ኢትዮጵያ የቆላ መስኖ ስንዴ ማልማት የጀመረችው ከዘጠኝ ዓመት በፊት እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2013/14 አካባቢ ነበር:: በአንድ ሄክታር መሬት ላይ የተጀመረው የቆላ ስንዴ በ2018 ዓ.ም 50 ሺህ ሄክታር መድረሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ:: ከአምስት ዓመት ወዲህ ደግሞ የቆላና የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት መስፋፋት በመጀመሩ፤ በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሌና በሌሎች ክልሎች ተስፋፍቶ ባለፈው የ2013/14 የምርት ዘመን በአጠቃላይ 404 ሺህ ሄክታር መሬት ለስንዴ ልማት ውሏል::
በቆላማ አካባቢዎች ስንዴን ለዛውም በመስኖ ማልማት፤ ለብዙ ኢትዮጵያውያን አርሶና አርብቶ አደሮች እጅግ እንግዳ መሆኑ የሚታወቅ ነው:: አሁን ግን በሺዎች የሚቆጠሩ አምራቾች እየተሳተፉበት ይገኛሉ:: ይህን ተከትሎ በስንዴ ምርት ልማት ኢትዮጵያ አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ቶን ስንዴ ምርት ልታገኝ እንደምትችል እየተገለጸ ይገኛል::
የግብርና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በየዓመቱ ከ30 በመቶ በላይ የስንዴ ፍጆታዋን ከውጭ የምታስገባው ኢትዮጵያ አጠቃላይ ፍላጎቷ 97 ሚሊዮን ኩንታል አካባቢ ነው:: እ.አ.አ በ2022 ግን ምንም ዓይነት ስንዴ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳላስገባች ተገልጿል::
የኢትዮጵያ የስንዴ ምርት ልማት የትኩረት አቅጣጫን ተከትሎ በተሠራው ሥራ ዘንድሮ በመኸር ምርት 112 ሚሊዮን ኩንታል፣ እንዲሁም በመስኖና በበጋ ስንዴ ምርት ደግም 52 ሚሊዮን ኩንታል ይገኛል ተብሎ ተተንብዮዋል:: በመሆኑም የተተነበየው የምርት መጠን ከሀገር ውስጥ ፍላጎት አንፃር ትርፍ ምርት ይገኛል ተብሎ የተገመተ ሲሆን፤ በትንሹ 32 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እንደሚቻል ተጠቁሟል።
በኢትዮጵያ የመስኖ ስንዴ ልማት በአሁኑ ወቅት በጥራትና በመጠን አድጎል፤ በዚህም የኢትዮጵያን ፍላጎት ማሟላት ብቻ ሳይሆን ወደ ውጪ እስከመላክ ተደርሷል ተብሏል:: ይህ በተለይ የሀገርን ገፅታ በመገንባት ደረጃ ትርጉሙ ላቅ ያለ ስለመሆኑም ይነገራል:: ይህንና አጠቃላይ የስንዴ ምርት ልማት የትኩረት አቅጣጫን በተመለከተ የኢኮኖሚ ምሁራን የተለያየ ሃሳብ ይሰነዝራሉ::
