አእምሮን እየጎዱ ያሉ ቀላል ልማዶች

አእምሯችን የሰውነታችን ዋነኛ አንቀሳቃሽ ክፍል ነው፡፡ ያለ አእምሯችን ምንም ማድረግ አንችልም። አእምሯችን ሲጎዳ ሃሳብ ማመንጨት የለም፡፡ እንደልባችን ሰውነታችንን ማዘዝ ይሳነናል። ጤናማ ሕይወት አይኖረንም፡፡ ለዛም ነው የአእምሮ ጤና የሁሉም የሰውነት ክፍል ጤና ነው የሚባለው። ከዚህ አንፃር የአእምሯችንን ጤና መጠበቅ ወሳኝ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ምንም እንኳን አእምሯችን በተለያዩ ከአቅም በላይ በሆኑ ውጫዊና ውስጣዊ ምክንያቶች ጤናው የሚቃወስበት ዕድል ቢኖርም አንዳንዴ ግን ቀላል በሆኑና በራሳችን ቸልተኝነት ምክንያት የሚጎዳበት አጋጣሚ አለ። ይህ ሲባል አእምሯችንን መጠቀም በሚገባን ልክ ካልሰራንበት ምንም ነው፡፡

እነዚህ ቀላል የሆኑ ነገሮች አእምሯችን ከአቅሙ በታች እንዲሰራ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ እንድንሰንፍና የተሻለ ሰው እንዳንሆን ያደርጋሉ። ለምሳሌ አንድ ገበሬ ማሳው ላይ ጤፍ ከዘራ ጤፍ ያጭዳል። ስንዴም ከዘራ ስንዴ ያጭዳል። ምንም ባይዘራ ደግሞ ያው አረም ያጭዳል። እኛስ አእምሯችን ላይ ምን እየዘራን ነው? ጥሩ ነገር ከሆነ እንቀጥልበት፡፡ መጥፎ ከሆነ ደግሞ እናስወግደው። ስለዚህ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን አእምሯችን እየጎዱ ያሉ ቀላል፣ ነገር ግን መጥፎ የሆኑ ልማዶችን ማስወገድ የግድ ይለናል፡፡

1ኛ. ረጅም ሰዓት ስክሪን ላይ መቆየት

አብዛኛዎቻችን በስልክ፣ ኮምፒዩተርና ላፕቶፕ ስክሪኖች ላይ ረጅም ሰዓት እናጠፋለን። አንዳንዴማ ረጅም ሰዓት እንዳጠፋን ሁሉ አይታወቀንም። ዓይኖቻችን በስልክና ላፕቶፕ ስክሪኖች ላይ ረጅም ሰዓት በቆየ ቁጥር white and gray matter የሚባለው የአእምሮ ክፍል ይጎዳል። እንደውም frontal lob የሚባለውና በጣም ከባድና ጠንካራ ሃሳቦችን የምናመነጭበት የአእምሮ ክፍል ይደክማል። በዚህ ምክንያት ጠንካራ ሃሳቦችን ማሰብ፣ በደንብ ማሰላሰል ይሳነናል፡፡ ደካማ እንሆናለን፡፡ ማንበብ እንድንጠላ፣ በጣም ጥሩ ጥሩ የሆኑና የአእምሮ ጡንቻን የሚያጠነክሩ ሥራዎችን እንዳንሰራና እንዳንለወጥ ያደርገናል። ስለዚህ በላፕ ቶፕ፣ የእጅ ስልክና ኮምፒዩተር ላይ በማፍጠጥ የምናጠፋውን ጊዜ መቀነስ አለብን፡፡

2ኛ. ዜናና ፊልም ማብዛት

ለምሳሌ እቤታችሁ ውስጥ ምግብ እያበሰላችሁ እያለ አንድ ሰው መጥቶ የምታበስሉት ምግብ ላይ የሆነ ቆሻሻ ቢጨምር ትጣሉታላችሁ፡፡ ዝም ብላችሁ አታልፉትም፡፡ ወይ ትሰድቡታላችሁ፤ ወይ ትደበድቡታላችሁ፤ አልያም ሰው ጠርታችሁም ቢሆን ታስደበድቡታላችሁ፡፡ ብቻ ዝም አትሉትም፡፡ ለምን? ወደ ሰውነታችሁ ውስጥ የሚገባ ምግብ ላይ ነው ቆሻሻ የጨመረው፡፡ ምግቡ ጤናማና ንፁህ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ ወደ ሰውነታችን ለሚገባው ነገር እንጨነቃለን ማለት ነው፡፡ ወደ አእምሯችን ለሚገባው ነገርስ ምን ያህል እንጨነቃለን? ዜና ወደ አእምሯችን ሲመጣ ምን ይዞ ነው የሚመጣው? ጥሩ ዜና ነው ወይ የምንሰማው፤ ጥሩ ዘገባ ነው ወ ይ የምናደምጠው?

