በመንገዴ ላይ…

እንደለመደብኝ ዘወትር ጠዋት ከእንቅልፌ እየተነሳሁ ወደ መስሪያ ቤቴ እሄዳሁ፡፡ መስሪያ ቤቴ ከመኖሪያዬ ብዙ አይርቅም፡፡ ለዚህም ነው ብዙውን ጊዜ በእግሬ የምመላለሰው፡፡ ይህን የወሰንኩት ከታክሲ ግፍያው ለመሸሽ ስል ነው።

ልማደኛው እግሬ ዛሬም መንገዱን ጀምሯል። ማየትን የማይታክቱ አይኖቼ ዙሪያ ገባውን መቃኘቱን ይዘውታል፡፡ የንጋቱ ማብሰሪያ የአዕዋፋት ዝማሬ ፣ የታክስ ረዳቶች ጩኸት፣ የኮቴ ድምፆች… ሁሌም ለጆሮዬ የእለት ተእለት ዜማ ናቸው ፡፡

እስከ አሁን ከርታታው ዓይኔ ብዙ አስደሳች፣ አሳዛኝ፣ ተስፋ አስቆራጭ ሁነቶችን ያየባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አልፈዋል፡፡ ጆሮዬም ቢሆን ለመስማት የማይጋብዙ ወሬዎችን ሳይወድ በግዱ እየተቀበለ እንዳልሰማ ማለፍ ከጀመረ ሰነባብቷል። በሁሉም ምልከታዬ ግን አይቼ እንዳላየሁ ሰምቼ እንዳልሰማሁ ማለፍ የሌለብኝ አያሌ ጉዳዮች አጋጥመውኛል ፡፡

ከእናታቸው ማህጸን እንደወጡ ጎዳና የተቀበለቻቸው፣ ብርድ፣ ቁርን፣ ረሀብና ስቃይን የጋበዘቻቸው ጨቅላ ህፃናት ዘወትር ከእይታዬ አይርቁም፡፡ ከእነዚህ ነፍሶች መሀል የትምህርት ደጃፍን በመርገጫቸው እጃቸውን ለልመና፣ ራሳቸውን ለተለያዩ ሱሶች ያስገዙ ወጣቶችን ስመልከት ሁሌም አዕምሮዬ በማይመለስ ጥያቄ ይፈተናል ፡፡

በሌላ በኩል ከህፃን እስከ አዋቂ መጠለያ በማጣት በየግንቡ ስርና በየአብያተ ክርስቲያናቱ ጥግ ተከልለው ለእለት ጉርሳቸው አላፊ አግዳሚውን የሚማፀኑት የአብዛኞቻችን ዓይኖች ያስተውላሉ ፡፡ ሁሌም ግርም የሚለኝ ጠዋት ወደ ስራ ስወጣ ዕቃቸውን ቋጥረው፣ ውሃቸውን ይዘው በዘወትር ቦታቸው ላይ የሚሰየሙ ሰዎች ነገር ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ምጽዋት ጠያቂዎች ናቸው፡፡ ባየኋቸው ቁጥር ምናልባት ለምዶባቸው ይሆን? እያልኩ እራሴን እጠይቃለሁ።

ይህ ሁሉ ወገን በየጎዳናው ህይወቱን እንዲመራ የተገደደበት ምክንያት ምን ይሆን? ለዚህስ ችግር ማን ይሆን ተጠያቂው? ራሴን እጠይቃለሁ፡፡ አለፍ ብዬም የሚሰጣቸው ምጽዋት በቂያቸው ስለ መሆን አለመሆኑ እየመዘንኩ እጨነቃለሁ፡፡ ሁሉንም መለወጥና ወደተሻለ ህይወት መምራት ባይቻል እንኳን ቁጥራቸውን መቀነስ ዋነኛው መፍትሔ እንደሆነ ይሰማኛል ። ነገር ግን አሁንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደጎዳና የሚወጡ ዜጎች ቁጥር እያሻቀበ መምጣቱን ልብ ይሏል።

መልስ በሌለው ሀሳብ ተሳፍሬ እያወጣሁ እያወረድኩ ሳለ የእድል ጮራ ወቶላቸው በወጉ እንዲኖሩ የተፈጠሩ ህፃናት የምሳ እቃቸውን አንጠልጥለው፣ በትካሻቸው የተወጠረ ቦርሳ ተሸክመው ወደ ትምህርታቸው ሲሄዱ አስተውላለሁ፡፡ እርስ በእርሳቸው ከእኩዮቻቸው ጋር የሚያወሩት ወሬ ደግሞ ሌላ ግርምት ያጭርብኛል፡፡ መደማመጥ በሌለው ድምጸታቸው ስለምዕራባዊያን የፊልም ተዋናዮች፣ ስለሚወዷቸው አርቲስቶች ፣ የእግር ኳስ ክለብ ወዘተ… በነጻነት ያወራሉ፡፡ ይባስ ብሎ ስለ ፍቅር አጋር፣ ፆታዊ ግንኘነት እና በእነሱ ዕድሜ ሊወሩ ቀርቶ ለአፍታም መታሰብ ስለማይገባቸው ጉዳዮች እያነሱ በጎላ ድምጽ ይጫወታሉ ።

