ተወዳዳሪነታቸው እየጨመረ የመጣው የሀገር ውስጥ የቆዳ ውጤቶች

የኢትዮጵያ የቆዳ ምርቶች በዓለም ገበያ ተቀባይነታቸው እየጨመረ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በተለይ ከቆዳ የሚሰሩ ቦርሳዎች በዓለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪ ሆነው መቅረባቸው ተመራጭ እያደረጋቸው መሆኑን በዘርፉ የተሰማሩ አምራቾች ይጠቁማሉ። የሀገር ውስጥ የቆዳ ምርቶች ጥራታቸውን ጠብቀው መመረታቸው በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ መሆን እያስቻላቸው መሆኑን ያመላክታሉ።

በሀገር ውስጥ የቆዳ ውጤቶች ከሚያመርቱት ድርጅቶች “የአስ ኢትዮጵያ” (AS Ethiopia) የቆዳ ምርቶች አምራች ድርጅት አንዱ ነው፡፡ የድርጅቱ የፕሮዳክሽን ማናጀር አቶ ተስፋዬ በየነም የሀገር ውስጥ የቆዳ ምርቶች በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ መሆናቸውን ይመስክራሉ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፤ ድርጅቱ በአብዛኛው የሴት ቦርሳዎችን ያመርታል፡፡ ቦርሳዎቹ ውበታቸውንና ጥራታቸውን የጠበቁ በምርጥ ዲዛይን የተሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ከውጭ ሀገር ከሚመጡት ቦርሳዎች ጋር መወዳደር እንደሚችሉም ገልጸዋል፡፡

የአስ ኢትዮጵያ ምርቶች በሀገር ውስጥ ገበያ ሰፊ ተቀባይነት እያገኘ መሆናቸው የሚናገሩት አቶ ተስፋዬ፤ ምርቶቹ ከዚህ ቀደም በገበያ ላይ ያልተለመዱና ለየት ያሉ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ህብረተሰቡ ምርቶቹን በጥራትና በይዘታቸው እንደሚወዳቸውና ፈልጎ እንደሚገዛቸውም ነው የተናገሩት፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፤ ድርጅቱ ወደዚህ ሥራ ከገባ ገና አንድ ዓመቱ ነው፤ ምርቶቹን ለሀገር ውስጥ ገበያ እያቀረበ ሲሆን፣ አሁን ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ያለው ምርቶቹን ለውጭ ገበያ በመላክ ተቀባይነት ለማግኘት ነው፡፡ ምርቶችን ለውጭ ገበያ የመላኩ ሂደት ተጀምሯል፡፡

በቆዳው ዘርፍ ላይ የረጅም ጊዜያት ልምድ እንዳላቸው የሚናገሩት አቶ ተስፋዬ፤ ድርጅቱ ከዚህ በፊት እንደዚህ ዓይነት የሴቶች ቦርሳዎችን አምርቶ እንደማያውቅና ይህ የመጀመሪያ መሆኑን ያነሳሉ፡፡ እነዚህ ምርቶች መሥራት ሲጀምር ፋብሪካ አቋቁሞ በሰፊው ወደ ሥራ እንደገባ ጠቅሰው፤ በምርቶቹ በጥራትም ሆነ በተወዳዳሪነት ምንም የማይወጣለቸው እንደሆነ ይገልጻሉ። በተለይ ከተለያዩ የውጭ ሀገራት በተለያዩ አጋጣሚዎች ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ሰዎች በደንብ ወደው የሚገዟቸው መሆናችን ተናግረዋል፡፡

የቆዳ ምርቶታቸው በኅብረተሰብ ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት ከፍተኛ ከመሆኑ በላይ እነዚህ ምርቶች ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ነው የተመረቱት›› የሚል ጥያቄ እያስነሳ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ተስፋዬ፤ ምርቶቹ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመመረታቸው ‹‹በኢትዮጵያ ተመረቱ/made in Ethiopia/ የሚል ጽሑፍ እያስገቡ እንደሚሰራም ነው ያስታወቁት፡፡›› ‹‹በኢትዮጵያ የተመረተ›› መባሉ ምርቶቹ ኢትዮጵያ ውስጥ የተመረተ መሆኑ እንዲታወቅና ችግር ካለበት ችግሩ እዚሁ እንዲፈታ የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው፤ ዋናው ነገር ጥራት ያላቸውን ምርቶች አምርቶ ሀገርና ራስን ማስተዋዋቅ እንደሚቻል ማሳየት ነው ብለዋል፡፡