ሶስተኛ ዲግሪያቸውን በልማትና ኢኮኖሚክስ ላይ የሠሩት እና በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህሩ ሞላ ዓለማየሁ (ዶ/ር) እንደሚናገሩት፤ ከዚህ በፊት ከአትክልት እና ፍራፍሬ ወጣ ተብሎ በመስኖ ሰብል ወደ ማምረት አይገባም ነበር:: በአብዛኛው በተለይ በመስኖ ስንዴ አይመረትም ነበር:: አሁን ግን በስፋት ወደ ጥራጥሬ ተገብቷል:: በተለይ ስንዴ በስፋት በመስኖ እየለማ ነው:: ይህ ደግሞ እጅግ የሚበረታታ ነው::
የበጋ ስንዴ በመስኖ የሚመረት ሲሆን፤ በክረምት ዝናብ ላይ ጥገኛ በመሆን ከሚመረተው ስንዴ የተሻለ ምርታማ ነው:: ምክንያቱ ደግሞ በበጋ በቂ ርጥበት ብቻ ሳይሆን በቂ ሙቀት ይገኛል:: ይህ የስንዴውን ምርታማነት ከፍ ያደርገዋል:: በሌላ በኩል ስንዴ በክረምት በሚመረትበት ወቅት ዝናብ ከሚፈለገው በላይ የሚሆንበት አጋጣሚ መኖሩን ጠቅሰው፤ በበጋ ግን የሰብሉን ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ፤ ውሃ ሲያስፈልግ ብቻ በመስኖ እንደሚሰጥ አስታውሰዋል:: ይህ ውሃ ሲበቃው እንዲቆም መደረጉም ምርቱን የተሻለ ያደርገዋል ብለዋል::
በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የግብርና ማዘመንና ገጠር ልማት ፖሊሲ ጥናት ማዕከል አስተባባሪ ታደሰ ኩማ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደሚገልፁት፤ ስንዴ በስፋት መመረት አለበት ተብሎ ከበልግ እርሻ ባሻገር በጋ ላይም መሞከሩ የሚበረታታ ነው:: በዓመት አንድ ጊዜ ከማምረት ይልቅ ሶስት ጊዜ እንዲመረት መደረጉ ምርታማነት የሚጨምር በመሆኑ ሃሳቡ የሚናቅ አይደለም:: ከአንድ ጊዜ በላይ በብዙ ቦታ ላይ ስንዴውን በስፋት ማምረት ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ብቻ ሳይሆን ሀገር ጠግባ ከተትረፈረፈ ወደ ውጭም ለመላክ ይቻላል:: ለውጭ ገበያ መዋሉ ደግሞ ሌላው ጥቅም ነው::
በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም ደረጃ ያሉ የዱቄት ፋብሪካዎች በጣም ብዙ ናቸው:: የኢትዮጵያም የስንዴ ፍላጎት በጣም ከፍተኛ ነው:: የፋብሪካዎቹ ዓመታዊ ፍላጎት እጅግ በጣም ብዙ ነው:: በኢትዮጵያ የፍላጎቱ መብዛት ስንዴ ላይ ጤነኛ ያልሆነ የገበያ ውድድር እንዲኖር አድርጓል:: ለምሳሌ ፋብሪካዎች ሲገዙ አንዱ 7ሺህ ቢሰጥ ሌላው ደግሞ ዓመቱን ሙሉ ቁጭ ብሎ ባዶ ከሚቀመጥ ብሎ 7ሺህ 500 ይሰጣል:: በእዚህ ጊዜ ዋጋው ሳይታሰብ እየናረ ይመጣል:: ስንዴ በስፋት መመረቱ ይህን ችግር ለማቃለል የሚረዳ መሆኑንም (ዶ/ር) ታደሰ ይናገራሉ::
በብዛት ስንዴ መመረቱን እጅግ አስፈላጊ መሆኑን የሚያስረዱት ሌላኛው የኢኮኖሚ ባለሙያው (ዶ/ር) ሞላ፤ በዓለም ላይ ስንዴ ታዋቂ ምግብ ነው:: አግሮ ኢኮሎጂን ታሳቢ አድርገው የወጡ ብዙ የምርምር ውጤቶች እና የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች አሉ:: ያንን ለመጠቀም ስንዴ ምቹ በመሆኑ በስፋት ማምረት እና ትኩረት መስጠት ተገቢ ነው ብለዋል::