በርግጠኝነት አምስት ዜና ብትሰሙ ከአምስቱ በጣም ጥሩ ዜና አንድ ወይ ሁለት ነው፡፡ እንትና አሸነፈ፤ እንትን ደግሞ ተመርቆ ተከፈተ የሚል ሊሆን ይችላል። ከዚህ ውጭ ግን አብዛኛው ዜና ወይ ሽብር ነው ወይ የሆነ ማስጠንቀቂያ አልያም ደግሞ አደጋ ነው። እንዲህ ሲባል ዜና አትስሙ ለማለት አይደለም። ነገር ግን በጣም ደጋግሞ አሰቃቂና አስከፊ ዜናዎችን ደጋግሞ መስማት አእምሮን በእጅጉ ይጎዳል። ቀላል ልማድ ይመስላል ግን ዜናው በሀገራችን ተስፋ እንድንቆርጥ ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ በገጠር ያለ ሰው እንዲህ ያለ ዜና ሲሰማ ‹‹አዬ! በቃ ይህች ሀገር እንዲህ ሆና ቀረች፤ መጥፊዋ እየቀረበ ነው›› ይላል፡፡ ለመሥራት ያሰበውን ቢዝነስም ይተዋል፡፡ በውጭ ሀገር ያለውም ‹‹እንደው ሀገሬ ላይ ሰላም የለ፤ ምን ላደርግ ነው ሀገሬ የምገባው›› ይላል ያችን ዜና ሰምቶ፡፡ ኢንቨስት ሊያደርግ ያሰበውን ነገርም ይተዋል፡፡ አያቹህ! መጥፎ ዜናዎች ህልማችሁን ሁሉ ይነጥቃችኋል፡፡

ሌላው ቀላል ነገር ግን ደግሞ አእምሮን የሚጎዳው ነገር ፊልም ማየት ነው፡፡ በነገራችን ላይ ፊልም ማየት ካበዛን በጣም መጥፎ ነው፡፡ ለምን መሰላችሁ? አብዛኛዎቹ ፊልም ላይ የሚሰሩ ሰዎች ከእኛ በብዙ የተሻሉ ናቸው፤ ለፊልሙ ሲባል፡፡ ለዛም ነው እየደጋገምን የምናያቸው፡፡ እናም እነሱን ስናይ የበታችነት ስሜት ሊሰማን ይችላል፡፡ እንደውም በአሜሪካን ሀገር በአፍላ የወጣትነት እድሜ ላይ በሚገኙ ወጣቶች ላይ በተደረገ ጥናት 85 ከመቶ ያህሉ አሁን ያላቸውን ሰውነታቸውን እንደማይወዱት ተረጋግጧል፡፡ ሰውነታቸውን መቀየር ይፈልጋሉ። ወይ ቀዶ ሕክምና መሰራት፣ ቦርጭ ካላቸው ማስወገድ፣ ውፍረት ካላቸው መቀነስ፣ ብቻ የሆነ ነገር ማድረግ ይፈልጋሉ፡፡

ለምንድን ነው? ሲባል ለካ በመዝናኛው ኢንዱስትሪው ላይ በተለይ በፊልም፣ ሙዚቃ ክሊፖችና ሌሎችም የመዝናኛ ዘርፎች ላይ የሚያዩዋቸው ሰዎች በሙሉ በጣም ቀጭን፣ የተስተካከለ የሰውነት ቅርጽ ያላቸው በመሆኑ እነሱን ለመምሰል የሚደረግ ጥረት መሆኑ ነው። ያ ማለት በፊልምና በሙዚቃ ክሊፕ ውስጥ በሚያዩዋቸው ተዋንያን ምክንያት የራሳቸውን ሰውነት እንዲጠሉ ተደርጓል፡፡ ስለዚህ የበታችነት ስሜት ይሰማቸዋል፡፡ እኛም አንዳንድ ጊዜ የምናያቸው ነገሮች በራሳችን ላይ የሚፈጥሩት ተጽዕኖ አለ፡፡ አእምሯችን ላይ በጣም ከባድ ጉዳት አላቸው፡፡ ስለዚህ ዜና መስማት መቀነስ አለብን፡፡ ፊልም ማየት ማብዛት የለብንም፡፡ ማየት አለብን፤ ግን በልኩ መሆን አለበት፡፡

