ለውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን እንዲከፍላቸው የጻፈው ደብዳቤ መኖሩን ይጠቁማል።
በተጨማሪም ለውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን እንዲከፍላቸው የጻፈው ደብዳቤ መኖሩና፣ የነበረኝ የቦታ ስፋት 6ሺ400 ካሬ ሜትር ሆኖ እያለ አለአግባብ ያለህ የቦታ ስፋት 2ሺ400 ካሬ ሜትር ነው ተባልኩ ላሉት በክፍለ ከተማው ያሉት ባለሙያዎች ቦታው ድረስ በመሄድ የሚነሳውን ቦታ በለኩት መሠረት አጠቃላይ የቦታው ስፋት ልኬት 5ሺ906.55 ካሬ ሜትር ሲሆን በዚሁ ካሬ ሜትር ላይ ለሰፈረው ንብረት በሁለት ጊዜ የካሣ ክፍያ እንዲከፈላቸው የሚገልጽ መረጃ መኖሩን ያሳያል።
ባለሙያዎቹ በጂ አይ ኤዝ (GIS) አስደግፈው በላኩት መረጃ ላይ እንደሚታየው ከ5ሺ906,55 ካሬ ሜትር በላይ ወደ 1ነጥብ92 ካሬ ሜትር የሆነ ቦታቸው በልማት ምክንያት የማይነሳ በመሆኑ እንዳልተካተተ ለማረጋገጥ የተቻለ በመሆኑ ስፋቱ ያነሰባቸው ምክንያት በልማት ምክንያት የማይነሳ ቦታቸውን ሳይጨምር የተለካ ለመሆኑ በመረጋገጡ የውሳኔ ሀሳብ እንደቀረበ ሰነዱ ያስረዳል።
የኮሚቴው ውሳኔ ሃሳብም፤ አቤቱታ አቅራ ቢው በተዘረዘሩት መረጃዎች መሠረት የባሕር ዛፍን በተመለከተ ግለሰቡ ራሳቸው አንስተው እየተጠቀሙበት ስለሆነ የካሣ ግምት እና ምትክ ቦታ አሰጣጥ መመሪያ ጥር 3/2002 አንቀጽ 16.5.2 ላይ ባለንብረቱ ከካሣ ይልቅ ዛፉን ቆርጠው ለመውሰድ ከመረጡ አይሰጣቸውም ስለሚል መከልከሉ አግባብነት ነው። ለተለካላቸው የቦታ ስፋት 5ሺ906.55 ካሜትር ሆነ የተከፈላቸው የጓሮ አትክልት የካሣ ክፍያ አግባብ ያለው በመሆኑ ያቀረቡት አቤቱታ አግባብ አይደለም የሚል የውሳኔ ሀሳብ የሚገልጽ ሰነድ የኮሚቴ አባላት ስም ዝርዝር ከነ ፊርማው በቀን 24/10/2007 ዓ.ም ተፈራርመው ያስቀመጡት መሆኑንም ሰነዱ ያሳያል።
የምርመራ ግኝት እና መልዕክት
አቶ ፀጋዬ ሽኩሬ ለዝግጅት ክፍላችን አቤቱታ ሲያቀርቡ፤ በፍርድ ቤት ጭምር ከሰው በሂደቱ ለእርሳቸው እንደተወሰነላቸው ተናግረዋል። ይሁንና ግን በክርክር አሸንፍኩ የሚሉበትን የፍርድ ቤት የውሳኔ ሰነድ ማቅረብ አልቻሉም። በአንጻሩ፣ የክፍለ ከተማው የመሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት የጠየኩት የይገባኛል ጥያቄ በፍርድ ቤት ውድቅ መደረጉን የሚያሳይ ሰነድ አቅርቧል።
በተጨማሪም አቶ ፀጋዬ በሚሊዮን የሚቆጠር ካሣ እንዳልተከፈላቸው ሲገልጹ፤ በመሬት ልማትና አስተዳደር በኩል ግን አቶ ፀጋዬ ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ የካሣ ክፍያ መቀበላቸውን፤ ይሄንንም በወቅቱ አሠራርና መመሪያ ተስማምተው ፈርመው መቀበላቸውን በሚያሳይ ሰነድ መኖሩ አረጋግጧል።
በመሆኑም በአቶ ፀጋዬ እና ቅሬታ ባቀረቡበት ጉዳይ ላይ እርሳቸው በቃል ከሚያቀርቡት የተበዳይነት አቤቱታ ባሻገር ይሄንን በደላቸውን የሚያስረዱበትን ማስረጃም መረጃም ማቅረብ ያልቻሉ ከመሆኑ ባሻገር፤ ቅሬታ ያቀረቡበት አካል ግን እርሳቸው ቀደም ብለው በጉዳዩ ላይ ተስማምተውና ተቀብለው የተቋጨውን ጉዳይ ለውጥ በመጣ፣ አመራር በተቀየረ ቁጥር እንደ አዲስና እንዳልተቀበሉት በማስመሰል እያቀረቡ ስለመሆኑ በመረጃ አስደግፎ አስረድቷል።
ሌላው ቀርቶ ቅሬታ አቅራቢው ተፈረደልኝ ያሉበትን የፍርድ ቤት ውሳኔ ማቅረብ ያልቻሉ ሲሆን፤ ቅሬታ የቀረበባቸው ተቋማት ግን ይሄ ሐሰት መሆኑንና ቅሬታ አቅራቢው በፍርድ ቤት ጉዳያቸው ውድቅ እንደሆነ ከማስረዳት ባለፈ፤ ውሳኔውን ተቃውመው ይግባኝ አለማለታቸው እንኳን በውሳኔው መስማማታቸውን እንደሚያመለክት፤ ቅሬታ አቅራቢው ግን የፍርድ ቤት ሽንፈታቸውን በመገናኛ ብዙኃን በኩል ጫና በመፍጠር ለማስቀልበስ ያሰቡት አካሄድ ስለመሆኑ የሚያስረዳ ነው። በመሆኑም ይሄን አይነት ጥያቄና ቅሬታ ሲኖር በተገቢው መረጃና ማስረጃ ሊደገፍ የሚገባው መሆኑን በቀጣይ መሰል ጉዳይ ይዘው ለሚቀርቡ አካላትም ለመጠቆም እንወዳለን።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር እና ሞገስ ተስፋ
አዲስ ዘመን ህዳር 12/2016