አሁንም የመንገድ ላይ አስተውሎቴ ቀጥሏል። ርምታዬ ከእኔው ጋር ነው፡፡የአንዳንድ ወጣቶችን የአለባበስ ስርዓት እየቃኘሁ ነው፡፡ አንዳንዶች የሀገራቸውን ባህል እና ወግ ፈጽሞ የዘነጉት ይመስላል፡፡ ሰውነታቸውን ለተለየ ትርዒት ያቀረቡ ያህል አላፍ አግዳሚውን አጀብ የሚያሰኙ ናቸው፡፡ በኔ ግምት ሁሉም የራሱ ጊዜ እና ቦታ አለው፡፡

ይህን እውነት አምነውና ተረድተው በተግባር የሚያሳዩ ሲኖሩ ማንነታቸው መልካም ትርጉም ይኖረዋል ፡፡ አንዳንዶች ግን ‹‹ካላያችሁን›› በሚመስል ድርጊት በየመንገዱ እጅ ለእጅ ተያይዘው፣ ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፈው ያለአንዳች እፍረት ከንፈር የሚቃመሱ ናቸው፡፡

በየጊዜው እንዲህ መሰሎቹ ቁጥራቸው መበራከቱን ስመለከት ውስጤ ከማዘን አልፎ ሲሸማቀቅ ይሰማኛል፡፡ መለስ ብዬ የወላጆችን ኃላፊነት አስባለሁ፡እርግጥ ነው አንዳንዴ ‹‹ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ›› ሊባል ይችላል፡፡እንዲያም ቢሆን ዋንኛ ትኩረት ከወላጆች መራቅ አይኖርበትም ፡፡ ልጆች ከተወለዱበት ቀን አንስቶ እራሳቸውን እስከሚችሉበት እድሜ ድረስ የወላጆችን ድጋፍና ክትትል ይሻሉ፡፡

ልጆች ነገሮችን ማድመጥ፣ መገንዘብና መናገር ሲጀምሩ የተለያዩ ሃሳቦችን ሊያስተናግዱና የአመለካከት መዛባት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ፡፡ ጓደኛ ማበጀትና ከሌሎች ልጆች ጋር መገናኘት ሲጀምሩ ደግሞ ክፉም ሆነ ደግ ባህሪያትን ሊወርሱ እንደሚችሉ ይገመታል ፡፡

ወደ ጉርምስና እድሜ ሲገቡ የሚስተዋልባቸው ስሜታዊ ድርጊት ለአጉል ልማድና ላልተገቡ ተግባራት የሚያጋልጣቸው ነው፡፡ ይህን በማሰብም በአግባቡ የቅርብ ክትትል ማድረግ የወላጆች ቀዳሚ ኃላፊነት ይሆናል፡፡ ስንቶች ይህን ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እየተወጡ ይሆን ? የምላሹን ነገር ቤት ይቁጠረው፡፡

በኢትዮጵያ የሚኖር አብዛኛው ዜጋ ሃይማኖት፣ ባህል፣ ወግና እሴት ያለው መሆኑ ይመሰከርለታል። ይህን እውነት እኛም በየአጋጣሚው ስንተርከው እንደመጣለን። አንዳንዴ በመንገዴ ላይ የሚገጥሙኝን ወጣቶች ሳይ ግራ የሚገባኝ ነገር አለ፡፡ ባህል፣ ወግና እሴት ማለት ብጣሽ ልብስ ከሰውነት ጣል አድርጎ መዞር ፣ በየመንገዱ መላላስ ነው እንዴ? በዚህ አይነቱ ገጽታ መታየትስ የኢትዮጵያውያን ባህልና ወግ ያስብል ይሆን ?

ታዲያ ለእነኝህ ግልጽ ጥፋቶች ሁሉ ተጠያቂው ማን ነው? ወላጆች፣ ትምህርት ቤቶች? ሀይማኖት ተቋማት? መንግስት? ማን ነው? ዋናው ጉዳይ ችግሮቹን ለመፍታት ‹‹እከሌ ነው›› ጥፋተኛ ብሎ ጣት መቀሳሰር ብቻ አይደለም፡፡ ሁሉም በያለበት ኃላፊነቱን ቢወጣ መልካም ነው እላለሁ፡፡ ‹‹አበቃሁ››

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ህዳር 8/2016

Recommended For You