ሀገሪቷ በምግብ ራሷን ለመቻል ምን ደረጃ ላይ ናት? የሚለውን በመመዘን በኩል ሰንዴ ከፍተኛውን ሚና እንደሚጫወትም (ዶ/ር) ሞላ ያብራራሉ:: አንዱ ሀገር የሚመረተው የምግብ ዓይነት ሌላ ሀገር ላይመረት ይችላል:: ለምሳሌ በፊት በኢትዮጵያ እንደውም በአጠቃላይ በአፍሪካ አፕል አይመረትም ነበር:: እነአውሮፓ ደግሞ በስፋት ያመርቱ ነበር:: የሀገሮችን የምግብ ዋስትና መጠን በአፕል እንስፈር ቢባል አይሆንም፤ ምክንያቱም በሁሉም ሀገር አይመረትም:: በተቃራኒው ስንዴ ግን በየትኛውም የዓለም አቅጣጫ ይመረታል ተብሎ ይታሰባል:: ስለዚህ በአብዛኛው በዓለም ደረጃ የሀገር ምርት የሚለካው በስንዴ መሆኑን አስታውሰው፤ ያለውን የእህል ምርት በሙሉ ወደ ስንዴ ተቀይሮ የሚሰላ መሆኑን ይናገራሉ::
የኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናዋ ምን ደረጃ ላይ ነው? የሚለውን ለማስላት፤ የሚሠራው የስንዴ አቅርቦት እና ፍላጎት ተሰልቶ ነው:: የሚሰላበት መንገድም ኢትዮጵያ ያመረተችው በቆሎ፣ ሽንብራም ሆነ አብሽ ማንኛውም ምርት ወደ ስንዴ ይመነዘራል:: ሁሉም ስንዴ ቢሆን ምን ያህል ይሆናል? የሚለው ታስቦ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ያህል ስንዴ ያስፈልጋል? አሁን የተመረተው ስንት ይሆናል? በምግብ እህል ራሷ ችላለች አልቻለችም? ምን አላት? ምን የላትም? የሚለው ሙሉ ሂሳቡ ሲሰላ የሀገር ፍላጎት ምን ይመስላል የሚለውም ታክሎበት በመጨረሻም የምግብ ዋስትናዋ ተሠልቶ ይቀመጣል ይላሉ::
እንደ ዶ/ር ሞላ ሁሉ ዶ/ር ታደሰም በስፋት ስንዴ መመረቱን ቢደግፉም፤ አጀማመሩ ላይ ግን ጥያቄ አላቸው:: ‹‹አመራረቱ ምን ያህል ሳይንሳዊ እና ምርታማነትን የሚጨምር ነው?›› ለሚለው ጥያቄ ምላሽ መገኘት አለበት ይላሉ:: ሥራው ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መደገፍ እንዳለበት በማስታወስ፤ ምርታማነትን የሚጨምሩ መሬቶች በደንብ መታየት እና መለየት እንዳለባቸው አብራርተዋል:: በተጨማሪ የውሃ ፍላጎት በቂነቱን በተመለከተም በደንብ ሊታሰብበት እንደሚገባ ተናግረዋል::
ጅምሩ መልካም ቢሆንም አብዛኛዎቹ ነገሮች በጥናት ላይ የተመረኮዙና ሳይንሳዊነት ቢኖራቸው ጥሩ ነው በማለት ያብራራሉ:: ለምሳሌ ሁሉም አፈር ተመሳሳይ አይደለም፤ ልዩነት አለው:: የአየር ሁኔታውም መታየት አለበት፤ በየትኛው አካባቢ በየትኛው የአየር ሁኔታ የሚለው መለየት አለበት:: ስንዴም የራሱ ባህሪ አለው:: ሁሉም ተመሳሳይ አይደለም ፤ ይለያያል:: ስለዚህ የበጋ ስንዴ ማምረቻ ቦታዎች፣ አፈር እና አየራቸው ምን ያህል ምቹ ነው? የሚለውን ሳይንሳዊ ጥናት ተደርጎበት ሊከናወን ይገባል ባይ ናቸው::