3ኛ. ብዙ ሥራ በአንዴ መሥራት

በአንድ ጊዜ ብዙ ሥራ ስለ ሠራን ጥሩ ነገር ያደረግን ሊመስለን ይችላል፡፡ ለምሳሌ እየበላን ይሆናል አልያም ደግሞ ሥራ እየሠራን ይሆናል፡፡ ዘፈን እንከፍታለን፡፡ ዜና ካለም እንከፍታለን፡፡ ምናልባት ተንቀሳቃሽ ስልካችን ላይ አጭር የጽሑፍ መልዕክት ከገባ እንመልሳለን፤ እንላላካለን፡፡ እያጠናንም ሊሆን ይችላል፡፡ ሥራም እየሠራን ሊሆን ይችላል፡፡ በአንድ ጊዜ የተለያዩ ሥራዎችን እንድንሰራ አድርጎናልና በዚህ ጊዜ አእምሯችን ጥምር ሥራዎችን ወደ መሥራት ውስጥ ይገባል፡፡

ስለዚህ የሆነ ጊዜ ደግሞ አንድ ሥራ ብቻ መሥራት ያለብን ሰዓት አለ፡፡ ለምሳሌ ጸሎት ማድረግ ሊኖርብን ይችላል፡፡ ያኔ አእምሯችን ስንት ቦታ ሊሆን ይችላል? ለምን? አልሰበሰብነውማ፤ ጎድተነዋል፡፡ ብዙ ሥራ እሠራነው፡፡ ስለዚህ አእምሯችን ትኩረት እንዳያጣ፤ ሃሳቡን መሰብሰብ እንዲችል በተቻለ አቅም አንድ ነገር ብቻ መሥራትን ማስለመድ አለብን፡፡ ብዙ ሥራ በአንዴ መሥራት አእምሯችንን ይጎዳዋል፡፡

4ኛ. ሁሌም ተመሳሳይ ሥራ መሥራት

አዲስ ነገር አለመሞከርና ሁሌም አንድ ዓይነት ሥራ መሥራት ቀላልና አእምሮን የሚጎዳ ሌላኛው ምክንያት ነው፡፡ ሕይወታችን የተለመደና ተመሳሳይ ነው። ጠዋት ወደ ሥራ ከሥራ ወደ ቤት እንመላለሳለን። ጋደም ብለን ቲቪ እናያለን። ቀኑ ያልፋል፤ ይመሻል፤ ይነጋልም። ቅዳሜና እሁድ ይመጣል፡፡ እቤት እናርፋለን፤ ወይስ ሥራ እንሠራለን። እሱም ያልፋል፡፡ አዲስ ነገር አንሞክርም፡፡ በዚህ ምክንያት አእምሯችን መሰልቸት ውስጥ ይገባል፡፡

ለምን? አእምሯችን አይፈተንማ፤ አዲስ ነገር ሙከራ አያደርግም፣ አዲስ ክሂሎት አይለምድም። ተመሳሳይ ኑሮ ነው የሚኖረው። ስለዚህ አእምሯችንን እንጎዳዋለን፡፡ ታዲያ ምን ይሻላል? የሚሻለው አዲስ ነገር ለማግኘት መሞከር ነው፡፡ አዲስ ነገር በማድረግ ሕይወትን መቀየር ያስፈልጋል፡፡ ሥራም ከሆነ ትላንት ከሠራነው ዛሬ ጨመር አድርገን መሥራት ነው፡፡ የሚያስደስቱንን ነገር ማድረግ፣ ክሂሎቶችን መልመድ ይገባል። ለምሳሌ ዳንስ የሚወድ ሰው ዳንስ ቢማር፣ የሙዚቃ መሳሪያ መጨዋት የሚወድ ሰው እንዴት እንደሚጫወት ቢማር፣ አዲስ ቋንቋ መልመድ የሚፈልግ ሰው ቋንቋውን ቢማር ብቻ በፊት ከነበርንበት ሁኔታ ሊቀይሩ የሚችሉ ነገሮችን መልመድ ያስፈልጋል፡፡

