
አዲስ አበባ፦ በመዲናዋ ከፍተኛ ጭስ የሚለቅ መኪና ያላቸው አሽከርካሪዎች አስቀድመው መፍትሄ እንዲያዘጋጁ የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ። የመኪና ጭስ ስታንዳርድ እየተዘጋጀ መሆኑንም ተገልጿል።
የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ድዳ ድሪባ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤የመኪና ጭስ ስታንዳር እየተዘጋጀ ነው። በዚህም እያንዳንዱ መኪና የሚያስወጣው ጪስ የሚለካ ይሆናል።
መኪናው ከተቀመጠው መለኪያ በላይ ጪስ የሚያመነጭ ከሆነ አገልግሎት እንዳይሰጥ ይደረጋል ብለዋል።
አብዛኛውን ጊዜ ከፍተኛ ጭስ የሚለቁ ተሽከርካሪዎች ከተመረቱ 23 ዓመትና ከዚያ በላይ ያገለገሉ ናቸው ያሉት ኃላፊው፤ ስለዚህ አሮጌ መኪና ያላቸው አሽከርካሪዎች ከአሁኑ መፍትሄ ሊያዘጋጁ ይገባል ብለዋል።
በመዲናዋ አሮጌና ከፍተኛ ጭስ የሚለቁ በርካታ መኪኖች መኖራቸውን በመጥቀስ፤ መኪናዎቹን በአንድ ጊዜ ሥራ እንዲያቆሙ ማድረግ እንደማይቻል አመላክተዋል፡፡
ሆኖም ቦሎ የሚሰጡ፣ መኪናዎችን የሚቆጣጠሩና መኪና የሚገዙ አካላት ባለሥልጣኑ የሚያወጣውን የጭስ ስታንዳርድ መሠረት እንዲያደርጉአቶ ድዳ አሳስበዋል።
እንደ ኃላፊው ገለፃ፤ ስታንዳርዱ በቅርቡ ተግባራዊ ይደረጋል። ስለዚህ አሮጌና ከፍተኛ ጭስ የሚለቅ መኪና ያላቸው አሽከርካሪዎች ጭስ የሚቀንስ ቴክኖሎጂን መጠቀም ወይም መኪናውን መቀየር ይኖርባቸዋል።
አገልግሎት የሰጡ መኪናዎች እንደበፊቱ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ቢደረግ ኖሮ አዳዲስ መኪናዎች ወደ ከተማዋ አይገቡም ነበር ያሉት አቶ ድዳ፤ እየተዘጋጀ ያለው የመኪና ጭስ ስታንዳርድ ለአየር መበከል አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ጋዞችና ብናኞች ጋር ተያይዘው የሚመጡ የጤና ችግሮችን ለመቀነስ ያስችላል ብለዋል።
በመዲናዋ የአየር ጥራት ለመቆጣጠር የሚያስችሉ 10 ዘመናዊ መሣሪያዎች የተገጠሙ ሲሆን በቅርቡ ደግሞ ከመኪና የሚወጣውን ጭስ መቆጣጠር የሚያስችል መሳሪያ ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የአየር ጥራት መረጃ በተለይ በተገቢው ጊዜና ቦታ መረጃ መስጠት የአየር ብክለትን ተጋላጭነትን ለመቀነስ ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።
በዓለም የጤና ድርጅት በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ሀገራት የአየር ጥራት ስታንዳርድ ያዘጋጃሉ። አዲስ አበባም ይህን መሠረት ስታንዳርዶች እያዘጋጀች ነው ያሉት አቶ ድዳ፤ ይህም ለጤና ተስማሚ የሆነ አየር ጥራት እንዲኖር እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 10 ቀን 2016 ዓ.ም