‹‹የሴቶች ቦርሳዎችን በተለያዩ ዲዛይኖችና ቀለሞች ዘመኑን በሚመጥን መልኩ ዘመናዊ አድርጎን መሥራት የቻልንበት ዋንኛ ምክንያት በገበያው ላይ ያሉ ክፍተቶችን አጠንተን ወደ ሥራ በመግባታችን ነው›› ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ ምርቶቹ በገበያው ያሉትን ክፍተቶች ሊሟሉ የሚችሉ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የፋሽን ኢንዱስትሪውን ለማነቃቃትም የራሳቸው አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው አመላክተዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ የድርጅቱ የሴቶች ቦርሳዎች ዋጋቸውም ተመጣጣኝ ነው፤ ከ5ሺ ብር ጀምሮ እስከ 20ሺ ብር ይጠየቅባቸዋል፡፡ የቦርሳዎቹ ጥራት የዓለም ገበያ ስታንዳርድ የሚያሟሉ በመሆናቸው የሚወጣባቸው ወጪ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዋጋቸውም ከዚያ አንጻር የተተመነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለቆዳ ምርቶች ሥራ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ቆዳውና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች በአብዛኛው በሀገር ውስጥ እንደሚገኙ አቶ ተስፋዬ ጠቅሰው፤ እንደ መለዋወጫ ሌሎች ግብዓቶች ከውጭ እንደሚመጡ ገልጸዋል፡፡ ይህ ሁኔታም የቆዳ ምርቶችን በስፋት ለማምረት በሥራቸው ላይ እንቅፍት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በአብነት ጠቅሰው እንዳብራሩት፤ አንድ ቦርሳ ለመሥራት በርካታ መለዋወጫዎች ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ እነዚህ መለዋወጫዎች ኢትዮጵያ ውስጥ አይመረቱም፤ አይሰሩም። ሁሉም ከውጭ የሚመጡ ናቸው፡፡ ከጉምሩክ ጀምሮ ያለው ሂደትም በጣም አስልቺና ጊዜ የሚወሰድ ነው፤ ይህ ሁሉ በሥራው ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡

 የቆዳው ዘርፍ ሰፊ የሰው ኃይል የሚይዝ ዘርፍ ስለሆነ ቀደም ሲል ጀምሮ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶት እየሰራበት ነው የሚሉት አቶ ተስፋዬ፤ አሁንም ከውጭ ለሚመጡት ግብዓቶች ትኩረት ሰጥቶ በደንብ ቢሰራ ከቆዳው ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ እንደሚቻል ይናገራሉ፡፡ ኢትዮጵያ በቆዳ ምርቶቿ በውጭ ሀገር ገበያ ላይ መታወቋ በራሱ ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ቀደም ሲል ቆዳው በጥሬ ሄዶ እነሱ እሴት ጨምረው ለኛ መልሰው የሚሸጡበት ሂደት እንደነበረም ይናገራሉ፡፡ ስለዚህ ቆዳው እሴት ተጨምሮበት በእንደዚህ ዓይነት መልኩ ተሰርቶ ለውጭ ገበያ መቅረቡ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል፤ የኢትዮጵያ እድገት አንድ መገለጫ እንደሆነም አንስተዋል፡፡

እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ ቀደም ሲል መንግሥት ለቆዳው ዘርፍ የሰጠው ትኩረትና እገዛ አሁንም መቀጠል አለበት፡፡ ድርጅቱ አሁን ላይ ለሃያ አምስት ሠራተኞች የሥራ እድል የፈጠረ ሲሆን፤ አሁን ያለው የሰው ኃይል ምርቶችን ለኤክስፖርት ለማድረግ ብቁ አይደለም፡፡ ይህ ድርጅት በደንብ ወደ ማምረት ሥራው ገብቶ ምርቶቹን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ሲጀምር የሚምርተው ምርት መጨመር ስላለበት የሚያስፈልገው የሰው ኃይል መጨመር ይኖርበታል፡፡

ለምሳሌ ድርጅቱ ለውጭ ገበያ 500 ቦርሳዎች ማቅረብ ቢጠበቅበት አሁን ላይ በቀን ከአንድ እስከ አምስት ቦርሳዎች ብቻ ነው የሚሰራው፡፡ ይህን መሥራት አሁን ባለው የሰው ኃይል ብዙ ቀናት ይወስዳል፡፡ ስለዚህ ለብዙ ሰዎች የሥራ እድል ለመፍጠር ያስችላል፡፡

ድርጅቱ አሁን ላይ በሀገር ውስጥ ሁለት መሸጫ ሱቆች ያሉት ሲሆን፤ ተጨማሪ ሱቆች ለመክፈትም አቅዷል፤ ከዚህ በተጨማሪ አሁን ላይ ምርቶቹን የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም በደንብ እያስተዋወቁ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይ እነዚህ የቆዳ ምርቶች ለውጭ ገበያ መላክ ብቻ ሳይሆን ድርጅቱ በዱባይና በአሜሪካ የራሱን ሱቅ የመክፈት እቅድ አለው ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ ምርቶቹን ወደ ውጭ ሀገር በመላክ ተቀባይ እንዲኖረው ብቻ ሳይሆን ራሱ ምርቶቹን ለመሸጥ እንደሚፈልግ አብራርተዋል፡፡

እንደ ሀገር ለቆዳው ዘርፍ አሁን ትኩረት ቢሰጠውና የቆዳ ሀብቱን ተጠቅመን በቆዳ ውጤቶች በተለይ በቦርሳዎች ብንወዳደር ጥሩ እድል እንዳለን ብዙ አመላካቾች ይታያሉ የሚሉት አቶ ተስፋዬ፤ ከዚህም በተጨማሪ የሥራ እድል በመፍጠር ረገድ ብዙ የሰው ኃይል መያዝ የሚያስችል ሁኔታ እንዳለም አመላክተዋል፡፡

 ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You