5ኛ. ዝምታ ማብዛት

ማህበራዊ ሕይወታችን ላይ በጣም ሰነፍ ከሆንን ወይም ደግሞ ከሰዎች ጋር መግባባት የማንፈልግ ከሆነ እንደማሽን ነው የምንንቀሳቀሰው። ለምን? ከሰዎች ጋር አናወራም፡፡ ሃሳብ አንለዋወጥም። መረጃ አንወስድም። አይብዛ እንጂ ጓደኛ መያዝ፣ ከቤተሰብ ጋር ጊዜ ማሳለፍ በጣም ወሳኝ ነው። አእምሯችን ይታደሳል፡፡ አንድ ጥግ ብቻ አይቀመጥም፡፡

አእምሯችን እንደጡንቻ ነው፡፡ እንዳሰለጠነው ነው የሚሆነው፡፡ ካጠነከርነውና ብዙ ነገር ካሰራነው በምላሹ የመሥራት አቅሙን ያሳድጋል፡ ከሰዎች ጋር መግባባት በራሱ የሚሰጠን ጥቅም አለ፡፡ ያነቃቃናል። ጉልበት ይሰጠናል፡፡ ይሁንና ጓደኛ ስንይዝ መምረጥ አለብን፡፡ ‹‹አንድ ዓይነት ቀለም ያላቸው ወፎች አብረው ይበራሉ›› እንደሚባለው ከእኛ ጋር ህልማችንን የሚጋሩ፣ በዓላማ የሚመሳሰሉ፣ ቁምነገረኛ የሆኑ፣ በጎ ነገርን የሚሰብኩ፣ ከእኛ ጋር ተመሳሳይ ሃሳብ ያላቸው መሆን አለባቸው። ዝምታ የምናበዛ ከሆነ፣ ብቸኝነት የምናበዛ ከሆነ፣ አእምሯችንን እየጎዳነው ነው፡፡

6ኛ. በቂ እረፍት አለማድረግ

ይሄ እንደ ቀላል ልማድ ሊወሰድ ይችላል፡፡ በተለይ አንዳንድ ሰዎች ሥራቸውን በትጋት ይሰሩና ማታ አምሽተው ፊልም ያያሉ፡፡ በቂ እረፍትና እንቅልፍ ሳያገኙ እንደገና በጠዋት ተነስተው ወደ ሥራ ይሄዳሉ። ወይ ደግሞ በቂ እረፍት ሳያደርጉ አሟቸውም ቢሆን በግድ ሥራቸውን የሚሰሩ ሰዎች አሉ፡፡ እንደውም ሳይንሱ ሰዎች እንቅልፋቸው በተመሳሳይ ሰዓት መሆን እንዳለበት ያስቀምጣል። ይህም በተመሳሳይ ሰዓት መተኛትና በተመሳሳይ ሰዓት መነሳት እንደማለት ነው። ሁሌም አራት ሰዓት የምትተኙ ከሆነ ሰዓቱን ማዛነፍ የለባችሁም። ከዛ አስራ ሁለት ሰዓት የምትነሱ ከሆነ ሰዓቱን ማዛነፍ አያስፈልግም፡፡

የእረፍት ቀን ቅዳሜና እሑድም ቢሆን፣ የበዓል ቀናትም ቢሆን የእንቅልፍና ከእንቅልፍ የመነሻ ሰዓት ማዛነፍ አይገባም፡፡ ለምን? አእምሯችን የማረፋ ፈድን በተለይ ደግሞ እንቅልፍ የመተኛት ሂደት መልመድ አለበት፡፡ ምክንያቱም ይሄ ከሆነለት አእምሯችን እንደ አዲስ ነው የሚነቃው። ለአእምሯችን እረፍት የማንሰጠው ከሆነ ግን አእምሯችንን እንጎዳዋለን፡፡ ስለዚህ ከላይ የተጠቀሱት ምክንያቶች ቀላል መስለው ቢታዩም አእምሯችንን እየጎዱት ነው፡፡ ስለዚህ በፍጥነት ማቆም አለብን፡፡

 አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ህዳር 8/2016

Recommended For You