መንግሥትም ባሳለፍነው ዓመት ክፍተቶቹ የትኛዎቹ ናቸው የሚለውን ለይቷል የሚል ተስፋ እንዳላቸው የተናገሩት (ዶ/ር)ታደሰ ፤ የነበረውን ገምግሞ ቀጣዩን የበለጠ ሳይንሳዊ አድርጎ መቀጠል እንዳለበት ይመክራሉ::
በሌላ በኩል በኢኮኖሚ ባለሙያው በዶ/ር ሞላ የተጠቀሰው፤ ለስንዴ ትኩረት መሰጠቱ አንደኛ ቴክኖሎጂ በስፋት ስለሚገኝለት ምርታማነቱን ለማሳደግ ያመቻል:: ሁለተኛው በዓለም ላይ የስንዴ ተጠቃሚ ብዙ ነው:: ብዙ ሀገሮች ስንዴን ይገዛሉ፤ ሰንዴ በዓለም ተፈላጊ እና ገበያ የማያጣ ምርት በመሆኑ ገዢ ይጠፋል የሚል ስጋት የለም:: እነዚህ ምክንያቶች በራሳቸው በስፋት መመረቱ ጠቃሚ መሆኑን የሚያረጋግጡ ናቸው ይላሉ::
ብዙ ሀገሮች ስንዴ ላይ ይሰራሉ፤ ኢትዮጵያም ስንዴ ማምረቷ በሀገር ገፅታ ላይ የሚኖረው ጠቀሜታ በቀላሉ የሚታይ አይደለም የሚሉት (ዶ/ር) ሞላ ፤ የምግብ ዋስትናዋ የት ደረጃ ነው፤ የሚለው የሚታየው ያመረተችው ከስንዴ ጋር ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ ጠቅላላ ሕዝቧ በዓመት ከሚፈለገው በላይ ከሆነ በምግብ እህል ራሷን ችላለች የሚባል መሆኑንም አስረድተዋል::
ጤፍ በስፋት ተመርቶ ወደ ውጭ ለመላክ ቢሞከር ውጤት ላያመጣ ይችላል፤ ምክንያቱም ምርቱ በዓለም የሚታወቅ አይደለም:: ስንዴ ግን ታዋቂ ነው:: ለስንዴ በዓለም ደረጃ የተገነባ ገበያ አለ:: ስንዴ ከተመረተ ገበያ አይጠፋም፤ ምክንያቱም ዓለም የሚሸምተው የስንዴ ምርት ነው:: ስለዚህ የዓለምን የገበያ አቅም መጠቀም ይገባል ብለዋል::
ነገር ግን ሁልጊዜም የሁኔታዎች ትንታኔ መሠራት አለበት ያሉት (ዶ/ር) ሞላ ፤ በስንዴ ያለንበት ደረጃ ከሌሎች ጋር ሲወዳደር ምን ደረጃ ላይ ነን? ምን ያህል ስንዴ አለ? የሚለው በየጊዜው እየተገመገመ መሔድ መቻል አለበት ሲሉ፤ እርሳቸውም ጥናት ላይ መመርኮዝ እንደሚገባ ይጠቁማሉ::
በዓለም ላይ ፍፁም የሚባል ነገር የለም:: አሁን ባለው ሁኔታ ስንዴ የተሻለ ገበያ አለው:: ወደፊት የሚሆነው አይታወቅም:: ዋናው ዘመኑ የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ያንን ማካካስ ይቻላል:: ስንዴ ሲመረት ሌሎች እየተተው በመሆኑ፤ እነሱ ሲቀሩ የሚካካሱበት እና በሌላ የሚተኩበት ወይም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡበት ሁኔታ መፈጠር እንዳለበት ያመለክታሉ:: እዚህ ላይ ከውጭ የሚገባው ሌላው ምርት ከስንዴ ከሚገኘው ገቢ ያነሰ ወጪን ወይም የስንዴው ገቢ የተሻለ መሆን እንዳለበት ያስገነዝባሉ::
(ዶ/ር) ሞላ እንደተናገሩት፤ ሌላው አመራረቱ ላይ የቴክኖሎጂ ሽግግሩን በደንብ ማካሔድ ያስፈልጋል:: አመራረቱን በደንብ ማሳለጥ እና የተሻለ ማድረግ ሀገሪቷ የበለጠ ተጠቃሚ ያደርጋታል:: ከገፅታ ግንባታ አንፃር ከታየ እስከ አሁን ድረስ ሀገሪቷ የስንዴ እርጥባን ተቀባይ ነበረች:: አሁን በምግብ እህል ራሷን ችላለች ባይባልም፤ ወይም የሕዝቧ የምግብ ፍላጎት እና ምርቱ የተመጣጠነ ባይሆንም ስንዴ ወደ ውጭ መላክ መጀመሯ በራሱ ገፅታዋን ለመገንባት የሚኖረው ጠቀሜታ ቀላል አይደለም::
ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ለአንድ ምዕተ ዓመት በሚባል ደረጃ የስንዴ እርዳታ ተቀባይ የምትባል ሀገር ስንዴ በብዛት እና በጥራት፤ ዓለም በሚፈልገው መልኩ አምርታ ከስንዴ ላኪ ሀገራት ጋር ተቀላቀለች መባሉ በራሱ ትርጉሙ ቀላል አይደለም ይላሉ:: እንደውም የውጭ ባለሃብቶችም በሀገሪቷ ኢንቨስትመንት ላይ እንዲሳተፉ የሚያደርግ እና የሚያነቃቃ ነው ብለዋል::
በሌላ በኩል ዶ/ር ታደሰ፤ ነገር ግን በኢትየጵያ ደረጃ ከስንዴ ጋር እኩል ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው የኢትዮጵያን የምግብ ፍላጎት ለማርካት በቆሎ ላይ ቢሠራ መልካም ነው የሚል እምነት አላቸው:: ምክንያቱም በብዙ የኢትዮጵያ አካባቢዎች እና የአየር ፀባይ መብቀል ይችላል:: ቴክኖሎጂው እና ልምዱም ብዙ ቦታ ላይ አለ:: ምርታማነቱም በቀላሉ እጥፍ መሆን የሚችል ነው:: የአፍሪካ ሀገሮች በቆሎ ተመጋቢዎች ናቸው፡ ይህንን ግንዛቤ ውስጥ በመጨመር ከስንዴው ጎን ለጎን በስፋት በቆሎ ላይ መሠራት አለበት የሚል እምነት እንዳላቸው ይናገራሉ::
በምግብ እህል ራስን ለመቻል ከአሁን በኋላ ጤፍ መጠቀም አያዋጣም:: ነባር ባህል ብቻ ያዋጣል ብሎ መቀጠል ትክክል አይሆንም:: ከዚህ በኋላ ጤፍ ቅንጦት እንደሚሆን አያጠያይቅም:: ስለዚህ ለውጥ ያስፈልጋል፤ ለውጡ ምን ላይ መሆን እንዳለበት የመንግሥት የቤት ሥራ ነው:: ስኳር ድንችን የመሰለ በብዙ ሀገራት ለምግብነት የሚውለው የሥራ ሥር ምግብ መዘንጋት የለበትም:: የምግብ ይዘቱ እና ጤናማነቱ ከተመሰከረለት ስኳር ድንች በተጨማሪ ካሳቫ እና የእንሰት ውጤት ቆጮ የመሳሰሉትንም ማየት ይገባል:: ከነባር ታዋቂ ምግቦች ውጭ ሌሎቹንም ማሰብ የግድ መሆኑንም አመልክተዋል::
በአጠቃላይ እንደ የኢኮኖሚ ምሁራኑ እምነት የበጋ ስንዴ ላይ ትኩረት ተደርጎ መሠራቱ መልካም ነው:: ከገበያም ሆነ ከቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት አንፃር አዋጪነቱ አያጠራጥርም:: ከስንዴ ተረጂነት ወደ ስንዴ ላኪነት መሸጋገር የሀገርን ገፅታ ለመገንባት የሚኖረው ጠቀሜታም በቀላሉ የሚታይ አይደለም:: ነገር ግን ሳይንሳዊ ጥናት ላይ መመስረት ቢቻል የበለጠ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል አመላክተዋል::
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ኅዳር 11 ቀን 2016 ዓ.ም